Wednesday, October 10, 2012

‹‹ለእንጀራ ብዬ ›› . . . አይባልም!

በሰላማዊት አድማሱ Selam.admassu@yahoo.com

ሸዋንግዛው፣ በላይነህ፣ ጌታ ነህ፣ ግርማዊ፣ ልዑል፣ ኩራባቸው  . . . እነዚህን እና እነዚህን የመሳሰሉ ስልጣንን፣ ጌትነትን ፣ልዕልናን የሚገልፁ በርካታ ኢትዮጵያዊ ሰሞች አሉ፡፡ ስለ ስም ካነሳን ዘንድ ስያሜ ጠባይን፣ግብርንና ሁኔታን የሚገልጥ ሆኖ በእስራኤል ዘንድ ይሰየም እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ ምናሴ፡- ‹‹ማስረሻ›› ዘፍ 41፡51 (የስም ሰጪውን ሁኔታ ሲገልጥ) ዮሴፍ ‹‹ይጨምር›› ዘፍ 30፡24 (የዮሴፍን ህይወት ያንጸባርቃል)፡፡ የእግዚአብሔር ስሞችም ባህሪውን ፤ስራውን እና አምላክነቱን ይገልጻሉ፡፡ የእኛዎቹ የኢትዮጵያውያን ስሞችስ ምን ያህሉ ይሆን እኛነታችንን የሚገልጹት? ወይንስ መግለጽ አይጠበቅባቸውም ይሆን?፡፡
    አንድ የቤተሰብ አባወራ ለልጁ የሚሰጠው ኩርማን እንጀራ፤የሚያወርሰው አንድ ክንድ መሬት ሳይኖረው ‹‹ ግዛቸው›› ብሎ ስም ያወጣለታል፡፡ ልጅዬውም ከእናቱ ጓዳ ዳቦውን እየገመጠ፤ ቆሎውን እየቆረጠመ አድጎ ለአቅመ አዳም ሲደርስ እርሱም ተራውን ለልጁ ‹‹በላይ ነህ›› ወይንም ‹‹ጌታ ነህ›› ብሎ ስም ያወጣለታል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ እስከ አስር ትውልድ ቢቆጠርም አንድም ጊዜ ከቤተሰቡ መሃል ‹‹እንደ ስሙ›› የሆነ ላይገኝ ይችላል፡፡ ‹‹ግዛቸው›› ተብሎ በድህነቱ ሳቢያ ላለው የተገዛ፤ ‹‹በላይነህ›› ተብሎ ‹‹ በታች›› የሆነ እጅግ ብዙ ሰው አለ፡፡ እንዲያው ለመግቢያ ያህል ምን ያህል ሥራችን እንደስማችን ወይንም ስማችን እንደስራችን ይሆን?  ስል መጠየቅ ፈለኩ እንጂ በዋንኛነት ላወራስ የፈለኩት ስለ ሥራ ነው፡፡ እንደው የስሞቻችን ነገር በሥራ ባህላችን ላይ ያመጡት አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖር ይሆን እንዴ? እናንተስ ምን ይመስላችኋል?
የሥራ ፈጣሪው ማን ነው?
   መቼም ሁሉም ነገር መነሻና ጅማሬ አለው ፡፡ ለመሆኑ ሥራን ማን ፈጠረው? ተፈጥሮ ወይንስ ፍጥረት? ሃጢያት ወይንስስተት?  . . ሁሉ የየራሱ መላ ምት ሊኖረው ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን ግን የሥራ ፈጣሪው ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ ይናገራል፡፡ ዘፍ 1፡28፡፡ ይህንን ሃሳብ መጋቢ ደሞዝ አበበ ሥራ-ሥራ በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ‹‹ ሥራ የሰዎች ግኝት አይደለም፡፡ ከእግዚአብሔር የተገኘ አምላካዊ በረከት ነው፡፡ በመሆኑም በአምሳሉ ለፈጠረው ሰው ሥራን ሰጠው ፡፡ እርሱ ቦዘኔ ስላልሆነ ሰውም ቦዘኔ እንዲሆን አይፈልግም፡፡›› በማለት ገልጸውታል፡፡ ስለዚህ በቀላል እና በማያሻማ መንገድ የሥራ ፈጣሪው ራሱ እግዚአብሔር መሆኑ ተገልጾልናል፡፡
ሥራ ለምን? ለሆድ ወይንስ? . . .
    እግዚአብሔር አምላክ በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ለአዳም ‹‹ሥራን›› የሰጠው ‹‹ለሆዱ›› ወይንም ለሚበላው አይደለም፡፡ ምናልባት እኛ ‹‹ለእንጀራ ብዬ ነው ስራ የምሰራው›› ብለን እንደምንለው አይነት አይደለም፡፡  ምክኒቱም ኤደን ገነት ‹‹ለእንጀራ›› የሚለፋባት አልነበረችም ዘፍ 2፡8፡፡ አንዳንድ መጽሐፍት ‹ገነት›› የሚለውን ቃል ሲተረጉሙት ሁለት ፍቺ ይሰጡታል፡፡ አንደኛው ‹‹ አትክልት ማለት ነው›› ሲሉ ሁለተኛው ‹‹ በቅጥር የተከለለ የአትክልት ስፍራ›› ማለት ነው ይላሉ፡፡ ስለሆነም የአዳም በገነት መቀመጥ እና ሥራን መስራት የተፈለገው የሚበላው ነገር ስለሌለው አልነበረም፡፡ ይልቁንም መልካሙን እና ክፉውን ከሚያሳውቀው ዛፍ በቀር በገነት ካለው ሁሉ እንዲበላ ተፈቅዶለታል፡፡ ታዲያ እግዚአብሔር አምላክ አዳም የሚበላው ነገር ሞልቶት ሳለ  ሰራተኛነቱን ለምን ፈለገ? ብለን ብንጠይቅ አዳም ከተፈጠረ በኋላ ምድርን የማበጀት እና የመጠበቅ ኃላፊነት ስለተሰጠው ነው፡፡ ‹ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በኤደን የአትክልት ቦታ አኖረው ሰው የአትክልቱን ቦታ እንዲያለማና እንዲንከባከበው ነው፡፡› ዘፍ 2፡15


   ከላይ የተጠቀሰው ይህ ሃሳብ የሚያመላክተን በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ስለ ‹‹ ሥራ›› የነበረው ዓላማ ከሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት ማሟያነት ያለፈ እነደነበረ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ክርስቲኖች ሥራን ስንሰራ ‹‹ለሆድ› ከሚሰሩት የተለየን መሆን አለብን፡፡ ከሆድ የበለጠ ተልዕኮ አለንና፡፡ ሁሉም ሰው ወደዚች ምድር ሲመጣ ይዞት የመጣው ተልዕኮ አለው፡፡ ይህ ተልዕኮ ከመብላት፣ ከመጠጣት፣ ከመልበስ፣ ከማግባት፣ ቤት ከመስራት..... ያለፈ ነው፡፡
ሥራ ሲፈቀር
  ሥራን በፍቅር ገብቶን ስንሰራው ውጤቱ አርኪ ነው፡፡ የእግዚአበሔርን ልብ የሚያሳርፍ ነው፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ሰራተኞች ሆነን ስንሰማራ ለምድር የምናበረክተው አስተዋጽኦ አለን፡፡ ምክኒያቱም እርሷን የመንከባበከብ እና የመጠበቅ ኃላፊነት የተሰጠው ለእኛ ነው፡፡ የአዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ለሚያምኑ ሰለማዊ መጠጊያ ብቻ መሆን ሳይሆን ለምድር ችግር መፍትሔ የሚሆኑ ሰዎችንም ማፍራት ነው፡፡ የሰላም አምባሳደሮች ከውስጧ መውጣት አለባቸው፡፡ ለረሃብተኞች ፍቅርን ከምግብ ጋር የምትቆርስ፣ በውስጥ ሰውነታቸውም ሆነ በውጪው አካላቸው ለታረዙት፤ የክርስቶስን ጸጋ ለውስጣቸው፤ ጨርቅን ደግሞ ለገላቸው ማልበስ ይኖርበታል፡፡ ይሕን ለማድረግ ደግሞ ምዕመኖቿ ስራ ወዳድ እና የዓላማ ሰራተኞች መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡
 እንበላለን፡፡ በእርግጥ እንበላለን! ሰውነታችንን ጤናማ እናደርጋለን፡፡ በዚህም እግዚአብሔርን እናከብራለን፡፡ ክርስቲያኖች የሚበሉት ለእግዚአብሔር ክብር መኖር እንዲችሉ ነው፡፡ ለመብላት ብቻ ግን አይኖሩም፡፡ ምኒያቱም ለመብላት ብቻ የሚኖር ሆዳም ነው፡፡ ስለዚህ እንስራ ሰራተኛ አምላክ ስላለን፡፡ ስንሰራ ግን ከሆድ የዘለለ ራዕይ ይኑረን!

ቸር ያሰንብተን!!