Monday, April 14, 2014

«ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ ከሆነ እኔም አክራሪ ነኝ» የሚሉ ድምጾች ምነው በዙሳ?



የሚያከሩ እስኪበጠስ ያክርሩ፤ የማያከርና ተግባብቶ የሚኖር የት ይድረስ?
 
በአንድ ወቅት ዳንኤል ክብረት የተባለው ሰውዬ በእንቁ መጽሔት ላይ እንደተናገረው «ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ ሆኖ የገደለው ሰው የለም!» ብሎ ነበር። በዳንኤል አስተሳሰብ «አክራሪ» ማለት በሃይማኖተኝነት ሰበብ ሰው የመግደል ደረጃ ላይ ሲደረስ መሆኑ ነው። ከመግደል በመለስ ያለው ኃይልና ዛቻ፤ማሳደድ ተፈቅዷል ማለት ነው? ሌላው የማኅበረ ቅዱሳን የሜሪላንድ አፈቀላጤ ኤፍሬም እሸቴ ደግሞ «አክራሪ ሃይማኖተኛ መሆን ጥሩ ነው» ሲል ተመራጭነቱን በማሳየት የማኅበረ ቅዱሳንን የማክረር እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ሲታትር ታይቷል።  አክራሪ በባህሪው እኔ ትክክል ነኝ ከሚል ጽንፍ ተነስቶ፤ የምለውን ተቀበሉኝ፤ እምቢ ካላችሁ ወግዱልኝ፤ አለበለዚያ እኔው በኃይል አስወግዳችኋለሁ በሚል ድምዳሜ የሚያበቃ አስተሳሰብ ነው።  አንዳንዶች አክራሪነት በዚህ ዘመን የተከሰተ አድርገው ሲመለከቱ ይታያል። ትርጉሙና የተግባራዊ እንቅስቃሴው ስፋትና ጥልቀት ተለይቶ ታወቀ እንጂ አክራሪነት ጥንትም ነበረ።  በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 9 ላይ እንደተመለከተው ኢየሱስ ለሐዋርያቱ እንደነገራቸው «አስቀድማችሁ ወደሰማርያ ከተማ ሂዱና፤ ጌታ ይመጣል ብላችሁ አስናድታችሁ ጠብቁኝ» ብሎ ባዘዛቸው ጊዜ የከተማይቱ ሰዎች መልዕክቱን እንዳልተቀበሉ ሐዋርያት ስለተመለከቱ «ጌታ ሆይ፥ ኤልያስ ደግሞ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን?» ብለውታል።  ጌታ ግን፤ «የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም» ብሏቸዋል።  አክራሪዎች ራሳቸውን የእግዚአብሔር ብቸኛ ወታደሮች አድርገው ራሳቸውን ያስቀምጣሉ። ስለዚህ እኛን ያልመሰለ ይጥፋ ባዮች ናቸው። አስተምሮ፤ ተከራክሮ መመለስ ስለማይችሉ አጭሩ መፍትሄ ማስወገድ ነው።
እንደዚሁ ሁሉ በፖለቲካው ከተሰማሩት ድረ ገጾች አንስቶ እስከጥቃቅኖቹ ብሎጎች ድረስ አንዱ ከአንዱ እየተቀባበሉ የማያውቁትን ማኅበር ለማሳወቅና ለሃይማኖት ማክረር እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ የሚገልጹ ጽሁፎችን እስከማራገብ ድረስ ዘልቀዋል።  በፌስቡክና በትዊተር ገጾች «ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ ከተባለ እኔም አክራሪ ልባል» ከሚለው ድምጽ አንስቶ የማኅበረ ቅዱሳንን ዓርማ የሚያሳይ ግለ ስእል በመለጠፍ አጋርነታቸውን ለማሳየት የሞከሩ ብዙዎች ናቸው።  ሁሉንም ስንመለከት «አክራሪ ሃይማኖተኛ» መሆን አስፈላጊ እንደሆነና «እኛም የዚሁ ሰልፍ አባሪ ሆነን ለሃይማኖታችን አክራሪ ነን» የሚል ይዘት ያለው አቋም እየተንጸባረቀ መገኘቱን መገንዘብ ይቻላል። ሃይማኖተኛ ነን የሚሉቱ ወገኖች ያሉበትን ምክንያት ከማየታችን በፊት ፖለቲከኞቹ ነገሩን ለማስጮህ የፈለጉበትን ምክንያት እንመልከት።

1/ ፖለቲከኞች ማኅበረ ቅዱሳንን የመደገፍ ምክንያት፤

ፖለቲከኛ ሃይማኖት የለውም ማለት ባይቻልም ሃይማኖተኛ ግን ፖለቲከኛ መሆን አይችልም። ፖለቲከኛ ሃይማኖት ሊኖረው የሚችለው ስለሃይማኖቱ አውቆና አምኖበት በመከተሉና እምነቱ የሚያዘውን ለመፈጸም እንደእግዚአብሔር ቃል ለመኖር ለራሱ ኪዳን የገባ ሳይሆን በውርስ ከቤተሰቦቹ የተረከበው ወይም በልምድ ሲከተለው ስለኖረ ራሱን ሃይማኖት እንዳለው አሳምኖ ሲያበቃ ከፖለቲካ የሚገኘውን የምድራዊ ሳይንስ ጫወታ የሚጫወት ሰው ነው።
 ምክንያቱም ፖለቲካ ባላጋራህ የሆነውን የሌላኛውን ሰው አመለካከትም ሆነ ተግባር በምትችለው መንገድ በልጠህ ወይም ጠልፈህ በመገኘት ምድራዊ ሥልጣንን መቆጣጠር ማለት ሲሆን ሃይማኖት ደግሞ የሰውን ልጅ ጠላትነት የማይቀበል፤ ባላጋራውም ሰይጣን ብቻ መሆኑ አምኖ ለእግዚአብሔር መንግሥት ሲል ሃይማኖታዊ መመሪያውን በመከተል ለማይታየው ሰማያዊ ሕይወት ሲል ከሚታየው ጠልፎ የመጣልና የመዋሸት ዓለም የጸዳ ማለት ነው። የዲሞክራሲ ጣሪያ ነክተናል ከሚሉት አንስቶ የነሱኑ መንገድ ተከትለናል እስከሚሉቱ ድረስ ሁሉም ፖለቲከኞች በፖለቲካል ቲዎሪ ከሚነገረው ታሪክ ባሻገር ማስመሰል፤ መዋሸት፤ ማታለል፤ ጠልፎ መጣል ወይም እውነተኛ መስሎ መታየት፤ ሀቀኛ፤ የህዝብ ወገንተኛ መሆንን መደስኮር በሁሉ ዘንድ መኖሩ በማስረጃ አስደግፎ መናገር ይቻላል።  በግርድፉ የተቀመጠውን የፖለቲካ ትርጉም ብንመለከት ለምድራዊ ስልጣን መታገል የመጨረሻ ግብ መሆኑ እውነት ነው።
« Politics is the activities associated with the governance of a country or other area, esp. the debate or conflict among individuals or parties having or hoping to achieve power»
« ፖለቲካ ከሀገራዊ ወይም ከክልላዊ የሕዝብ አስተዳደር ክንዋኔዎች ጋር በተዛመደና በተለይም በተቃርኖአዊ የእርስ በእርስ የሃሳብ ፍጭት የተነሳ ተስፋ በሚሰጥ የፓርቲዎች ስነ ሞገት ብልጫ አግኝቶ የስልጣን ኃይልን የመጨበጥ ግብ ያለው ነው»
ፖለቲካዊ ስልጣን ማለት ግን ለሃይማኖተኛ ጥቅም አይሰጥም፤ ወይም አይጎዳም ማለት አይደለም። እንደሚመራበት የፖለቲካ ርእዮት /አመለካከት/ ይወሰናል። ሃይማኖታዊ መንግሥት ባለበት ሀገር መንግሥቱ ለተመሰረተበት ሃይማኖት አብላጫውን ወይም ዋናውን አገልግሎት ይሰጣል። ሌሎች ሃይማኖቶች እንደመንግስታዊው ሃይማኖት እኩል መብት ሊኖራቸው አይችልም።  ሃይማኖት የለሽ መንግሥት ከሆነ ደግሞ ሁሉም ሃይማኖቶች የመንግስቱ ጠላቶች ነው። ሴኩላር/ ገለልተኛ/ የመንግስት አወቃቀር ባለበት ሀገር ደግሞ መንግስት በሃይማኖቶች ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ይደነግጋል። ጣልቃ የማይገባው ለሴኩላር መንግሥታዊ አወቃቀሩ ስጋት እስካልሆኑ ድረስ ብቻ ነው። እንደመንግሥታዊው የፖለቲካ አወቃቀር ሥርዓቱ ሃይማኖትን ሊጠቅም ወይም ሊጎዳው መቻሉ እርግጥ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ በአፄዎቹ፤ በደርግና በኢህአዴግ መካከል ባለው የፖለቲካ ርእዮት የተነሳ ፖለቲከኞቹ ሃይማኖትን የሚመለከቱበት መነጽር የተለያየ ነው። ሃይማኖትን በተለያየ መነጽር የሚያዩ ፖለቲከኞች፤ ሃይማኖተኞች ሊሆኑ አይችሉም።  ፖለቲከኞች የቆሙለትን የተለያየ የፖለቲካ ስርዓት ያገለግላሉ።  ፖለቲከኛ ሆኖ ሃይማኖተኛ ለመሆን ከባድ የሚሆነው ለዚህ ነው። ሃይማኖተኛ ሆኖ መዋሸት አይቻልም። ፖለቲከኛ  ስርአቱን እስከጠቀመ ድረስ ይዋሻል፤ የሌለ ተስፋ ይሰጣል።  አላስፈላጊ ወይም ጠቃሚ ካልሆነ ደግሞ ማስተባበያ ወይም ይቅርታ ሊጠየቅ ይችላል። ለሃይማኖተኛ ንስሀ እንጂ ማስተባበያ ወይም ይቅርታ የሚል የአደባባይ ዲስኩር የለም። ፖለቲከኛ ሃይማኖት ሊኖረው ቢችልም ሃይማኖተኛ ግን በጭራሽ ፖለቲከኛ መሆን አለመቻሉ እርግጥ ነው። ታዲያ የልምድ ሃይማኖት ያላቸው ነገር ግን ሃይማኖተኛ መሆን የማይችሉ ፖለቲከኞች ማኅበረ ቅዱሳን ሲነካ የሚጮሁት ለምንድነው? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት። ዋናው ነጥብ «የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው» ከሚል የፖለቲካ ፍልስፍና የተነሳ ነው። 

 ሃይማኖት የሌላቸው /እምነት የለሾች/ ይሁኑ ማኅበረ ቅዱሳንን በልምድ የሚመሳሰሉ ባለሃይማኖቶች እና «ማኅበሩ ተነካ ማለት የእግዚአብሔር መንግሥት ተነካ» ባይ የዋሆች ሁሉም በአንድነት ውጥንቅጡ በወጣ አቋም ውስጥ ሆነው ለማኅበሩ ለመጮህ ሞክረዋል። የሚገርመው ደግሞ የማኅበረ ቅዱሳንን መጥፋት የሚመኙ እስላሞች ሳይቀሩ «የሃይማኖት ነጻነት ይከበር» በማለት ለማኅበሩ ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት መሞከራቸው ነው። ዋነኛ ዓላማቸው የሃይማኖት መከበር ስላሳሰባቸው ሳይሆን በእስልምና ጎራ ያሉ ታሳሪዎችን ድምጽ ከማኅበረ ቅዱሳን ጎራ ካሉት ጋር በማስተሳሰር ጉዳዩን ለማጦዝ ከመፈለግ የተነሳ ነው።  በዘመነ ኢህአዴግ እስልምና ተጨቁኗል ቢሉ ለሰሚው ግራ ነው።  በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ የእስላም መስጊድ ከቤተ ክርስቲያን ቁጥር የበለጠው በዘመነ ኢህአዴግ መሆኑ በጭራሽ ሊስተባበል የሚችል አይደለም።  ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ 16% ለሆነው የእስልምና ተከታይ 180 በላይ መስጊዶች ሲኖሩት 74% ከመቶው ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ቁጥር 150 ገደማ ብቻ ነው። በኦርቶዶክስ ተጨቁነን ነበር የሚሉትን አቤቱታ እንደኢህአዴግ ያካካሰላቸው መንግስት ለእስላሞች የለም ማለት ይቻላል። በዘመነ ኢህአዴግ የተሰራው መስጊድ በሺህ ዘመናት ውስጥ ከተሰራው ይበልጣል።
 እንዳላት ተከታይ ብዛትና ሊኖራት እንደሚችለው የድርሻ ስፋት ድምጿ ያልተደመጠው ኦርቶዶክስ ናት ማለት ይቻላል። ከመንግሥታዊ ክፍል ያሉ፤ ፕሮቴስታንቱም፤ እስልምናውም፤ ኦርቶዶክሳዊ ነኝ የሚለው አሮጌ ፖለቲከኛው ሁሉንም ስንመለከት በግልጽም ይሁን በስውር ይህች ቤተ ክርስቲያን ለሀገሪቱ ባበረከተችው ከመጠቀምና በስሟ ከመነገድ በስተቀር ያደረጉላት አንዳችም ድጋፍ የለም። ላበረከተችው በጎ አስተዋጽኦ ዋጋ መስጠት በራሱ ትልቅ ነበር።

ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን «ልጠፋ ነው» እያለ ለሚያሰማው ጩኸት ፖለቲከኞቹን ያስተባበራቸው ኢህአዴግን እንደጋራ ጠላት ለመፈረጅ እንጂ በሃይማኖት ስለተሰሳሰሩ አይደለም። ኦርቶዶክስ እንድትጠፋ ሲሰሩ የቆዩ የቀድሞ መንግስት ፖለቲከኞች፤ የተለያዩ የሌኒናዊ ፓርቲ አባላትና ርዝራዦች ሳይቀሩ ለማኅበረ ቅዱሳን ሲጮሁ እያየን ነው። እውን ለኦርቶዶክስ አዝነው ነው? የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖታዊ መሪዎች ከመግደል አንስቶ፤ ጣልቃ ገብቶ በመሾም፤ ሲኖዶሱን በመከፋፈልና በማዳከም ትልቅ ድርሻ ያላቸው እነዚህ ጮኸው የማይሰለቹ ፖለቲከኞች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳንን ለመደገፍ መሞከራቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን የማዳከም ቀጣይ ተግባራቸው ማሳያ ተደርጎ ከሚወሰድ በስተቀር ቤተ ክርስቲያኒቱ ከማኅበሩም ሆነ ከፖለቲከኞቹ ያተረፈችውም ምንም ነገር የለም።

2/ ሃይማኖተኞች የማኅበሩ ደጋፊዎች፤

ማኅበሩ ራሱ እንደሚለው ከሆነ 35,000 መደበኛ አባላትና 500,000 ተከታይ አባላት እንዳሉት ይነገራል። ያለውን የፋይናንስ አቅም በትክክል ባይናገርና ባናውቅም ቅሉ ከልዩ ልዩ የንግድ ተቋማት ገቢ ምንጮቹ የሚያገኘውን ካፒታል ሳንጨምር ከ35,000 አባላቱ ላይ ብቻ በግርድፉ ብንገምት በወርሃዊ መዋጮ መልክ 10 ብር ቢሰበስብ 350,000 ብር ወርሃዊና ከ500,000 ተከታይ አባላቱ ላይ ደግሞ ለልዩ ልዩ የማኅበሩ ልማታዊ ስራዎች ሰበብ በዓመታዊ ድጋፍ 10 ብር በነፍስ ወከፍ እንዲሰጡት ቢጠይቅና ካሉት ተከታይ አባላቱ መካከል 400,000 ያህሉ ለ10 ብር የድጋፍ ጥያቄው ምላሽ ቢሰጡ 4,000,000 ብር ያገኛል ማለት ነው። ከወርሃዊ  የአባልነት መዋጮ ገቢው ጋር በዓመት ሲሰላ ከ8 እስከ 9 ሚሊዮን ያላነሰ በዓመት ይሰበስባል ማለት ነው። ይህ ስሌት በመንፈሳዊ ጉዞ ሰበብ፤ በመጽሔት፤ በሆቴልና በሱቅ ሽያጭ፤ በካሴት፤ በሲዲ፤ በእርዳታ ጥሪ፤ ከበጎ አድራጎት፤ ከለጋሽ፤ ከቤት ኪራይ ወዘተ የሚገኘውን ግዙፍ ገቢ ሳይጨምር መሆኑ ታሳቢ ይደረግ።  ጆርጅ በርንስ እንዲህ ይላል። « Don't stay in bed, unless you can make money in bed»  «አልጋህ ላይ ሆነህ ገንዘብ ካላገኘህ በቀር አልጋህ ላይ አትቆይ» እንደማለት ነው። ይህ ብሂል የገባው ቅዱስ ማኅበር «መኒ» ይሰራል። «መኒ» የማይገዛው ስልጣን፤ ጉልበትና እውቀት በሌለበት ዘመን የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር አይባልም።

ይህ ማኅበር ከአንታርክቲካ በስተቀር በሁሉም ዓለማት ላይ ቢሮዎች አሉት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ቦታ ሁሉ አለ። በሳንባዋ ይተነፍሳል፤ በደም ስሯም ይዘዋወራል። ነገር ግን መዋቅሩና የመዋቅሩ መረብ ማኅበረ ቅዱሳዊ ነው። አብዛኛው አባላቱና ደጋፊዎቹ አብረው የተሰለፉት ቤተ ክርስቲያኒቱን የደገፉና የረዱ እየመሰላቸው መሆኑ እርግጥ ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር ከዘመኑ ጋር መዘመን ባይችልና ባንቀላፋበት ቦታ ሁሉ ማኅበሩ እየተገኘ ከበሮ እየመታ፤ እየዘመረ አለሁልሽ እያለ ማኅበሩንና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለይቶ የሚያይ ተከታይ ባይኖር አያስገርምም።  የሚገርመው እንመራሃለን የሚሉቱ የማኅበሩ ተመሪ ሆነው መገኘታቸው ነው።

ሀ/ ሊቃነ ጳጳሳቱ፤

ሊቃነ ጳጳሳቱን ማኅበሩ እንዴት አባል አድርጎ እንደሚይዝ ዝርዝር ውስጥ አንገባም። ነገር ግን ሊቃነ ጳጳሳቱ የሲኖዶስ አባልና በቤተ ክርስቲያኒቱ የአንዱ ሀገረ ስብከት ወይም ክፍል ተጠሪ ሆነው ሲያበቁ የማኅበሩን ዓላማ ተቀባይ፤ የማኅበሩ ጠበቃና ተከራካሪ ሲሆኑ ግርምት ይፈጥርብናል። ዋናው ጥያቄ የሚነሳውም ማኅበሩ የሲኖዶሱ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ነው ወይ? ሊቃነ ጳጳሳቱ በሀገረ ስብከታቸው መሥራት ያልቻሉትን የሚሰራላቸው ወኪላቸው ነው ወይ?  ምን መስራት ያልቻሉትን፤ ምን መስራት እንዲችልላቸው፤ የትኛውንስ ጉዳይ እንዲያስፈጽም ውክልና ተሰጥቶታል?
 በማኅበሩ ስያሜና ቁመና እንዲሁም በሲኖዶስና በሊቃነ ጳጳሳት መካከል ያለው የሥልጣን፤ የደረጃ ክፍተት የሚለካው በምንድነው? የሚሉ ጥያቄዎች ግራ የሚያጋቡና ምላሻቸውንም በውል የሚያውቅ አለመኖሩ ጉዳዩን አስደማሚ ያደርገዋል።  ስለዚህ ጥርት ያለ መልስ የሌለው የአንድ ማኅበር ዓላማ በአእምሮአቸው የሰረጸ ነገር ግን የሲኖዶስ አባል ነን የሚሉ ሊቃነ ጳጳሳት በአንድም፤ በሌላ መንገድም የማኅበሩ ጉዳይ ፈጻሚ ሆነው መገኘታቸው እርግጥ ነው።

ለ/ ወጣት የሰንበት ት/ቤት አባላት፤ የጥምቀት ተመላሽ ማኅበር፤ የጉዞና መንፈሳዊ ማኅበራት፤

እነዚህ ወጣት ክፍሎች ከማኅበሩ ሰፊና ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ አንጻር በቁጥጥር ስር መዋላቸው የግድ ነው። ደግሞም አስፈላጊ መሳሪዎች ናቸው። በአንድ በኩል በችግር ወቅት ለማንቀሳቀስ፤ በሌላ መልኩም በችግር ቀን ለመደበቅ ሊያገለግሉ ይችላሉ። መሰረታዊ የትጥቅ መሳሪያቸው ደግሞ «ቤተክርስቲያንን ከልዩ ልዩ ኃይሎች መጠበቅ» የሚል መንፈሳዊ መሰል ትጥቅ ሲሆን ወጣቶቹ ዓይናቸውን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በእምነት እንዲጥሉ በማድረግ ማኅበሩ ለሚፈልገው ዓላማ ማገልገል እንዲችሉ ተደርገው ይቀረጻሉ። ወጣቶቹ በእርግጥም ከልባዊ እምነት ተነስተው የሚከተሉ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያንን እንደማገልገል እንጂ ማኅበሩን እንደመታዘዝ አይቆጥሩም ወይም ማኅበሩን ማገልገል የቤተ ክርስቲያኒቱን ፈቃድ እንደመፈጸም አድርገው እንዲያስቡ ተደርገዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ሰንበት ተማሪዎች፤ የጥምቀት ተመላሽ ቡድኖችና የጉዞ ማኅበራት የማኅበሩ ታዛዥና ተጠባባቂ ኃይሎች ናቸው። የእነዚህ ማኅበራት አባል ሆኖ ማኅበረ ቅዱሳንን ማውገዝ ወይም መቃወም በጭራሽ አይታሰብም።

ሐ/ የመንግሥት ተቋማት አባሎቹ፤

ማኅበሩ ከሚያገኘው ሰፊ የፋይናንስ አቅም አኳያ አባላትን ለመመልመል መጠቀሙ እንዲሁም ከሚጓዝበት አደገኛ የስብከት ዘዴው አንጻር አእምሮአቸውን የመጠምዘዝ ስልት ረገድ በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ብዙ አባላትን ማደራጀት ችሏል። የማኅበሩን አቅም ማደራጀት ብቻ ሳይሆን አንድ አቅጣጫ ማየት እንዲችሉ ተደርገው የተቀረጹ የመንግሥታዊ ተቋማት አባላቱ በጣም ጠቃሚ ክፍሎቹ ናቸው።  በመንግሥት ጉዳይ እንደማይገቡ ማሳያዎቹ ናቸው። በሌላ መልኩም የመረጃ ምንጭ ሆነውም ያገለግላሉ። የየትኛውም የመንግሥት ተቋማት ሰራተኛ በየትኛውም ማኅበርና የእምነት ተቋም ውስጥ አባል የመሆን መብት ያለው መሆኑ ባይካድም የያዘውን የመንግስት ስራ ለማኅበሩ አገልግሎት ማዋል ግን ወንጀል ነው። ፖሊሳዊ ስልጣናቸውን በመጠቀም ለማኅበሩ አገልግሎት ተሰማርተው ያላግባብ ያሰሩ፤ የደበደቡ አሉ። ቤተ ክርስቲያኒቱ ስትጠይቃቸው ከመተባበር ይልቅ ማኅበሩ ሲጠራቸው አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጡ የመንግሥታዊ ስልጣን አካላት መኖራቸው ማኅበሩ የቱን ያህል ስር እንደሰደደ ያሳያል። እነዚህ አካላት ከማኅበሩ ጎን በግልጽም፤ በስውርም መቆማቸው ነገሩን ከባድ ያደርገዋል።

3/ ማኅበሩ ራሱን ለማዳን የሚቀያይራቸው ስልቶች፤

ማኅበሩ የልዩ ልዩ ሰዎች ተዋጽኦ መሆኑ እንዳለ ሆኖ አመራሩ ራሱን ከወቅቱ የፖለቲካ ሙቀት ጋር በማስማማት የሚያደርጉት የጉዞ ስልት እጅግ የሚደነቅ ነው። ማኅበሩ ሃይማኖታዊ ድርጅት እንዳይደለ ይታወቃል። የድርጅት/ Organization/ ቅርጽ ያለው ነገር ግን በተቋምነት/ Institution/ ደረጃ የተደራጀ ይመስላል። ደግሞም በቤተ ክርስቲያን ስር ያለ የሰንበት ተማሪዎችም ማኅበር ለመምሰልም ይሞክራል። ምሁራን አመራሩ በሳል ስለሆኑ ከሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ መምሪያ ስር ያወጡት አለምክንያት አይደለም። የሰንበት ት/ቤት በመባልና የሚንቀሳቀስበት ቅርጽ ተመሳሳይ ስላይደለ እንዳይበላሽበት ከመፈለግ የተነሳ የተዘየደ መላ መሆኑ ነው። ዛሬም ያ የማኅበሩ አመራር ኢህአዴግ ከገባበት የሙስሊሞች እንቅስቃሴ፤ ከምርጫ 2007 ዝግጅት እና የጥላቻ ፖለቲካ ካሰባሰባቸው ኃይሎች ጋር ያለበትን ክፍተት በመጠቀም ከመንግሥት ጋር ያለውን ልዩነት ለመጠቀም እየሰራ ይገኛል። በአንድ ወገን ስለማኅበሩ ጉዳይ እያስጮኸ ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ከጩኸቱ በሚገኘው የስውር ድምጽ ብዛት መንግሥት ወደያዘው ፤ልቀቀው እሰጥ አገባ እንዳይሄድ ባለበት በማስቆም ለመንግስት ፈቃዳት ሁሉ ታማኝ መሆኑን ለማሳየት በመሞከር ራሱን በማዳን ስልት ላይ ተጠምዷል። የቅዱሳን ማኅበር ሳይሆን ጠንካራ የፖለቲካ ቅዱሳን ያሉት ማኅበር ስለሆነ ሊደነቅ ይገባዋል።

4/ ማኅበሩና የመጨረሻ ውጤቱ፤

በትግርኛ የሚተረት አንድ ተረት አለ። «ወጮስ እንተገምጠልካዮ ወጮ» ይላሉ። «ብርድ ልብስን ብትገለብጠው ያው ብርድ ልብስ ነው» እንደማለት ነው። ያውም የደብረ ብርሃን ብርድልብስን ብትገለብጠው ያው ዥንጉርጉሩ  የደብረ ብርሃን ብርድ ልብስ ነው። የሰንበት ት/ቤት?/Sunday school/  ድርጅት? /organization/ ተቋም? /Institution/ የቱ እንደሆነ ማኅበረ ቅዱሳን እስካሁን የለየለት አይደለም። ነገር ግን ቅርጹንና መልኩን እንደእስስት እየቀያየረ 22 ዓመት ቆይቷል። ቤተ ክርስቲያኒቱ ለማኅበሩ ምኑ እንደሆነች ሲኖዶሱ በእርግጥ አያውቅም። ማኅበሩ ግን ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዴት እንደሚጠቀምባት አሳምሮ ያውቃል። በጣም አደገኛና ስልታዊ ጉዞ የማድረግ ብቃት ያለው አመራር እንዳለው በጉዞው ላይ የሚያጋጥመውን ሳንካ ካለፈበት ተነስቶ መናገር ይቻላል። እውነተኛና ቅን የቤተ ክርስቲያን አባላት የሱም አባል መሆናቸው ሳይዘነጋ ማለት ነው። ነገር ግን ማኅበሩ  ቢደግፉት፤ ቢከተሉት፤ ቢጮኹለት፤ ቢታገሱት እንደ«የደብረ ብርሃን ብርድ ልብስ ቢገለብጡት ያው ብርድ ልብስ» ከመሆን የሚያልፍ አይደለም!!