Monday, December 5, 2011

ይከራከሩኛል!


                 ይከራከሩኛል
ይከራከሩኛል፣ እየተጋገዙ
በከንቱ ላይረቱኝ፣ አምላክን ሳይዙ።
እንዳገሩ ልማድ- ለተማረ ዳኛ፣
ቅጣት ይገዋል-ይህ ደፋር አፈኛ፣
ብሎ ፈረደብኝ- የወንጌል ምቀኛ።
ክርስቲያን የሆነ-ሲኖር በዓለም፣
መመርመር ነው እንጂ- ክፉና መልካም።
እውነት እስኪገለጽ አጥብቆ መድከም፣
እንዲሁ ቢያከፉት- የወንድምን ስም፣
እጅጉን ነውር ነው-ጌታ አይወደውም።
ማርያምን ጻድቃንን-አይወድም ያሉት፣
በምቀኝነት ነው- ስሜን ለማክፋት።
በክስ ቢጠይቁኝ- ስለሃይማኖት፣


ያለወልደ እግዚአብሔር-የዓለም ሕይወት፣
ለሰው የተሰጠው-የሚድንበት፣
ለነፍስ የለም ብል ነው-ሌላ መድኃኒት፣
ተጽፎ ያለውን -ብናገር እውነት፣
ነቢያት ተንብየው-ጽፈው በኦሪት፣
ሐዋርያት በግዝት- ወንጌል ያጸኑት፣(ገላ1፣8)
ላንጨምር ላንቀንስ- ይዘነው በእምነት፣
መኖር ይበቃናል- አልኩኝ በእውነት፣
ግዝቱን ጠብቄ፣ ፈርቼ መቅሰፍት፣
እነሱ ግን አሉኝ-የማርያም ጠላት።
ወልደ እግዚአብሔር ነው- የኃጢአት ሥርየት፣
መንገዱ መሄጃው-ለሰማይ መንግሥት፣
የአዳራሹ ጌታ-ሰማያዊ ርስት፣
ሌላ መንገድ የለም-ለሰው ልጅ መድኃኒት፣
ብዬ በተናገርኩ- ማርያምን ትተሃል፣
ቤዛዊት መሆኗን፣ እነሆ ክደሃል፣
ብለው ወረወሩኝ፣ ከርቸሌ ወኅኒ ቤት።
በመጻፍ ያለውን፣ እኔ መመስከሬ፣
ስህተት የለብኝም- እውነት መናገሬ፣
ቤዛችን ክርስቶስ- ሌላ ማንም የለም፣
እኔ ከእርሱ በቀር- በሌላ አላምንም፣
ክርስቲያኖች ነን -የምትሉ ሁሉ፣
ይህ ነው ሃይማኖቴ- ብትወዱም ብትጠሉ።
ምንጭ፤ ጮራ መጽሔት- አለቃ ታዬ ገ/ማርያም ከርቸሌ ተወርውረው ሳሉ ከጻፉት ግጥም ተሻሽሎ የቀረበ