ጌታችን መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ ባለች አንዲት ምኩራብ ሲያስተምር በቆየበት ወቅት ከፈሪሳዊያን አንዳንዶች ቀርበው እንዲህ ሲሉ መናገራቸውን አንብበናል።
«በዚያን ሰዓት ከፈሪሳውያን አንዳንዱ ቀርበው። ሄሮድስ ሊገድልህ ይወዳልና ከዚህ ውጣና ሂድ አሉት» ሉቃ 13፤31
ጌታችንም ሲመልስላቸው «እንዲህም አላቸው፦ ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ። እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ በሽተኞችንም እፈውሳለሁ፥ በሦስተኛውም ቀን እፈጸማለሁ በሉአት» ሉቃ 13፤32 አላቸው።
እንግዲህ በሰይጣን መንፈስ የሚነዳው ሄሮድስ፤ ክርስቶስ ኢየሱስን ለመግደል ቢፈልግም በጉ ከመታረዱ በፊት የፈውስና የማዳን ጊዜ እንዳለው በማመልከት የበግ ጠላት የሆነው፤ ቀበሮው ሄሮድስ ጥቂት እንዲታገስ በቀበሮ መስሎ መናገሩን እንመለከታለን።
እንደዚሁ ሁሉ «ኢትክሉ ገቢር ተቀንዮ ለክልዔ አጋእዝት» እንዳለው መጽሐፉ ለጌታ ከመገዛት ይልቅ መንግሥተ ንዋይ ራሳቸውን በግልጽ ያስገዙና ከሥጋ አልፈው አጥንት ዘልቀው ይግጣሉ ለሚባሉት ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ የአዲስ አበቤው ካህን «አቶ ኑረዲን» የሚል ስመ ተቀጽላ አውጥቶላቸዋል።
«ንቡረ እድ» የሚለውን የማእርግ ስም ወደ «ኑረዲን» ቀይሮ «ኑረዲን ኤልያስ» በማለት ይጠራቸዋል። ለምን? ቢሉ ኑረዲን ኤልያስ ከዚህ ቀደም የነበረውን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለቅጥር የሚከፈል የጉቦ ዋጋ እንደዘመኑ የኑሮ ውድነት አሳድገውት ስለሚገኙ እንደሆነ ሰለባዎች ያስረዳሉ። መምህር ገ/ማርያም ገ/ሥላሴ ዘግተውት የነበረውን የጅቦችን አፍ አቶ ኑረዲን በደብዳቤ ክፍት ሆኖ የዘረፋ አገልግሎቱን እንዲቀጥል በደብዳቤ ከማዘዙም በላይ በሥራ ምክንያትና በጉብኝት ሰበብ ወደ አድባራት ከወረደ ለአቶ ኑረዲን ከ15ሺህ ብር ያላነሰ ጉርሻ እንደሚሰጠው ለጉዳዩ ቅርበት ያለው ሰው ለዚህ ጽሁፍ አቅራቢ አውግቷል።
ከአንድ ሺህ ብር ለማይበልጥ ደመወዝ ለመቀጠር አንድ መነኩሴ አስራ ስምንት ሺህ ብር ጉቦ የከፈሉ ሲሆን መነኩሴው የተጠየቀውን ክፍያ ለማሟላት ባለመቻላቸው ይህንን የጉቦ ገንዘብ ከወዳጅና ዘመድ በማዋጣት ያስተባበረ አንድ ዲያቆን የኑረዲንን ገፈፋ በምሬት አውግቶናል።
አቶ ኑረዲን ለቢሮ የስራ መደብ ከሰላሳ ሺህ እስከ ስልሳ ሺህ ብር ጉቦ እንደሚቀበሉ የተገለጸ ሲሆን የጉቦው ዋና አቀባባዮችና ግብረ አበሮቻቸው ኪሮስና ዘካርያስ የሚባሉ ነፍሰ በላዎች እንደሚባሉም ይታወቃል። አቶ ኑረዲን ክፍት የስራ መደብ ማግኘት ካልቻሉ እንደሚያፈናቅሉና ያለፍላጎት ሰራተኛውን በማዘዋወር ክፍት ቦታ እንደሚፈጥሩ ተያይዞ ተገልጿል።
የአክሱም ጽዮን ንቡረ እድና፤ የአክሱም ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው በማገልገል የሚታወቁት ንቡረ እድ ገ/ማርያም ገ/ሥላሴ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው እንደተመደቡ የሙዳየ ምጽዋት ገልባጮችን አፍ በመሸበብ ህግና ስርዓት እንዲያዝ በማድረግ፤ ኢፍትህና ግፍ እንዲቆም በመታገላቸው ከጅቦቹ መንደር ጩኸትና ማጓራት ተሰምቶ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉ አይዘነጋም። የጅቦቹን ጩኸት በማስተባበር ፊት አውራሪ የነበረው ቀንደኛው መሪና እድሜውን በክፋት የጨረሰ፤ ንስሐ ለመግባት የማይፈልግና ከመልካም ነገር ጋር ዘወትር የተጣላው የሽማግሌው ነውረኛ ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሲሆን ለንቡረ እድ ገ/ማርያምን መነሳት በማስተባበር፤ የአድማ ፊርማ በማስፈረም ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
ቤተክህነት መቼም ቢሆን የክርስቶስ አገልጋይ ነኝ ብላ ብታወራም በተግባር ግን ታማኝና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለውን አገልጋይ መቼም አክብራ አታውቅምና እውነተኛውን አገልጋይ ንቡረ እድ ገ/ማርያምን አስነስታ በቦታቸው የጅቦች አባት የሆነውን «ኑረዲን ኤልያስን» አስቀምጣ በገንዘብ ቆጠራ ላይ እንዳይገኙ የታገዱትን የአድባራት ክፍሎችን ሁሉ የገንዘብ ቆጣሪ ሆነው እንዲሰሩ ህልውና ያገኙ ዘንድ አስደርገዋል።
አቶ ኑረዲን የርኅራኄ እንጥፍጣፊ የሌላቸው ጨካኝ ገዢ እንደሆኑ በምሬት የሚናገሩ ሰዎች በየቦታው ድምጻቸው ይሰማል። ንቡረ እድ ኤልያስ ለምን «ኑረዲን ኤልያስ» ተባሉ? ለሚለው ጥያቄያችን ያገኘነው መልስ ፤ከጥንት ግብጻውያን የኢትዮጵያ ጳጳስ ሆነው ከመጡት መካከል አንዱ እስላም ነበረና ቤተክርስቲያን ከመስራት ይልቅ በጳጳስ ሽፋን አምስት መስጊድ ሰርቶ ሄዷል። ይህኛውም የዘመናችን ኑረዲንም፤ ክርስትና የሌለው እስላም ካልሆነ በስተቀር በቤተክርስቲያን ውስጥ ከአምስት ሺህ ብር ወደ ስልሳ ሺህ ብር ጉቦውን በማሳደግ እንዲሁም በዘረፋ የተሰማሩ ክፍሎችን እግድ በማንሳት ወደዘረፋው እንዲመለሱ አይፈቅድም ነበር ሲሉ አውግተውናል። አንዱ ደግሞ ምነው ምንም የማታውቀው ሚስቱ ከምትሞት እሱ ሞቶ እኛም በተገላገልን ነበር ብሎናል። በሞት ማን መቅደም እንዳለበት የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ስለምናምን በአዲስ አበቤው ካህን ኑረዲን የተባሉት ንቡረ እድ ኤልያስ ሆይ! በዚህ ምድር ለሚኖሩባት ጥቂት ዘመንና ነገ በእጅዎ ለሌለው እድሜዎ ግፍና እርግማንን ለራስዎና ምንም ለማያውቁ ጨቅላ ልጆችዎ ትተውላቸው እንዳይሄዱ እባክዎትን ንስሐ ይግቡ፤ ግፍዎትንም በልክ ያድርጉ ብለን መንፈሳዊ ምክራችንን እናቀብልዎታለን። እባክዎን ቀበሮ ሄሮድስን ሆነው የቤተክርስቲያን አባግእን በግፍ አይፍጇቸው!!!
ቤተክህነቱም ከክህደት እኩያ ግብር ያላቸውን ሳይሆን ፈጣሪን የሚፈሩ፤ እውነትን፤ ልማትንና እድገትን የሚያስቡ ሰዎችን ለመመደብ ብትሞክሩ ሀገርን ከእርግማንና ከእግዚአብሔር ቁጣ ማዳን ትችላላችሁ እንላለን።