Friday, December 9, 2011

የጳጳሳት ጆሮ የተነፈገው የአዲስ አበባ ካህናት ጩኸት!


የጳጳሳት ጆሮ የተነፈገው የካህናት ጩኸት(to read in PDF click here)

ከደጀብርሃን፣

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የገንዘብና የንብረት ዘረፋ ሀገር ያወቀው፣ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው። ኰሌጅ፣ ሙአለ ህጻናት፣ አውቶቡስ፣ ታክሲ፣ ሆቴል፣የተለያየ ደረጃ ያላቸው ህንጻዎች፣ ሱቆች፣ የሚከራዩ አፓርትማዎች፣ የቤትና የንግድ መኪናዎች ያላቸውን አስተዳዳሪዎች፣ ፀሐፊዎች፣ ሂሳብ ሹሞች፣ የቁጥጥር ሠራተኞች፣ገንዘብ ያዢዎችና ንብረት ክፍሎችን ማየት እንግዳ ነገር አይደለም። ይህንን ሁሉ ሀብት ሲያጋብሱ የቀድሞ ደመወዛቸው ቢበዛ የአስተዳዳሪው ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ብር የሚበልጥ አልነበረም። የሌሎቹ ደግሞ ሺህ ብር ባልገባ ደመወዝ ነበር ይህንን ሁሉ ሃብት ማፍራት የቻሉት። የዘረፋ ቁንጮ እንደሆነ የሚነገርለትና አውቶቡስ፣ ት/ቤት፣ ትልቅ ህንጻ እንዳለው የሚነገርለት (ሊቀ ሊቃውንት)አባ እዝራ የሚባለው የሽማግሌ ማፊያ ለዚህ የሚጠቀስ አብነት ነው። ሊቀሊቃውንት ብላ ቤተክርስቲያን የምትጠራው ጡቷን ምጎ፣ ምጎ አጥንቷን ስላወጣው እውቀቱ ይሆን? ይህንን እንግዲህ እውቅና የሰጠው ሲኖዶስ የሚባለው የአባቶቹ ማኅበር ያውቃል። ሌሎቹንም የዘረፋ ሊቀ ሊቃውንት በስምና በአድራሻ ማንሳት ይቻላል። የሚያሳዝነው ግን ንቡረ እድ አባ ገ/ማርያም ገ/ሥላሴን ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነት ለማስነሳት የዘመቻው ፊት አውራሪዎች እነዚህ የቤተክርስቲያንን ሀብት እያገላበጡ የሚዘርፉ የቀን ጅቦች መሆናቸው ነው። ከማሳዘን አልፎ የሚገርመው ንቡረ እድ አባ ገ/ማርያም የቀን ጅቦቹን አፍ የዘጉት በየትኛውም የቤተክርስቲያን ገንዘብና የንብረት ቆጠራ ላይ አስተዳዳሪው፣ ፀሐፊውና ሂሳብ ሹሙ እጃቸውን ሳያስገቡ ቁጭ ብለው እንዲመለከቱና አገልጋይ ካህናቱ ብቻ በአንድነት ቆጥረው የተገኘውን ገንዘብ በሞዴል 64፣ የገባውን ንብረት በሞዴል 19 ገቢ አድርገው በግልጽ መጠበቅና ማስጠበቅ መቻላቸውን ሲኖዶስ የሚባለው ስብስብ እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው ለዘራፊዎቹ ጩኸት ምላሽ በመስጠት ባለፈው ጉባዔ ሥራ አስኪያጁን ከቦታው እንዲነሱ አድርጓል።
ከ5 ሚሊዮን ያላለፈውን ለጳጳሳት ደመወዝና ሥራ ማስኬጃ ፈሰስ የሚደረገውን የጠቅላይ ቤተክህነት ገቢ ወደ 27 ሚሊዮን ከፍ ስላደረጉላቸው ሽልማት መስጠቱ ይቅርና ይህንን አጠናክረህ ቀጥል ማለት አቅቷቸው እንደጥፋተኛ ሰው የልማቱን አባት ለቦታው አትሆንም ብሎ ማንሳት ሲኖዶስ በእውነት በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ነው? የሚያስብል ነገር ነው። የአባ ገ/ማርያምን መነሳት የሚሹ ወገኖች(ፓትርያርኩን ጨምሮ) የዝውውር ጥያቄ ውድቅ ሊያስደርግ የሚችል ተግባር ለማየት ሲኖዶስ የሚባለው ክፍል በመንፈሳዊነት ደረጃ ይቅርና በመስማትና በማሽተት እንዴት ሳይረዳው ቀረ? ይልቁንም ጊዜውን በአባ ሠረቀ ጉዳይ ላይ የማኅበረ ቅዱሳንን ውክልና በማስፈጸም መጠመዱን ስራዬ ብሎ ዋለ እንጂ!! እውነትም የመንፈስ ቅዱስ ጉባዔ!!!!!!!
ከታች የቀረበው በሰዓታቱ፣በማኅሌቱ፣በቅዳሴው፣በፍትሃቱ ሌሊትና ቀን እየጮሁ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩ ካህናት ጩኸትና ትዳር አንፈልግም፣ እኛ መንኩሰናል፣ እያሉ ግን ብዙውን ጊዜያቸውን ሽቶ የተለወሰ ቀሚሳቸውን አስረዝመው፣ ወለተማርያም፣ወልደ ማርያም እያሉ የመበለት ቤቶችን የሚበዘብዙ አስተዳዳሪዎች መካከል የተደረገው የአቤቱታ ክርክርና ከላይ እስከታች ረዳት የሌለውን ካህን ድምጽ የሚያሳይ ነውና መልካም ንባብ ይሁንልዎ!! ኅሊናዎትም ፍርዱን ይስጥ!!ከታች ያለውን ተጭነው ያንብቡ!(http://dejebirhan.blogspot.com)



                                                                       
                                                                                     ጥቅምት5/2004 ዓ/ም


ለብፁዓን አበው ሊቃነጳጳሳት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂዎች፣

አዲስ አበባ፣

«ሤመክሙ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳተ ከመ ትርዓዩ ቤተክርስቲያኑ ለክርስቶስ እንተ አጥረያ በደሙ»

በዚህ መሪ ጥቅስ አቤቱታችንን መጀመር የፈለግንበት ምክንያት አለን። እንደሚታወቀው በ2003 ዓ/ም በጥቅምት ወር ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው ዓመታዊ ስብሰባ ከአጀንዳዎቹ አንዱ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተንሰራፋውን ሙስናና ብልሹ አሰራር፣ እንዲሁም እጅግ አስከፊ የሆነውን የአስተዳደር በደል ተገንዝቦ ብፁዓን አባቶችም የመንፈስ ቅዱስ አደራና ኃላፊነት ስላለባችሁ በስብሰባው ወቅት በጽሞናና በጥልቀት ተወያይታችሁ፣ አውጥታችሁ፣ አውርዳችሁ ይሆናል ያላችሁትን አባት እንደሾማችሁ ይታወቃል።
በእውነትም የደከማችሁት ድካምና ጥረት ከንቱ ሆኖ አልቀረም፣በሾማችሁልን አባት በክቡር ንቡረእድ አባ


ገ/ማርያም ገ/ሥላሴ አማካይነት ሀ/ስብከቱ እጅግ የሚደነቅ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።ባጭር ጊዜ የመጣው ለውጥ በዓይን ሊታይ የሚችልና በእጅ ሊጨበጥ የሚችል ሥራ መሠራቱን የሚመሰከር ነው።ሥራው ራሱ ይህንን ያስረዳል።

ከዚህ አንጻር በየገዳማቱና አድባራቱ የምንገኝ ሠራተኞች ያየነውንና የተረዳነውን እውነት ሳንመሰክር ብናልፍ የኅሊናና የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን አንድንም የሚል እምነት አለን። ምክንያቱም የቤተክርስቲያኒቱ ሀብትና ንብረት ሲዘረፍ የመኖሩን ጉዳይ እንተወውና ከ2003 ዓ/ም በፊት በየአድባራቱና ገዳማቱ ያሉት አለቆችና ጸሐፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የመምሪያ ኃላፊዎች ተጨምረውበት ሲደርስብን የነበረውን ግፍና መከራ እጅግ አስከፊና አሳዛን ድርጊቶችን ስናስታውስ ያ ሁሉ ችግር አልፎ የአሁኑ ሥራ አስኪያጅ ከተሾሙ ጊዜ ጀምሮ ያለው ጊዜ መልካም አስተዳደር እየሰፈነ ያለበት፣ ፍትህ ያገኘንበት፣ የነጻነትና የእኩልነት ዘመን ነው ብንል ማጋነን አይሆንብንም።

የግፉ ቀንበር ተሰብሮ ነጻነት ያገኘነው በብፁዓን አባቶቻችን አማካይነት ነውና እግዚአብሔር አምላካችንን እያመሰገንን፣ ለአባቶቻችንም ረጅም እድሜና ጤና ዘወትር እንመናለን። በመቀጠልም በ2003 ዓ/ም አንዳንድ ጥቅማቸው የቀረባቸው አልጠግብ ባዮች ለምን ተነቃብን፣ የሙስና በሩ ለምን ተዘጋብን? በሚል የቀደመውን ብልሹ አሠራር ለመመለስና ቤተክርስቲያኒቱን ለማራቆት የተዘረጋውን መልካም አስተዳደር አጥብቀው ሲቃወሙትና ሲያወግዙት ታይተዋል። ይሁን እንጂ በአባቶች አኩሪና ታሪካዊ ውሳኔ እንቅስቃሴያቸው ተቀልብሷል። እኛም በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ስር የምንገኝ ካህናትና ሠራተኞች በሙሉ የአለቃና የጸሐፊ ዛቻና ማስፈራሪያ ሳያስደነግጠን ቀፎው እንደተነካ ንብ በመሆን ከአባቶቻችን ጎን ተሰልፈን ሐምሌ 23/2003 ዓ/ም በተደረገው ስብሰባ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ መርጦ የሰጠን አባት ታማኝና ቆራጥ፣ ከሙስና የጸዱ፣ በገንዘብ የማይደለሉ፣ በዘመድ አዝማድ ሥራ የማይታሙ፣ በሙሰኞችና በኪራይ ሰብሳቢዎች አድማና ሴራ አንነጠቅም በማለት የድረሱልን ጩኸት እስካሁን በሥራ ላይ እንዲቆዩ በመደረጉ ተደስተናል። አሁንም በ2004 ዓ/ም የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ ሲጨነቁበትና ሲያድሙበት የቆዩትን ሥራ እስኪያጁን ከቦታቸው ለማስስነሳት የተጀመረው የዘራፊዎች ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ይህንን የጥፋት ዘመቻ በመቃወም ሃሳባችንን እኛ ካህናትና ሠራተኞች ከታች አቅርበናል።

የተከበሩት ሥራ አስኪያጅ ካከናወኗቸው መልካም ተግባራት መካከል በአጭሩ በመግለጽ ያለንን ጥብቅ አቋም ለማስረዳት እንሞክራለን።

1/የግል ጥቅም መስመሮችን በመበጣጠስ የወሰዱትን አርአያነት ያለው ተግባር በመቃወም ጥቅማችን ለምን ቀረ ባዮች ሥራቸውን በማንኳሰስና ስም በማጥፋት ተግባር ላይ መሰማራታቸውን እንቃወማለን።

2/ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ይሰበሰብ የነበረው 20% ገቢ በአድባራት አለቆችና ፀሐፊዎች እየተበላና እየተዘረፈ ሳይሰበሰብ የቆየውን ድርጊት በማስቆም እስካሁን በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ታሪክ ተሰምቶ የማይታወቀውን 58,030,844.00/ሃምሳ ስምንት ሚሊዮን ሰላሳ ሺህ ስምንት መቶ አርባ አራት/ብር እንዲሰበሰብ አድርገዋል። ይህንን ሥራ ለማጨናገፍና ወደኪሳቸው ለማስገባት የሚሯሯጡትን ሰዎች ክስና ውንጀላ እንቃወማለን።

3/በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ታሪክ (በአቡነ ሳሙኤል) ዘመን እንኳን 5 ሚሊዮን ብር ለጠቅላይ ቤተክህነት ፈሰስ ተደርጎ እጅግ ሲደነቅ ከነበረው በተለየና ወደፊትም ዘረፋ ካልቆመ በስተቀር መቼም ቢሆን ሊደረግ የማይችለውን 27,543,587.00/ሃያ ሰባት ሚሊዮን አምስት መቶ አርባ ሦስት ሺህ/ብር ገቢ ማድረግ ችለዋል። ስለዚህ እኒህ አባት ሊመሰገኑና ሊሸለሙ ሲገባ ከቦታቸው እንዲነሱ የሚደረገውን አድማና ዘመቻ አጥብቀን እንቃወማለን።

4/በሀ/ስብከቱ ተንሰራፍቶ የቆየውን በብሔር፣ በጎሳ፣ በወንዝ፣ በጎጥና በቡድን የሚደረጉ ቅጥሮች፣ ዝውውሮች፣ የደረጃ እድገትና ደመወዝ ጭማሪዎች በማስቀረትና በግፍ የማባረር፣ የመቅጣት፣ ከደረጃ ዝቅ፤ ከሥራ የማገድ እርምጃዎችን ከምንጩ ያደረቁ ትልቅ አባት በመሆናቸው ባሉበት ቆይተው የበለጠ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ተጋድሎአቸውን እንዲፈጽሙ ማድረግ ይገባል እንላለን። ይህንን በመቃወም ሥራ እስኪያጁን ለማስነሳት በገንዘብና በአድማ የተያዘውን የህገወጦች ዘመቻ አጥብቀን እንቃወማለን።

5/ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት በ10 የአዲስ አበባ ክ/ከተሞች ዓይነት እንዲከፋፈል የተያዘው ዘመቻ ለቁጥጥር እንዳይመች ለማድረግ የታለመ ስለሆነ አጥብቀን እንቃወማለን።

6/በሰዓሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን አንድን ጸሐፊ ለማስደሰት ተብሎ አስራ ሦስት ሠራተኞችን ከምስራቅ ወደምእራብ፣ ከሰሜን ወደ ደቡብ እንዲዘዋወሩ በማድረግ ከመኖሪያ ሰፈሮቻቸው በማፈናቀል በትራንስፖርት ወጪ እንዲጉላሉ የተደረገው የብቀላ ሥራ ዳኝነት እንዲታይ አጥብቀን እንጠይቃለን።


ስለሆነም ንቡረእድ አባ ገ/ማርያም የሙሰኞችና የጥቅመኞችን አፍ በመዝጋታቸው ከታች በአገልግሎት ላይ ሌሊትና ቀን ደፋ ብለን ገቢውን በሥራችን የምናስገኘው ካህናት ስንደሰት፣ ሥልጣኑ ላይ ቁጭ ብለው የሚገኘውን የመብያ ቀዳዳ እየፈጠሩ የድካማችንን ፍሬ የሚቀራመቱት እጅግ ተበሳጭተዋል። የሃይማኖታችን መሰረት «ሊሰራ የማይወድ አይብላ» እንዲሁም «አትስረቅ» የሚለውን ሕግ አርአያ ሆነው ሰርተው በማሰራት የሚገኙትን አባት ከቦታቸው በማስነሳት ወደተለመደ ስራቸው ለመመለስ የሚፈልጉትን እንድታስቆሙልንና ሥራ እስኪያጁ የጀመሩትን መንፈሳዊ ተጋድሎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ እንድታደርጉልን በቤተክርስቲያናችን ስም እንጠይቃችኋለን።
የአባቶቻችን ቡራኬ ይድረሰን

የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት የአብነት መምህራን፣ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች
አዲስ አበባ፣