(በትናንትናው
ዕለት ቅዱስ ሲኖዶሱ በሰበር ያስተናገደው አጀንዳ በዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ የተጻፈ ርዕሰ አንቀጽን የተመለከተ ነው። ርዕሰ አንቀጹ ለምን አወያየ? የሚለው በብዙዎች ዘንድ መወያያ ስለሆነ ርዕስ አንቀጹን እንዳለ አቅርበነዋል። መልካም ንባብ ይሁንላችሁ)
ምንጭ፤ዐውደ ምሕረት
« የዜና ቤተክርስቲያንን» ከፊል ዘገባ ለመመልከት ( እዚህ ይጫኑ)
« የዜና ቤተክርስቲያንን» ከፊል ዘገባ ለመመልከት ( እዚህ ይጫኑ)
ቤተ
ክርስቲያን የጳጳሳት፣ የካህናትና የምእመናን ድምር ውጤት ናት፤ ጳጳሳት፣ ካህናትና ምእመናን ባልን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ማለታችን ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ብለን በጥቅሉ በምንናገርበትም ጊዜ ጳጳሳት፣ ካህናትና ምእመናን ማለታችን ነው፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ሁሉ አካላት የተካተቱባት ቤተ ክርስቲያን አንዲት ተቋም ስለሆነችም ማኅበር ተብላ ትጠራለች፤ ራሷ ማኅበር ስለሆነችም ከዝክርና ከሰንበቴ ማኅበር በስተቀር በተቋም የተደራጀ ሌላ ማኅበር አያስፈልጋትም፡፡
ሆኖም
ቤተ ክርስቲያናችን ቃለ ዓዋዲ የተሰኘ የመተዳደሪ ደንብ አውጥታ በሰበካ ጉባኤ ከመደራጀቷ በፊት የእርሷ ወኪልና ደጋፊ በመሆን ድምፅ የሚያሰሙላት አንድ አንድ የወጣት መንፈሳውያን ማኅበራት እንደነበሩ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በሰበካ ጉባኤ ከተደራጀች ወዲህ ግን ሕገ ልቡና እስከ ሕገ ኦሪት፤ ሕገ ኦሪትም እስከ ሕገ ወንጌል መዳረሻ ሆነው ወይም አገልግሎት ሰጥተው እንዳለፉ ሁሉ እነሱም አልፈዋል፡፡ ይህም ማለት በቃለ ዓዋዲው የመተዳደሪያ ደንብ በየድርሻቸው ተካትተዋል ማለት እንጅ ጨርሰው ወድመዋል ማለት አይደለም፡፡
ቤተ
ክርስቲያን የምትመራበትና የምትተዳደርበት ሕገ ቤተ ክርስቲያን ወይም ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ሕገ ቤተ ክርስቲያን በዘመነ ሐዋርያት በቅዱሳን ሐዋርያት የተደነገገ ሕግ ሲሆን በመላው ዓለም የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሚመሩትና የሚተዳደሩት በዚሁ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት አካል እንደመሆኗ መጠን የምትመራውና የምትተዳደረው ወይም የምትዳኘው ከፍ ሲል በሕገ ቤተ ክርስቲያን፤ ዝቅ ሲል በቃለ ዓዋዲ የመተዳደሪያ ደንብ ነው፡፡