Tsige Sitotaw
በሁሉም ቤተ እምነቶች ዘንድ የሚታየው የፈውስ ጉዳይ ብዙ ሰዎችን ጥርጣሬ ውስጥ እያስገባ ነው ።
እስቲ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንነጋገርበት
1. ፈውስ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ
ክርስቲያን ፦
በዚች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታየው የፈውስ ሥነ ሥርዓት ያለ ፀበል የሚከናወን አይደለም ። ስለዚህም በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ፀበል በምንጭም ይሁን ከቧንቧ በተጠለፈ ውኃ የሚጠመቁ በርካታ ናቸው ።
እንዲሁም ፀበል እየተባለ በተለያዩ ቦታዎች እየተዘጋጄ በብዙ ሰልፍ የሚጠመቅ ሕዝብ ቀላል አይደለም ። በዚያ ቦታ ላይ የሚታዩትን ትርዒቶች ማየት አስገራሚ ነው ።
በክፉ መናፍስት የተያዙ ሰዎች አእምሯቸውን እየሳቱ እየወደቁ ከልባቸው እያለቀሱ ራሳቸውን እየሳቱ በብዙ መኃላ እየተገዘቱ ሲወጡና የታመሙት ነጻ ሲወጡ ይታያሉ ።
ይህ ሁሉ የሚሆነው በተለያዩ ቅዱሳን ስም በተሰየሙ ፀበሎች ነው ። ስለሆነም ኦርቶዶክሳውያን ትክክለኛ እምነት እንዳላቸውና ቅዱሳን ያማልዳሉ ለሚለው ማረጋገጫቸው ይኸው ተአምራት የሚታይበት ፀበል ቦታ ነው ።
በተጨማሪም ፦ በክፉ መንፈስ የተያዘው ሰው ራሱን ስቶ መንፈሱ በላዩ ላይ ሆኖ ሲለፈልፍ ከየትና ምን ሲያደርግ እንደያዘው መናገር ይጀምራል ።
ከየት ያዝኸው ሲባል ከጴንጤ ቸርች ምን ሲያደርግ ሲባል ኢየሱሴ ኢየሱሴ እያለ ሲለፈልፍ ትክክለኛው ሃይማኖት የትኛው ነው ሲባል ኦርቶዶክስ ሌላውስ ሲባል የውሼት እያሉ ካስለፈለፉ በኋላ ያንን በካሴት ቀድተው እውነተኛዋ ሃይማኖት ሰይጣን እንኳ የመሠከረላት ቅድስት ተዋሕዶ እያሉ ከሰይጣን በሰሙት መረጃ ሃይማኖታቸውን የሚሰብኩ ሰዎች አሉ ።
እንደገናም ሰይጣኑ ተቃጠልሁ ነደድሁ ልሂድ ልውጣ እያለ ሲጮህ ምስህ ምንድን ነው ? ተብሎ ይጠየቃል እሱም አመድ ወይም አተላ ወይም ደም ወይም ሌላ ነገር እንዲመጣለት ይጠይቃል ያዘዘው ነገር ሲቀርብለት ያንን ጠጥቶ ለቀቅሁ ብሎ ሦስት ጊዜ ጮኸህ ውጣ ዳግም ላትመለስ የሚካኤል ሰይፍ ይቁረጠኝ ብለህ ምለህ ተገዝተህ ውጣ ተብሎ ያንን ቃል ፈጽሞ ሄድሁ ብሎ ይጮሃል ። ከዚያ በኋላ ሕመምተኛው ጤነኛ ሆኖ በአእምሮው ይሆናል ማለት ነው ።
እሺ ነገሩን ተመልክተናል የሚካድም አይደለም ። ግን በመንፈሳዊ ዓይን ሲታይ በእርግጥ ፈውሱ ተከናውኗል ወይ ? ብለን ጠይቀን መልስ ማግኜት አንችልም ።
ምክንያቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምናደርገውን ሁሉ በማን ስም ማድረግ እንዳለብን አዝዞናል ።
ለምሳሌ ፦ እንደዚህም ያለውን አንድ ሕፃን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል ። የማቴዎስ ወንጌል 18÷5
ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና ። የማቴዎስ ወንጌል 18÷ 20
የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ በስሜ ጽዋ ውኃ የሚያጠጣችሁ ሁሉ፥ ዋጋው እንዳይጠፋበት እውነት እላችኋለሁ ። የማርቆስ ወንጌል 9÷41
ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ ። የማርቆስ ወንጌል 16÷17
በተጨማሪም የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14, 15,16 ሁሉንም ብንመለከታቸው በኢየሱስ ስም ብቻ መለመን ወይም መጸለይ እንዳለብን ታዝዘናል።
አጋንንት የሚወጡት በእርሱ ስም ሙታን የሚነሡት ለምጻሞች የሚነጹት ማናቸውም ፈውስ የሚከናወነው በጌታ ስም ብቻ እንደሆነ ታዝዘናል ።
ታዲያ እንዲህ ከሆነ በፀበልና በቅዱሳን ስም እንደሚለቁ ሆነው የሚጮሁት ለምንድን ነው ?
እንግዲያው ሰይጣን እያታለለን እያዘናጋን እንደሆነ ልናውቅበት ይገባል ። ባልተሰበከልን ልዩ ወንጌል ታስረን ከእርሱ ጋር ወደ ገሃነም እንዳንገባ ።
ስለዚህ የምናደርገውን ሁሉ በኢየሱስ ስም ብቻ ። አሜን ። አሜን ። አሜን ። ወአሜን ለይኩን ለይኩን ።
2 . ፈውስ በወንጌላውያን ፦
በአሁኑ ሰዓት እርስ በእርሳቸው የማይተዋወቁ በፕሮቴስታንትነት የሚታወቁ በርካታ ቤተ እምነቶች እየተመለከትን ነው ። አንዳንዶች በሽማግሌዎች ሲመሩ አንዳንዶች ደግሞ በግለ ሰቦች ብቻ የሚመሩ ናቸው ።
በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተመሳሳይነታቸው ይበዛል ። በአደባባይ የሚፈጸመውን ሥርዓተ አምልኮ ስንመለከትም ጸሎቱ ዝማሬው ስብከቱ አለባበሱ ልሣኑ ትንቢቱ ጥምቀቱ ቊርባኑ ሁሉ አንዱን ከሌላው መለየት አይቻልም ።
ሁሉም ለኢትዮጵያ እንግዶችና መጤዎች የሚያስመስላቸውን እንግዳ ነገር ሲፈጽሙ ይስተዋላል ። ምንም እንኳ ገድልና ድርሳን ባይኖራቸውም አሁን ባሉት አገልጋዮቻቸው በእጅጉ ስለሚደገፉባቸው የተሳሳቱ መልእክቶችን ሊያስተናግዱ ይችላሉ የሚል የብዙ ሰዎች ስጋት አለ ።
ለምሳሌ ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ ትላልቅ የእግዚአብሔር ባሪያዎች የተጠሩበትን ስም በባለቤትነት መያዝ "የግዚአብሔር ሰው" እንዲባሉ መፍቀድና ከሌላው አማኝ ልዩነት ማሳየት ።
ሰውነታቸው ከሁሉም በላይ ወፍሮና ገዝፎ እየታየ እነሱ ግን ከሁሉ በላይ እንደሚጾሙና እንደሚጸልዩ ራሳቸውን መስበክ ቲፎዞ ማብዛት ።
መናፍስትን ከሰው ሲያስወጡ መንፈሱ ለእነሱ እውቅና እንዲሰጥ እድሉን ማመቻቸት ከዚያም ከሕዝቡ ሙገሳን ጭብጨባንና አድናቆትን መቀበል ።
የሚያሳፍረው ግን ሰይጣኑ ሲለቅ ሦስት ጊዜ ጮኸህ ውጣ እየተባለ መታዘዙ ነው "ዝም ብለህ ውጣ" መባል ሲገባው ብዙ ምሥክርነት እንዲሰጥና ሰው ሁሉ እንዲገረም ማድረግና አጋንንትን ለደቀ መዝሙርነት እንደመጠቀም ያስቆጥራል ።
ያልተፈወሱ ሰዎችን ተፈውሳችኋል በማለትና ሐኪም ያዘዘላቸውን መድኃኒት እንዲያቋርጡ በማድረግ ለበርካታ ሰዎች ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት መሆናቸውና ይህም በሕግ ፊት ደርሶ እያነጋገረ መሆኑ በተጨማሪም የገንዘብ ብክነት ሁሉ ደርሷል መባሉና በጉዳዩ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባበት መገደዱ ሌላው ፈተና ሆኗል ።
እንግዲህ በዚህ ሁሉ ፉክክር እያንዳንዱ ቤተ እምነት ለመተራረም ፈቃደኛ ባለመሆኑ አንዱ በአንዱ እየሳቀ እውነተኛ ፈውስም እየጠፋ ክርስቶስን ከሚያምነው ይልቅ የሚተወው እየበዛ መጥቷል።
አሕዛብን ዝም የሚያሰኝ በሁሉም ዘንድ መገረምን የሚያመጣ ዓይን ለሌለው ዓይን እግር ለሌለው እግር የሞተንና የተቀበረን ከሞት ማስነሣት የተካተተበት ፈውስ እንጂ ጨጓራና አንጀት ብቻ እየተባለ አገልግሎቱ ጥርጣሬ ላይ ይወድቃል እንጂ የትም አይደርስም ።
ስለዚህ በሁሉም ቤተ እምነት የሚከሰቱትን ችግሮች ማስተካከልና እንደ እግዚአብሔር ቃል ማስሄድ ቢቻል ማለፊያ ነው ።
እናንተስ ምን ታዘባችሁ ?