ሰው መሆን ከቻልን ስደትም ያልፋል!


ማንንም መውቀስ አንሻም። እየሆነ ያለውን ግን ከመናገር አንቆጠብም። ኢትዮጵያውን ዓለሙን ሁሉ እንደጨው ዘር ተበትነው መሙላታቸው እውነት ነው። ከደርግ ዘመን ልደት ጀምሮ የፖለቲካና ከረሀብ የመሸሽ ስደት እንደአማራጭ የተወሰደ ሲሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ብሶበታል። ሰው «ብሞትም ልሙት» በሚል መንገፍገፍ ሀገር ለቆ መሰደድን እንደአማራጭ ሳይሆን ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል። የሞቱ፤ መከራ የደረሰባቸውና የተጎዱ እንዳሉ እያየ፤ እየሰማ ይሰደዳል። በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ሰው ለማለፍ መሰደድን የሚመርጠው ለምንድነው? ብሎ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው። ዓይናችንን ጨፍነን ከእውነታው ለማፈግፈግ ካልፈለግን በስተቀር ኢትዮጵያ የኔ ናት፤ ሠርቼ ልኖርባትና ልለወጥባት እችላለሁ የሚል ስሜት ከውስጡ ያለቀ ይመስላል። ሁሉም ስደተኛ በተመሳሳይ ሁኔታ ስለሚገኝ ይሰደዳል ባይባልም አብዛኛው ግን የኢኮኖሚ አቅሙ እንደሰው ለማኖር ስላልስቻለው ማንኛውንም ሥራ ሰርቶ የተሻለ ክፍያ በማግኘት ራሱን መለወጥ ወደሚችልበት ሀገር መሰደድን እንደሚመርጥ ለማወቅ ምርምር አይጠይቅም። የሕይወታችን አንዱ ገጽታ ስለሆነ እናውቀዋለን።
  ሀገር ውስጥ ባለው ልማትና እድገት ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ብዙዎች መሆናቸውም አይካድም። የሚጨበጥ፤ የሚዳሰስና የሚታይ እድገት መኖሩም እውነት ነው። የእድገቱ መነሻና ሂደት፤ መጠንና ስፋት፤ የተጠቃሚነት አንጻራዊ ሚዛንን እንዴትነት በተመለከተ ለባለሙያዎቹ ትንተና ትተን ለስደት የሚዳርገውን አንዱን ነጥብ በመምዘዝ የስደት እንግልቱን ልክ ለመመልከት እንሞክር።

በቅርብ የማውቀው ወዳጄ በባህር አቋርጦ የመን፤ ከዚያም ሳዑዲ ዐረቢያ፤ በለስ ቀንቶት ወደአንዱ አውሮፓ ሀገር ከመሻገሩ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት በመምህርነት ይሰራ ነበር። ደመወዙ ተቆራርጦ አንድ ሺህ ከምናምን ብር እንደነበር አውቃለሁ። ለአካለ መጠን ከደረሰ በኋላም ቢሆን ከወላጆቹ ጋር ተዳብሎ እንዳይኖር ቤተሰቦቹ ያሉት ክፍለ ሀገር ነው። ስለዚህ ቤት ተከራይቶ ከመኖር ውጪ በረንዳ እያደረ አስተማሪነቱን ሊቀጥል አይችልም። በወር 700 ብር እየከፈለ አራት በአራት በሆነች ጠባብ ክፍል እየኖረ ጊዜ ለማይሰጠው ለሆዱና ካላስተማረ ስለማይከፈለው ለትራንስፖርት የምትተርፈውን ገንዘብ እናንተው ገምቱት። የልብስ ጉዳይ በዓመት አንዴ ለዚያውም የሆነ መና ነገር ከወረደለት በቂ ነው። ቤት ሰርቶ፤ ሚስት አግብቶ የሚባለውን ነገር ሌሎች ሲያደርጉት በማየት ከሚጎመዥ በስተቀር አስቦትም፤ አልሞትም አያውቅም። የሀገሬ ሰው «እዬዬም ሲደላ ነው» ይል የለ!
  የኮንዶሚኒየም ቤት ምዝገባ ቤት ለሌላቸው የሚል ይመስለኛል። ይህ አስተማሪ ወዳጄ ቤት ከሌላቸው ሰዎች ግንባር ቀደሙ ነው። ነገር ግን የኮንዶሚኒየም ቤት ለሌላቸው የሚለው መስፈርት ይህንን ወዳጄን አይመለከተውም። ወዳጄን ቤት ከማግኘት የከለከለው ቤት ስለነበረው ሳይሆን ገንዘብ መክፈል ስላልቻለ ብቻ ነው። እናም ኮንዶሚኒየም ቤት ለሌላቸው ሳይሆን መክፈል ለሚችሉ የሚሰጥ በመሆኑ ወዳጄ ኢትዮጵያ ውስጥ መቼም ቢሆን  ቤት ለመሥራት ወይም ለመግዛት እንደማይችል ስለተረዳ ቀለም የሚዘራበትን፤ አዲስ ትውልድ የሚፈጥርበትን የመምህርነቱን ሥራ ትቶ እየቆሙ ከመሞት፤ እየሄዱ መሞትን ምርጫው አድርጓል። በአንድ ወቅት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምህራን የሚሆን የጋራ ቤት የመሥራት ጉዳይ ሊኖር እንደሚችል ሰምቼ ነበር። ምን እንደደረሰ አላውቅም። የሆኖ ሆኖ ከኑሮው ውድነት ማለትም የቤት ኪራዩ፤ የቀለብ ዋጋ፤ የትራንስፖርቱ እጥረት፤ የሥራ ቦታ ጫና ተዳምሮ በሚፈጥረው ኅሊናን ሞጋች የዘወትር የሃሳብ ተጽዕኖ ሥር የወደቀው ወዳጄ ለስደት ቢዳረግ ብዙም ሊያስገርመን አይገባም።

ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካውን ወሬ ትተን እንደሰው ለመኖር ሦስት ዋና ዋና ነገሮችና ዐራተኛው የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነጥብን ማግኘት አስፈላጊ ይመስሉኛል።
  1/ የምግብ እህሎች ዋጋና አቅርቦት አለመመጣጠን ያስከተለው ንረት በአስቸኳይ ማስተካከል ካልተቻለ እድገታችን ካላመጣው ገቢ ጋር እንዴት መኖር እንደሚቻል አይገባኝም። የጠገበ የተራበ ያለ ስለማይስለው ካልሆነ በስተቀር ውድነቱ መግለጽ ከሚቻለው በላይ ነው።

 2/ የቤት ኪራይ ዋጋን ማርገብ፤ የቤት መሥራት አቅምን ማመቻቸት፤ ለሽግሩ ደራሽ አማራጭን መፈለግ የግድ ይላል።  ሰው በልቶ ለማደር ቤት ያስፈልገዋል። የሰው ቁጥርና የመኖሪያ ቤት አይመጣጠንም። ኪራይ ተወደደ፤ ቤት ለመሥራት አቅም የለም። መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ እየጣረ ቢሆንም የችግሩ ግዝፈት እየተሄደ ካለበት መንገድ ጋር አይመጣጠንም።  በአንድ ዓይነት መንገድ ማለትም የኮንዶ ቤቶች ግንባታ ላይ ችክ በማለት የተለያዩ አማራጮችን  የማመንጨት  ችግር አለ።  
  3/ እያደገ ለመጣው የስራ አጥ ቁጥር አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት ወቅታዊና አንገብጋቢ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ገቢና ኑሮ ካልተመጣጠኑ ስደት መቼም አይቀርም። 30 ሺህ ቢመጣ፤ 60 ሺህ መውጣቱን አያቆምም። «የማይሰራ አእምሮ የተንኮል ጎተራ ነው» ያለው ማነው? ግድያ፤ ቅሚያ፤ ዘረፋና ስርዓተ አልበኝነት እንዳይመጣ በሥራ መጥመድ ከሚመጣው ተንኮል ሊታደግ ይችላል። ሥራ ፍጠሩ ይባላል። ከሜዳ ተነስቶ ሯጭ መሆን አይቻልም። ዋጋ ያለው ሩጫ ምን እንደሚመስልና ጥቅሙን ማስረዳት ተገቢ ነው። ያለበለዚያ ዝም ብሎ ሩጫ እብደት ነው። ቁጭ ማለትን ለተለማመደ ሥራ አጥ፤ ሥራ እንዴት መፍጠር እንደሚቻል መንገድ ማሳየት ተገቢ ይመስለኛል።

 አራተኛውና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ጉዳይ ማንኛውም ዜጋ በሀገሪቱ ውስጥ ተንቀሳቅሶ በመስራት ሀብት ማፍራት የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። ሕገ መንግሥቱ ይህንን ይፈቅዳል ቢልም መሬት ላይ ያለው እውነታ ለየቅል ናቸው። ተንቀሳቅሶ በሕጋዊ ሥራ፤ ሕጋዊ ሀብትን ማፍራት መቻል በራሱ የስራ አጥ ቁጥርን ይቀንሳል። አዲስ አበባ ላይ መሬት በሊዝ ገዝቶ ቤት ለመሥራት በቂ ገንዘብ የሌለው ሰው፤ ዲላ ሄዶ በአቅሙ መስራት ከቻለ ወይም ለመነገድ የሚከለከልበት ምክንያት አይገባኝም። የክልሉ ነዋሪ የሚለው ዜማ እንደሀገር ለማስቀጠል አቅም የሌለው ርካሽ ቃል ነው።
  ፖለቲካው የራሱ መንገድ ቢኖረውም ያለፖለቲካ ለመኖርም እንኳን ምግብና መጠለያ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም። ዝንጀሮ «አስቀድሞ መቀመጫዬን አለች» አሉ ይባላል። ኢትዮጵያዊያን ወደሳዑዲ ዐረቢያ የተሰደዱት ዲሞክራሲን ፍለጋ ሳይሆን ዳቦ መግዢያ ለማግኘትና ሳዑዲዎችም ኢትዮጵያውያንን እየገደሉና እየደበደቡ ያባረሩት በፖለቲካዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ስለተንበሸበሹ ሳይሆን በፔትሮ ዶላር ስካር ስለጠገቡ ብቻ ነው።
  የኢትዮጵያ ምድርና ሕዝብ ከሌላው በተለየ እርግማን የለበትም። እግዚአብሔርም ስለጠላን የደረሰብን ቁጣ አይደለም። መንግሥታችን እየሰራ ቢሆንም ችግሩ እየጨመረ የመሄዱ ዋና ምክንያት ብዙ መስራት ስላልቻለ ነው። ብዙውን ጊዜ ለወሬና ለስብሰባ፤ ትንሹን ጊዜ ለሥራ ስለሰጠ ነው። ችሎታ የሌላቸው ሰዎች አመራሩን ሲይዙ ሥራ ፈቀቅ አይልም። ውሸት እውነትን ከተካው መንግሥቴ ታማኝ ነው የሚል አይገኝም። ሌብነት ሥራ ከሆነና ፍትህን ቁልቁል ከደፈቁት እንኳን መገንባት፤ የተገነባው ራሱ ይፈርሳል።  «የትም ሥሪው ወንበሩን አምጪው» ሀገርና ሕዝብ ይጎዳል።  ቀናነትና ሀገራዊ ቀናዒነት ከሌለን ኢትዮጵያዊ ለመሰኘት የሚያችለን ምናችን ይሆን? ቀናነት ጠፍቷል። ቀናዒነትም ደብዛው የለም። እንደእሪያ ለራስ በልቶ፤ ለራስ ኖሮ፤ በኅሊና ቆሻሻ ውስጥ መጨቅየት ጥሩም አይደል።  ኢትዮጵያዊ መሆን ባንችል ሰው እንሁን። ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሰዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያዊ ውስጥ ገብተው በጉልበታቸውና በሙያቸው እያገለገሉ ያሉት ሰው መሆን በመቻላቸው ይመስለኛል። ብር፤ስንዴና ዘይትስ የሚረዱንም ሰዎች በመሆናቸው እንጂ ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ አይደለም። ሰው መሆን መቻል በራሱ ለሰው ደራሽነት ትልቅ ድርሻ አለው።  እግዚአብሔር ሰው እንድንሆን ይፈልጋል። በአርአያውና በምሳሌው የፈጠረን እንደሰው ተፈጥረን እንደእንስሳ እንድንኖር አይደለም። እኛ ወደን ባመጣነው ስግብግብነት የተነሳ የመጣብንን ስደት ከእግዚአብሔር የተሰጠንን እድል አድርገን ልንቆጥር አይገባም። ስስት፤ ስግብግብነትና የቀናነት እጦት እንስሳዊ ጠባይ ነው። የቤት እንስሳት ሳይጣሉ የተሰጣቸውን ተስማምተው መብላት አይችሉም። በእኛም ዘንድ ይህ ይስተዋላል። ለሥልጣን ስስት፤ ለገንዘብ ስስት፤ ለሹመት ስስት አለ። ስግብግብነትና ቀና አለመሆን ሲከተሉት ጠኔና ችጋር ሊጠፋ አይችልም። እስኪ ሰው እንሁን። ይህም ዘመን ያልፍና እንዲህም አሳልፈን ነበር የምንልበት ቀን ይመጣል። ሰው መሆን ከቻልን አዎ መምጣቱ አይቀርም።
Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 1 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
November 30, 2013 at 4:48 PM

Why we blame other countries,do we
have a right to live free region to region,why we forgot it what happened
in beneeshangule region and other
areas,to me I can't see a difference,
may be they doing less what we do
here.that is why we pay the consequences know.let us look out self first,I am not saying they doing right,before we wash our hands we need to do a lot back home.as a government as people as country.

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger