ቀን 08/27/2016
ይድረስ
ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣
ለኢትዮጵያ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሙሉ ።
በቅድምያ እናንተ በዚህ በአገራችን በኢትዮጵያ የሥልጣን ወንበር ላይ ለበጎም ይሁን ለክፉ ያስቀመጣችሁ ቸሩ አምላክ እግዚአብሔር እርሱ ባወቀው መንገድ እንደሆነ ስለማምን ለዚህም ኃላፊነትና ሥልጣን የተሰጣችሁ ናችሁና በእየ መዓርጋችሁ የከበረ የአክብሮት ሰላምታዬን አቀርባለሁ።
ከዚህ በመቀጠል ሌላው
፩ኛ ሳሙ ፲፭፥፳ "....ሳሙኤልም እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀደዳት፥ ከአንተም ለሚሻል ጎረቤትህ አሳልፎ ሰጣት...."ይላል።
ይህንን ካልኩ በኋላ በእውነቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት የደርግን መንግሥት አስተዳደራዊ ሥርዓትን አስወግዳችሁ እናንተ በትረ መንግሥቱን በጨበጣችሁ ጊዜ ምናልባት ከደርግ የተሻለ ለአንድነት ለእኩልነትና ለነፃነት የሚያስብልን፣የብሔር ብሔረሰቦችና፣ሁሉን ያቀፈ፣በሕገ መንግሥቱ የሚተዳደር መንግሥት ይፈጠራል ብሎ ሲጠብቅ እናንተ ግን የሕገ መንግሥቱን ሥርዓት ባልጠበቀ መልኩ የኢትዮጵያን ሕዝብና የኤርትራን ሕዝብ ፍላጎት ባላካተተ፣ ባልጠበቀና፣ባላገናዘበ መልኩ የኹለቱን ሰላማዊ ሕዝብ አንድነት አጥፍታችሁ፣በአንድነቱ ፈንታ ኹለትነትን ፈጥራችሁ፣ ለያይታችሁ፣በኹለቱ ሕዝብ መካከል ጥቁር ነጥብ ጥላችሁ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት፣ነፃነትና እኩልነት ያልቆማችሁ ለመሆናችሁ የምልክት ማህተብ በአንገታችሁ ያጠለቃችሁባትን ቀን ሳስብ መቼ ይሆን ይህ ዘመን የሚያልፈው ብዬ አስብ ነበር። የሚመጣውም ዘመን ምን እንደ ሚመስልና እንደሚሆን ስገምት በጣም ያስፈራኛና ያስጨንቀኝ ነበር።ታዲያ ዘመናትም ተቆጥሮ ዕለታትም አልፎ ኢየዋለ ኢያደረ ልዩነቱ፣መከፋፈሉ፣መለያየቱ፣መናናቁ፣መተራረዱ፣መገዳደሉና፣መጠላላቱ...ወዘተ በዝቶ ተባዝቶ እነሆ ዛሬ ያለንበት የደም ጎርፍ ዘመን ላይ ደርሰናል።
ቅዱስ መጽሐፍ በማቴ ፩፪፥፳፭ ላይ "....ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው።እርስ በእርሷ የምትለያይ መንግሥት ሁሉ ትጠፋለች፤እርስ በእርሱ የሚለያይም ከተማም ወይም ቤት አይቆምም....."ይላልና ይህንን በአንድነት ሊያኖረን የማይችለውን ነገር አስወግደን ለሕዝብ የፈለገውን የመጠየቅ፣የመኖር፣ፍትህ የማግኘት እድል ካልሰጠን የኛም ሕልውና አጠራጣሪ ነው የሚሆነው።ሕዝብን ሁሉ በመግደልና፣በማሰር የምንመራው ከሆነ የሚቀረው ማነው?ሁሉም ከሞተ? ሁሉ ከታሰረ? በመንግሥት ስር የሚተዳደረው ማነው?ሕዝብ አልገዛም፣ አልተዳደርም፣እምቢ ካለ? ካመፀ? ።
ስለዚህ መንግሥት ለሕዝቡ ተማርኮ እጁን ሰጥቶና በቃኝ ብሎ መውረድና ሥልጣኑንም ለሕዝቡ መልቀቅ ላለፈው ላጠፋው ጥፋትና፣ በደል ይቅርታ ጠይቆ መቀመጥ አለበት።
ምክንያቱም እስከ ዛሬ ድረስ ለተፈጠረው ጥፋት ሁሉ በየሚድያችሁ የመንግሥት የመልካም አስተዳደር ብሉሽነት ነው ኢያላችሁ ትናገራላችሁ።ሕዝቡም ያላችሁ ይህንኑ ነው።ትርፍ ነገርም አልጨመረም።መልካም አስተዳደር ከሌለ ያለው በተቃራኒው ክፉ አስተዳደር ነው ማለት ነው።ክፉ አስተዳደር ደግሞ ለሃያ አምስት ዓመታት ከመምረር አልፎ ይጎመዝዛል።አሁን ዛሬ የናንተን የመንግሥት አስተዳደር ማብቃት የሚፈልግና የሚጠይቅ ሁሉ ዕድሜ ተርፎትና በሚመጣው አዲስ የመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ገብቶ ተደስቶና ተንደላቆ ለመኖር ፈልጎ ሳይሆን ለቀሪውና ለተተኪው አዲስ ትውልድ መልካም አስተዳደር ይምጣለት ሲል ብቻ ነው እንጂ፤እርሱማ አስራ ሰባት ዓመታት በደርግ መንግሥት፣ሃያ አምስት ዓመታት በእናንተ/ኢህአዴግ/ በአጠቃላይ ከአርባ ዓመታት በላይ በጥይት ሲቆላና ሲታመስ፣አንጀቱ አሮና ከስሎ፣ተስፋው ተሟጦ፣የሞተው ሞቶ፣የቀረው ያለ ፍትህ በየእስር ቤቱ ታፍኖና፣ታስሮ፣ሌላውም በዘር፣በጎሳ፣ቋንቋና፣ክልል ተከፏፍሎና፣ተበትኖ፣በስደት የአውሬና የውቅያኖስ እራት ኢየሆነ ይገኛል።
ስለዚህ እናንተ የኢትዮጵያ መንግስት ባለሥልጣን ሆይ፥እስቲ እናንተም አሁን ይብቃችሁና ይህንን ምስኪን ሕዝብ በተራው በቃህ በሉትና ዕረፍት ስጡት፤እናንተም ደግሞ ዕረፉ።ደክሞአችኋል፣ዝላችኋል።አሥራ ሰባት ዓመታት በጫካ ሃያ አምስት ዓመታት በሕዝብ ጫንቃ ላይ ሳትወርዱ ተንጠላጥላችሁ በጣም ብዙ ዓመታትና ዘመናት ነው ይከብዳል።ከዚህ በላይ ብዙ ብትደክሙ መልካም አስተዳደርን ለሕዝቡ ልታመጡ በፍፁም አትችሉም።ምክንያቱም ሃያ አምስት ዓመታትን በሙሉ ተደክሞበት ያልታየ መልካም አስተዳደር በአንድ ሌሊት ስብሰባና ግምገማ በተአምራት ልታመጡ አትችሉም፣አይሆንም።ጊዜያችሁና ዕድላችሁ ሻግቶ ተበላሽቶአል።ስለሆነም እናንተ በሰላማዊ መንገድ እውነተኛ ሰላምን ፈልጋችሁ መልካም አስተዳደራዊ መንግሥት ሊፈጠርበት የሚችለውን የሕዝብ የሆነ የሽግግር መንግሥት ይመሠረት ዘንድና ሥልጣናችሁንም ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ድርጅት ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስረክባችሁ በሰላም ውረዱና የዘመኑን ታሪክ ሥሩ።ያን ጊዜ የታሪክ ባለቤቶች ትሆናላችሁ።
አለበለዚ ግን ነቢየ እግዚአብሔር ሳሙኤል ለእስራኤል ንጉሥ ለሳዖል እንደ ነገረው ሳዖል በእስራኤል ሕዝብ ላይ መልካም አስተዳደርን አላመጣምና "... እግዚአብሔር መንግሥትህን ዛሬ ከአንተ ላይ ቀደዳት፣ለጎረቤትህም ሰው ሰጣት.." እንዳለው የዚህ ምስኪንና ደግ ሕዝብ እንባ
ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ወደ ፀባዖት ጌታ ደርሶ መንግሥታችሁን ከእናንተ ላይ በቀደደ ጊዜ ያን ሰዓት ወየውላችሁ፣ወዮታ አለባችሁ።ምክንያቱም ያን ወቅት እናንተ በሰፈራችሁበት መስፈሪያ፣በመዘናችሁበት ሚዛንና፣በፈረዳችሁበት ፍርድ መሰፈር፣መመዘንና መፈረድ አለና ነው።
ያን ጊዜ ጩኸት ይሆናል የማይጠቅም ጩኸት ነው፤ያን ጊዜ ልቅሶ ይሆናል የማይጠቅም ልቅሶ ነው።ይህ ሁሉ የብድራታችሁ ክፍያ ውጤት ነው።
ጊዜያት ሁሉ የአምላክ ናቸው።ሰዎች የጊዜያት ባለቤቶች አይደሉም።ነገር ግን በተሰጣቸውና፣ በተወሰነላቸው ጊዜ ውስጥ ኖረው መልካምም ይሁን ክፉ ሠርተው ያልፋሉ።ያ የሠሩትም መልካምም ይሁን ክፉ ሥራቸው ለዘለዓለም ሲነገርና ሲዘከር ይኖራል።እናም ምናልባት እናንተም ሥልጣናችሁን ተመክታችሁ ያላችሁበትን ወቅትና ሰዓት ሁሉ የእኛ ብቻ ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ ተሳስታችኋል።ትላንት ያልነበራችሁብትን፣ዛሬ ደግሞ ያላችሁበትንና ነገ ደግሞ በተራው የማትኖሩበትን ጊዜ እንዳለ ማስተዋል ያስፈልጋችኋል ነው የምለው።ነገር ግን
እናንተ የደነደነ ልባችሁን ሰብራችሁ በይቅርታ ከዚህ ንፁህ፣ቅዱስና፣ደግ ሕዝብ ጋር ባትደራደሩ ነገ የጊዜያት ባለቤት ቸሩ አምላክ በጊዜው ለዚህ የዋህ ሕዝብ እጁን አጥፎና፣አመሳቅሎ፣ኢየታሰረ፣ኢየተደበደ፣ኢየደማና፣ኢየሞተ፣ለነፃነቱ፣ለእኩልነቱ፣ለአንድነቱና፣ለፍትህ ለሚጮኸው እናንተ ጩኸቱን ባትሰሙትና፣ባትፈርዱለት የሰማይ አባታቸው ቸሩ አምላክ ግን እንኳን ወደ እርሱ ጮኸው ለምነውት ቀርቶ ያልለመኑትንና ያልጠየቁትን
ሳይለምኑትና ሳይጠይቁት ይሰማቸዋል፣
ይሰጣቸዋል፣ይፈርድላቸዋል።
ክቡር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም፥
ክቡራን የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለ ሥልጣናትና ኃላፊዎች በሙሉ፥
እስከ ዛሬ ድረስ ለሃያ አምስት ዓመታት እኛ ብቻ ነን የምንናገረው፣እኛ ብቻ ነን የምናውቅላችሁ ብላችሁ ስትናገሩልንና፣ስታውቁልን እውቀታችሁንም፣ንግግራችሁንም ሰምተናል፣ተቀብለናል።ዛሬ ደግሞ የእኛ ተራ ነው።እናንተም ስሙን።ስለ እናንተ እናውቅላችኋለን አድምጡን።
እግዚአብሔርን በማመን የሚሠሩት ሥራ ይባረካል፣ ይቀደሳል።
እግዚአብሔር በማመን የሚጓዙት መንገድ ቀና ነው።
እግዚአብሔርን በማመን ለሚቀርቡት ይቀርባልና እመኑበት።
እግዚአብሔርን በማመን የሚመሩት ሕዝብ
ታዛዥ ይሆናል።
ስለዚህ እስቲ እናንተ ደግሞ ዛሬ ላለፈው ጊዜና ዘመን በሕዝብ ላይ ለሠራችሁት በደልና ግፍ ምህረቱ ይደረግላችሁ ዘንድ ከልባችሁ ቸሩ እግዚአብሔርን በነገሮች ሁሉ ጠይቁት።ንስሐ ጠማማውን ያቀናል፣ኃጥኡን ጻድቅ፣ክፉውን መልካም፣
መልካም አስተዳደርን፣ቅን ፍርድንና ሰላማዊ ሕይወትን ለሕዝቡና ለአገሩ ያጎናፅፍላችኋል። ለዚህ ሁሉ ጥፋት ጉስቁልና የመሪዎች ከእግዚአብሔር ሕግና መግቦቱ መራቅና ከእርሱ ጋር ያይደለ ድካም ለብቻቸው በክፉ መንፈስ ኃይል ስለሚድክሙ ጭምር ነው።
ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙሩ
መዝ፦፻፳፮፥፩-፫
"እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ
ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፤
እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ
ጠባቂ በከንቱ ይተጋል፤
በማለዳ መግሥገሣችሁም ከንቱ ነው...."
ይላልና እናንተ መሪዎች ቸሩ አምላካችን በነገሮች ሁሉ ተጨምሮ ለአገሪቱና ለሕዝቡ ሥልጣናችሁን በማስረከብ መልካም አስተዳደርን የምታመጡበትን የንስሐ ዘመንን ይሰጣችሁ ዘንድ አምላኬን እለምነዋለሁ።ለዚህም ቅን ልቡናን፣ አስተዋይ አእምሮን፣እግዚአብሔርን የምትፈሩበትን፣ሰውንም የምታከብሩበት ሕሊናን ይስጣችሁ።አሜን።
ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር.
ተፃፈ
በቀሲስ አሸናፊ ዱጋ ዋቄ።