Tuesday, April 1, 2014

አንዳንድ “ማኅበራት” ራሳቸውን «ቅዱስ» ሲሉ በጣም ያስቁኛል...





 (an article by Tedy Sih) በመጠነኛ መሻሻል የቀረበ
መቸም ለጽድቅ የሚሰሩ ፖለቲከኞች እንደሌሉት ሁሉ ፖለቲካን ስራየ ብለው የሚሰማሩበትና በሱም ለፅድቅ የበቁ ቅዱሳን የሉም፡፡ ለፖለቲካ ሲሉ ተደራጅተው ራሳቸውን ‹‹ቅዱሳን›› ብለው የሚሰይሙ ደፋሮች ግን አይጠፉም፡፡ የፖለቲካ ግባቸውን ለማሳካት የሚከተሉት እኩይ የትግል ስነ ዘዴንም ጭምር ‹‹ቅዱስ ጦርነት›› ብለው የሚጠሩ ነፈዞዎችም ሞልተዋል፡፡ እኛ ሀገር ወስጥ በእንዲህ ያለ ፖለቲካ ላይ የተጣዱ ‹‹ቅዱሳን ፖለቲከኞች›› እንደምናየው ሁሉ ‹‹ቅዱሳን›› ገጣምያን፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን፣ ጥላቻ ቀስቃሾች፣ ጠብ ተንኳሾች፣ አመጽ ናፋቂዎች፣ ጦር አውርድ ባዮች ወዘተ መታዘብ ከጀመርን ሰነባብተናል፡፡ አሁን ደግሞ እነዚህን ሁሉ የሚያገናኘውን የሚስጥር ቋጠሮ ሊገልፅልን ፈልጎ በትጋት የተነሳ የሚመስል አንድ ‹‹ቅዱሳን ማኅበር»ኢህአዴግ ሊያጠቃኝ ተነስቷልእያለን ነው። ከስሞታው ዜና እንደምንረዳው ይህ ማኅበር ራሱን እንደፖለቲካ ፓርቲ እንደሚቆጥር እማኝነት ይሰጣል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከፖለቲካ የለሁበትም ማለትም ይከጅለዋል። ባለህንጻ፤ ባለሆቴል፤ ነጋዴና ገንዘብ የሚሰበስብ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ አልተሰማም። ተቋም ነኝ ወይም ድርጅት ነኝ ማለት አንድ ነገር ነው። ነገር ግን «ቅዱስ ማኅበር» እባላለሁ ቢለን «ቅዱሱ ማኅበር» ለማለት የሚያስችለን ምክንያት የለውም። ሲጀመር ብላቴ የጦር ካምፕ ተነሳ፤ ሲጨረስ በስመ ክርስትና ባለቢዝነስ መሆን ቻለ፤ እውነታው ይህ ነው። ማኅበሩና ቅድስና ከመነሻው እስካሁን  ድረስ አይተዋወቁም። በስምም ሆነ በግብር ከማኅበሩ ጋር የሚመሳሰሉ የቅዱሳን ታሪክ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ አልነበረም።
ከሁለት ዓመት በፊት ዲያቆን መልከጸዴቅ የተሰኘ የማኅበሩ አባል እንዲሁም የማኅበሩ መስራችና መሪ የነበረው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በጻፏቸው እማኝነቶች ማኅበሩየቄሳርን ለቄሳርየሚለውን ህግ በደፈጠጡ ህቡእ ፖለቲከኞች እንደሚመራ በስፋት ጽፈው አስነብበው ነበር። እስቲ ለዛሬ ከመልከጸዴቅ ጽሁፎች ቀነጫጭቤ ላቅርብላችሁ። በቀጣይ ክፍሎች ሙሉ ጽሁፎቻቸውን በተከታታይ አቀርባለሁ።
“...አዎ! ፖለቲካና ቅዱስነት ለየቅል ናቸው። ሰዎች ራሳቸውን በጀማ ቅዱሳን የሚል መጠርያ ሰጥተው በይፋ መንቀሳቀሳቸው ራሱ ችግሮች አሉበት። በጥላቻ የሚመራ ጽንፈኛ ዓለማዊ አጀንዳ ለማስፈጸም በፖለቲከኞች ሲደረግ ደግሞ ችግሮቹ የከፉ ናቸው። ቅድሚያ ነገር «ስም ይመርኆ ኅበ ግብሩ» ቅድስና ላይ አይሰራም። ቅዱስ ስም ፍጹም እምነትንና ቅዱስ ምግባርን ተከትሎ የሚመጣ ነገር ነው እንጂ ስምህን ቅድስት ወይም ቅዱስ ስላልክ ቅዱስ ትሆናለህ ማለት አይደለም። በተጨማሪም ጥቂቶችም ሆኑ ብዙሃን ተደራጅተው ራሳቸውን በወል ቅዱሳን ብለው መሰየማቸው የግብዝነታቸውና የትእቢታቸው መጠን ከፍ አድርጎ ከወደ ቤተ ሳጥናኤል እንደመጡ ይነግረን እንደሁ እንጂ ከእግዚአብሔር ቤት እንዳልሆኑ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በይበልጥም በአስተምህሮተ ቤተክርስቲያን ይህ ድርጊት መንፈስ ቅዱስን እንደመሳደብም ይቆጠራል። የቄሳርን ለቄሳር ቁም ነገር ያስተዋሉ የሚመስሉት የዘመናችን ፖለቲካዊ አስተሳሰቦችም ይህንን አይደግፉም። ከየትኛውም ቲዮሎጂያዊም ሆነ ዓለማዊ ፍልስፍና እና አመክንዮ አንጻር ሲታይም ድርጊቱ ርኩሰት ነው።
በስሙ በአመሰራረቱና በግብሩ ይህን መሰል ርኩሰት የተሸከመ ወገን በሃገራችን ስለመኖሩም ተጨባጭ ማስረጃ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያለ የለም። የማኅበሩ አባላት ሙሉ በሙሉ ፖለቲከኞች ባይሆኑም አመሰራረቱ፣ መስራቾቹና እስካሁንም እየመሩት ያሉት ፖለቲካኞች እንጂ ሃይማኖት መሪዎች አልነበሩም።አሁንም አይደሉም። እርግጥ በመንፈሳዊ ሰናይ ምግባር ቤተክርስቲያኗን ሊያገለግሉ ማኅበሩን የተቀላቀሉ ብዙ ቀና ወጣቶችና አባቶች ነበሩበት።አሁንም አሉ። እነሱም ስላሉ በጎ ገጽታ እንዲኖርው ስለማድረጋቸውም በማንም አይካድም። ቢሆንም እስትንፋስ ዘርተው ይዞት እንዲጓዝ የፈለጉትን ፖለቲካዊ ተልእኮ በማሸከም ማኅበሩን ያቆሙትና የሚመሩትታላላቅ ወንድሞችየሚል የኮድ ስም ያላቸው ፖለቲከኞች ናቸው።አሁንም ድረስ አመቺ ሽፋን በሚሰጥ ተቋም ውስጥ አድፍጠው ማኅበሩን ይመሩታል። ቆምኩለት ከሚለው መንፈሳዊ ተልእኮው ተጻራሪ ለሆኑ የጥላቻና የጥፋት እንቅስቃሴዎች መፈናጠጫ ፈረስ እድርገውታል።.....”
“...ማኅበሩ ስለ ፖለቲካዊ ስነፍጥረቱ እና ብላቴ ስለመመስረቱ አንዳችም ትንፍሽ አይልም። ስለ አመሰራረቱና ተልእኮው በማኅበሩ ድረ ገጽ የሚነበበውም የሚስጥራዊነቱና የአደናጋሪነቱ ተቀጽላ ሊባል የሚችል ነው። በአምላክና በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ 1984 .. በኢ... ሰንበት /ቤቶች ማደራጃ ስር መንፈሳዊ አገልግሎትና ምግባረ ሰናይ ለማስፋፋት እንደቆመ ይገልጻል። ግቡም በከፍተኛ ትም/ተቋማት ያሉ ወጣት ተማሪዎች ወንጌል በማስተማር ኃላፊነት የሚሰማቸው የቤተክርስቲያንና የሃገሪቱ አባላት ማድረግ ነው ሲል፤ ጥናት ተኮር ስራዎች በመስራትም የቤተክርስቲያናን ችግሮች ለመፍታት እንደሚጥር ይናገራል።...
እርግጥ በጎ አደራጎታዊ ስራዎቹንይበል! እባክህን እነሱን ብቻ አጠናክረህ ቀጥል፤ ቤተክርስቲያኗንም አገልግል!” ይሰኝባቸዋል እንጂ ማንም አይከፋባቸውም። ችግሩ ይሄኛው ገጹ የሚያምር ሽፋን ሁኖ ሌላኛውን ገጹ መደበቂያ መሆኑ ላይ ነው። ምስረታው ለፖለቲካ ሲባል ነበር። መስራቾቹም ፖለቲካኞች ናቸው። አንቀሳቃሽ ሞተሩ የሆነውን ፖለቲካዊ ተልእኮውንም ሆነ ተግባሩን እስካሁን በኅቡእ እየመሩ የሚያሽከረክሩትም በማኅበሩ ይፋዊ መዋቅር የማይታዩ ነገር ግን ወሳኝ ስልጣን ያላቸውታላላቅ ወንድሞችናቸው።...”
ከመልከጸዴቅ ዘማኅበረበኩር ጽሁፍ የተቀነጨበ