Thursday, October 11, 2012

ቋሚ ሲኖዶስ ጀግኗል!

በቤተ ክርስቲያን ትልቁ ችግር ከአናቱ እስከ እግሩ ጥፍሩ ያለው መዋቅር በበሰበሰ አስተዳደር መተብተቡ ነው። 2 ሺህ ዘመናትን በመከራና በወጀብ ስትናጥ፤ የደም አበላ ግብሯን ጠያይም ልጆችዋን እየሰጠች፤ ከጉዲት እስከ ግራኝ፤ ከድርቡሽ እስከጣሊያን ድረስ ከልጆቿ እስከ ንብረቷ ስትገብር የቆየችና እዚህ 21ኛው ክ/ዘመን ላይ የደረሰች ቤተክርስቲያን ሉላዊ እውቀትና አስተዳደር በዘመነበት ዘመን ላይ ምን እንደነካት ሳይታወቅ የገዛ ልጆቿ የስልጣንና የሀብት ክምሯ ላይ ሰፍረው እንደ ዳልጋ ዝንጀሮ እየፈነጩ ሲንዷት ማየቱ ውሎ ያደረ ከመሆኑም በላይ ሁሉም እየተባበሩ በአንድ ድምጽ ውድቀቷን እናፋጥን የሚሉ እስኪመስል ድረስ በጥፋት እድምተኞች መሞላትዋ ግልጽ ነው።
ሙዳየ ምጽዋት የሚገለብጡ ይሁዳዎች፤ አፍኒንና ፊንሐስ አመንዝራዎች፤ በነጻ የተሰጣቸውን የሚሸጡና በእናጸድቃለን ካባ የመበለት ቤቶችን የሚመዘብሩ ግብረ በላዎች፤ ስመ ብጽእናን ለምግባረ ብልሹ ስራቸው የደረቱ አባዎች ሞልተው የጋራ ክንዳቸውን በዐመጽና በጥፋት «አንስእ ኃይለከ» ተባብለው የተማማሉ የግብረ እከይ ሰዎችን ማንነትና አድራጎት መመልከቱም እንግዳ ነገር አይደለም። ሆዳቸው ከሞላ የበሻሻ አቦ ምእመናን ሰይፍ በአንገታቸው ቢያልፍ አፋቸው በስብ የተዘጋ ይመስል የማይናገሩ አፈ ዲዳዎች መሪ በሞላባት ዘመን ላይ ቤተክርስቲያን መድረሷ አጥፊዎቿ የውጪ ጉዲት ሳይሆን የራሷ እሬቶዎች መሆኑንም ብዙ ታዝበናል። በአዲስ አበባ ከተማችን የ2000 ብር ደመወዝ እየበላ የሁለት መቶ ሺህ ብር መኪና የሚነዳ የመሪነት ስምን የተሸከመ ሙዳየ ምጽዋት ገልባጭ ማየት የተለመደ ሆኗል። የዘረፋ መዋቅር ዘርግተው የቤተክርስቲያኒቱን ጡት ያለርኅራኄ የሚመጠምጡ አይጠ መጎጦች ተንሰራፍተው ይገኛሉ። ገንዘብ የሚገኝበትን ቤተክርስቲያን ለመምራት ከላይ እስከታች በሚደረገው መቆላለፍ ጅቦቹ አፋቸውን ከፍተው ሲያሰፈስፉ መስማትም ዛሬ ዛሬ እንደተገቢ እየተቆጠረ ይገኛል። በአንድ ወቅት የወይብላ ማርያም ቤተክርስቲያን ከነበራት የ400,000 ብር ካዝና ውስጥ በወራት ልዩነት ወደ 20 ሺህ ደርሶ ለካህናት ደመወዝ መክፈል እስኪያቅት መደረሱን አይተን እነሆ እስከዛሬ በአስገራሚነቱ መዝግበነዋል። ከማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም እስከ ዑራኤል ቤተክርስቲያን፤ ከመርካቶ ሚካኤል እስከ ግቢ ገብርኤል የጅብ መንጋ ሲግጥ ማየት እንግዳ መሆኑ ቀርቷል።  በየደረጃው የእያንዳንዱን አብያተ ክርስቲያን ካዝና ገልብጠው ባዶ ካደረጉ በኋላ ወደተረኛው ቤተክርስቲያን የሚዛወሩ ወሮ በሎች በዚህ አጭር ጽሁፍ ዘርዝሮ የሚዘለቅ አይደለም።
 የሚያስደንቀው ደግሞ ቤተክርስቲያኒቱ ምን ዓይነት ቁጣ ወረደባት እስኪያሰኝ ድረስ ከሀገር ቤት አንስቶ እስከባህር ማዶ ድረስ የአበሻ ጅቦች የሰፈሩባት መሆኑ ያስገርማል። ከቦርድ እስከ ሰበካ ጉባዔ ከተገንጣይ እስከ ገለልተኛ፤ ከግለሰብ ቤተክርስቲያን እስከ ሁለ ገብ ድረስ እየተቧደኑ መዝረፍና ማስዘረፍ፤ የየሀገራቱን ፍርድ ቤቶች ፋይል እስከማጨናነቅ ያደረሰ የዘረፋ ስልጣኔ መንገሱም ፀሐይ የሞቀው፤ አገር ያወቀው ጉዳይ ነው።
የክህነቱና የመሪነቱ መስፈርት የማንነት ሚዛንስ ምኑ ተነግሮ? እንዲያው ተከድኖ ይብሰል! ይህ ሁሉ ሲሆን ቤተክርስቲያንን በመንፈስ ቅዱስ እመራለሁ የሚል ከፍተኛው የሥልጣን እርከን ሲኖዶስ ነበራት። ለመብላትና ለመናገር ካልሆነ ለመሥራት አቅሙና ፍላጎቱ የሌለው፤ ቤተክርስቲያን ብትሞት እንጂ ለእሷ ሞት ራሳቸውን ለማስቀደም የሚደፍሩ የመሪ ቁርጠኞች በሌለበት ሁኔታ ውስጥ መገኘቷ ችግሯ እንዲባባስና ከልካይ የሌለበት እንድትመስል አድርጓታል። ወጉ ደርሶ ማስቆም ባይችሉ ራሳቸውም አብረው ወራሪና አስወራሪ መሆናቸውን ቢያቆሙ እንኳን እሰየው ባልን ነበር! ነገሩ ግን የተገላቦጦሽ ነው። ሕዝቡ በG ማይነስ ቤት ውስጥ እየኖረ እነሱ በG ፕላስ ውስጥ መኖራቸው ነገሩን ሁሉ አስከፊ ያደርገዋል።


ይህንን ጽሁፍ እንዲህ አክርሮ ለመጻፍ ፍላጎቴ አልነበረም። የሆነውንና እየሆነ ያለውን ብዙውን ነገር ብናውቅም እንዲያው ገመናችንን መግለጥ ልቡናዬን ደስ ሳያሰኘው መቆየቱ እንደተጠበቀ ሆኖ  ጥፋቱና ዘመቻው ከሚቀንስ ይልቅ እየጨመረ መገኘቱ እያስገረመኝ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ቋሚ ሲኖዶስ ዛሬ ወግ ደርሶት የድሬ ዳዋ ሀገረ ስብከትን ዝርፊያ ለማስቆምና ለመመርመር ቀሚስ ብቻ የለበሰ ሳይሆን ከሥር ሱሪም መታጠቁን ለማሳየት ከሊቀጳጳሱ ጀምሮ በተዋረድ ተጠያቂነት ያለባቸውን ኃላፊዎች ማገዱን ከደጀ ሰላም ደጅ የጀገነ ማንነትን ገላጭ ጽሁፍ በማንበቤ ነበር።
እንዲያው አለን፤ ዘራፍ ለማለት እስካልሆነ ድረስ ልብን የሚያንገበግበውን የቤተክርስቲያንን ሀብትና ንብረት ዘረፋ፤ የጋጠ ወጥነትና የሥርዓተ አልበኝነቱን ተግባር ለማስቆምና ለመከላከል ሁሉን አቀፍ የድርጊት መርሃ ግብር በመንደፍ ሂደቱን በአፋጣኝ ማስኬድ ካልተቻለ በስተቀር በድሬዳዋ እግድና ማጣራት ብቻ ከጓዳ እስከ ጎድጓዳ ያለውን ዘረፋ ማስቆም አይቻልም። ደጋግሞ በርገር ስለበላ አንድ ሰው ወደ በርገርነት እንደማይለወጥ ሁሉ የድሬ ዳዋ እግድና ማጣራት ብቻውን የቤተክርስቲያንን የተግማማ መዋቅራዊና አስተዳደራዊ ችግር ሊፈውስ አይችልም።
ታዲያ በዚህ በነካካ እጃችሁ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ ገጠሪቱ የሳር ክዳን አጥቢያ ድረስ ያለውን የሥነ ምግባር፤ የጥመት አስተምህሮ፤ የሀብትና ንብረት ዘረፋ ለማስቆም ቁርጠኛ ሁኑ! ይህንንም በስብሰባ ብዛት ሳይሆን በሥራ አሳዩ!
ለአሁኑ በአጭር ቃል ቋሚ ሲኖዶሱ ጨክኖ ጀግኗል ብለናል!