«የነብር ጅራት አይዙም፤ ከያዙም አይለቁም!»

በጥያቄ እንጀምር! ማኅበረ ቅዱሳን ይፍረስ፤ ይበተን አልተባለም። ወደሕግና ሥርዓት ይገባ ነው እየተባለ ያለው። ማኅበሩ ይሁን ማፈሪያ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዚህ አባባል የሚናደዱት ለምንድነው? «ደረጃ፤ ቦታና መጠን ተበጅቶለት መቀጠል ይገባዋል» የሚለውን የማኅበረ ካህናቱን ድምጽ ለመስማት ያለመፈለግ ምክንያት ከምን የመነጨ ነው? እኮ አሳማኝ ምክንያት አቅርቡ!!
 አለበለዚያ «እኛ ሊቃነ ጳጳሳት ስለሆንና ጉባዔው በድምጽ ብልጫ ስለሚመራ የአድማ እጃችንን ቀስረን ማኅበረ ቅዱሳን የሚደሰትበትን እንወስናለን» የሚለው ፈሊጥ የተበላ ዕቁብ ነውና ዘንድሮ አይሠራም።  በትክክል ዘንድሮ አልሠራም፤ አይሠራምም።

 ሊቃነ ጳጳሳቱ በየአህጉረ ስብከታቸው የካህናት ማሰልጠኛ ኮሌጆችን በመክፈት፤ የሴሚናሪ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት የመንፈሣዊና ሳይንሳዊ እውቀት ባለቤት እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን እድገት እንዲሁም ፤ ለህብረተሰቡ ደግሞ በአካባቢ ልማት ተሣትፎ፤ በመንገድ ሥራ፤ በጤና ጣቢያና በንጹህ ውሃ አቅርቦት ተግባር ላይ በመትጋት ያንን ድሃ ምእመን ሕዝባቸውን መርዳት፤ መደገፍና በሥራ ማሳየት ሲገባቸው ተሸፋፍነው በመቀመጥ ሠራተኛ ሲቀጥሩ፤ ሲያባርሩ፤ ደመወዝ ሲቀንሱና ከቦታ ቦታ ሲያዘዋውሩ እድሜአቸውን ይፈጃሉ። ንቡረ እድ አባ ገ/ማርያም የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ጊዜ ሊቀ ጳጳስ አባ ቀውስጦስ ከራሳቸው ብሔርና ጎጥ ብቻ የመጣውን እየለዩ ለመቅጠር ሲታገሉ በተነሳ አለመስማማት የሙስና አፍ የዘጉትን ሥራ አስኪያጅ አይታዘዘኝም በሚል ውንጀላ ከስሰው እንዲቀየሩ ማስደረጋቸው አይዘነጋም። አሁን ደግሞ አባ ቀውስጦስ «ሞቴን ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ያድርገው» እያሉ ለያዥ ለገራዥ እያስቸገሩ እንዳሉ ይሰማል። ለምእመናን ልጆቹ በእኩል ዓይን አባት ይሆን ዘንድ ቃል የገባ ሊቀ ጳጳስ በዘረኝነትና በጎጠኝነት ሲታወር ሥጋውያኑማ እንዴት ይሆኑ?
የጎጃሙ ለጎጃም፤ የወሎው ለወሎ፤የጎንደሩ ለጎንደር፤ የሸዋው ለሸዋ የዘረኝነትን ገመድ የሚጎትት ሊቀ ጳጳስ ቤተ ክርስቲያንን እያወካት እንደሚገኝ ፀሀይ የሞቀው፤ አገር ያወቀው ጉዳይ ነው። እነማን? እንዴትና የት? ለሚለው በማስረጃ የተደገፈ ዝርዝር ማቅረብ ይቻላል።
ከብዙ መልካምና ጥሩ ነገሮቻቸው መካከል ሙት ወቃሽ አያድርገንና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የፈጸሟቸው ስህተቶች ለጵጵስና ማዕረግ ቀርቶ ለአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት የማይበቁ ሰዎችን የመሾማቸው ጉዳይ ትልቁ ስህተታቸው ነበር። እሳቸውም በሕይወት ሳሉ ሊሾሙ የማይገባቸውን ሰዎች በመሾማቸው ይጸጸቱ እንደነበር እናውቃለን። ዛሬም የዚያ ስህተት ውጤት የሆኑ ሊቃነ ጳጳሳት ስንት ሥራና አገልግሎት ባለባት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለአንድ ማኅበር ጥብቅና ቆመው «ሞታችንን ከማኅበረ ቅዱሳን ጓሮ ያድርገው» ሲሉ ይታያሉ። ከተመቻቸውና ከሞቃቸው ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ሞታችንን ያድርገው ያሉት ይሁንላቸው። ነገር ግን ማኅበረ ቅዱሳን ራሱ ወደሕግና ሥርዓት ካልገባ መሞቱ አይቀርም። ያን ጊዜ ምን ሊውጣቸው ይሆን?

ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የማኅበረ ካህናቱ ሙሉ ድጋፍ እንዳላቸው ይታወቃል። ማኅበሩን ሥርዓተ አልበኛ የሚያሰኙ ተግባራቱ የማኅበሩን የመጨረሻ እድል ይወስናሉ። የጳጳሳቱ ጩኸት መነሻውና መድረሻው ከጎጥ፤ ከጥቅምና ከፍርሃት የመነጨ እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ከማሰብ አይደለም። ምክንያቱም ማኅበረ ቅዱሳን ሳይኖር ቤተክርስቲያን ነበረችና። ማኅበረ ቅዱሳንም ባይኖር ትኖራለች።  ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በሊቀ ጳጳሳቱ አድማ እንዳይፈቱ አደራችን ጥብቅ ነው። ከሕግና ከኃይል በላይ የሚሆን ማንም የለምና በበሉበት ለሚጮኹት ቦታ ሳይሰጡ ሥርዓትና ደንብ የማስገባት እርምጃዎትን ይቀጥሉ ዘንድ አበክረን እናሳስባለን። ዘንድሮን ነካክተው ከተዉት ይሄ የተደራጀ አውሬ እስከመጪው ዓመት ይበላዎታል። አቡነ ጳውሎስንም የበላው እንደዚሁ ነው። ዕድሜአቸውን በዐሥር ዓመት አሳጠርነው እያሉ የሚፎክሩት እስከየት የመጓዝ እልክ እንዳላቸው ማሳያ ነውና ይጠንቀቁ። ክፉ ሥራቸውን የሚጸየፍ እግዚአብሔር ይረዳዎታል።

«የነብር ጅራት አይዙም፤ ከያዙም አይለቁም!»


Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 1 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
October 29, 2014 at 10:18 AM

The fact you are supporting Abba Mathias view on Mahbire Kidusan show that Abba Mathias unknowingly is paving the way for Tehadiso!

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger