«እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል» ዮሐ 8፤32


ሐዋርያቱ ጌታችንን ከጠየቁት አስደናቂ ጥያቄዎች አንዱ «የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው?» በማለት ያቀረቡለት ጥያቄ ነው። ከክርስቶስ ዳግም መምጣት በፊት የሚሆነውን የዓለሙን ነገር ከተናገራቸው መካከል አንዱ ደግሞ የመንግሥት ወንጌል በዓለሙ ሁሉ እንደሚሰበክ የተናገረው ይገኝበታል። ማቴ 24፤14
መንግሥተ ሰማያት የሚያስገባውና ዳኝነት የሚያሰጠው የሕግ መጽሐፍ ወንጌል በመሆኑ ማንም ቢሆን ይህንን ቃል እንዲሰማ በመጨረሻውና በክርስቶስ መምጫው መዳረሻ ላይ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ እንደሚሰበክ የተናገረው ምልክት እነሆ በዓለሙ ሁሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ እየተሰበከ መገኘቱ እውነት ነው። በንግግር፤ በጽሑፍ፤ በምስል፤ በድምጽ፤ በምልክትና የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ወንጌል እየተሰበከ ይገኛል። በእርግጥ ወንጌልን የሚሰብኩ ሁሉ እውነተኞች፤ እንዲሁም ወንጌል የሰማ ሁሉ ይድናል ማለት አይደለም። የተጠሩ ብዙዎች፤ የተመረጡት ግን ጥቂቶች በመሆናቸው ለመዳንም ይሁን በፍርድ ለመውደቅ ድርሻው የእያንዳንዱ ሕይወት ከወንጌል ቃል መስማማቱ ነው። ወንጌል ሕጋችን ነው የሚሉ እነዚህ በሁለት ይመደባሉ።
1/ ወንጌል የሚናገረውን የእውነት ቃል አምነው እንደቃሉ የሚኖሩ
2/ ወንጌል የሚናገረውን የእውነት ቃል አምነው እንደራሳቸው የሚኖሩ ናቸው።
ወንጌል የሚናገረውን የእውነት ቃል አምነው እንደቃሉ የሚኖሩ በመልካም መሬት ላይ እንደተዘራ ዘር የወንጌልን ቃል አፍርተው ለብዙዎች መዳንና ወደእውነት መድረስ መንገድ የሚሆኑ ናቸው። ለዚህ አብነት ሆኖ የሚጠቀስ የመልካም መሬት ዘር ሐዋርያው ጳውሎስ ነው። ሐዋርያው መንፈሳዊ ትግሉ ምንጊዜም ሰዎች የክርስቶስ ብቻ ሆነው መልካም ፍሬ ያፈሩ ዘንድ ይተጋ ነበር።
«እንዲሁ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተ ደግሞ በክርስቶስ ሥጋ ለሕግ ተገድላችኋል፤ ለእግዚአብሔር ፍሬ እንድናፈራ፥ እናንተ ለሌላው፥ ከሙታን ለተነሣው፥ ለእርሱ ትሆኑ ዘንድ» ሮሜ 7፤4
እኛ በወንጌል አምነን በቃሉም የምንኖር ለሕግ ሞተን፤ ለክርስቶስ የሆንን የሌላ የማንም ፍሬ አይደለንም። የተክልዬም አይደለንም። የአቦዬም አይደለንም። የሚካኤልም አይደለንም። የማርያምም አይደለንም። የማንም ጻድቅ አይደለንም። የየትኛውም ቅዱሳን አይደለንም ማለት ቅዱሳንን እንደማቃለል አድርገው የሚመለከቱ አሉ። ከክርስቶስ በቀር የሞተልን፤ ከሞት የታደገንና ያዳነን ማንም የለም ማለት ነው። ጳውሎስ እንደተናገረው «ከሙታን ለተነሳው ለእሱ ትሆኑ ዘንድ» እንዳለው የእግዚአብሔር ብቻ እንደሆንን ይነግረናል። ወንጌል በክርስቶስ ብቻ ድነን የክርስቶስ እንሆን ዘንድ ሲያዘን ለቅዱሳን ያለንን ክብር የገለጽን እየመሰለን በማኅበራዊ ድረ ገጾችና በመረጃ መረቦች ላይ «እኔ የማርያም ነኝ፤ እናንተስ? እኔ የተክልዬ ነኝ፤ እናንተስ? ያለድንግል ማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም! የሚል ጥሪ ወንጌልን አመንን ከሚሉ ነገር ግን የወንጌል ቃል ተቃራኒ ድምጾች ይስተጋባሉ።  እውነቱን ስንነጋገር ዓለም የዳነው መቼ ነው? ዓለሙን ሁሉ ያዳነው ማነው? እግዚአብሔር አብ ዓለሙን ለማዳን አንድያ ልጁን ሲልክ የማን አማላጅነት እረፍት ስለነሳው ነው?
በጣም አሳዛኝና ወንጌልን የሚጻረር ድምጽ እየሰማን እንገኛለን። ቅዱሳንን በማክበር ሽፋንና ቅዱሳን በመቀበል ከለላ «ዓለም ያለቅዱሳኑ አማላጅነት አይድንም» ማለት ፈጽሞ ክህደት ነው ።  የእግዚአብሔር ፍርዱን ማን ሊመረምር ይችላል? ጳውሎስ እንዳለው።
«የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም።የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው?ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው?ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን» ሮሜ 11፤33-36
ወንጌልን አምነው ነገር ግን  እንደራሳቸው ቃል የሚኖሩት ደግሞ የራሳቸው የሆነ ፍሬ አላቸው። ፍሬአቸው ከወንጌል ቃል ጋር ፈጽሞ አይስማማም።  ለአብነትም ይህንን እውነት ከታችኛው ምስለ ድምጽ በማስረጃ ያመሳክሩ!!Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 2 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
March 8, 2014 at 10:02 AM

What a joke history my brethren Orthodox's are believing? No body could change the judgment that was given from the Almighty.

Anonymous
March 8, 2014 at 8:43 PM

false teachings truly exposed!

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger