ይህንን ጽሁፍ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በተሾሙ ማግስት በመካነ ጦማራችን ላይ አውጥተነው ነበር፤ እነሆ አንድ ዓመት አለፈው። ከተናገርናቸውና ይፈጸሙ ዘንድ ከምንጠብቃቸው ተስፋዎች ውስጥ ምን ያህሉ ተግባራዊ ተደርጓል የሚለውን ወደኋላ መለስ ብለን ለማየት እንዲቻል ደግመን አቀረብነው። ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደጥንቱ ዛሬም በልምድና በግምት እየተጓዘች ነው ወይስ የተሻለ የአስተዳደር ማዕከል መገንባት ችላለች? የሚለውን ጥያቄ አሁንም ማንሳታችንን አልተውንም። ከወቅቱ ሰሞነኛ ዜናዎች መካከል በማኅበረ ቅዱሳን ላይ እየቀረቡ የሚገኙት የማኅበረ ካህናቱ አቤቱታዎች (በማኅበሩ ዘንድ በጣት የሚቆጠሩ እየተባሉ ይናቃሉ) እንዲሁም ፓትርያርኩም እያመረሩ የመገኘታቸው ጉዳይ ብዙ እየተባለለት ነው። ( የፓትርያርኩ ለመታዘዝ ፈቃደኛ አለመሆንም ማኅበሩ እያናደደው ነው) በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ማኅበሩን ቦታ ካላስያዙት የፓትርያርኩ የስራ ሂደት አስቸጋሪ እንደሚሆን የዛሬ ዓመት ጠቁመን ነበር። አጠቃላይ የመዋቅር ለውጥና የአዲስ ሕግ አወጣጥ የፓትርያርኩ አዲስ የስራ ጅማሮ እንዲሆን አሳስበን የነበረ ቢሆንም ማኅበሩ ግን ፓትርያርኩን አስቀምጦ በአባ እስጢፋኖስ በኩል ራሱ ፓትርያርክ የሆነበትን ሂደት ለመታዘብ መገደዳችንንም እንድናስታውስ አድርጎናል። ለሁሉም ሊሆን ይገባል ብለን በግላችን ያሳየንበትን ሁኔታ መታዘብ እንዲቻል ለአንባብያን በድጋሚ አቅርበናል። መልካም ንባብ!!
በዚህም ተባለ፤ በዚያ አቡነ ማትያስ ፮ኛው ፓትርያርክ ሆነው ተሹመዋል። ባለፈው ግድፈትና እውነት ላይ እያነሳንና እየጣልን ጊዜ አናጠፋም። ይልቅስ ብዙዎች የታገሉለት የምርጫው ስኬት
እንዳሰቡት ጥሩ የሥራ ጊዜ ይዞ ይመጣላቸው እንደሆነ የምናይበት፤
ገሚሶቻችንም የምናያቸው የቤተ ክህነት ተግዳሮቶች የሚቀረፉበት፤ ሰናይ
የአስተዳደርና መንፈሳዊ ዘመን ናፍቆታችንን ተስፋ በማድረግ እንደዚህ በፊቱ አስቀድመን አንዳንድ ነገሮችን ለማመልከት ወደድን።
የአዲሱ ፓትርያርክ አዲስ የሥራ ዘመን ቀላል እንደማይሆን ይገመታል። የተጠራቀሙ የቤተ ክህነቱ ችግሮችና ብዙ እንከኖች
ከፊታቸው ይጠብቋቸዋል። የችግሮቹ ዓይነቶች፤ ደረጃና ጥልቀት የተለያዩ
እንደመሆናቸው መጠን የተለያየ ውሳኔና እርምጃንም የሚጠይቁ ናቸው። ለዚህ የተዘጋጀ የአእምሮ ዝግጁነት፤ የእውቀት በሊህነት፤ ድፍረትና
ማስተዋል እንደሚጠይቁም አይጠረጠርም። ያንን ዓይነት ሰው ከየት እናገኛለን
ብለን አናሳብም። ምክንያቱም ምርጫው /ከተባለ/ ትልቅ አባት ሰጥቶናልና። ስለዚህ ወደችግሮቹ እንንደርደር።
1/ የቤተ ክህነቱ ላዕላይና ታህታይ መዋቅር ማሻሻል
የቤተ ክህነቱ ቀዳሚው ችግር ሥራና ሠራተኛ የተገናኘበት ተቋም አለመሆኑ ነው። ሥራና ሠራተኛ ካልተገናኘ ደግሞ በየትኛውም መልኩ የቤተ ክህነቱ የሥራ አፈጻጸም «ከርሞ ጥጃ» መሆኑ አይቀርም።
ሥራና ሠራተኛ ማለት ለተገቢው ሥራ ተገቢ ባለሙያ ወይም ተቀራራቢ ችሎታ ያለው ሰው ማለት ነው። እንደዚህ ባለው ሰው ላይ የተቋሙን
ዓላማና ግብ በደንብ ካስጨበጡት ከችግሮቹ ብዛት አንጻር ባንድ ጊዜ ፈጽሞ ባይወገድም፤ ከየትኛውም ጊዜ የተሻለ ለውጥ ሊመጣ ይችላል።
በዘመድ አዝማድ የተለጣጠፉና የተደረቱ ክፍሎችን ይዞ መቀጠል ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይሆናልና አሁን ያለን የሥራና ሠራተኛ
አቋም የችግሩ ዋና ምንጭ ነው ባይባልም የችግሩ አካል ነውና ከጥገናዊ ለውጥ ወይም ከማስመሰል /pseudo/ የራቀ ለውጥ ያስፈልገዋል።
ከአቅም በታች ለመሥራት የእድሜ ጣሪያ የገደባቸውም በየመልኩ ቦታቸውን
መያዝ ካልቻሉ ቤተ ክህነት የዘመዳ ዘመዶች የጡረታ ተቋም ሆኖ ይቀጥላል
እንጂ የሥራ ብቃት መለኪያ ስፍራ ሊሆን አይችልም።
ሀገር
አቀፍ ተቋም የሆነው ቤተ ክህነት ሀገር አቀፍ አደረጃጀት ሊኖረው የግድ
ነው። ከላይ እስከታች አደረጃጀቱ መሻሻል አስፈላጊ ከሚባልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል ብለን እናምናለን። በአንድ ወቅት
በአሁኑ ሰዓት የአንበሳ
አውቶቡስ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ በድሉ አሰፋ የቤተ ክህነቱን የአቅም ግንባታ ክፍል ሆነው ጥናት
አቅርበው እንደነበር
አስታውሳለሁ። ቤተ ክህነትና የዘመኑ ጥናት ሊግባቡ ባለመቻላቸው ቤተ ክህነትም በአሮጌ ልምዷ ስትቀጥል፤ አቶ በድሉም
አሮጌው ጎዳና አላሰራ ስላላቸው ትተውት የተሻለ ቦታ ሄደዋል። ስለዚህ ቤተ ክህነትን ከአሮጌ መዋቅር ወደዘመነ
ሥርዓት ለማስገባት አዲሱ ፓትርያርክ
ትልቁ ሥራቸው መሆን አለበት እንላለን። የተደረተውን በመጠገን ላይ ካተኮሩ ግን ልባቸው ወልቆ እርጅናቸውን ከማፋጠን በስተቀር ለእርሳቸውም
ይሁን ለቤተ ክህነቱ ቀጣይ አስተዳደር አንዳችም ነገር ጠብ ሳይል
ይቀጥላል ማለት ነው። ይህን ማስተካከል የአዲሱ ፓትርያርክ ፈታኝ ሥራ ነው ብለን እናስባለን።
2/ እርምጃ አወሳሰድ፤ የሥራ ብቃት መለኪያና አፈጻጸሙን
የመቆጣጠሪያ ስልት፤
ቤተክህነትን በብቃት የሚመራ ሕግ፤ መመሪያና ደንብ የለውም።
ያለውንም በሥራ የሚያውል አካል አልነበረም። ነገሮች ሁሉ በልምድና በስምምነት የሚሰራበት ሆኖ ቆይቷል። ሥልጣንና ተግባር ለክቶ
የሚሰጥ መመሪያ ባለመኖሩ ሥራና ኃላፊነት ተደበላልቀው በባለሥልጣን ይጣሳል፤ ወይም በመሞማዳሞድ ይሸፈናል። መመሪያው ሕግ ሳይሆን ሹመኛው ራሱ ሕግ ሆኖ ያገለግላል። የአድርግና አታድርግ፤ የጌታና
የሎሌ አስተዳደር እንጂ የ21ኛው ክ/ዘመን የተጠያቂነት አሠራር በቤተ ክህነት የለም። ባለሥልጣናቱ ከፈለጉ ከአፈር ይቀላቅሉሃል፤ ከወደዱም ጣሪያ ላይ ይሰቅሉሃል። ሰው የሚያድገውም ይሁን ድባቅ
የሚመታው ተጠያቂነት በሌለው ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ቆይቷል። ለሠራው ሥራ ብቃትና
ጉድለት መለኪያ ሚዛን የለም። ሌላው ይቅርና የፓትርያርክ የምርጫ
ሕግ እንኳን ከእንከን የጸዳ ባለመሆኑ በነቶሎ ቶሎ ቤት ጥበብ ተለክቶ
የተሰፋው በቅርቡ መሆኑን ልብ ይሏል። እንግዳነቱ ብዙ ጭቅጭቅና ክርክር
ማስነሳቱም አንዱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ መሆኑ አይዘነጋም። ነገም ይህ ችግር ላለመደገሙ ዋስትና
የለም። ስለዚህ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ወጥነት ያለው ሕግ፤ መመሪያና ደንብ ሊኖር ይገባል። ይህንን ችግር አጥንቶ የተሻለ መፍትሄ በማምጣት ላይ አዲሱ ፓትርያርክ ትልቅ
ሥራ ይጠብቃቸዋል።
3/ መንፈሳዊ ሲመት/ሹመት/ በተገቢው መለኪያ ማከናወን
ከጵጵስናው ጀምሮ እስከ እልቅና ድረስ ያለው የሲመት አሰጣጥ ሲባል እንደቆየውና እንደምናውቀው ወይ ገንዘብ ያለው፤ ወይ
ዘመድ ያለው እንጂ በችሎታና በብቃት ልኬት የሚገኝ አልነበረም። ጉልበት
ስር መንበርከክን ዝቅ ሲልም ትቢያ መላስን እንደመስፈርት ሲሰራበት ቆይቷል። መከባበር ተገቢ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ትሕትናን ገንዘብ በማድረግ ያይደለ ሥጋዊ ክብርን ከመፈለግና
ለሹመት ሲባል ወደአምልኮ የተቀየረ ስግደት የመስጠት ትእቢታዊ ግብር ማላቀቅ ተገቢ ነው። ጵጵስናውንም እንደሲሞን
መሰርይ ሽጡልኝ ወደሚባልበት ደረጃ ማውረድ ወይም በአማላጅና በሽማግሌ የሚረከቡት ንብረት መሆኑ መቆም አለበት። መሪው በተመሪው
የተመሠከረለት ቢሆን እንዴት ባማረ ነበር? ጳውሎስም የመከረን ይህንኑ እንድናደርግ ነበር። ብዙ ጊዜ እንደሚታየው መሪውን ገንዘብ ይመርጥና ወደተመሪው ሕዝብ ይላካል።
እዚያም እንደደረሰ መሪው ለሚመራው ሕዝብ ሳይሆን አገልጋይነቱ ለመደቡት ክፍሎች ይሆናል። ሕዝቡም በሚወርድበት የዐመጻ ሥራ
የተነሳ እምነቱን እንዲጠላ፤ እንዲያፍርና እንዲሸማቀቅ ብሎም እንዲኮበልል ይገደዳል። ሕገ ወጥነት የሰለጠነበት የቤተ ክህነት ሥልጣን እንደገና
መበጠር ይገባዋል። ሕዝቡ መጣብን ሳይሆን መጣልን
የሚል መንፈሳዊ
መሪ ይፈልጋል። በመጡበት ተላላኪዎች እስከዛሬ መሮታል። እናም አዲሱ ፓትርያርክ ይህንን ሁሉ ችግር ተረክበው የጣፈጠ
ሥራን ሊያሳዩት ይጠበቃል። ያለፈውን ችግር ተሸክመው በምን ቸገረኝነት ይቀጥላሉ ወይስ ይህንን
የሚሸከም ጀርባ የለኝም ይሉ ይሆን? እሳቸውንና ደጋፊዎቻቸውን የምንጠይቃቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ትልቁ ፈታኝ ሥራቸው እንደሆነ ግን በበኩላችን አስምረንበት እናልፋለን።
4/ የመንፈሳዊ ሀብት ጥበቃና ልማት አንጻር፤
ቤተክህነት ጥንታዊ የመንፈሳዊ ሀብት ባለቤት ብትሆንም አሁን ያለችበት ደረጃ ግን በተገቢ ሥፍራዋ ላይ አይደለም። ግእዝ ቋንቋ የሀገሪቱ ሀብት መሆኑ ቀርቶ ዛሬ በዱርና በበረሃ ተደብቆ የሚገኝ
በመጥፋት ላይ ቅርስ ሆኗል። ይህንን ቋንቋ በሕይወት ለማቆየት የአብነት መምህራን ግሱን እያስገሰሱ፤ ቅኔውን እያስዘረፉ በጥቂቶች
እጅ ብቻ የሚገኝ ቋንቋ ሀብት ከማድረግ ባሻገር የብዙዎች ለማድረግ ቤተ ክህነት አቅሟ ተሰልቧል። ሐምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ኢንስቲቲዩት ግእዝን ሲያስተምር የቋንቋው ባለቤት
ግን ለዚህ ነገር እንግዳ ናት። መምህራኖቹ ከውሻ ጋር እየታገሉ ከተማሩት
ውጪ ቤተ ክርስቲያኒቱ በወጥ የትምህርት ሥርዓት ለማስተማር ጊዜ አላገኘችም። ወይም ጊዜውን ለመጠቀም አልፈለገችም። ትውልዱ እንግሊዝኛ፤ ዐረቢኛና ፈረንሳይኛ ሲማር የራሱ የሆነውን ግእዝን እየፈለገ
አላገኘውም። ከመንፈሳዊ ቀጣይ ልማት ውስጥ የግእዝ ቋንቋን እንደሙሉ ቋንቋ ለትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅባታል። ከጥቂት የአብነት
መምህራን እጅ ወደ ሁሉን አቀፍ ቋንቋ እንዲቀየር በኮሌጅ ደረጃ ማስተማር ይጠበቅባታል። ሌሎቹንም የአብነት ትምህርቶች ደረጃና ብቃት በማሻሻል ቀጣይነቱን ማረጋገጥ
የቤተክህነቱ ድርሻ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቴኦሎጂ ኮሌጆችም ካለው የቤተ ክርስቲያኒቱ የሰው ኃይል ብዛት ጋር ፈጽሞ እንደማይመጣጠን
ይታወቃል። ሁለት ጡት ሆኖ መቅረቱ ያሳዝናል።/እንደምን?/ ሌላው ቢቀር የላምን
ጡት ቁጥር ሞልቶ የምሁራን ወተት የሚታለበው መቼ ይሆን? እያንዳንዱ
ሀገረ ስብከት የኮሌጅ ባለቤት መሆን በሚገባው ሰዓት፤ አንድም የሴሚናሪ/ ት/ቤት የሌለው መሆኑ ያስከፋል። ጳውሎስ መንፈሳዊ ት/ቤት እንኳን ባለበት መርገጥ ከጀምረ ሦስት መንግሥታት
አለፉት። ለዚያውም እስከነ ግዙፍ ችግሩ። እያንዳንዱ ሀገረ ስብከት የካህናቱን ብቃትና ችሎታ ማሳደግ በሚገባው ወቅት በዲያቆን ቅጥርና ማባረር ጊዜውን ማጥፋቱ አሳዛኝ ነገር ነው።
የአጫጭር፤ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የትምህርትና የስልጠና መስኮች መከፈት ይኖርባቸው ነበር። የእድሜአችንና የስፍራችንን መራራቅ ቢያንስ ማቀራረብ ተገቢ ነው።
በመንፈሳዊ ሃብት ጥበቃና ልማት አንጻር ሌላው የሚነሳው
ነገር ማን እንደጻፋቸው የማይታወቁ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ የሚጻረሩ፤ ተረት፤ ቧልት፤ ቀልድና ክህደት የሚያስፋፉ መጻሕፍትና
ትምህርቶች ሁሉ በሊቃውንቱ እንዲታረሙና እንዲመረመሩ መደረግ ይገባዋል። በተሀድሶ መጣና በመናፍቃን በላህ ዘመቻ እንከኖቻችንን ተሽከመን መዝለቅ ችግሩን
ከሚያባብስ በስተቀር መፍትሄ አይሆንም። ገሚሱም ከእውቀት ማነስ የተነሳ ሲመቸው ከሚነቅፍ፤ ገሚሱም ባልዋለበት ቦታ ሊቅ ሆኖ ጠበቃና
ተከራካሪ ከሚመስል ምሁራኑ የተሳሳተውን አርመው፤ የጎደለውን መልተው ሊያስተካክሉ ይገባል። ቤተ ክህነት የማታውቀውን ጠልሰም ሁሉ በይፋ ማውገዝ ይገባታል። ዝምታ በራሱ
ወዶ እንደመቀበል ይቆጠራልና። የተሻለ የህትመትና የሚዲያ ዘመን ላይ
ብንገኝም ማንም ተነስቶ እኔ ጠበቃ ነኝ በሚል ዲስኩር ኑፋቄን ሲያሰራጭ፤ ሲያሳትም፤ ሲዘፍን/ ሲዘምር?/ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዝምታዋ
አስገራሚ ሆኗል። የቤተ ክርስቲያኒቱን ስርዓትና ደንብ የተከተለ በሚል
ሽፋን መድረኳን የርግብ ለዋጮች ገበያ ሲያስመስለው ዝምታው ያስገርማል።
ይህ ሁሉ የሚሆነው ሊቃውንት ጉባዔውን ሊቃውንት ስላልመሩት ወይም ሊቃውንት መሰኘት በምንም ልኬታ እንደሆነ ትርጉሙ ጠፍቷል ማለት ነው።
እነዚህን ሁሉ ችግሮች የመለየት፤ የማስወገድና የማረም መንፈሳዊ ልማት
ከአዲሱ ፓትርያርክ የሚጠበቅ ሥራ ነው።
እንደዚሁም ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላትን ቅርስና ሀብት በአግባቡ መዝግባ፤ በዘመነ የመረጃዋ ቋት አስገብታ መያዝ ይገባታል።
የፈረሰውን በመጠገን፤ ያረጀውን በማደስ ልትሰራው የሚገባት አንገብጋቢ ጉዳይ ሞልቷታል። በጉብኝትና ጎብኚ /Tour &
Tourism operation / ረገድ የሰራችው ምንም ነገር የለም። በሀብቷ የሚበለጽጉት ሌሎች ናቸው። «ከሞኝ በራፍ፤ ይቆረጣል
እርፍ» እንዲሉ አስጎብኚዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ስንፍና፤ ጉብዝናቸውን በቤቷ ውስጥ እያሳዩ ያሉት ያተርፉባታል ። ስለሆነም በመንፈሳዊ ሀብት ልማትና ጥበቃ አዲሱ ፓትርያርክ ብዙ ይጠበቅባቸዋል።
5/ ማኅበራዊ ልማትና እንቅስቃሴ
ከኋላዋ የመጡ አብያተ እምነቶች በተሻለ ደረጃ በሕብረተሰብና በመንግሥታዊ የልማት ተሳትፎ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።
እያንዳንዷን የምጽዋት ገንዘብ በልማትና ልማቱን ተከትሎ በሚደረገው ስብከት ላይ ያውላሉ። የቤተ ክህነት ሙዳየ ምጽዋት ግን ሌላ
የልማት ገቢ ስለሌለ የካህናት ደመወዝ ከመሆን ወጥቶ የሕብረተሰብ ልማት ላይ መዋል አልቻለም። ለኃጢአት ማስተስረያ የሚሰጥ ገንዘብ
ተመልሶ ሕይወት ወዳለው ልማት የመዋል እድል አላገኘም። አድባራትና ገዳማት በልማት ሥራ ላይ ጉልበታቸውን እንዲያውሉ ማስቻልና ይህንንም በገንዘብና በሙያ ቤተ ክህነት ማገዝ ሲገባት የልመና ደብዳቤ በመስጠት
ወደጎዳና ትልካቸዋለች። በየአድባራቱ የልማት ክፍል እንዲስፋፋ የገንዘብ ዘረፋንና ብክነትን መቆጣጠር መቻል በራሱ ልማት ነበር።
ይሁን እንጂ ያንን ገንዘብ ወደተሻለ ልማት ማዋል በሚል ሰበብ ገንዘብ የሚዘረፍበት ዘዴ ሆኖ ቆይቷል። ይህንን ማስቆም ካልተቻለ አዲሱ ፓትርያርክ
ስኬታማ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል። መራጮቻቸውንም በመምረጣቸው መመካት የማይችሉ ድኩማን ሆነው ያፍራሉ። ስለዚህም ሁሉም ወገን የሚጠብቀው
ልማት በሰው ኃይል ብቻ ሳይሆን በገንዘብ አጠቃቀም፤ በማኅበራዊ እንቅስቃሴ፤ በሕብረተሰብ አቀፍ ልማት ውስጥ ተሳትፎ ማድረግን ያጠቃልላል።
እነአቡነ ቴዎፍሎስ ያስገነቡትን ህንጻዎች እያከራዩ የጳጳሳት ደመወዝ በየሁለት ዓመቱ መጨመር ሳይሆን በየሁለት ዓመቱ ደመወዝ የሚያስጨምር
ልማት ሰርቶ ማስረከብ ይጠበቃል። የተሻለ ደመወዝና ሥራ ፍለጋ የሚጎርፈው ቄስና አባ የትየለሌ ነው። ቤተ ክህነት ሁሉንም ማርካት
የሚችል ቅጥር በመፈጸም ጊዜዋን ማጥፋት የለባትም። ሥራ በመፍጠር የተጨማሪ ባለሙያ ባለቤት ማድረግም ትችላለች። አድባራት /በተለይም/
አዲስ አበባ የቅጥር ሁኔታ ሞልቶ ወደመፍሰስ/ saturated/ ወደ መሆን ደረጃ ደርሷል። ካህን ሁሉ የግድ መቀደስ ወይም ማኅሌት
ብቻ ካልቆመ መኖር አይችልም የሚል ህግ የለም። ስለዚህ በልዩ ልዩ ሙያ ማሰልጠን፤ ትርፋማ ልማትን መፍጠር ይጠበቅባታል። በመቅጠርና
በማዘዋወር ዘመኗን መፈጸም የለባትም።
በሌላ መልኩም ቤተ ክህነት እመራዋለሁ በምትለው ሕዝብ
ውስጥ በጤና፤ በአካባቢ ጥበቃ፤ በንጹህ የመጠጥ ውሃ፤ ወዘተ ልማት ውስጥ መኖሯን ማሳየት አለባት። የአባልነት መዋጮ እያለች ከተከታዮቿ ላይ በፐርሰንት መልቀም ብቻ ሳይሆን የተለቀመውን ገንዘብ መልሳ በልማት ውስጥ ለተከታዮቿ ማፍሰስ ይገባታል። የቤተ ክህነቱ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በስሩ እስካሉት መምሪያዎች
ጭምር ባለፉት ዓመታት ያልተወራረደ የእርዳታ ገንዘብ ተሸክሞ መቆየቱ ይነገራል። ቀጣዩ የልማት ኮሚሽኑ የቡድን ተሿሚው አባት ይህንን
ያብሱት ይሆን ወይስ ያርሙት? ጊዜው ሲደርስ የምናየው ሆኖ ለአሁኑ
ግን አዲሱ ፓትርያርክ ቀጣይ ብዙ ሥራ እንደሚጠብቃቸው እንጠቁማለን።
5/ ማኅበራት፤ ቡድኖችና ግለሰቦች እንደ ቅልጥም ሰባሪ
አሞራ ማኮብኮባቸውን ማስቆም፤
ቤተ ክህነት ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ አንድ ወጥ መዋቅር አላት። በዚህ መዋቅር ውስጥ ሥፍራ የሌለው ነገር ግን የሚጠጋበትን ጥግ እየቀደዱ ወይም
እየቦረቦሩ ባዘጋጁለት ቦታ ሆኖ በእንቅስቃሴው፤ ቤተ ክርስቲያኗን አክሎ፤ እሷን መስሎ የራሱን የሀገረ ስብከት ተቋም በሀገር ውስጥና በውጪው ያደራጀው ራሱን «ማኅበረ ቅዱሳን»
እያለ የሚጠራውን ክፍል አዲሱ ፓትርያርክ ተገቢውን ቦታ ሊሰጡት ይገባል። በሲኖዶሱ፤ በሀገረ ስብከቱ፤ በአድባራትና ገዳማቱ ሁሉ
ያልታጠበ እጁን እያስገባ መቀጠል የለበትም። ሰንበት ተማሪ ነኝ የሚል ከሆነም የሰንበት ተማሪዎችን ሕግና ደንብ አጥብቆ የሚይዝበት
ምክር ሊሰጠው ተገቢ ነው። ራሴን የቻልኩ ማኅበር ነኝ ካለም ራሱን የቻለ ተቋም ሆኖ ይኑር እንጂ ከቤተ ክህነት ጀርባ ላይ እንደትኋን ተጣብቆ ሲመቸው አዛዥና ናዛዥ፤
ሳይመቸው ደግሞ ትሁት መስሎ ነጣላውን እያጣፋ ከበሮ መደብደቡን ያቁም። ከእሱ ጋር ሲነፍስ የሚነፍሱ ጳጳሳትም ያሉበትን ተቋምና ደረጃ እንጂ የቡድን
ዋሻ አድርገው መጠቀማቸውን ማቆም አለባቸው። ይህ ሃሳብ የብዙዎች ሃሳብ ስለሆነ እንደቀላል ነገር መታየት የለበትም። ከሁሉም በላይ
የአዲሱ ፓትርያርክ የሥራ እንቅፋት አንዱ ይኸው በቅዱሳን ስም የተሰባሰበው ማኅበር ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ቤተ ክህነቱን የወረሩ
የቀን ጅቦችና ወሮ በሎች የቤተ ክህነቱን ዓርማና መለያ ለብሰው በጨዋ ደንብ ተቀምጠዋል። እነዚህም ቤተ ክህነቱን እንደቅንቅን የበሉ
ምንደኞች ቦታ ቦታቸውን መያዝ ይገባቸዋል። ትዳር አልሆን ያላቸው፤ እድሜአቸውን ለንስሐ ያልተጠቀሙ አሞራዎችም ሲኖዶስን እስከመበጥበጥ
ልምድና ችሎታ ያላቸው ስለሆኑ ከአዲሱ ፓትርያርክ ጋር ክንፋቸውን እያማቱ ሰላማዊ ርግብ ለመመስል መሞከራቸው አይቀርምና ለእንደዚህ
ዓይነቶቹም ቤተ ክህነት ሥፍራ እንደሌላት ማሳየት የአዲሱ ፓትርያርክ ሌላው ፈታኝ ሥራ ነው። እንዳለፈው ሁሉ አዲሱም ተመሳሳይ ድርጊትን ካራመዱ ራስን ወደእሳት ውስጥ ማስገባት ይሆንባቸዋል። እኛም ብለን ነበር፤ የሚሰማን ጠፋ
እንጂ ማለታችንን አንተውም። ችግሮች ተባባሱ ከማለት ይልቅ መፍትሄ
አገኙ የሚል የምስራች የምናወራ እንድንሆን እንሻለን። አሁንም የሦስት
ረድፍ ቡድኖች ይታዩናል። ራሳቸውን አሸዋ ውስጥ ከተው የተደበቁ ቢመስሉም ዓመላቸው ስለማያስችላቸው ብቅ ብለው በቅርቡ ቦታ ቦታቸውን ሲይዙ እናገኛቸዋለን። የሆኖ ሆኖ ቤተ ክርስቲያኗን ብቻ ማዕከል
አድርገው የመሥራት ድርሻው በአዲሱ ፓትርያርክ ጫንቃ ላይ ወድቋል።
6/ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር ኅብረትና ስምምነት ማድረግ
ይህንን ሁሉ ሥራ ለመሥራት የሲኖዶሱ ኅብረትና ስምምነት አስፈላጊ ስለመሆኑ ምንም ጥርጣሬ የለንም። አንዱን በማቅረብና
ሌላውን በማራቅ የሚሰራ ሥራ ውጤታማ አይሆንም። በሁሉ ነገር ነገር ሙሉ ስምምነት መኖር ባይችል እንኳን ሰፊ ውይይትና አብላጫ ድምጽ
መኖሩ በራሱ እንደሙሉ ስምምነት ያስቆጥራልና ይህንን ማዳበር ካለፉት የሲኖዶስ ጉባዔዎች እንደተሻለ ተሞክሮ መጠቀም ተገቢ ነው እንላለን።
መከፋፈል፤ መምታት፤ መነጠል፤ ማሳደም፤ መግፋት የመሳሰሉት ከዚህ በፊት ተሞክረው የትም አላደረሱምና ከዚህ ዓይነቱ ጥቃቅን የሚመስል
ግን አደገኛ አካሄድ መጠበቅ ይበጃልም ጥቆማችን ነው። ሥልጣንን ሰብስቦ ሳይሆን በየደረጃው ከፋፍሎ ነገር ግን አስረክቦ ያይደለ ጠብቆ የመሥራት ጥበብ ጠቃሚ ነው። ወደታች ወርዶ ቄስ እስከመቅጠርና እስከማዛወር መሄድ ግን የፓትርያርክ አንባ
ገነንነት መገለጫ ነው። አሞራዎች ማንዣበባቸው የፍቅራቸው ጥግ ሰማይ
ስለደረሰ ሳይሆን የሹመት ጥንብ የት እንዳለ ለማየት ሲሉ እንደሆነ ወደ ላይ መሰቀላቸውን ማጤን ይገባል። ጣል ጣል ይደረግልን ማለታቸው እንደማይቀር ከዓመላቸው ተነስተን ብንገምት ግምታችን
ከእውነታው የራቀ አይደለም። ይህንን ይፈልጋሉና አዲሱ ፓትርያርክ በቅጥር ላይ ተጠምደው እጃቸውን ማድከም የለባቸውም። መንፈሳዊ የተባለው ሥልጣን ወዳጅ መጥቀሚያ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኗን ችግር
መፍቻ ማድረጉ ይበጃል። የቀድሞውን በነቀፉበት አፍ ራስን እዚያው ውስጥ ማስገባት በሰውም ያስተዛዝባል፤ ፈጣሪንም ያስቀይማል። ቢሞቱ ምን የመሰለ አባት ሞተብን እንጂ እንኳንም ተቀሰፈልን ከሚል ክፉ ስም
ለመጠበቅ ቢያንስ ራስንና የተናገሩትን ቃል መጠበቅ መልካም ነው።
ጠቢቡ በመጽሐፉ «ከመልካም ሽቱ መልካም ስም፥ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል» እንዳለው። በተቻለ መጠን ከመልካም ሽቱ ለተሻለው መልካም ስም መሥራት ብልኅነት ነው።
ስለዚህ ከሲኖዶስ አባላት ጋር ተስማምቶ መሥራት ለሁለንተናዊ የቤተ
ክርስቲያን እድገት ጠቃሚ መሆኑን እየገለጽን ሲኖዶሱን ለመጠምዘዝ ወይም ለማሽከርከር የሚፈልጉ ሰንጎ ያዢዎችንም እያስታገሱ መጓዝ ተገቢ መሆኑንም ሳንዘነጋ ነው።
7/ አቤቱታዎችን፤ እሮሮዎችንና ጩኸቶችን መስማት መቻል፤
ቤተ ክህነት የእሮሮና የአቤቱታ ፋብሪካ መሆኗ ይታወቃል። በአንድ ወቅት ምሬት ያንገሸገሸው የልጆች አባት፤ አንዱን ጳጳስ
በሽጉጥ እስከማስፈራራትና አንዱን ሹም እስከ መግደል ያደረሰው ጉዳይ
ምሬትና እሮሮን የሚሰማ ሰው በመጥፋቱ የተነሳ ነው። ይህ እሮሮና የምሬት ጩኸት እስከዛሬም ከቤተ ክህነቱ ግቢ አላባራም። የቤተ
ክህነቱ ቢሮ ይዘጋል። ባለሥልጣኑ ጩኸት አልሰማ ይላል። በዘመድ ወይም
በገንዘብ ድምጹ የሚታፈን ወገን ብዙ ነው። ልቅሶ
እና ወይኔን ይዞ
እንዲመለስ ይደረጋል። የፓትርያርክ ቢሮ ለመድረስማ እንዴት ይታሰባል? መንግሥተ ሰማይ በእምነትና በጥቂት ሥራ
መግባት ሲቻል ለመንበረ
ፓትርያርክ በር ግን እምነትና ምግባር ዋጋ የላቸውም። በእነሱ ፋንታ ገንዘብና ዘመድ በሩን ሁሉ ከፍተው ደንበኛቸውን
ይጋብዛሉ።
ይህ አባባል የሚያቅለሸልሽ ቢሆንም የተገለጠ እውነት ነው። አዲሱ ፓትርያርክ ከዚህ ጋር ብዙ ትግል ይጠብቃቸዋል።
የእሳቸው ቢሮም ወፍ እንዳያሾልክ ተደርጎ ካልተጠረቀመ በስተቀር ቤተ ክህነት በአቤቱታና በመብት ጥሰት እሮሮ
ከመሞላቱ የተነሳ
ባለጉዳይን እንዴት እንደሚያስተናግዱ ስናስበው ግራ ይገባናል። ከላይ
እስከታች ድረስ የአቤቱታ አቀራረብና የመፍትሄ አሰጣጥ መንገድ ካልተዘረጋ በስተቀር አዲሱ ፓትርያርክም ያለፈውን ደግመው በአዳራሻቸው
ጥቂት ወፋፍራሞችንና ጉንጫቸው ሊፈነዳ የደረሰውን ብቻ የሚያስተናግዱ የዘመነኞች ፓትርያርክ ሆነው እንዳይቀሩ እንሰጋለን።
ፍርድ የመስጠት ሥልጣኑ የነበራት ቤተ ክህነት በፍርደ ገምድል ሰዎች በመሞላቷ ከደረጃው የወረደ፤ ከሥራ የተባረረ፤ እድገት
የተከለከለ፤ ደመወዙን የተቀማ፤ በሀሰት ምስክሮች ወህኒ የማቀቀ ብዙዎች እንዳሉ እናውቃለን። ከዘበኛው ጀምሮ በየደረጃው ባለጉዳይን
እንደ ልጅነት ልምሻ በሽታ የሚያማቅቅ ሞልቷል። ለዓመታት የተከማቸውን ችግር ባንድ ሌሊት ማስወገድ እንደማይቻል ቢታወቅም ችግሩ
የት እንዳለ አውቆ ለማስተካከል መነሳቱ በራሱ የፍጻሜው መጀመሪያ ነውና በዚህ ዙሪያ ብዙ እንጠብቃለን። በየፍርድ ቤቱ የቤተ ክህነት
የክስ ፋይል እና በየከርቸሌው የቤተ ክህነት ተያያዥ ሰዎች ውሳኔ ዓለማውያኑን ሳይቀር በሚያሳፍር ደረጃ ላይ መገኘቱም የአደባባይ
ሐቅ ነው። ይህንን ሁሉ የቆየ እንቅፋት ለማስወገድ አዲሱ ፓትርያርክ ረጅም መንገድ ይጠብቃቸዋል።
የከተማ አወደልዳዩን እና በባህል መድኃኒት ሰበብ በየሰፈሩ ያለውንና በቤተክህነቱ ዓርማ የሚዘርፈውን አጭልግ ሁሉ አንድ ፈር ማስያዝ የወቅቱ ተግዳሮት ነው። እንደዚሁም
ሁሉ የሴቶች መብት የተከበረ እንደመሆኑ መጠን በተገቢ ሙያቸው ማሰራት አግባብ መሆኑ ባይካድም ባለሙያ ካህናት ሊሰሩ የሚችሉትን
ሥራ ሁሉ ምክንያቱ በታወቀና ባልታወቀ መንገድ ቤተ ክህነቱን የሴቶች ማኅበር አድርጎ መሰግሰጉም አንዱ ችግርና ሰሚ ያጣ እሮሮ ነው።
ያዝ ለቀቅና የአንድ ሰሞን ግርግር አድርጎ መተዉ የቤተ ክህነቱን
ስምና ክብር ሊጠግን አይችልም። ይህ ሁሉ ውዝፍ ሥራ አዲሱን ፓትርያርክ
የሚጠብቅ ነው። ቀድሶ ማቁረብና ቡራኬ መስጠት አባታዊ ተግባር መሆኑ ባይዘነጋም በየአድባራቱ በዓላትን ጠብቆ በመሄድ
ፈጣን ምላሽ የሚያሻቸውን ፋይል ጠረጴዛ ላይ እንዲወዘፍ ያደርጋልና «በሉ ተነሱ» በሚል ቀጭን ትእዛዝ መሄድ ጠቃሚ አይደለም። በታቀደና በተያዘ መርሐ ግብር ብቻ መመራትም እሮሮዎች እንዳይበዙ ያግዛልና
ይኼም ሊታሰብበት የሚገባ ይመስለናል።
ይህ ሁሉ የርእሰ መንበሩ ሰርቶ የማሰራት ኃላፊነት ነው። በባሌ ይሁን በቦሌ ስልጣንን በእጅ ማድረጉ ብቻ ለቤተ ክርስቲያን
ምንም አይጠቅማትም። ካለፈው ተምሮ፤ ያለበትን የአሁኑን ተንትኖ የወደፊቱን የሚያይ ባለርእይ መሪ እንጂ ቤተ ክህነት የሹመኛ ችግር
የለባትም። ስንወቃቀስ ሳይሆን ስንነጋገር ብቻ ነው ለችግራችን መፍትሄ ማምጣት የሚቻለው። አለበለዚያ በመጫጫህ አንድም ነገር ሳንሰራ ዘመናችን ያልፋል። እንግዲህ ቢሰራ
የምንመኘው፤ ካለፉት ሂደቶች ወደዚህ የተሻገሩ ናቸው የምንላቸውን ችግሮች በጥቂቱ አንስተናል። አጠቃላይ ጥናት ቢደረግ ደግሞ የገዘፈ
ነገር እንደሚኖር ይገመታል። ይህ የግል ምልከታ ነው። ከዚህ የግል ምልከታ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይሁን በከፊል ደስ የማይላቸው ወገኖች
ይኖራሉ። ደስ የማይላቸው ከራሳቸው ጥቅም አንጻር ሊሆን ይችላል ወይም ከማንም የተሻለ ጠቃሚ ርእይ አዘጋጅተው ይሆናል። እኛ ግን
እያየን ስንለው የቆየነውን ፤ ያዩትም ሲሉት የኖሩትን፤ ብዙዎችም
ሲሉት የደከሙበትን አጠራቅመን በትንሹ ማለት ያለብንን እነሆ ብለናል። ወደፊት ችግሮቹ እዚያው ሆነው ስናገኛቸው ደግሞ
ዳግመኛ ብለን ነበር እንላለን።ችግሩ ሲቀረፍ ደግሞ እሰየው ማለታችን
የግድ ነው። ችግሮቹ ካልተቀረፉም የሁሉም ሃሳብ ወደመሆን መሻገሩ አይቀርም። ያኔ ደግሞ አዲስ ፊት አይተን ምን አተረፍን፤ ምንስ አጎደልን? ማለታችን አይቀርም።
« ለዚሁ ነው በሬዬን ያረድኩት» ማለትም ይመጣል። ከዚያ በፊት ያለንበትን እና የምንሄድበትን ማየት እስካልተቻለ ድረስ «ጉልቻ
ቢለዋወጥ….» ከመሆን አይርቅም።
በስተመጨረሻም ብዙ ሥራ ከፊታቸው ለተደቀነው ለአዲሱ ፓትርያርክ
ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ መጪው ዘመን የሰላም፤ የፍቅር፤ የአንድነት፤
የእድገትና የመንፈሳዊ ብልጽግና ዘመን እንዲሆንላቸው እንመኛለን።