Thursday, October 11, 2012

የሽጉጡ ጦስ ሁለት የአቡነ ገብርኤልን የቅርብ ረዳቶች ከሥራ አፈናቀለ


source: dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com
የሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የሆኑት አቡነ ገብርኤል ወደ ሀዋሳ በሥራ ተመድበው ከሄዱበት ጊዜ ጀምሮ አንድም ቀን ሠላምና ዕረፍት አግኝተው አያውቁም፡፡ ልባቸው ከሠላምና ከዕርቅ ርቋል፡፡ ከቤተክርስቲያን የተባረሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናንን ጥያቄ በመመለስ ፈንታ ሕልምና ሃሣባቸው ለጥቂት ጥገኛ ነጋዴዎችና ለ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባላት እየተሸነፈ ማንኛውም ዕርቅ እንዳይደረግ ከማገድ ውጪ ምንም ነገር አይታያቸውም፡፡
በሺዎች ከሚቆጠሩ ምስኪን ምዕመናን ይልቅ ጥቅም ሊያገኙ የሚችሉት ከጥቂት ጥገኛ ነጋዴዎችና ከ"ማኅበረ ቅዱሳን" እንደሆነ ራሳቸውን አሳምነውታል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ሁለት አካላት አቀነባባሪነት በድሃዎቹ የሀዋሳ ምዕመናን ላይ ጥቃት ሲፈጸም፣ አይተው እንዳላየ፣ ሰምተው እንዳልሰማ በመሆን ፍትሕን ከሀገረ ስብከቱ የሰማይ ያህል አራቁት፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል እንዳይሰበክ ሲታፈን ነገሮችን ሁሉ በፊርማና በማኅተማቸው እያፀደቁ የድኆቹ የአምልኮ ነፃነት በጠራራ ፀሐይ ሲቀማ ምንም አልተሰማቸውም፡፡
ይሁንና በዚህ ሁኔታ የተማረሩት የሀዋሳ ምዕመናን ስለመልካም አስተዳደርና ስለ ፍትሕ ጮኹ፡፡ ቁጣቸውን በተለያዩ መንገዶች ገለጹ፡፡ ግጭቱ ተጋግሞ ሀገረ ስብከቱን አልፎ በመላው ሀገሪቱ በተለይም በጠቅላይ ቤተክህነት ውስጥ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ ቋሚና ቅዱስ ሲኖዶሶች ተከታታይ ስብሰባዎችን በማድረግ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን አስተላለፉ፡፡ ይሁን እንጂ አቡነ ገብርኤል ያላወረዱትን ዕርቅ፣ ዕርቅ አውርጃለሁ፣ ያልመሠረቱትን ሠላም፣ ሠላም መሥርቻለሁ፣ ያላመጡትን አንድነት፣ አንድነት አምጥቻለሁ እያሉ ጠቅላይ ቤተክህነት አካባቢ ቢዋሹም ሐቁ ግን እየገዘፈ መጥቶ ለስድስት ወራት (ጥር/2003 -ሐምሌ/2003) ያህል ለሕይወታቸው በመስጋት ሸሽተው አዲስ አበባ ላይ መቀመጥ ግዴታ ሆነባቸው፡፡
ይሁን እንጂ፣ ከእትብቱ እንደተቆረጠ ጽንስ መተንፈስ የተሳናቸው ጥቂት ጥገኛ ነጋዴዎቹና የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባላት እንደምንም ተሟሙተው ሐምሌ 18 ቀን 2003 ዓ.ም ምሽት በአንዲት አሮጌ ሃይላክስ ፒክ አፕ መኪና በስውር ወደ ሀዋሳ መልሰው ወሰዷቸው፡፡
ከዚያም ዙሪያውን ጥበቃ ተጠናከረላቸው፡፡ ሲወጡም ሲገቡም በግል ሴኪዩሪቲ ማሠልጠኛ የሠለጠኑ ጠባቂዎችን በመመደብ፣ ብርሃን ቀርቶ አየር እንኳን እንዳያገኙ እፍንፍን አድርገው አጀቧቸው፡፡ ዐውደ ምሕረቱ በልዩ ልዩ መሰናክል ታጥሮ ምዕመናን በቅጡ ማስቀደስ ተሳናቸው፡፡
በዚህን ጊዜ ይላሉ ውስጥ ዐዋቂዎች፣ በዚህን ጊዜ የአቡነ ገብርኤልን መንፈስ ለማረጋጋት ሲባል፣ በአግባቡ የተመዘገበ ስለመሆኑ እንኳን በቅጡ የማይታወቅ ለራስ መጠበቂያ የሚሆን አንድ ሽጉጥ ከጥገኛ ነጋዴዎቹ በአንዱ በእጅ አዙር ተበርክቶላቸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ የተነቃቁት ሊቀጳጳስ ምስኪኖቹን የሀዋሳ ምዕመናንን ለግል የወሲብ መጽሔት በሰጡት ቃለ መጠይቅ "ቀበሮዎች ናቸው" ብለው እስከመሳደብ ደረሱ፡፡ በሠላም የሚመጣውን በእጅ መስቀላቸው፣ በኃይል የሚመጣባቸውን ደግሞ በተሰጠቻቸው ራስ መጠበቂያ ቀልጥመው ሊያሳርፉት ንቁ ሆነው መጠበቅ ያዙ፤ በሠለጠነ ዘመን ማን ይሞታል ታዲያ?
አቡነ ገብርኤል እንዲህ እንዲህ እያሉ፣ ልባቸው ዕርቅና አንድነትን እየተፀየፈች፣ ልታረቅ ቢሉ እንኳን ጥገኛ ነጋዴዎቹና የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባላት እንዳይታረቁ እያከላከሏቸው የሠላም መንፈስ አንድ ቀን እንኳን በውስጣቸው ሳትገባ፣ ሀዋሳ ላይ ሥራ ከጀመሩ ሁለት ዓመት ሊሞላቸው አንድ ሁለት ወራት ብቻ ቀራቸው፡፡ ታዲያ በአንድ ዕድለ ቢስ የነሐሴ 2004 ዓ.ም የተረገመች ቀን፣ ያቺ ለራስ መጠበቂያ የተሰጠቻቸው ሽጉጥ ጠፋችባቸው፡፡ ከሁኔታው መረዳት እንደተቻለው አቡነ ገብርኤል ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሥርዓተ ቀብር አዲስ አበባ በተገኙበት ወቅት ሽጉጣቸውን መኝታ ክፍላቸው ውስጥ ረስተውም ይሁን አስቀምጠው ያገኘ ሰው እንደወሰደባቸው ተገምቷል፡፡
በዚህ ሁኔታ የተበሳጩትና የተቆጡት አቡነ ገብርኤል ከእነርሱ በስተቀር አንስቶ ሊወስድብኝ የሚችል የለም በማለት የጠረጠሯቸውን ፍጹምን (ተላላኪያቸው) እና ሊቀመዘምራን ልሳነወርቅን (ሾፌራቸው)፣ በቅርብ እንዲከታተሉላቸውና እንዲያጠኗቸው የጥገኛ ነጋዴዎችንና የ"ማኅበረ ቅዱሳን"ን ጥምር ኮሚቴ አይሉት ስብስብ ነገር ይመድቡባቸዋል፡፡ የሽጉጧ ነገር የውሃ ሽታ ሆነ ቀረ፡፡ ፍጹም ሲጠየቅ ከልሳነወርቅ በስተቀር ሊወስድባቸው የሚችል የለም እርሱን ጠይቁት ይላቸዋል፡፡ ልሳነወርቅ ደግሞ በበኩሉ "አብሯቸው የሚያድር ማን ሆነና ነው እኔን የምትጠይቁት? ለመሆኑ ለእርሳቸው ከፍጹም የቀረበ አለ እንዴ? ፍጹምን መርምሩት" ይላቸዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ያችን ውድ ዕቃ ሳያገኟት መስከረም ወር እንደዋዛ ሊጠናቀቅ ተቃረበ፡፡ እንደ እርሳቸው እምነት በእነዚህ ሁለት ሰዎች መጠቃታቸው ያንገበግባቸዋል፡፡ በተለይ የፍጹም እንዲህ መጨከን ሊገባቸው አልቻለም፡፡ ፍጹም እኮ ሁለ- ነገራቸው ነው፡፡ ቃል አቀባያቸው፣ ጠባቂያቸው፣ አስገቢና አስወጪ አጋፋሪያቸው፣ አንዳንዶች ደግሞ እንደሚሉት፣ የላመ የጣፈጠ ምግባቸውን ቀምሶ ለይቶ የሚያስቀርብላቸው ወጥ ቀማሽ እልፍኝ አስከልካያቸው፣ ኧረ ስንቱ . . . ? የፍትሕ ጥያቄ ለማቅረብ ወደ መንበረ ጵጵስናው የሚመጡትን የሀዋሳ ምዕመናንን "እርሳቸው የሉም"፤ "ተኝተዋል"፤ "ዕረፍት ላይ ናቸው"፤ "አሁን ሊያነጋግሯችሁ አይችሉም" እያለ የሚያባርርላቸው አለኝታቸው ነው፡፡ ሲያስፈልግም ከእርሳቸው ቀደም፣ ቀደም እያለ ምዕመናኑን ላቀረቡት ጥያቄ መልስ ሳያገኙ አፍ አፋቸውን እያለ ወደ መጡበት ይመልስላቸዋል፡፡ እርሱን እንደ እሳት መከላከያ አስቤስቶስ ነው የሚጠቀሙበት፡፡ እንደሻንጣቸው ሁልጊዜ የትም ነው ይዘውት የሚዞሩት፡፡ በተለይ ረፋድና አመሻሽ ላይ በፌስታልና በብብቱ ሥር በጋዜጣ የተጠቀለሉ የሚበሉና የሚጠጡ ፍሬሽ ፍሬሽ ነገሮችን ባሻው መንገድ በማቅረብ እርሱን የሚተካከለው አንጀት-አርስ የለም፡፡ ፍጹም እኮ በፍጹም ተተኪ የሌለው ረዳታቸው ነው፡፡
ሲያሻው ደግሞ "ተቀመጥ በወንበሬ፣ ተናገር በከንፈሬ" ብለው በሀገረ ስብከቱ ልዩ ልዩ ወረዳዎችና ከተማዎች እየወከሉት ልዩ ልዩ ካህናትን እየሰበሰበ ይገስጽላቸዋል፡፡ የተበላሹ አሠራሮችን ያስተካክልላቸዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ሆኖ የሚገባቸውን ግብዣ ስለእርሳቸው ይጋበዝላቸዋል፡፡ ታዲያ "ፍጼን" ምን ነካው? ደግሞ እኮ እርሱን ላለማጣት ቃለ ዐዋዲን ሽረው በመዋቅር የሌለ የሥራ መደብ ፈጥረው "የጳጳሱ የመልዕክት ክፍል"     የሚል የሥራ መደብ መጠሪያ አውጥተው በወር ብር 930 ከአሮጊቶች መቀነት ከሚሰበሰብ ገቢ ወርሃዊ ደመወዝ እንዲከፈለው ቆርጠውለታል፡፡ ይህም ብቻም አይደለም፤ እርሱን ከመውደዳቸው የተነሳ ቅጥሩ ያለ ማስታወቂያና ያለ ነፃ ውድድር በመስከረም 2004 ዓ.ም ሆኖ፣ ደመወዙ ደግሞ ከቅጥሩ ቀን በፊት አንድ ወር ወደ ኋላ ተደርጎ ከነሐሴ 2003 ዓ.ም ነው የተደረገለት፡፡ እርሳቸው ይህንን ሁሉ ሕግን እየተላለፉለት፣ እየጣሱለት፣ እንዲህ ጉድ ያደርጋቸዋል? ወይኔ! ወይኔ! ወይኔ! ሰውየዉ . . . !!


ከአገልግሎት ሰዓት ውጪ በጂንስ ሱሪ በቦዲ ቲሸርትና በስኒከር ጫማ ነጠር ነጠር እያለ ከተማ ውስጥ መዝናናት የሚወደውን ፍጼን በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች እንደሚሉት ልዩ ልዩ አሳቻ ቦታዎች እንደመገኘቱና እንደማምሸቱ ያቺን ሽጉጥ የሚምር አይመስልም ይሉታል፡፡ ኅሊናቸው ከልሳነወርቅ ይልቅ ፍጹምን እንዲጠረጥሩ ያስገድዳቸዋል፡፡ ልሳኑ በሾፌርነቱ ካለው ቅርበት በስተቀር ያን ያህል ወደ መኝታቸው ክፍል ዘው የሚልበት አጋጣሚ እምብዛም ስለሆነ እርሱን መጠርጠር ይከብዳል፡፡ ያም ሆነ ይህ የጥርጣሬው ምሕዋር በሁለቱ ላይ እንዳጠነጠነ ምንም ውጤት ሳይገኝ ቀረ፡፡ ጉዳዩ ለፖሊስ እንዳይመራ ሌላ መዘዝ ሊያመጣ ሆነ፡፡ ሁሉም ነገር ውስጥ ውስጡን እየተብላላ እህህህ . . . ብቻ ሰፈነ፡፡
በመጨረሻም፣ አቡነ ገብርኤል የሚያደርጉትን ቢያጡ ከመስከረም 17 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት በምሽት ዳንስ (የናይት ክለብ) ባለቤት የተመራ የጥቂት ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎችና የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባላት ቡድን ሁለቱን ሰዎች አጥብቀው እንዲመረምሩላቸው አደረጉ፡፡ ይሁን እንጂ የተፈለገው ውጤት ሊገኝ አልቻለም፡፡ በመጨረሻም ግራ ሲጋቡ ልሳነወርቅ በቅጥር ግቢው ካለው መኖሪያ ቤት ለቆ እንዲወጣ፣ እንዲሁም ፍጹም ጨርሶ ከመንበረ ጵጵስናውና ከሀገረስበከቱ እንዲባረር ይወስናሉ፡፡
ሊቀጳጳሱም ሳያቅማሙ ውሳኔውን አፀኑባቸው፡፡ ቡድኑም ፍጹምን ተከታትሎ ዕቃውን ሸክፎ ወዲያውኑ ከመንበረ ጵጵስናው ቅጥር ግቢ ለቆ እንዲወጣ ያጣድፈዋል፡፡ ፍጹም ዕቃውን አግበስብሶ ሲወጣ "ለመሆኑ ላፕቶፑ (ኮምፒውተሩ) የት ነው ያለው"? ብለው ሲጠይቁት፣ "እኔ ምን አውቃለሁ? ልሳነወርቅን ጠይቁት" አላቸው፡፡ እነርሱም እስቲ የያዝከውን ሻንጣ ክፈት ሲሉት ላፕቶፑን ሻንጣ ውስጥ አግኝተው ፍጹምን እጅ ከፍንጅ ይዘው ያፋጥጡታል፡፡ በፖሊስ እንዳያስይዙት የዚያች ሽጉጥ ነገር ልትቀሰቀስባቸው ነው፡፡ ስለዚህ የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው ላፕቶፑን ብቻ ቀምተውት ያባርሩታል፡፡
በአሁኑ ወቅት "ፍጹሜ" አዲስ አበባ ላይ ሆና፣ ይህ ክፉ ቀን አልፎ ሁሉም እሰኪረሳሳ፣ ዕድል የሚሰጣትን እየተጠባበቀች መሆኗ ተገልጿል፡፡ ልሣነወርቅ ከእንግዲህ ወዲህ የአቡነ ገብርኤል መኪና ሾፌር ሆኖ መቀጠል እንደማይፈልግ እቅጩን ነግሯቸዋል፡፡ ለደረሰበት የስም ማጥፋት ዘመቻ ሁላቸውንም በፍርድ ቤት እንደሚገትራቸው ዝቷል፡፡ የሽጉጡ ባለቤት ነው የተባለው አቶ ዓለማየሁም "አባቴ ለእርስዎ ደህንነት የሰጠሁዎት ሽጉጥ ወንጀል ከተሠራበት እኔን ያሰጋኛል፡፡ እባክዎን ያድኑኝ" እያለ በመወትወት ላይ መሆኑን ውስጥ ዐዋቂዎቹ ጠቁመዋል፡፡
መቼም "የዓይንህ ቀለም አላማረኝም" ካልተባለ በስተቀር የሽጉጡ መጥፋት በኦፊሴል ተጠቅሶ ለሁለቱ የአቡነ ገብርአል የቅርብ ሰዎች የስንብት ደብዳቤ ይሰጣቸዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ልሳነ ወርቅ ስሙን በፍርድ ቤት ለማስጠበቅ ከከሰሰ፣ ብዙ ነገሮች ተጎልጉለው ስለሚወጡ ይህ እንዳይሆን ምናልባት ከለጋ ወጣቶች ዕርቃን ገላ ሽያጭ ከተገኘ የምሽት ዳንስ ቤት ገንዘብ ላይ አፍ ማበሻ ሊሰጠው ይሞከር ይሆናል፡፡
ሆኖም ፍጹምና ልሳነ ወርቅ ጠንካራ ከሆኑ፣ ጉዳዩን ለማድበስበስና ከሁለቱም ወገን የባሰ ነገር እንዳይመጣ "የዓመት ዕረፍት ላይ ነበሩ" ተብሎም ወደ ሥራ ገበታቸው ሊመልሷቸውም ይችሉ ይሆናል፤ ካልሆነም ደግሞ በምንም ምክንያት ሆነ በምንም፣ ሊቀጳጳሱ የሚሉት የመጨረሻ ስለሚሆን በወጡበት ሊቀሩም ይችላሉ፡፡ በቤተክርስቲያናችን ምን የማይሆን ነገር አለ . . . ?  አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ! ለነገ ደግሞ ምን ታሳየን ይሆን?

በቸርነትህና በምሕረትህ ጎብኘን!!!
አሜን!!!