Thursday, December 29, 2011

እውነትም ፍቅር ትቀዘቅዛለች!


ሩቅ ሳንሄድ ኢትዮጵያ ውስጥ እስላሙ በክርስትያኑ ላይ «የአላሁአክባር» ዘመቻውን በደንብ እያስፋፋው ስለመገኘቱ ከታች ባለው ርእስ የተመለከተው የቪዲዮ ምስል ማሳያ ነው። እራሱ ክርስቲያን ነኝ የሚለው ኦርቶዶክሱ እርስ በእርሱ እየተባላ፣ እየተካሰሰ፣ የአሸናፊነት ከበሮ ለመደለቅ በአንድ ወገን ሲኖዶሱ እርስ በእርስ፣ በሌላ ወገን ማኅበረ ቅዱሳንና ደጋፊዎቹ በእነ በጋሻው ላይ የተያዘ የሞት ሽረት ትንቅንቅ፣ በእስልምናው በራሱ የሱኒና የሐነፊ ሽኩቻ በመጨረሻው ዘመን የተነገረው ትንቢት እየደረሰ ይሆን? ያስብላል። «ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል» ማቴ 24፣7ከሁሉ የሚገርመውና ትንቢቱን በትክክል የሚያረጋግጥልን ነገር ክርስቶስ በተወለደበት ቤተልሔም መቅደስ የፈረንጆቹ ገና በሁለት ወገን ጦርነት ደምቆ መዋሉ ነው። ኳኳታና የሰው ግንባር ፍንዳታ በተሰማበት አዲስ ዜማ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ክርስቲያን ቀርቶ አረሚ የማያደርገውን ፈጽመው አክብረው ዋሉ። እውነትም «ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች» ማቴ24፣12 ያለው ደርሷል። ግሪኮችና አርመኖች ተፈጣፈጡ!!



Wednesday, December 28, 2011

የኢየሱስ ክርስቶስ አስታራቂነትና አምላክነት

«ክርስቶስ ማለት በቁሙ ወደአማርኛ የተገለበጠው የግሪኩ(ጽርእ)ቃል «Χριστός»«ክሪስቶሽ ሲሆን ትርጉሙም «የተቀባ» ማለት ነው። መቀባት « χριστῷ» የሚለውን ብቻውን የሚያመለክተው ከሌላ መቀበልን ሲሆን «ክርስቶስ» የሚለው ቃል ግን የቅብእ ባለቤትነትንና የመቀባት ግብርን አያይዞ የሚጠራ ስም ነው። (ኢሳ 45፣1) ይመልከቱ። «ክርስቶስ» በእብራይስጡ «המשיח» ሀመሺያኽ ቅቡእ፣ የተቀባ ሲሆን ግእዙ «መሲህ» በሚለው ይተካዋል። የቤተክርስቲያን ሊቃውንትም «የክርስቶስን መቀባት ወይም ቅቡእ መሆን ለማመልከት ሲያስተምሩ «አብ ቀባኢ፣ ወልድ ተቀባኢ፣ መንፈስ ቅዱስ ቅብእ» በማለት ይገልጻሉ። በእርግጥ ይህ ትምሕርተ መለኰት ሰፊና ጥልቅ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ዙሪያ የተነሱ ትምህርቶችና ክርክሮች ብዙ ሲያምሱ ቆይቷል፣ ዛሬም ቢሆን ጨርሶ የጠፋ ስለመሆኑ የሚታወቅ ነገር የለም። እኛም ያንን ላለመድገም እንደመንደርደሪያ ይህንን ያህል ካልን ወደተነሳንለት ዓላማ እናምራ!
«ክርስቶስ» የተቀባ ማለት ነው ብለናል። እንደዚሁ ሁሉ «ኢየሱስ» የሚለውን ስንመለከት የእብራይስጡ «ישוע» የሹአ ሲሆን ትርጉሙም «መድኃኒት» ማለት ነው። ግሪኩም «Ιησούς» መድኃኒት፣( ማዳን)፣ አዳኝ የሚለውን ትርጉም ይሰጣል። ከዚህ የተነሳ «ኢየሱስ ክርስቶስ» ማለት «የተቀባ፣ቅቡእ እና መድኃኒት፣ አዳኝ» የሆነ ማለት ነው። ይህንን የስም ትርጉም ካገኘን ለሚቀጥሉት ሃሳቦቻችን መረዳት መጠነኛ ግንዛቤ ጨብጠናል ማለት ነው።
የሚቀባው ማነው? የሚቀባውስ ለምንድነው?
እነዚህን ነገሮች አጥርቶ ማወቅ የብሉይ ኪዳን አስተምህሮዎችን መመርመር ግድ ይላል። ያንንም ማድረግ አስፈላጊ የሚሆነው «ስለመሲሁ» ክርስቶስነት ላይ በሚነሱ ልዩ ልዩ አመለካከቶች ከብዥታ የወጣ እይታ እንዲኖረን ይረዳናል።
ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ........>>>(እዚህ ላይ ይጫኑ

Thursday, December 22, 2011

መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ደሳለኝ የአራዳውን ምድብ ችሎት በመሳጭ ስብከቱ አስደመመ


ጽሁፉን በፒዲኤፍ ማንበብ ከፈለጉ ........>>>To read in PDF click here


ታህሣሥ 9 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው የአራዳው ምድብ ችሎት የዐቃቤ ሕግ አንደኛ ምሥክር ሆኖ የቀረበው መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ደሳለኝ ችሎቱን ፍጹም ወደ ሆነ መንፈሳዊ ድባብ ለውጦ አስተምሮ መውጣቱን የዜና ምንጮቻችን አረጋገጠዋል፡፡ ዘመድኩን በቀለ በግሉ አርማጌዶን ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት ሲዲና ቪሲዲ በማሠራጨት እና የተሳሳተ መልዕክት በማስተላለፍ ምዕመናንን በማወናበዱና በወንድሞች ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ በመክፈቱ በአራዳው ምድብ ችሎት ላይ ክስ የተመሠረተበት ሲሆን እርሱ ራሱ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባል የሆነ ጠበቃ አቁሞ ለመከላከል ሞክሯል፡፡ በዚሁ ዕለት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ 10፡25 በቆየው የክርክር ሂደት የዘመድኩን ጠበቃ የተልፈሰፈሰ መስቀለኛ ጥያቄ ለማቅረብ ሞክሮ በታዳሚው ሲሳቅበት እንደዋለ እነዚሁ ምንጮቻችን አስታውቀዋል፡፡

ጠበቃው ባቀረበው መስቀለኛ ጥያቄ ቤተክርስቲያንን "አሮጊቷ ሣራ" ብለህ ተሳድበሃል፤ ታዲያ ቤተክርስቲያንን በምንፍቅና ጥለው ከሄዱት ከእነ አባ ዮናስ በምን ትለያለህ? ብሎ የጠየቀው ሲሆን፣ መጋቤ ሀዲስ በጋሻው በሰጠው ምላሽ፣ እናታችን ሣራ በዕድሜ ብታረጅም፣ እግዚአብሔር አከበራት፤ ልጆችን ሰጣት፡፡ እኔም፣ ጥንታዊት ቤተክርስቲያናችን በአሁኑ ሰዓት በማገልገል ላይ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች አገልጋዮችን አፍርታለች ነው ያልኩት፡፡ የእኛ ሣራ ልጆችን ወልዳለች፤ የእነ አባ ዮናስ ሣራ ግን ስለመወለዷ አይታወቅም፤ በዚህ እንለያለን በማለት መመለሱ ታውቋል፡፡

መጋቤ ሀዲስ በመቀጠል የቀረበለት ጥያቄ፣ ራስህን በራስህ ሰባኪ አድርገሃል፤ የቤተክርስቲያን ትምህርት ሳይኖርህ ታስተምራለህ፤ ለመሆኑ ዲቁናውን ማን ሰጠህ? መጋቤ ሀዲስ የሚለውንስ ማዕረግ ከወዴት አገኘኸው? የሚል ነበር፡፡ እርሱም በበኩሉ ሲመልስ፣ ዲቁናውን የተቀበልኩት ከብፁዕ አቡነ በርተለሜዎስ የቀድሞው የሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ነው፡፡ የስብከት መምህርነት ኮርስም ተከታትዬ የተሰጠኝ የምሥክር ወረቀት አለኝ፡፡ የመጋቤ ሀዲስነት ማዕረጉንም ሰባ ሺህ ያህል ሕዝብ ባለበት የሰጡኝ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በዚያን ወቅት የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ናቸው፡፡

መምህር በጋሻው ሌላው የቀረበለት ጥያቄ የእኛ ጌታ ተኝቶ ይገዛል ብለሃል፡፡ ይህ አባባልህ ልክ ነው? የሚል ነበር፡፡ እርሱም ሲመልስ ታዲያ ይሄ ምን ስሕተት አለው? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር በጀልባ ሲጓዝ፣ ተኝቶ ነበርና ማዕበሉ በተነሳ ጊዜ ሲቀሰቅሱት፣ እምነት የጎደላችሁ ስለምንድርነው አላላቸውም? በከርሰ መቃብር ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ባደረበት ወቅት ዓለምን አልገዛም? ጌታችን፣ አምላካችን በሰው አስተሳሰብ የተኛ ፣ የሞተ ቢመስልም እርሱ ግን ሁሉንም በኃይሉ ይጠብቅ ነበር፤ በማለት መልሷል፡፡ መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ሌሎችንም ተጨማሪ ማብራሪያዎችን የሰጠ ሲሆን፣ እርሱ ጥያቄዎችን በሚመልስበት ወቅት ሁሉም ከመመሰጡ የተነሳ የችሎቱ ሂደት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ እስከሚመስል ደርሶ እንደነበር በስፍራው የነበሩ እማኞች ገልጸዋል፡፡