Wednesday, October 22, 2014

ማኅበረ ቅዱሳንን ክርስቲያናዊ ብራዘር ሁድ የሚያሰኙ ማስረጃዎችና መመሳሰሎች!

ሙስሊም ብራዘር ሁድ ወይም የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር የተባለው ድርጅት በ1928 ዓ/ም በግብጽ ተመሠረተ። ከሰማንያ ዐመታት በኋላ በጄኔራል አልሲሲ መንግሥት በአሸባሪነት ተፈርጆ ድምጥማጡ እስኪጠፋ ድረስ በ70 ሀገሮች ውስጥ ቅርንጫፎቹን ከፍቶ በዘመናዊና ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች፤ በገበያ ማዕከላት፤ በንግድ ሱቆች፤ በማከፋፈያ ድርጅቶች፤ በሚዲያ ተቋማት ወዘተ የሀብት ማግበስበሻ መንገዶች እየተሳተፈ ክንዱን በማፈርጠም ለእንቅስቃሴው የሚጠቅመውን የገንዘብ ምንጭ ሲፈጥር ቆይቷል። ይህ የግብጹ ሙስሊም ብራዘር ሁድ በዐረብ ሀገራት ውስጥ ተመሳሳይ የሙስሊም ወንድማማች ማኅበራትን በማደራጀትና በማሰልጠን መንግሥታቱን ሲያስጨንቅ የቆየ ሲሆን አሁንም እያስጨነቀ ይገኛል።

የሙስሊም ብራዘር ሁድ ለተባለው ሃይማኖታዊ-ፖለቲካዊ ድርጅት ዋነኛ ተቀባይነት ማግኘት ዋናው ምክንያት የሆነው በእስላሙ ሕብረተሰብ ውስጥ ቶሎ ሰርጾ እንዲገባ የሚያካሂደው ሃይማኖታዊ አስተምህሮቱና  ለዚህ እምነት መክፈል የሚገባውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል ከአላህ ዘንድ የሚከፈለውን ምንዳ ለመቀበል ቶሎ መሽቀዳደም ተገቢ መሆኑን አበክሮ በመስበኩ የተነሳ ነው።

1/ የሙስሊም ብራዘር ሁድ መዋቅራዊ እንቅስቃሴ 

 ሙስሊም ብራዘር ሁድ መዋቅሩ በሀገሪቱ የመንግሥት ሲቪላዊ መዋቅር ደረጃ የተዘረጋ ነው። ይህም ከማዕከላዊ ቢሮው ተነስቶ አባል በሆኑ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ በሰንሰለት የተያያዘ ነው። ቤተሰባዊውን የአባልነት ማኅበር «ኡስራ» ይሉታል። አንድ «ኡስራ» አምስት አባላት ሲኖሩት ከአምስት በላይ ከሆነ በሁለተኛ የኡስራ ስያሜ ደረጃ ይዋቀራል። በቤተሰቡ ያሉትን ኡስራዎች የሚመራ ደግሞ የቤተሰቡ አባል የሆነ በእስልምና ሃይማኖቱ የበሰለና የብራዘር ሁድ አስተምህሮት በደንብ የገባውን ሰው የቤተሰቡ ጉባዔ ይመርጠውና «ናቂብ» ተብሎ ይሰየማል። ይህ «ናቂብ» የተባለው ሰው የቤተሰቡ አባላት በእስልምናው ደንብ ዘወትር ስለመንቀሳቀሱ ይቆጣጠረዋል፤ ያስተምረዋል፤ ይነግረዋል። ያልተመለሰውን በማኅበረሰቡ ደረጃ ለተቀመጠውና ከፍ ላለው ሃይማኖታዊ መሪ ያቀርበዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ስለእስልምናው የሚደረግ እርምጃ በመሆኑ በደስታ ከሚቀበል በስተቀር ማንም በተቃውሞ አያንገራግርም፤ ሊያንገራግርም አይችልም። ምክንያቱም ጸረ እስልምና እንደሆኑ ራሳቸውን አስገዝተዋልና። በዚህ ዓይነት አደረጃጀት የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር ከላይ ወደታችና ከታች ወደላይ የተሳሰረ መዋቅር አለው።

2/   የገንዘብ ምንጮቹን ማሳደግ

ገንዘብ የዚህ ዓለም እንቅስቃሴ የደም ሥር ነው። አባላት ለመመልመል፤ እንቅስቃሴውን ለማስፋፋት፤ የሽብር ተግባሩን ለመፈጸም፤ ለመደለል፤ ለመሰለል፤ ሃይማኖታዊ ዶክትሪኑን ለማስተማር  እጅግ ጠቃሚ ነገር መሆኑን ጠንቅቆ የተረዳው ብራዘር ሁድ የገንዘብ አቅሙን ለሀገር ውስጥና ድንበር ዘለል ተግባሩ ያውለው ዘንድ ተግቶ ይሰራል።

የእስላም ወንድማማቾች ማኅበር ሁለት ዓይነት የገንዘብ ምንጮች አሉት። አንዱ በውጪ ሀገራት ካሉ አባላቱ በመዋጮ የሚሰበሰብ እንዲሁም ብዙ ሃብት ካላቸው የድርጅቱ ደጋፊ ሚሊየነሮች  የሚደረግለት የገንዘብ ፈሰስና በእስላማዊ መንግሥታት ስር ከተሸሸጉ ባለስልጣናት የሚዋጣለት ገንዘብ ነው።  ሁለተኛው ደግሞ በተራድዖ ስም ከውጭ የሚያሰባስበውን ገንዘብ ወደልማት ካዝና በመቀየር በአካባቢ ልማት፤ በትምህርት ቤቶችና መድራሳ ማቋቋም፤ ሥራ አጥ ህብረተሰብን በማደራጀት፤ የራስ አገዝ እንቅስቃሴን በመመሥረት የሚሳተፍ ሲሆን ለዚህም ሀገር በቀል የእርዳታ ስልት በመቀየስ መዋጮውን ቅርጹን ለውጦ ያግበሰብሳል። ይህም፤

ሀ/ ከአባልነት መዋጮ
ለ/ ከንግድ ድርጅቶቹና ከሚዲያ ተቋማቱ የሚገኝ ገቢ ነው።


ይህንን ገንዘብ በተለያየ የገንዘብ ማስቀመጫ ስልቶችና በብዙ የሂሳብ አካውንቶች ቋት ውስጥ በተለያየ ስም በማስቀመጥ ለሚፈልገው ዓላማ በፈለገበት ሰዓት ማንም ሳያውቅበት ያውለው ነበር። በተለይም የእስልምና ባንኮች ተመራጭ መንገዶቹ ነበሩ።

3/ በመንግስታዊ ተቋማት ውስጥ ሰርጎ መግባት

ብራዘር ሁድ አባላቱን ሲመለምል ነጻና ገለልተኛ የሆኑትን ብቻ አይደለም። ከሚኒስትሮች እስከፍርድ ቤቶች፤ ከመከላከያ እስከ ፖሊስ መምሪያዎች፤ ከድርጅት ሥራ አስኪያጆች እስከ አስተዳደር ኃላፊዎች ድረስ በአባልነት መልምሎ፤ አሰልጥኖና ሃይማኖታዊ ትጥቅ አስታጥቆ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነበር። እነዚህ የመንግሥታዊ አካላት ክፍሎች ድርጅታቸው ለሚነሳበት ተቃውሞና ኅልውናውን ፈታኝ ለሆኑ ችግሮች የግብዓት ምንጭ ሆነው ያገለግላሉ። አስፈላጊ በሆነ የመረጃ፤ የፋይናንስና የአፈና ሥራው በትጋት ይሰራሉ።
ይህ ድርጅት እንደሃይማኖታዊ ተቋም አራማጅነት ተነስቶ ወደፖለቲካዊ ሥልጣን መቆናጠጥ እርምጃው ለማደግ መሠረት አድርጎ የሚነሳው የእስልምና ሃይማኖትን ነው። ይህም ብራዘር ሁድን መቃወም እስልምናን እንደመቃወም እንዲቆጠር በሕብረተሰቡ ዘንድ የኅልውናውን ስዕል በማስቀመጥ እንዳይነካ ወይም እንዳይጠፋ ረድቶታል። የእስልምናውን አስተምህሮ መነሻ በማድረጉ የማይነቃነቅ ፖለቲካዊ ግብ ለማስረጽ ያገዘው ሲሆን የዚህም መገለጫው በአልሲሲ መንግሥት ላይ በአንድ ጊዜ እስከ 33 ሚሊዮን ተቃዋሚ ሰልፈኞችን በመላ ሀገሪቱ ማንቀሳቀስ የሚችል ድርጅት አድርጎታል።
 ይሁን እንጂ የጀነራል አልሲሲ መንግሥት እርምጃ ስልታዊ በመሆኑ በአንድ ቀን ብቻ ከሁለት ሺህ በላይ ከፍተኛና ዝቅተኛ አመራሩንና የሃይማኖታዊ ተፍሲር መምህራኖቹን ለቃቅሞ ወደማጎሪያ ካምፕ በመክተቱ ድርጅቱ በ85 ዓመት እድሜው አይቶት የማያውቀውን ውድቀት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያስተናግድ አድርጎታል። በአልሲሲ መንግሥት የተተገበረው «ወፎቹ እንዲበተኑ ቅርንጫፉን መቁረጥ» የሚለው አባባል ብቻ ሳይሆን ግንዱን መንቀል በመሆኑ የብራዘር ሁድ ዋና መሪ መሐመድ ሙርሲን ጨምሮ ከፍተኛውን የሹራ ካውንስል ሳይቀር ከስር ገርስሶታል። በሺዎች የሚቆጠሩ አባላቱም የሞትና የእስራት ፍርድ ተከናንበዋል። አልሲሲ በቲቪ ቀርበው "ብራዘር ሁድን ከስረ መሠረቱ ነቅለን ካላጠፋን ሰላም የለንም" በማለት ድራሹን አጥተውታል። ዛሬም ድረስ የተቃውሞ ሰልፎች ያሉ ቢሆንም በሃይማኖት ካባ ስር በተሸፈነው ድርጅት በኩል የአእምሮ አጠባ ተደርጎ የተታለለው ሕብረተሰብ እንጂ ብራዘር ሁድ እንደተቋም በግብጽ ታሪክ ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሟል። ያ ማለት ግን ብራዘር ሁድን የሚደግፍ፤ የሚጠባበቅና እንዲያንሰራራ የሚፈልግ የለም ማለት አይደለም።

4/ማኅበረ ቅዱሳን እንደክርስቲያን ብራዘር ሁድ ስንል ምን ማለታችን ነው?

1/ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ከመንግሥትም፤ ከቤተ ክህነትም ቁጥጥር ነጻ መሆኑ
2/ የራሱን አባላት የሚመለምልና የሚያደራጅ መሆኑ
3/ የራሱ የሆነ የገቢ ምንጭ ያለውና የንግድ ተቋማትን የሚያንቀሳቅስ መሆኑ
4/ ከአባላቱ ልዩ ልዩ መዋጮዎችና የስጦታ ገቢዎችን በመሰብሰብ በልማት ውስጥ እየተንቀሳቀሰ እንዳለ የማሳየት ብልሃት ያለው መሆኑ
5/ በመንግሥት ተቋማትና መሥሪያ ቤቶች፤ ፍርድ ቤቶች፤ ፖሊስ መምሪያዎች፤ በኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ስውር መዋቅር ያለው መሆኑ
6/ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላዕላይ መዋቅርና እስከ አጥቢያ ድረስ በተዘረጋው አስተዳደር የራሱ አደረጃጀት የዘረጋ መሆኑ
7/ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ውስጥ የራሱን ጳጳሳት በመመልመል ማስሾም የቻለ መሆኑ
9/ ከሀገር ውጭ ዓለም አቀፍ ቢሮዎችን ከፍቶ የሚንቀሳቀስና አባላት ያሉት መሆኑ
10/ ከዓለም አቀፍ የገቢ ፈጠራው ውስጥ በልማት ሰበብ የሚያጋብስ መሆኑ
11/ የመረጃ፡ የስለላና የትንተና መዋቅር ያለው መሆኑ
12/ የቤተ ክርስቲያኒቱን አደረጃጀቶች ለራሱ ዓላማ የመጠቀም አቅም ያለው መሆኑ
( ሰንበት ት/ቤቶችን፤ የጥምቀት ተመላሽና የጽዋ ማኅበራትን)
14/ የግለሰቦችን ስም በማጥፋት ወይም ራሳቸውን በማጥፋት፡በማባረር፡በመደብደብ ወይም ግለታሪካቸውን ለራሱ ዓላማ ጠምዝዞ በማዋል እርምጃ መውሰድና ማስወሰድ የቻለ መሆኑ
15/ ስሙን ለማግነን፤ ክብሩን ለማስጠበቅ የሚያስችል በራሱ የሚመራ እንዲሁም በፖለቲካ የተቃውሞው ጎራ የተሰለፉ ደጋፊዎችና በስውር መረብ የሚንቀሳቀስ የሚዲያ ተቋም ያለው መሆኑ፤
ማኅበረ ቅዱሳንን ክርስቲያናዊ ብራዘር ሁድ እንድንለው ያስችለናል።

እስካሁንም ማንም ምላሽ ሊሰጥበት ያልቻለው ዋናው ነጥብ ማኅበረ ቅዱሳን ከመንግሥት እይታ ውጪ መሆን ባይችልም ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሆነ ክርስቲያናዊ ማኅበር መሆኑ ሲሆን እንደክርስቲያናዊ ተቋምነቱ  ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ በማኅበሩ ላይ ቁጥጥርና ክትትል የማድረግ ችሎታ አንዳችም አቅም የሌላት በመሆኑ ያሳዝናል:: በመንግሥትም፤ በቤተ ክህነቱም ማንም ጠያቂ የሌለው ሆኖ መቆየቱን ለማመን ያለመፈልግ ዝንባሌ መኖሩም ያስገርማል::  ማኅበሩ እንደምክንያት ሁልጊዜ የሚያቀርበው ሲኖዶስ በሰጠኝ ደንብ እመራለሁ ቢልም እውነታው ግን ብራዘር ሁድ በሆኑ ጳጳሳት አባላቱ በኩል የሚመቸውን ደንብ አስጸድቆ ያለጠያቂ በነጻነት ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የገቢ አቅሙን እያሳደገ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት ለራሱ አባላት እየመለመለ፤በቤተ ክርስቲያኒቱ ቁመናና መልክ የራሱን አደረጃጀት፤ መዋቅርና እንቅስቃሴ እያከናወነ ያለ ማኅበር መሆኑ የማይካድ እውነታ ነው። ለምሳሌ የማኅበሩ ብራዘር ሁድ አባላት ጳጳሳቱ አባ ማቴዎስ፡አባ ቀውስጦስ፡ አባ ቄርሎስ፡ አባ ያሬድ፡አባ አብርሃም፡አባ ሳሙኤል፡ በአባ ማቴዎስ አደራዳሪነት የትግሬን መንግስት በጋራ መዋጋት በሚል ፈሊጥ ከማኅበሩ እግር ላይ ወድቀው የታረቁት አባ ፋኑኤል ተጠቃሾች ናቸው:: አባ ገብርኤል ግን ከአቶ ኢያሱነታቸው ጀምሮ የተጠጋቸው የውግዘት በሽታ  መቼም አይለቃቸውም::

5/ ለመሆኑ አሁን ያለው ማኅበረ ቅዱሳን አደረጃጀት፤   

የሰንበት ት/ቤት ስብስብ ነው? እርዳታ ድርጅት ነው? የልማት ተቋም ነው? የበጎ አድራጎት ማኅበር ነው? ራሱን ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ውጪ አስደርጓል። በዋና ሥራ አስኪያጅ ሥር የሚተዳደር ነገር ግን የቤተ ክህነቱ መምሪያ ያልሆነ መምሪያ ነው?
በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሥፍራው ከየት ነው? በምንስ እንመድበው? ማኅበሩ በምን ሂሳብ እንደተቋቋመና በምን አደረጃጀት ኅልውና እንዳገኘ አይታወቅም::

እስከሚገባን ድረስ እንቅስቃሴውንና ያለውን አደረጃጀት ተመልክተን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳናዊ ብራዘር ሁድ ብንለው ተግባሩ ያረጋግጣል።
በሌላ መልኩ መንግሥት በኢትዮጵያ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ እንዲህ ዓይነት ማኅበር ከእስልምና ምክር ቤቱ ውጪ እንዲቋቋም ይፈቅዳል ወይ ብለን እንጠይቃለን? መልስ የሚያሻው ጥያቄ ነው።