ከዶ/ር አምሳሉ ተፈራ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፊሎሎጂ ዲፓርትመንት
ረዳት ፕሮፊሰር
ለሁሉ ፈጣሪ ለእግዚአብሔር ራስን መቀደስና ከኃጢአት መለየት ለሰው ሁሉ የቀረበ ጥሪ ነው። ይህን ዘንግተው የነበሩ ሕዝበ እስራኤል ወደ አምላካቸው እንዲመለሱና ሁለንተናቸውን ለእርሱ እንዲሰጡ የተላከላቸው መልእክት ነው ርእሳችን እኛንም ይመለከታልና እንደሚከተለው በዝርዝር እንየው።የሚታየውንም የማይታየውንም የፈጠረ፣ በባሕርም በየብስም ያሉትን ያስገኘ፣ ሰውን ለክብሩ ወራሽነትና ለስሙ ቀዳሽነት የወሰነ፣ ዓለምን ሲፈጥር አማካሪ ያልፈለገ፣ ፍጡሩን በመመገብና በመውደድ ወደር የሌለው፣ ለሰው ልጆች ራሱን አሳልፎ የሰጠ ነው ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔር። ይህን ጌታ በምንም ልንለውጠውና ልንተካው አንችልም። አምላክ ነውና ተወዳዳሪ የለውም (ኢሳ. ፵፣ ፲፪ - ፲፬)
የርእሳችን መነሻ የሆነው «እጃችሁን ለእግዚአብሔር ስጡ» የሚለው ትምህርት የተሰጠው፣ ሃያ ዘጠኝ ዓመታት በእስራኤል ላይ በነገሠው ንጉሥ ሕዝቅያስ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የእግዚአብሔርን ፋሲካ ለማድረግ የሚደረግ ቅድመ ዝግጅትን ይመለከታል። እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ ስለሆነ፤ ወደ እርሱ መቅረብና ማገልገል የሚቻለው በንጽሕና ሆኖ ነው፤ አገልግሎትንም የሚቀበለው ያለቸልታ በትጋት ሲሆን ነው። «ልጆቼ ሆይ በፊቱ ትቆሙና ታገለግሉት ዘንድ፥ ታጥኑለትም ዘንድ እግዚአብሔር መርጦአችኋልና ቸል አትበሉ፤ ብሎ ያዘዘን ለዚህ ነው (፪ዜና. ፳፱፣፲፩)።
«ንጉሡ ሕዝቅያስ ለእግዚአብሔር ፋሲካ እንዲደረግ ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ለዐሥራ ሁለቱም ነገደ እስራኤል መልእክት ላከ። ነገር ግን ካህናቱ ገና በሚገባ ስላልተቀደሱ፣ ሕዝቡም በኢየሩሳሌም ተጠቃለው ስላልተሰበሰቡ፤ ፋሲካው በደንብ ሲዘጋጁ በቀጣዩ ወር እንዲከበር ተወሰነ። ለቀጣዩ ወር ግን ሁሉም ከያለበት ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እንዲሰባሰብ እንዲህ የሚል ዐዋጅ ተነገረ፣ «የእስራኤል ልጆች ሆይ ... እግዚአብሔርን እንደ በደሉ እንደ አባቶቻችሁና እንደ ወንድሞቻችሁ አትሁኑ። አባቶቻችሁም እንደ ነበሩ አንገተ ደንዳና አትሁኑ፤ እጃችሁንም ለእግዚአብሔር ስጡ፤ ለዘላለም ወደ ተቀደሰው ወደ መቅደሱም ግቡ፤ ጽኑ ቁጣው ከእናንተ እንዲመለስ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ። (፪ዜና ፴፣፯-፰)።