Monday, April 3, 2017

ከእንግዲህ የክርስትና ኃይማኖት ተከታይ አትበሉኝ!


አይደለሁምና፤ አዎን አይደለሁም።
የፕሮቴስታንትም ኃይማኖት ተከታይ አትበሉኝ።
አይደለሁምና።
የሆነ ጊዜ መናፍቅ ትሉኝ እንደነበረም አስታውሳለሁ።
ለምን አላችሁኝ ብዬ አልከፋም!
ታላቁ የእምነት ሞዴላችን ቆራጡ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም በአንድ ጠርጠሉስ በሚባል አእምሮ በደነዘዘው አይሁድ "መናፍቅ!" ተብሏልና።(የሐዋ.ሥራ 24:5)
ግድ የለም።
የክርስትና ኃይማኖት ተከታይ በመሆን መንግሥተ ሰማይ አይገባም።
ክርስቶስም ይህንን ቃል አልገባልንም፣ የአባቱን ፈቃድ የሚፈጽሙትን ነው እንጂ..።
ጌታ ጌታ ስላልክ፥ በሃሌ ሉያ ስላንጋጋህ፥ በፉጨት በእልልታ ስለቀወጥክ፥ ባይብል በእጅህ ስላልተለየ፥ኢየሱስ ኢየሱስ ስላልክ፣ በየማምለኪያ አዳራሽ ስለተገኘህ፥ በአዲስ ቋንቋ ስለተናገርክ፤ ፐ! አንተ የእግዚአብሔር ሰው ስላሉክ፣በሱፍ በከረባት በየአደባባዩ ስለተገለጥክ፥ ከባህር ማዶ ጀምሮ የአገልግሎትህ ኮሜንት "ተባረክ" ስለጎረፈልህ...በቃ ....እንዲያ በማለት ሰማይ የገባክ አይምሰልህ።
ይሄም ዋስትና አይደለም።
አርብ እሮብ ስለጾምክ፥ ይሄም ሳያንስህ ወራትን ሳምንታትን በመላምት ስያሜ እያቆላመጥክ ክርስትና አይሉት ግብዝና በመጾምህ የተመጻደቅክ ቢመስልህ፣በባዶ እግርህ ስለተጓዝክ፣ግሽን፤ ኩክ የለሽን ስለተሳለምክ፥ ደብረ ዳሞን ስለወጣክ፣ ስዕለትህን በሩቅ ሀገር ንግስ ስላደረስክ፣ ሰባት አመትኮ በአንድ እግሩ ቆሞ ፐ! ብለህ ተከታይህ ነኝ ስላልክ አይደለም፥ዳገት ቁልቁለቱን ወጥተህ ስለወረድክ አይምሰልህ።
በቀን 5 ጊዜ ስለሰገድክ፣ ጥፍርህን ስለሞረድክ፣አፍንጫህን አሻሽተህ ሼይጢያንን እያሳደድኩ ነው ብትልና፣ዘካ ስላወጣክ፥ ጁምአ ስለሰገድክ አይደለም መንግሥተ ሰማይ በዚህ አይገኝም።
በዉል ማንነቱን ባታውቅም የአንድ አምላክ ተከታይ ነኝ ስላልክ፣ ይህ ሁሉ የመንግሥተ ሰማይ ዋስትና ሊሆን አይችልም።
አመቱን እያሰላህ በጨረቃ ተመርተህ ወሩን ሙሉ ስለጾምክ፣ ሱሪህን ስላሳጠርክ፣ ቆቡን ስለደፋህ፣ አንቺም ከጥፍር እስከራስ ስለተከናነብሽ፤ በቀዳደa አጮልቀሽ ስላየሽ መንግሥተ ሰማይ መግባት እንዲያ እንዳይመስልሽ። ይህ ሀሉ እንኳን የምትወርሽበት ለመውረስ በሚደረገው ጉዞ አንድ እርምጃ እንኳን አይሸፍንም።

አይሁድ ነሽ ሙስሊም፣ቡዲዝም ነሽ ሂንዱዝም ኦርቶዶክስ ነሽ ጴንጤ ይህ ሁሉ የመደራጃ እድር ነው።

እኔ ግን የክርስትና የኃይማኖቱ ተከታይ አትበሉኝ እያልኩኝ አንድ ነገር የምለው አለኝ፣
ማንም ምንም ብትሆን ማንነትህና ምንነትህ ለኔ ምንምምም ነው።
ነገር ግን እውነት መንገድና ህይወት እነሰ ነኝ ያለውን፤ በእኔ በቀር ወደአብ የሚደርስ ማንም የለም ያለውን፣በእኔ የሚያምን ለዘላለም ይኖራል ያለውን፣በመካከላችን ያለውን የጥል ግድግዳውን በደሙ አፍርሶ የመጣበትን አላማ ጨርሶ ተፈጸመ በማለት ወደሰማይ ያረገውን፡መጥቼም እወስዳችኃለሁ፣ከእኔም ጋር ለዘላለም ትኖራላችሁ በማለት የማናችሁም አምላክ ያልገባላችሁን ታላቅ የማይታጠፍ የተስፋ ቃል የገባልንን ፥ ስለአንተና ስለእኔ ብሎ ወደምድር በመምጣት ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር ያልቆጠረውን፤ የአብ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን ያላመነ ፤ በእርሱም በቃሉ ያልኖረ፤ በወንጌሉም ያላመነ፤ እርሱ በደሙ በመሠረተው በመሠረቱ ያልቆመ፣ጌታና መዲኅን፣የነፍሱም ዋስትና አድርጎ ያልተቀበለ ሁሉ ምንም ዋስትና የለውም። ። ። ።

ምንም የህይወት ዋስትና የለውም። ።

ይህን ስታሟላ ብቻ ነው የመንግሥተ ሰማይን የመውረስ ዋስትና የሚኖርህ።
እኔም የክርስትና አምነት ተከታይ ሳልሆን የክርስትና እምነት የመሥራቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ነኝ።
ስለዚህ ከዚህ በኋላ ኢትዮ ቴሌኮምም ቢሆን ክርስቲያናዊ ለሆኑ በዓላት መልካም ምኞታቸውን ሲገልጹ "የክርስትና እምነት ተከታዮች" ከማለት ይልቅ "የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታዮች"ቢሉን ደስ ይለናል።

አዎን የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታይ ነኝ።
የእግዚአብሔር የመንግሥቱ ሰባኪ፣
የትንሣኤው መስካሪ፣
የክርስቶስ የወንጌሉ ዘማሪ፣
አዋጅ ነጋሪ፣
የአንድ መሪ፣የአንድ አምላክ የአንድ ጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ነኝ እንጂ ""የማንም ድርጅት ወይም ቸርች"" ተከታይ አይደለሁም።

በርሱ በማመኔ ብቻ በውድ ደሙ የታጠብኩ የማይሻር ኪዳን የተገባልኝ ምጽአቱንም በማራናታ የምጠባበቅ
እእእ የደሙ ፍሬ ነኝ!!!

( Fitsum @yalkbet )

Wednesday, February 1, 2017

ፈውስ!


Tsige Sitotaw

በሁሉም ቤተ እምነቶች ዘንድ የሚታየው የፈውስ ጉዳይ ብዙ ሰዎችን ጥርጣሬ ውስጥ እያስገባ ነው ።
እስቲ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንነጋገርበት
1. ፈውስ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ
ክርስቲያን ፦
በዚች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታየው የፈውስ ሥነ ሥርዓት ያለ ፀበል የሚከናወን አይደለም ። ስለዚህም በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ፀበል በምንጭም ይሁን ከቧንቧ በተጠለፈ ውኃ የሚጠመቁ በርካታ ናቸው ።
እንዲሁም ፀበል እየተባለ በተለያዩ ቦታዎች እየተዘጋጄ በብዙ ሰልፍ የሚጠመቅ ሕዝብ ቀላል አይደለም ። በዚያ ቦታ ላይ የሚታዩትን ትርዒቶች ማየት አስገራሚ ነው ።
በክፉ መናፍስት የተያዙ ሰዎች አእምሯቸውን እየሳቱ እየወደቁ ከልባቸው እያለቀሱ ራሳቸውን እየሳቱ በብዙ መኃላ እየተገዘቱ ሲወጡና የታመሙት ነጻ ሲወጡ ይታያሉ ።
ይህ ሁሉ የሚሆነው በተለያዩ ቅዱሳን ስም በተሰየሙ ፀበሎች ነው ። ስለሆነም ኦርቶዶክሳውያን ትክክለኛ እምነት እንዳላቸውና ቅዱሳን ያማልዳሉ ለሚለው ማረጋገጫቸው ይኸው ተአምራት የሚታይበት ፀበል ቦታ ነው ።
በተጨማሪም ፦ በክፉ መንፈስ የተያዘው ሰው ራሱን ስቶ መንፈሱ በላዩ ላይ ሆኖ ሲለፈልፍ ከየትና ምን ሲያደርግ እንደያዘው መናገር ይጀምራል ።
ከየት ያዝኸው ሲባል ከጴንጤ ቸርች ምን ሲያደርግ ሲባል ኢየሱሴ ኢየሱሴ እያለ ሲለፈልፍ ትክክለኛው ሃይማኖት የትኛው ነው ሲባል ኦርቶዶክስ ሌላውስ ሲባል የውሼት እያሉ ካስለፈለፉ በኋላ ያንን በካሴት ቀድተው እውነተኛዋ ሃይማኖት ሰይጣን እንኳ የመሠከረላት ቅድስት ተዋሕዶ እያሉ ከሰይጣን በሰሙት መረጃ ሃይማኖታቸውን የሚሰብኩ ሰዎች አሉ ።
እንደገናም ሰይጣኑ ተቃጠልሁ ነደድሁ ልሂድ ልውጣ እያለ ሲጮህ ምስህ ምንድን ነው ? ተብሎ ይጠየቃል እሱም አመድ ወይም አተላ ወይም ደም ወይም ሌላ ነገር እንዲመጣለት ይጠይቃል ያዘዘው ነገር ሲቀርብለት ያንን ጠጥቶ ለቀቅሁ ብሎ ሦስት ጊዜ ጮኸህ ውጣ ዳግም ላትመለስ የሚካኤል ሰይፍ ይቁረጠኝ ብለህ ምለህ ተገዝተህ ውጣ ተብሎ ያንን ቃል ፈጽሞ ሄድሁ ብሎ ይጮሃል ። ከዚያ በኋላ ሕመምተኛው ጤነኛ ሆኖ በአእምሮው ይሆናል ማለት ነው ።
እሺ ነገሩን ተመልክተናል የሚካድም አይደለም ። ግን በመንፈሳዊ ዓይን ሲታይ በእርግጥ ፈውሱ ተከናውኗል ወይ ? ብለን ጠይቀን መልስ ማግኜት አንችልም ።
ምክንያቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምናደርገውን ሁሉ በማን ስም ማድረግ እንዳለብን አዝዞናል ።
ለምሳሌ ፦ እንደዚህም ያለውን አንድ ሕፃን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል ። የማቴዎስ ወንጌል 18÷5
ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና ። የማቴዎስ ወንጌል 18÷ 20
የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ በስሜ ጽዋ ውኃ የሚያጠጣችሁ ሁሉ፥ ዋጋው እንዳይጠፋበት እውነት እላችኋለሁ ። የማርቆስ ወንጌል 9÷41
ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ ። የማርቆስ ወንጌል 16÷17
በተጨማሪም የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14, 15,16 ሁሉንም ብንመለከታቸው በኢየሱስ ስም ብቻ መለመን ወይም መጸለይ እንዳለብን ታዝዘናል።
አጋንንት የሚወጡት በእርሱ ስም ሙታን የሚነሡት ለምጻሞች የሚነጹት ማናቸውም ፈውስ የሚከናወነው በጌታ ስም ብቻ እንደሆነ ታዝዘናል ።
ታዲያ እንዲህ ከሆነ በፀበልና በቅዱሳን ስም እንደሚለቁ ሆነው የሚጮሁት ለምንድን ነው ?
እንግዲያው ሰይጣን እያታለለን እያዘናጋን እንደሆነ ልናውቅበት ይገባል ። ባልተሰበከልን ልዩ ወንጌል ታስረን ከእርሱ ጋር ወደ ገሃነም እንዳንገባ ።
ስለዚህ የምናደርገውን ሁሉ በኢየሱስ ስም ብቻ ። አሜን ። አሜን ። አሜን ። ወአሜን ለይኩን ለይኩን ።
2 . ፈውስ በወንጌላውያን ፦
በአሁኑ ሰዓት እርስ በእርሳቸው የማይተዋወቁ በፕሮቴስታንትነት የሚታወቁ በርካታ ቤተ እምነቶች እየተመለከትን ነው ። አንዳንዶች በሽማግሌዎች ሲመሩ አንዳንዶች ደግሞ በግለ ሰቦች ብቻ የሚመሩ ናቸው ።
በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተመሳሳይነታቸው ይበዛል ። በአደባባይ የሚፈጸመውን ሥርዓተ አምልኮ ስንመለከትም ጸሎቱ ዝማሬው ስብከቱ አለባበሱ ልሣኑ ትንቢቱ ጥምቀቱ ቊርባኑ ሁሉ አንዱን ከሌላው መለየት አይቻልም ።
ሁሉም ለኢትዮጵያ እንግዶችና መጤዎች የሚያስመስላቸውን እንግዳ ነገር ሲፈጽሙ ይስተዋላል ። ምንም እንኳ ገድልና ድርሳን ባይኖራቸውም አሁን ባሉት አገልጋዮቻቸው በእጅጉ ስለሚደገፉባቸው የተሳሳቱ መልእክቶችን ሊያስተናግዱ ይችላሉ የሚል የብዙ ሰዎች ስጋት አለ ።
ለምሳሌ ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ ትላልቅ የእግዚአብሔር ባሪያዎች የተጠሩበትን ስም በባለቤትነት መያዝ "የግዚአብሔር ሰው" እንዲባሉ መፍቀድና ከሌላው አማኝ ልዩነት ማሳየት ።
ሰውነታቸው ከሁሉም በላይ ወፍሮና ገዝፎ እየታየ እነሱ ግን ከሁሉ በላይ እንደሚጾሙና እንደሚጸልዩ ራሳቸውን መስበክ ቲፎዞ ማብዛት ።
መናፍስትን ከሰው ሲያስወጡ መንፈሱ ለእነሱ እውቅና እንዲሰጥ እድሉን ማመቻቸት ከዚያም ከሕዝቡ ሙገሳን ጭብጨባንና አድናቆትን መቀበል ።
የሚያሳፍረው ግን ሰይጣኑ ሲለቅ ሦስት ጊዜ ጮኸህ ውጣ እየተባለ መታዘዙ ነው "ዝም ብለህ ውጣ" መባል ሲገባው ብዙ ምሥክርነት እንዲሰጥና ሰው ሁሉ እንዲገረም ማድረግና አጋንንትን ለደቀ መዝሙርነት እንደመጠቀም ያስቆጥራል ።
ያልተፈወሱ ሰዎችን ተፈውሳችኋል በማለትና ሐኪም ያዘዘላቸውን መድኃኒት እንዲያቋርጡ በማድረግ ለበርካታ ሰዎች ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት መሆናቸውና ይህም በሕግ ፊት ደርሶ እያነጋገረ መሆኑ በተጨማሪም የገንዘብ ብክነት ሁሉ ደርሷል መባሉና በጉዳዩ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባበት መገደዱ ሌላው ፈተና ሆኗል ።
እንግዲህ በዚህ ሁሉ ፉክክር እያንዳንዱ ቤተ እምነት ለመተራረም ፈቃደኛ ባለመሆኑ አንዱ በአንዱ እየሳቀ እውነተኛ ፈውስም እየጠፋ ክርስቶስን ከሚያምነው ይልቅ የሚተወው እየበዛ መጥቷል።
አሕዛብን ዝም የሚያሰኝ በሁሉም ዘንድ መገረምን የሚያመጣ ዓይን ለሌለው ዓይን እግር ለሌለው እግር የሞተንና የተቀበረን ከሞት ማስነሣት የተካተተበት ፈውስ እንጂ ጨጓራና አንጀት ብቻ እየተባለ አገልግሎቱ ጥርጣሬ ላይ ይወድቃል እንጂ የትም አይደርስም ።
ስለዚህ በሁሉም ቤተ እምነት የሚከሰቱትን ችግሮች ማስተካከልና እንደ እግዚአብሔር ቃል ማስሄድ ቢቻል ማለፊያ ነው ።
እናንተስ ምን ታዘባችሁ ?

Wednesday, October 5, 2016

"የጎርፍ ዘመን ላይ ደርሰናል"


ቀን 08/27/2016

ይድረስ
       
ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣
ለኢትዮጵያ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሙሉ ።

   በቅድምያ እናንተ በዚህ በአገራችን በኢትዮጵያ የሥልጣን ወንበር ላይ ለበጎም ይሁን ለክፉ ያስቀመጣችሁ ቸሩ አምላክ እግዚአብሔር እርሱ ባወቀው መንገድ እንደሆነ ስለማምን ለዚህም ኃላፊነትና ሥልጣን የተሰጣችሁ ናችሁና በእየ መዓርጋችሁ የከበረ የአክብሮት ሰላምታዬን አቀርባለሁ።

  ከዚህ በመቀጠል ሌላው
 ፩ኛ ሳሙ ፲፭፥፳ "....ሳሙኤልም እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀደዳት፥ ከአንተም ለሚሻል ጎረቤትህ አሳልፎ ሰጣት...."ይላል።

 ይህንን ካልኩ በኋላ በእውነቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት የደርግን መንግሥት አስተዳደራዊ ሥርዓትን አስወግዳችሁ እናንተ በትረ መንግሥቱን በጨበጣችሁ ጊዜ ምናልባት ከደርግ የተሻለ ለአንድነት ለእኩልነትና ለነፃነት የሚያስብልን፣የብሔር ብሔረሰቦችና፣ሁሉን ያቀፈ፣በሕገ መንግሥቱ የሚተዳደር መንግሥት ይፈጠራል ብሎ ሲጠብቅ እናንተ ግን የሕገ መንግሥቱን ሥርዓት ባልጠበቀ መልኩ የኢትዮጵያን ሕዝብና የኤርትራን ሕዝብ ፍላጎት ባላካተተ፣ ባልጠበቀና፣ባላገናዘበ መልኩ የኹለቱን ሰላማዊ ሕዝብ አንድነት አጥፍታችሁ፣በአንድነቱ ፈንታ ኹለትነትን ፈጥራችሁ፣ ለያይታችሁ፣በኹለቱ ሕዝብ መካከል ጥቁር ነጥብ ጥላችሁ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት፣ነፃነትና እኩልነት ያልቆማችሁ ለመሆናችሁ የምልክት ማህተብ በአንገታችሁ ያጠለቃችሁባትን ቀን ሳስብ መቼ ይሆን ይህ ዘመን የሚያልፈው ብዬ አስብ ነበር። የሚመጣውም ዘመን ምን እንደ ሚመስልና እንደሚሆን ስገምት በጣም ያስፈራኛና ያስጨንቀኝ ነበር።ታዲያ ዘመናትም ተቆጥሮ ዕለታትም አልፎ ኢየዋለ ኢያደረ ልዩነቱ፣መከፋፈሉ፣መለያየቱ፣መናናቁ፣መተራረዱ፣መገዳደሉና፣መጠላላቱ...ወዘተ በዝቶ ተባዝቶ እነሆ ዛሬ ያለንበት የደም ጎርፍ ዘመን ላይ ደርሰናል።

  ቅዱስ መጽሐፍ በማቴ ፩፪፥፳፭ ላይ "....ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው።እርስ በእርሷ የምትለያይ መንግሥት ሁሉ ትጠፋለች፤እርስ በእርሱ የሚለያይም ከተማም ወይም ቤት አይቆምም....."ይላልና ይህንን በአንድነት ሊያኖረን የማይችለውን ነገር አስወግደን ለሕዝብ የፈለገውን የመጠየቅ፣የመኖር፣ፍትህ የማግኘት እድል ካልሰጠን የኛም ሕልውና አጠራጣሪ ነው የሚሆነው።ሕዝብን ሁሉ በመግደልና፣በማሰር የምንመራው ከሆነ የሚቀረው ማነው?ሁሉም ከሞተ? ሁሉ ከታሰረ? በመንግሥት ስር የሚተዳደረው ማነው?ሕዝብ አልገዛም፣ አልተዳደርም፣እምቢ ካለ? ካመፀ? ።
ስለዚህ መንግሥት ለሕዝቡ ተማርኮ እጁን ሰጥቶና በቃኝ ብሎ መውረድና ሥልጣኑንም ለሕዝቡ መልቀቅ ላለፈው ላጠፋው ጥፋትና፣ በደል ይቅርታ ጠይቆ መቀመጥ አለበት።
   ምክንያቱም እስከ ዛሬ ድረስ ለተፈጠረው ጥፋት ሁሉ በየሚድያችሁ የመንግሥት የመልካም አስተዳደር ብሉሽነት ነው ኢያላችሁ ትናገራላችሁ።ሕዝቡም ያላችሁ ይህንኑ ነው።ትርፍ ነገርም አልጨመረም።መልካም አስተዳደር ከሌለ ያለው በተቃራኒው ክፉ አስተዳደር ነው ማለት ነው።ክፉ አስተዳደር ደግሞ ለሃያ አምስት ዓመታት ከመምረር አልፎ ይጎመዝዛል።አሁን ዛሬ የናንተን የመንግሥት አስተዳደር ማብቃት የሚፈልግና የሚጠይቅ ሁሉ ዕድሜ ተርፎትና በሚመጣው አዲስ የመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ገብቶ ተደስቶና ተንደላቆ ለመኖር ፈልጎ ሳይሆን ለቀሪውና ለተተኪው አዲስ ትውልድ መልካም አስተዳደር ይምጣለት ሲል ብቻ ነው እንጂ፤እርሱማ አስራ ሰባት ዓመታት በደርግ መንግሥት፣ሃያ አምስት ዓመታት በእናንተ/ኢህአዴግ/ በአጠቃላይ ከአርባ ዓመታት በላይ በጥይት ሲቆላና ሲታመስ፣አንጀቱ አሮና ከስሎ፣ተስፋው ተሟጦ፣የሞተው ሞቶ፣የቀረው ያለ ፍትህ በየእስር ቤቱ ታፍኖና፣ታስሮ፣ሌላውም በዘር፣በጎሳ፣ቋንቋና፣ክልል ተከፏፍሎና፣ተበትኖ፣በስደት የአውሬና የውቅያኖስ እራት ኢየሆነ ይገኛል።

      ስለዚህ እናንተ የኢትዮጵያ መንግስት ባለሥልጣን ሆይ፥እስቲ እናንተም አሁን ይብቃችሁና ይህንን ምስኪን ሕዝብ በተራው በቃህ በሉትና ዕረፍት ስጡት፤እናንተም ደግሞ ዕረፉ።ደክሞአችኋል፣ዝላችኋል።አሥራ ሰባት ዓመታት በጫካ ሃያ አምስት ዓመታት በሕዝብ ጫንቃ ላይ ሳትወርዱ ተንጠላጥላችሁ በጣም ብዙ ዓመታትና ዘመናት ነው ይከብዳል።ከዚህ በላይ ብዙ ብትደክሙ መልካም አስተዳደርን ለሕዝቡ ልታመጡ በፍፁም አትችሉም።ምክንያቱም ሃያ አምስት ዓመታትን በሙሉ ተደክሞበት ያልታየ መልካም አስተዳደር በአንድ ሌሊት ስብሰባና ግምገማ በተአምራት ልታመጡ አትችሉም፣አይሆንም።ጊዜያችሁና ዕድላችሁ ሻግቶ ተበላሽቶአል።ስለሆነም እናንተ በሰላማዊ መንገድ እውነተኛ ሰላምን ፈልጋችሁ መልካም አስተዳደራዊ መንግሥት ሊፈጠርበት የሚችለውን የሕዝብ የሆነ የሽግግር መንግሥት ይመሠረት ዘንድና ሥልጣናችሁንም ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ድርጅት ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስረክባችሁ በሰላም ውረዱና የዘመኑን ታሪክ ሥሩ።ያን ጊዜ የታሪክ ባለቤቶች ትሆናላችሁ።
አለበለዚ ግን ነቢየ እግዚአብሔር ሳሙኤል ለእስራኤል ንጉሥ ለሳዖል እንደ ነገረው ሳዖል በእስራኤል ሕዝብ ላይ መልካም አስተዳደርን አላመጣምና "... እግዚአብሔር መንግሥትህን ዛሬ ከአንተ ላይ ቀደዳት፣ለጎረቤትህም ሰው ሰጣት.." እንዳለው የዚህ ምስኪንና ደግ ሕዝብ እንባ
ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ወደ ፀባዖት ጌታ ደርሶ መንግሥታችሁን ከእናንተ ላይ በቀደደ ጊዜ ያን ሰዓት ወየውላችሁ፣ወዮታ አለባችሁ።ምክንያቱም ያን ወቅት እናንተ በሰፈራችሁበት መስፈሪያ፣በመዘናችሁበት ሚዛንና፣በፈረዳችሁበት ፍርድ መሰፈር፣መመዘንና መፈረድ አለና ነው።
ያን ጊዜ ጩኸት ይሆናል የማይጠቅም ጩኸት ነው፤ያን ጊዜ ልቅሶ ይሆናል የማይጠቅም ልቅሶ ነው።ይህ ሁሉ የብድራታችሁ ክፍያ ውጤት ነው።

    ጊዜያት ሁሉ የአምላክ ናቸው።ሰዎች የጊዜያት ባለቤቶች አይደሉም።ነገር ግን በተሰጣቸውና፣ በተወሰነላቸው ጊዜ ውስጥ ኖረው መልካምም ይሁን ክፉ ሠርተው ያልፋሉ።ያ የሠሩትም መልካምም ይሁን ክፉ ሥራቸው ለዘለዓለም ሲነገርና ሲዘከር ይኖራል።እናም ምናልባት እናንተም ሥልጣናችሁን ተመክታችሁ ያላችሁበትን ወቅትና ሰዓት ሁሉ የእኛ ብቻ ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ ተሳስታችኋል።ትላንት ያልነበራችሁብትን፣ዛሬ ደግሞ ያላችሁበትንና ነገ ደግሞ በተራው የማትኖሩበትን ጊዜ እንዳለ ማስተዋል ያስፈልጋችኋል ነው የምለው።ነገር ግን
እናንተ የደነደነ ልባችሁን ሰብራችሁ በይቅርታ ከዚህ ንፁህ፣ቅዱስና፣ደግ ሕዝብ ጋር ባትደራደሩ ነገ የጊዜያት ባለቤት ቸሩ አምላክ በጊዜው ለዚህ የዋህ ሕዝብ እጁን አጥፎና፣አመሳቅሎ፣ኢየታሰረ፣ኢየተደበደ፣ኢየደማና፣ኢየሞተ፣ለነፃነቱ፣ለእኩልነቱ፣ለአንድነቱና፣ለፍትህ ለሚጮኸው እናንተ ጩኸቱን ባትሰሙትና፣ባትፈርዱለት የሰማይ አባታቸው ቸሩ አምላክ ግን እንኳን ወደ እርሱ ጮኸው ለምነውት ቀርቶ ያልለመኑትንና ያልጠየቁትን
ሳይለምኑትና ሳይጠይቁት ይሰማቸዋል፣
ይሰጣቸዋል፣ይፈርድላቸዋል።

ክቡር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም፥
ክቡራን የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለ ሥልጣናትና ኃላፊዎች በሙሉ፥
እስከ ዛሬ ድረስ ለሃያ አምስት ዓመታት እኛ ብቻ ነን የምንናገረው፣እኛ ብቻ ነን የምናውቅላችሁ ብላችሁ ስትናገሩልንና፣ስታውቁልን እውቀታችሁንም፣ንግግራችሁንም ሰምተናል፣ተቀብለናል።ዛሬ ደግሞ የእኛ ተራ ነው።እናንተም ስሙን።ስለ እናንተ እናውቅላችኋለን አድምጡን።
እግዚአብሔርን በማመን የሚሠሩት ሥራ ይባረካል፣ ይቀደሳል።
እግዚአብሔር በማመን የሚጓዙት መንገድ ቀና ነው።
እግዚአብሔርን በማመን ለሚቀርቡት ይቀርባልና እመኑበት።
እግዚአብሔርን በማመን የሚመሩት ሕዝብ
ታዛዥ ይሆናል።
ስለዚህ እስቲ እናንተ ደግሞ ዛሬ ላለፈው ጊዜና ዘመን በሕዝብ ላይ ለሠራችሁት በደልና ግፍ ምህረቱ ይደረግላችሁ ዘንድ ከልባችሁ ቸሩ እግዚአብሔርን በነገሮች ሁሉ ጠይቁት።ንስሐ ጠማማውን ያቀናል፣ኃጥኡን ጻድቅ፣ክፉውን መልካም፣
 መልካም አስተዳደርን፣ቅን ፍርድንና ሰላማዊ ሕይወትን ለሕዝቡና ለአገሩ ያጎናፅፍላችኋል። ለዚህ ሁሉ ጥፋት ጉስቁልና የመሪዎች ከእግዚአብሔር ሕግና መግቦቱ መራቅና ከእርሱ ጋር ያይደለ ድካም ለብቻቸው በክፉ መንፈስ ኃይል ስለሚድክሙ ጭምር ነው።
ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙሩ
መዝ፦፻፳፮፥፩-፫
"እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ
ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፤
እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ
ጠባቂ በከንቱ ይተጋል፤
በማለዳ መግሥገሣችሁም ከንቱ ነው...."
ይላልና እናንተ መሪዎች ቸሩ አምላካችን በነገሮች ሁሉ ተጨምሮ ለአገሪቱና ለሕዝቡ ሥልጣናችሁን በማስረከብ መልካም አስተዳደርን የምታመጡበትን የንስሐ ዘመንን ይሰጣችሁ ዘንድ አምላኬን እለምነዋለሁ።ለዚህም ቅን ልቡናን፣ አስተዋይ አእምሮን፣እግዚአብሔርን የምትፈሩበትን፣ሰውንም የምታከብሩበት ሕሊናን ይስጣችሁ።አሜን።

ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር.
ተፃፈ
በቀሲስ አሸናፊ ዱጋ ዋቄ።