Friday, November 15, 2013

እናቶቻችን ጥንታውያን ሃኪሞች ናቸው!!


 
    ወላድ ሴቶች በአብዛኛው ያውቁታል። ያውቁታል ብቻ ሳይሆን አበክረው ይጠቀሙታል። የሚጠቀሙት በቤተ ሙከራ ተመራምረውና ያለውን የንጥረ ነገር ይዘት ስለደረሱበት አይደለም። በልምድና ባገኙት የጥቅም አገልግሎት ነው። አልፎ አልፎ ከሚወጣው የሚተነፍግ ጠረንና መጠነኛ ምረት በስተቀር እህልነቱ እንከን አይወጣለትም። በሁሉም የሀገሪቱ ክልል ይገኛል። ወይና ደጋማ አየር ክልል በደንብ ይስማማዋል። ስሙ በሁሉም ዘንድ እንግዳ አይደለም። እንግዳነቱ የሚጠቀሙት በአብዛኛው እናቶች ብቻ መሆናቸው ነው። ለዚያው ከእንስትም ወላዶች ብቻ!! ይህ የእህል ዘር ማነው? አወቃችሁት? ወይስ ጠረጠራችሁት?

  እንግዲያውስ እኛው እንንገራችሁ። በሀገርኛው ስሙ «አብሽ» ይባላል። በፈረንጆቹ (Fenugreek) ነው። መነሻው ኢራቅ እንደሆነ ታሪክ ይነገራል። ከዚያም ወደዓለሙ ሁሉ ተስፋፋ። ሕንድ ደግሞ ከዓለም ሀገራት የአምራች መሪነቱን ይዛ ትገኛለች። ኢትዮጵያም ለዚህ ዘር ባእድ አይደለችም። ታዲያ ስለአብሽ ምን እንግዳ ነገር ተገኘና ነው ዛሬ ስሙ የተነሳው እንዳትሉ። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ስለአብሽ ጠቀሜታ በሰፊ ከሚያትት መጽሐፍ ላይ ያገኘነው መረጃ ስለእናቶቻችን ቀዳሚ የምርምር ባለሙያነት እንድናደንቅ አስገደደን። እናቶቻችንን ብቻ አድንቀን ዝም ከምንል አብሽን እናቶቻችን እንዲመርጡ ያደረጋቸውን የንጥረ ነገር ይዞታና ጥቅም ልናካፍላችሁና እናንተም አብሽን እንድትካፈሉ ጥቂት ለመጻፍ ወደድን። «አብሽ» እንዲህ ነው።

አብሽ /Fenugreek/የሚሰጠው ጥቅም ምንድነው? ከብዙ በጥቂቱ ከታች የተዘረዘሩትን  ይሰጣል።

1/ የጡንቻ፤ የጣት፤ የቅልጥምና የመገጣጠሚያ አካባቢን ህመም ለመቀነስና ለማስታገስ ያገለግላል።
2/ ሊንፍኖድስ/በጉሮሮ፤ በብብትና በሆድ አካባቢ የሚገኝ የመከላከያ አቅምን የሚጠብቅ እጢ ሲሆን አብሽ ይህ ስራውን በተገቢው እንዲወጣ ያደርገዋል።

3/ ቁስልና ጥዝዛዜ ያለው ህመም በመቀነስ ብሎም ቶሎ እንዲድን በማድረግ ያግዛል።
4/  በስኳር ህመም ለሚሰቃዩ ሰዎች የኢንሱሊንን አቅም በማጎልበት፤ የጉሉኮስን ክምችት በመቀነስ ከፍተኛ ጥቅም አለው።

5/ በሆድ አካባቢ የስብ ክምችት እንዳይኖር ይከላከላል። ከመጠነኛ እንቅስቃሴ ጋር ስብ በማቅለጥም እገዛ ያደርጋል።
6/ የምግብ ፍላጎት ለቀነሰባቸው ሰዎች ፍላጎትን በመጨመር ካልተፈለገ ክሳትና የምግብ አለመስማማት ተመሳሳይ ችግሮች ይከላከላል።
7/ለሆድ ሕመም፤ ለጨጓራ አልሰርና ለቃር ከፍተኛ ማስታገሻ ነው።

8/ የልብ አርተሪ ስራውን በአግባቡ እንዲያካሂድ ያግዛል።ለደም ቅዳና ደም መልስ ዝውውር፤ ለኮሌስትሮል መጠን መስተካከል፤ለኩላሊትና በቫይታሚን እጥረት ለሚከሰት የቤሪቤሪ በሽታ ከፍተኛ የፈውስ ድጋፍ አለው።

9/ ለአፍ ቁስለት፤ ለንፋስ ተገንጣይ ቧንቧ ህመም፤ ለሳምባ፤ ለደረቅ ሳልና ትክትክ ፍቱን መድኃኒት ነው።
10/ ለቆዳ፤ ለራሰ በራነትና ለጸጉር መመናመን፤ ለካንሰር፤ ለጉበት ህመም መከላከል ጠቃሚ ንጥረ ነገር ይዟል።

11/ ለስንፈተ ወሲብና አቅም ማጣት፤ ለሴቶች የጡት ግት መጨመርና የወተት አወራረድ መጨመር ከፍተኛ ድርሻ አለው,።
12/ የአፍ፤ የጉሮሮና የውስጥ እርጥበትን በመቆጣጠር ያልተፈለገ ቆሻሻን በማስወገድ፤ እንደየመኪና ሞተር ግራሶ ለሰውነታችን የሚያገለግለውን ዝልግልግ ፈሳሽ /mucus/ በመቆጣጠርና በማስተካከል መጥፎ የአፍ ጠረን፤ ከሆድ የሚወጣ ትኩሳትና ሽታ፤ በመከላከል ከመጠን በላይ የተበላሸና የለገገ አክታ እንዳይኖረን በማድረግ በኩል አብሽን የሚወዳደረው የለም።

አብሽ ለምን ይህንን ሁሉ አቅም ለመያዝ ቻለ? የዘመኑ ሳይንስ እንዲህ ይላል።

አብሽ ስኳር የለሽ /Polysacchirides/ ንጥረ ነገር አለው። ይህ በራሱ  ክር መሳይ /Fiber/ ሟሚ ንጥረ ነገር ከፍተኛ ተሸካሚ አድርጎታል። saponons, hemicelluloses,macilege, tannin, pectin የተባሉ ለደም ዑደትና ለዘይት መጠን ልኬታ ጠቃሚ ንጥረ ነገርን በመያዙ ከአዝርዕት መካከል እጅግ ተመራጭ ያደርገዋል። ኢንሱሊንን በማምረት ረገድ አሚኖ አሲድ 4 ሀይድሮክሲአይዞሉሲን ይዟል። የፋይቶኬሚካል ክፍል የሆኑትን ንጥረ ነገሮች ማለትም  ኮሊን፤ ትራይጎኔሊን ዳዮስጄኒን፤  ያሞጄኒን፤ ጂቶጄኒን፤ ቲጎጄኒን የተባሉትን ንጥረ ነገሮችን/substance/አጣምሮ የያዘ ነው።
በሚኒራሎችም ረገድ አብሽ የያዛቸው ነገሮች  መዳብ፤ ፖታሺየም፤ ካልሲየም፤ ብረት፤ ሴሌኒየም፤ ዚንክ፤ ማንጋኒዝ፤ ማግኒዢየም፤ በመሳሰሉት በጣም ያዳበረ ነው።
በቫይታሚን ረገድም የተዋጣለት ነው። ታያሚን፤ ቫይታሚን ቢ 6፤ ፍሎሪክ አሲድ፤ ሪቦፍላቪን፤ ናያሲን፤ ቫይታሚን ኤ፤ ቫይታሚን ሲ፤ ቤታ ካሮቲን፤ ፎሌት/DFE/ የመሳሰሉት ይገኙበታል። በአሚኖ አሲድ ንጥረ ክፍሎች በጣም የዳበረ ሲሆን  ከካርቦ ሃይድሬት ምንጮች ውስጥም ሟሚ ከሆነው ጭረት/ ፋይበር /በስተቀር ከስታርች፤ ስኳር፤ ሱክሮስ፤ ግሉኮስ፤ ፍሩክቶስ፤ ላክቶስ፤ ማልቶስና ጋላክቶስ ፍጹም ነጻ መሆኑ ከሁሉም ተመራጭ ያደርገዋል። ፋቲ አሲድና ስብነት ካላቸው ውሁዶችና ንጥረ ነገሮች ነጻ ነው።
 
ከምዕራባውያኑ ጸሐፊያን  ጊዮርጊስ ፔትሮፓውሎስ ስለአብሽ ጥቅም በሰፊው አትቷል። ሕንዳዊው ዶ/ር ኩማር ፓቲ በ328 ገጽ  ባሰፈረውና ስለእጽዋት መድኃኒትነት በዘረዘረበት መጽሐፉ ላይ ስለአብሽ ጥቅምና ቅመማው  በደንብ ዘርዝሯል።
አብሽ በዱቄት መልክ፤ አንጥሮ ዘይት በማውጣት፤ በበቆልት፤ በፈሳሽ መልክ አዘጋጅቶ ለሻይ፤ ከሌላ ምግብ ጋር ቀላቅሎ በማዘጋጀት፤ መጠቀም ይቻላል። አወሳሰዱን በተመለከተ የቅርብ ሐኪምን ማማከር ይገባል።
በአሉታዊ ጎኑ ሲታይ ደግሞ በእርግዝና ላይ ያለች ሴት አብሽን አብዝታ እንድትጠቀም አይመከርም።
የአብሽን ጥቅም አውቀው በአገልግሎቱ የቆዩት እናቶቻችን ሳይማሩ የተማሩ አይደሉምን?
ለተጨማሪ መረጃ ቢመለከቱ ይጠቀማሉ።
1. Adamska M, Lutomski J. C-flavonoid glycosides in the seeds of Trigonella foenum graecum [in German]. Planta Med . 1971;20:224-229.
2. Gupta RK, Jain DC, Thakur RS. Minor steroidal sapogenins from fenugreek seeds, Trigonella foenum-graecum . J Nat Prod . 1986;49:1153.
3. Karawya MS, Wassel GM, Baghdadi HH, Ammar NM. Mucilagenous contents of certain Egyptian plants. Planta Med . 1980;38:73-78.
4. Valette G, Sauvaire Y, Baccou JC, Ribes G. Hypocholesterolaemic effect of fenugreek seeds in dogs. Atherosclerosis . 1984;50:105-111.
5. Singhal PC, Gupta RK, Joshi LD. Hypocholesterolemic effect of Trigonella foenum-graecum (METHI). Curr Sci . 1982:51:136.
6. Stark A, Madar Z. The effect of an ethanol extract derived from fenugreek ( Trigonella foenum traecum ) on bile acid absorption and cholesterol levels in rats. Br J Nutr . 1993:69:277-287.
7. Sauvaire Y, Ribes G, Baccou JC, Loubatieeres-Mariani MM. Implication of steroid saponins and sapogenins in the hypocholesterolemic effect of fenugreek. Lipids . 1991;26:191-197.
8. Yadav UC, Moorthy K, Baquer NZ. Effects of sodium-orthovanadate and Trigonella foenum-graecum seeds on hepatic and renal lipogenic enzymes and lipid profile during alloxan diabetes. J Biosci . 2004;29:81-91.
9. Hannan JM, Rokeya B, Faruque O, et al. Effect of soluble dietary fiber fraction of Trigonella foenum graecum on glycemic, insulinemic, lipidemic and platelet aggregation status of Type 2 diabetic model rats. J Ethnopharmacol . 2003;88:73-77.
10. Gupta A, Gupta R, Lal B. Effect of Trigonella foenum graecum (fenugreek) seeds on glycaemic control and insulin resistance in type 2 diabetes mellitus: a double-blind placebo controlled study. J Assoc Physicians India . 2001;49:1057-1061.
11. Thompson Coon JS, Ernst E. Herbs for serum cholesterol reduction: a systematic view. J Fam Prac . 2003;52:468-478.
12. Sowmya P, Rajyalkshmi P. Hypocholeserolemic effects of germinated fenugreek seeds in human subjects. Plant Foods Hum Nutr . 1999;53:359-365.