Thursday, December 22, 2011

መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ደሳለኝ የአራዳውን ምድብ ችሎት በመሳጭ ስብከቱ አስደመመ


ጽሁፉን በፒዲኤፍ ማንበብ ከፈለጉ ........>>>To read in PDF click here


ታህሣሥ 9 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው የአራዳው ምድብ ችሎት የዐቃቤ ሕግ አንደኛ ምሥክር ሆኖ የቀረበው መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ደሳለኝ ችሎቱን ፍጹም ወደ ሆነ መንፈሳዊ ድባብ ለውጦ አስተምሮ መውጣቱን የዜና ምንጮቻችን አረጋገጠዋል፡፡ ዘመድኩን በቀለ በግሉ አርማጌዶን ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት ሲዲና ቪሲዲ በማሠራጨት እና የተሳሳተ መልዕክት በማስተላለፍ ምዕመናንን በማወናበዱና በወንድሞች ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ በመክፈቱ በአራዳው ምድብ ችሎት ላይ ክስ የተመሠረተበት ሲሆን እርሱ ራሱ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባል የሆነ ጠበቃ አቁሞ ለመከላከል ሞክሯል፡፡ በዚሁ ዕለት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ 10፡25 በቆየው የክርክር ሂደት የዘመድኩን ጠበቃ የተልፈሰፈሰ መስቀለኛ ጥያቄ ለማቅረብ ሞክሮ በታዳሚው ሲሳቅበት እንደዋለ እነዚሁ ምንጮቻችን አስታውቀዋል፡፡

ጠበቃው ባቀረበው መስቀለኛ ጥያቄ ቤተክርስቲያንን "አሮጊቷ ሣራ" ብለህ ተሳድበሃል፤ ታዲያ ቤተክርስቲያንን በምንፍቅና ጥለው ከሄዱት ከእነ አባ ዮናስ በምን ትለያለህ? ብሎ የጠየቀው ሲሆን፣ መጋቤ ሀዲስ በጋሻው በሰጠው ምላሽ፣ እናታችን ሣራ በዕድሜ ብታረጅም፣ እግዚአብሔር አከበራት፤ ልጆችን ሰጣት፡፡ እኔም፣ ጥንታዊት ቤተክርስቲያናችን በአሁኑ ሰዓት በማገልገል ላይ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች አገልጋዮችን አፍርታለች ነው ያልኩት፡፡ የእኛ ሣራ ልጆችን ወልዳለች፤ የእነ አባ ዮናስ ሣራ ግን ስለመወለዷ አይታወቅም፤ በዚህ እንለያለን በማለት መመለሱ ታውቋል፡፡

መጋቤ ሀዲስ በመቀጠል የቀረበለት ጥያቄ፣ ራስህን በራስህ ሰባኪ አድርገሃል፤ የቤተክርስቲያን ትምህርት ሳይኖርህ ታስተምራለህ፤ ለመሆኑ ዲቁናውን ማን ሰጠህ? መጋቤ ሀዲስ የሚለውንስ ማዕረግ ከወዴት አገኘኸው? የሚል ነበር፡፡ እርሱም በበኩሉ ሲመልስ፣ ዲቁናውን የተቀበልኩት ከብፁዕ አቡነ በርተለሜዎስ የቀድሞው የሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ነው፡፡ የስብከት መምህርነት ኮርስም ተከታትዬ የተሰጠኝ የምሥክር ወረቀት አለኝ፡፡ የመጋቤ ሀዲስነት ማዕረጉንም ሰባ ሺህ ያህል ሕዝብ ባለበት የሰጡኝ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በዚያን ወቅት የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ናቸው፡፡

መምህር በጋሻው ሌላው የቀረበለት ጥያቄ የእኛ ጌታ ተኝቶ ይገዛል ብለሃል፡፡ ይህ አባባልህ ልክ ነው? የሚል ነበር፡፡ እርሱም ሲመልስ ታዲያ ይሄ ምን ስሕተት አለው? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር በጀልባ ሲጓዝ፣ ተኝቶ ነበርና ማዕበሉ በተነሳ ጊዜ ሲቀሰቅሱት፣ እምነት የጎደላችሁ ስለምንድርነው አላላቸውም? በከርሰ መቃብር ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ባደረበት ወቅት ዓለምን አልገዛም? ጌታችን፣ አምላካችን በሰው አስተሳሰብ የተኛ ፣ የሞተ ቢመስልም እርሱ ግን ሁሉንም በኃይሉ ይጠብቅ ነበር፤ በማለት መልሷል፡፡ መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ሌሎችንም ተጨማሪ ማብራሪያዎችን የሰጠ ሲሆን፣ እርሱ ጥያቄዎችን በሚመልስበት ወቅት ሁሉም ከመመሰጡ የተነሳ የችሎቱ ሂደት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ እስከሚመስል ደርሶ እንደነበር በስፍራው የነበሩ እማኞች ገልጸዋል፡፡



በዚሁ ችሎት ሌላኛው ምሥክር ዘመድኩን ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ዋዜማ የአባቶች ሥርዓተ ጸሎት መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ይረብሹ ለነበሩ ጎረምሶች በምሥራቅ በር በኩል፣ ወደ አራት ኪሎ መሄጃ አቅጣጫ ቆሞ ብር ይከፍል እንደነበር አረጋግጦበታል፡፡ የምሥክር ቃል ተሰጥቶ እንዳበቃም፣ ለብይን ለታህሣሥ 19 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ 8፡30 ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ ተነስቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ በችሎቱ ላይ በዝቶ ለመታየት እና ጫና ለማሳደር ከየሥፍራው ተጠራርተው በመጡ ቅጥር ወጣቶች መሞላቱ ሲታወቅ፣ ይህንኑ የቅጥረኛ ሠራዊት የምታስተባብረው ፌቨን (ለጊዜው የአባቷ ስም ይቆየን) የምትባል ቀንደኛ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ደጋፊ ናት ተብሏል፡፡ ይህችው ሰው ልደታ ለማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ መዝሙር ቤት ያላት ሲሆን፣ በሰዋስወ ብርሃን ወጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የ3ኛ ዓመት የክፍል 3A ተማሪ መሆኑዋን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡

ፌቨን ከዚሀ በፊት ዘማሪ ሐዋዝን ለማስደብደብ፣ የሞከረች ሲሆን፣ በደብረ አሚን ከተከሰተው ሁከት ጋር በተያያዘም ዱርዬዎችን ልካ ወንድሞችንና እህቶችን ታስደበድብ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ እንዲሁም፣ ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ዋዜማ የአባቶች ሥርዓተ ጸሎት መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ሲረብሹ እጅ ከፍንጅ ተይዘው ለታሠሩት ተላላኪዎቿ ስንቅ ታቀብል እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

ፌቨን ኮሌጁን በመበጥበጥ የምትታወቅ ሲሆን፣ የወንጌል መምህራንን ከቤተክርስቲያን እና ክክርስቶስ ፍቅር ለመነጠል በምታደርገው ያላሠለሰ ጥረት ሳቢያ እዚያው አብረዋት በሚማሩ መነኮሳት ዘንድ "ኮቲባ" የሚል ቅጽል ስም ወጥቶላታል፡፡ (ኮቲባ መነሻው የአንዲት ሴት ስም ሲሆን፣ ይህች ሴት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ግብፅ በተሰደደች ጊዜ ሕፃኑን ተቀብላ መሬት ላይ ስለጣለችው፣ በፈጸመችው በደል ምክንያት ወደ ዝንጀሮነት መለወጧን በተአምረ ማርያም ተጽፎ ይገኛል)፡፡ ከምንጮቻችን በተጨማሪ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ፌቨን በጄኔራል ቸርች ኮርስ "F" ያገኘች ሲሆን፣ ይህንን ማርክ የሰጧትን ሲሳይ የተባሉ መምህሯን ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ ድረስ በመሄድ መክሰሷ ታወቋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ መንፈሳዊ ኮሌጁ ባለው የውስጥ አስተዳደር ሥልጣን መሠረት ለአቡነ ፊሊጶስ ሕገወጥ መመሪያ ሳያጎበድድ ውሳኔውን እንዳጸና ለመረዳት ተችሏል፡፡ አቡነ ፊሊጶስ ቀደም ሲል በጥቅምቱ ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ ከአቡነ ሕዝቅኤል በተሠነዘረባቸው ሰፊ ትችት ጠቅላይ ቤተክህነቱን የጋለሞታ እና የቤተሰብ መሰብሰቢያ አደረጉት መባላቸው ሲታወስ ለፌቨን (ለ"ኮቲባ")ያደረጉት ሽፋንም ከዚህ የተለየ አይደለም ተብሏል፡፡ በመጨረሻም "ኮቲባ" ባላት የመጨረሻ ዕድል ተጠቅማ ኮርሱን እንደገና በመውሰድ ውጤቷን ወደ "C" ማስቀየሯ ታውቋል፡፡

"ኮቲባ" በሌሎች ክፍሎች ተመድበው ከሚማሩ ወንዶች ጎደኞቿ ጋር በማበር እና አድማዎችን በማስተባበር ኮሌጁን በአንድ እግሩ እንዳቆመችው እዚያው ያሉ ደቀመዛሙርት መስክረዋል፡፡ እርሷ በዚህ ብቻም ሳትወሰን፣ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ደጋፊ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ያሬድ ወደ ኮሌጁ የበላይ ጠባቂነት ከተሾሙበት ጊዜ አንስቶ ግቢው አልበቃት እንዳለ እና ለማኅበሩ ጠንካራ የስለላ ሥራ በመሥራት ላይ መሆኗ ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል የቦሌው ምድብ ችሎት በትላንትናው ዕለት (ታህሣሥ 10 ቀን 2004 ዓ.ም) ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ በችሎቱ ላይ የተመደቡት ሌላ ዳኛ መሆናቸውን በመረዳት ዘመድኩን በጠበቃው አማካይነት አዲስ አቤቱታ በማቅረብ ሊያምታታ ቢሞክርም ዳኛው ገስጸዋቸው፣ በእጃቸው ባለው መረጃ መሠረት የመከላከያ ምሥክሮቻቸውን እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ "ሞት ቢዘገይ የቀረ ይመስላል" እንዲሉ፣ እነ ዘመድኩንም የመከላከያ ምሥክሮቻቸውን ይዘው ባለማቅረባቸው ይቅርታ ጠይቀው በተለመደው የመለማመጥ ችሎታቸው በቀጣይ ቀጠሮ ማቅረብ እንዲችሉ እንዲፈቀድላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ዳኛውም የተጨማሪ ቀኑን ጥያቄ ፈቅደው የመከላከያ ምሥክሮቻቸውን መቼ ይዘው መቅረብ እንደሚችሉ ሲጠይቋቸው፣ ጠበቃው ፈጠን ብሎ፣ "ክቡር ፍርድ ቤቱ፣ ደምበኛዬ ከታኅሣሥ 24 እስከ ጥር 4/ 2004 ባለው ጊዜ ላሊበላ የመንፈሳዊ ጉዞ ፕሮግራም ስላለው፣ ከጥር 4 በኋላ ባሉት ቀናት ይቀጠርልን" ብሎ በድፍረት ጠየቀ፡፡ ዘመድኩን መከላከያ ምሥክሩን ያላቀረበው ሆን ብሎ መሆኑን በግልጽ የሚታወቅ ሲሆን፣ ላሊበላ የመንፈሳዊ ጉዞ ፕሮግራም አለብኝ የሚለውም ግፋ ቢል ካሴቱን ለመቸርቸር እና ዐውደ ምህረቱንም እንደ ግሸን ደብረ ከርቤ ዐውደ ምሕረት የወንድሞችንና የእህቶችን ሥጋ ለመቦጨቅ እንዲሁም የራሱን ስም ለመጠገን ነው በማለት ብዙዎች ይተቻሉ፡፡ የሆነው ሆኖ፣ ዐቃቤ ሕግ ስለቀጣይ ቀነ ቀጠሮ በበኩሉ በሰጠው አስተያየት፣ ይህን ያህል ጊዜ መስጠት አሳማኝ አለመሆኑን ማስረዳት በመቻሉ ለታኅሣሥ 23 ቀን 2004 ዓ.ም ከረፋዱ 4፡00 ላይ እንዲቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ዲያቆን ደስታ ጌታሁን በበኩሉ የራሱን ሁለት የመከላከያ ምሥክሮች ይዞ ያቀረበ ሲሆን፣ እነርሱም የአዲሱ ሚካኤል ስብከተ ወንጌል ክፍል አባል የሆኑት መምህር መኮንን ደስታ እና ዳንኤል ግርማ የተባሉ ናቸው፡፡ ሆኖም ዳንኤል ግርማ የት እንደሚሠራ ሲጠየቅ፣ እዚሁ አዲስ አበባ ነው፤ እዚሁ በማለት ትክክለኛ የሥራ ቦታውን መግለጽ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ሆኖም ዳንኤልን በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች እንደገለጹት፣ መጠኑ ለጊዜው ያልታወቀ ገንዘብ ሲያጭበረብር እጅ ከፍንጅ ተይዞ ከደቡብ አፍሪካ ቤተክርስቲያን አስተዳደር የተባረረ ነው ይሉታል፡፡ መልሱን ጥርት ባለ ቋንቋ እንዳይናገር ያደረገውም ይኸው ችግሩ ነው ተብሏል፡፡

አንደኛው ምሥክር መምህር መኮንን ደስታ በዐቃቤ ሕጉ በኩል "አንድ ግለሰብ ተነስቶ ያለ ሲኖዶሱ ዕውቅናና ውሳኔ ሌላውን ሰው፣ ተሃድሶ ወይም መናፍቅ በማለት፣ በአስተምህሮ ሊተቸው ይችላል ወይ"? ተበሎ ለቀረበለት መስቀለኛ ጥያቄ "አይችልም"!! በማለት በችሎቱ የታደሙትን ሁሉንም አካላት ያስገረመና መጋቤ ሀዲስ በጋሻውን የደገፈ መልስ አስመዝግቧል፡፡

ተከሳሽ ዲያቆን ደስታ ጌታሁን መጋቤ ሀዲስን የሚያጥላላ ጽሑፍ ለመጻፍ ምን እንዳነሳሳው ሲጠየቅ፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤልና ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ለአንድ የፕሬስ ሕትመት የሰጡት ቃለመጠይቅ ነው በማለት "አሳሳቱኝ" ወይም "ሕጋዊ ነኝ" የሚል ትርጉሙ በውል ያልለየ መልስ ሰጥቷል፡፡ ለማስረጃነትም የጽሑፉን ፎቶ ኮፒ ያቀረበ ሲሆን ለማንበብ አዳጋችና የተጨማደደ በመሆኑ ለቀጣዩ ቀጠሮ ትክክለኛውን ቅጅ በግልጽ ጽሑፍ ታይፕ አስደርጎ እንዲያቀርብ ታዟል፡፡

ዲያቆን ደስታ ጌታሁን በታኅሣሥ 4 ዕለቱ ችሎት ላይ አምስት ሺህ ብር በዋስትና እንዲያስይዝ መታዘዙን የገለጽንላችሁ ሲሆን የዋስትናው መጠን ወደ ሁለት ሺሀ አምስት መቶ እንዲቀነስለት ዳኛውን በግል ለማነጋገር ቢሞክርም የፍርድ ቤት ውሳኔ በመሆኑ በዕለቱ እሰከ ቀኑ 10፡00 ሰዓት ድረስ በሕግ ጥላ ሥር ለመቆየት ተገዷል፡፡ በመጨረሻም፣ "ማኅበሯ" አምስት ሺውን ከፍላ አስወጥታዋለች ተብሏል፡፡ ስለዕለቱ ችሎት ባቀረብንላችሁ ዘገባ ላይም፣ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ገንዘብ ቁጥጥር የማይደረግበት በመሆኑ ለእንደእነዚህ ዓይነቶቹ ሕገ ወጥ ወጪዎች መሸፈኛ ጭምር እንደሚውል መግለጻችን አይዘነጋም፡፡ dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com