Friday, March 21, 2014

የአቶ ግርማ ወንድሙ የማጭበርበር ጥምቀት የተፈቀደ አይደለም!



  

ግርማ ወንድሙ አጠምቃለሁ፤ ሰይጣንም አስወጣለሁ እያለ ማጭበርበርና ገንዘብ መዝረፍ ከጀመረ ሰነባብቷል። ማታለል በሀገሪቱ ህግ ወንጀል ቢሆንም ይህንን አታላይ የሚዳኝ ህግ እስካሁን አልተገኘም።  ከሁሉም የሚያሳዝነው ደግሞ ሊቃነ ጳጳሳቱም ከእነዚህ ዓይነቶች አጭበርባሪዎች ጋር ግንባር ፈጥረው ቤተ ክርስቲያኒቱ እመራበታለሁ ከምትለው የሥልጣነ ክህነት የአሰጣጥ ሂደት በተቃራኒው ግርማ ወንድሙ ለተባለው ነፍሰ በላ ወታደር  የቅስና ማዕርግ ሰጥተውት «ይፍታህ» እያለ ኃጢአት ሲደመሰስ እንደሚውል መዝጊያ የሚያክል መስቀል ጨብጦ እያየን ነው። ከስጋ ለባሽ መካከል ኃጢአትን የሚያስተሰርይ ቢገኝ ኖሮ የክርስቶስ ሰው መሆን ባላስፈለገም ነበር። 
  ዳሩ ግን እንኳን የሌሎችን ኃጢአት ሊያስተሰርይ ይቅርና ከማጭበርበር ዓለም ወጥቶ ራሱን መግዛት ያልቻለው ግርማ ወንድሙ መውጊያ በሚያክል የብረት መስቀል «ይፍታሽ፣ ይፍታህ» እያለ እንዲደበድብ ጳጳሳቱ ቅስና ሰጥተውታል። ጳጳሳቱ ገንዘብና የሚቀበላቸው ካገኙ እንኳን ቅስና ጵጵስናም ከመስጠት አይመለሱም። የትም ሳይማሩ የክብር ዶክተሬት ዲግሪ እንደሚሰጠው ሁሉ «ፈቀደ እግዚእ» ብለው የሰኞ ውዳሴ ማርያምን መዝለቅ ለማይችሉ ሁሉ የክብር የቅስና ማዕርግ ሲሰጥ እያየን ነው።  እስካሁን በአደባባይ የክብር የቅስና ማዕርግ እንደምትሰጥ ከቤተ ክርስቲያኒቱ በኦፊሴል ባንሰማም በተግባር ግን የማይሰራበት የክብር የቅስና ማዕርግ ይዘው ያሉ እንዳሉ እናውቃለን። ማኅበረ ቅዱሳን ደግሞ በዚህ መልኩ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። የሚያገለግሉበት ወይም ያገለገሉበት ደብርና ገዳም ሳይኖር ወይም ለማገልገል የሚያበቃ ሙያ ወይም ትምህርት ሳይኖራቸው ቅስናና ዲቁና አለን ብለው በእጃቸው ትላልቅ መስቀል ጨብጠው መንገድ የሚያጣብቡ ሁሉ ለወደፊቱ መለየት አለባቸው።
 ይህንን የዲቁና፤ የቅስናና ሌሎች ማዕርጋት ልክ የንግድ ፈቃድ እድሳት እንደሚደረገው የእድሳት ዘመን ተደርጎለት ማዕረጉን ከየት እንዳገኘው? የት እንደሚያገለግልበትና ምን እንደተማረ? እየተመረመረ ተገቢ ሆኖ ያልተገኘው ሁሉ እንዳጭበረበረ ተቆጥሮ ወዳቂ ካልተደረገ በየሜዳው «ቀሲስ» የሚባሉ ጩልሌዎችን አደብ ማስገዛት አይቻልም። ከእነዚህም የክብር የቅስና ማዕርግ ተሸካሚ አንዱ አቶ ግርማ ወንድሙ ነው። ሌሎቹም ቢሆኑ ሙያውና እውቀቱ እያላቸው ነገር ግን ሥነ ምግባርና ለተመደቡበት ማዕርግ የሚያበቃ ማንነት የሌላቸው ዲያቆናት፤ ቀሳውስትና መነኮሳት ከዚሁ ጋር ተያይዞ ካልታየ በስተቀር የዝቅጠትና የውርደት መለያ ሆኖ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ውድቀት አስተዋጽኦ ማድረጉ አይካድም። ምዕመናንና ምዕመናት በእንደዚህ ዓይነቶቹ ተቆጣጣሪ አልባ ባለማዕርጋት ስርዓተ አልበኝነት የተነሳ በሀፍረት ተሸማቀው  እንደሚገኙም ይታወቃል።

   ከእነዚህኞቹ አንዱ የሆነው አቶ ግርማ ወንድሙ በስመ ማጥመቅ የሚሊዮን ብሮች ባለቤት መሆኑ ሳያንስ ከዚህ ዓይነቱ ተግባር እንዲላቀቅ ቤተ ክርስቲያኒቱ ብትመክረውም ለመስማት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ( እሱ ይሁን ወዳጆቹ) ማን እንዳስጻፈው ያልታወቀ የማጥመቅ ፈቃድ አውጥተው እንደነበር አይዘነጋም። ( ደብዳቤውን ለማንበብእዚህ ይጫኑ )

  ይሁን እንጂ በአባ ገሪማ ፊርማ ቅዱስ ፓትርያርኩ የማጥመቅ ፈቃድ ሰጥተውታል የተባለበት ደብዳቤ ከቤተ ክህነቱ ደርሶ ኖሮ ሲመረመር የሀሰትና የማጭበርበር ተግባር መሆኑ በመረጋገጡ ቤተ ክህነት ይህንኑ ለማሳወቅ ተገዷል። በዚሁ መሠረት ለአቶ ግርማ ወንድሙ የማጥመቅ ሥራ ምንም ዓይነት ፈቃድ እንዳልተሰጠና ፈቃድ የተሰጠው በማስመሰል የተበተነው ወረቀት የማጭበርበር ውጤት እንጂ የቤተ ክህነቱን የፕሮቶኮል ቁጥር የያዘ እንዳይደለ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ገልጿል። በአባ ገሪማ የተጻፈውን ደብዳቤ ለማንበብ  ( እዚህ ላይ ይጫኑ ) 

አቶ ግርማ ድሮም አጥማቂ አልነበረም፤ አሁንም አጥማቂነት እንዳልተፈቀደለት ተረጋግጧል።  ግርማ ወንድሙ ከእጁ በምን ዓይነት ተአምር ሊለያት በማይፈልጋት መቁጠሪያ ሰይጣናዊ አስማት የሚጠቀም አስመሳይ እንጂ አጥማቂ አይደለም። ስለዚህ አፍቃሬ ግርማ ወንድሙ የሆናችሁ ሁሉ እርማችሁን አውጡ።

 ዳሩ በማስመሰል የሚያጠምቀው ግርማ ወንድሙ ይቅርና «እኔ ጥቁሯ ድንግል ማርያም ነኝ» እያለች ስታጭበረብር የነበረችው ሴት እንኳን ብዙ ተከታዮች ማፍራቷን አይተናል፤ ከእሷ አታላይነትም የበለጠ «ጥቁሯ ድንግል ማርያም» እንደሆነች አምነው የሚከተሏት ሰዎች ያስገረመን ጉዳይ ሆኖ አልፏል። ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን እንጂ የወንጌልን ቃል ስለማይመረምር ለእንደዚህ ዓይነት ትንግርቶች ተጋላጭ ነው።  

«በዚያን ጊዜ ማንም እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፤ ወይም ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ»    ማቴ 24፤23-25