«እርስዎም በአማካሪዎችዎ የተነሳ ዕድሜዎ እንዳያጥር ያስቡበት!» ያሉት አባ ማቴዎስ ጠንቅ ዋይ ወይስ የሞት መንፈስ?ዋና ሥራ አስኪያጁ ‹‹ውድቀት እንዳይደረስብዎ አማካሪዎችዎ ሊያዝንልዎ ይገባል፤›› ማለታቸውን የገለጹት የስብሰባው ተሳታፊዎች አያይዘውም ‹‹ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በአማካሪዎቻቸው ክፋት ከዕድሜያቸው ዐሥር ዓመት አሳጥረዋል፤ እርስዎም በአማካሪዎችዎ የተነሣ ዕድሜዎ እንዳያጥር ያስቡበት፤›› ሲሉ መምከራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ( ሐራ)

«እርስዎም በአማካሪዎችዎ የተነሳ ዕድሜዎ እንዳያጥር ያስቡበት!» ያሉት አባ ማቴዎስ ጠንቅ ዋይ ወይስ የሞት መንፈስ ናቸው?

የሁላችንም ዕድሜ ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነው። ማንም የማንንም ዕድሜ አያውቅም። ነገር ግን የሰውን ዕድሜ እናውቃለን የሚሉ ጠንቅ ዋዮችና መናፍስት ጠሪዎች ቢኖሩም አታላዮችና አጭበርባሪዎች ናቸው። ታዲያ አባ ማቴዎስ የፓትርያርክ አቡነ ማትያስን እድሜ በዐሥር ዓመት ማሳጠር የሚችሉት በምን ጥበባቸው ነው? ደግሞስ ነፍስ ኄር አቡነ ጳውሎስ ሊቆዩ ከሚችሉበት ዕድሜ በዐሥር ዓመት ያሳጠሩትስ በምን ኃይል ነው? አባ ማቴዎስ ስለሟቹ ፓትርያርክ አሟሟት የሚያውቁትን ምሥጢር በፓትርያርክ ማትያስ ላይ ለመድገም እንደሚችሉ «እርስዎም ዕድሜዎ በዐሥር ዓመት እንዳያጥር ያስቡበት!» ሲሉ ማስጠንቀቃቸው የሚነግረን አንድ ምሥጢር አለ። እግዚአብሔር ማኅበረ ቅዱሳንን የማይወደውን ሁሉ ይገድላል እያሉን ነው ወይም ማኅበረ ቅዱሳንን የማይወደውን ሁሉ እኛ እንገድላለን ማለታቸው ነው። እንደዚያ ካልሆነ ማኅበረ ቅዱሳንን ባለመውደድና በሞት መካከል ምን ግንኙነት አለ?

    አባ ማቴዎስ በግልጽ ቋንቋ የተናገሩት ዐረፍተ ነገር እንደሚያስረዳው ስለፓትርያርክ ጳውሎስ አሟሟት በትክክል እንደሚያውቁ ነው። ይህንኑ ዕውቀት በፓትርያርክ ማትያስ ላይ እንደሚደግሙት ማስጠንቀቂያቸው ያስረዳናል።
«የአቦን ግብር የበላ ይለፈልፋል» እንዲሉ በማኅበሩ ላይ የደረሰው የማኅበረ ካህናቱና የፓትርያርኩ ግልጽ አቋም ያበሳጫቸው ሸዌው እጩ ፓትርያርክ አባ ማቴዎስ በንዴት ሳያውቁት ድብቁን አደባባይ ላይ አዋሉት። «አቡነ ጳውሎስን የገደልናቸው እኛ ነን» ሲሉ ራሳቸው መሠከሩ። እኛም በመጠየቅ ጨምረን እንዲነግሩን የምንፈልገው እንዴት አድረገው እድሜአቸውን ማሳጠር እንደቻሉ ምስጢሩን ከቻሉ በጀመሩበት መንገድ በፈቃዳቸው እንዲነግሩን፤ እምቢ ካሉ ደግሞ በሕግ ፊት እንዲዘከዝኩልን ለሚመለከታቸው ክፍሎች እናሳስባለን። 

በአንድ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር ላይ «ዕድሜህን በዐሥር ዓመት እናሳጥራለን!» የሚለው ዛቻ «ልብስ አጥበን እንተኩሳለን» እንደሚባለው የሠፈር ማስታወቂያ ተነቦ በቀላሉ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። በተዘዋዋሪ «እንገድልሃለን» ማለት ነው። የግድያ ዛቻ ደግሞ በምድራዊው ሕግ ወንጀል ነው።  በሰማያዊውም ቃል ዐመጻና ክፋት ነው።

«አስበው ክፉ ነገርን ተናገሩ። ከፍ ከፍ ብለውም በዓመፃ ተናገሩ» መዝ 73፤8 

አስበው የተናገሩት ቃል ከፍ ያለ የግድያ ዐመጻ ነው። አባ ማቴዎስ ቀድመው እንደማይሞቱ ያረጋገጡ ይመስል የአቡነ ማትያስን በፍጥነት በሞት መወገድ በአደባባይ እንደማወጅ ነውረኛና የከፋ አነጋገር ይኖር ይሆን? እግዚአብሔር አምላክነቱ ለአባ ማቴዎስና ለማኅበረ ቅዱሳን ብቻ የሆነ ያህል አቡነ ማትያስን ቶሎ እንደሚገድል መናገር አሳፋሪ ነው። እንግዲህ እነዚህ ናቸው፤ ቤተ ክርስቲያንን የሚመሩት!

በማኅበረ ካህናቱ ስብሰባ ላይ የነበሩ አንድ ካህን ከተናገሩት አንድ ቃል እዚህ ላይ ልዋስ። « እነዚህ እኮ መንግሥትን ከአንድ ክ/ሀገር ወደሌላ ክ/ሀገር ያመጡ ሰዎች ናቸው እኮ፤ በዚያን ዘመን እንዲህ ማድረግ የቻሉ ዛሬ «አቢሲዲ ቆጥረውማ ማን ይችላቸዋል?» ማለታቸው አንድ ነገር ያሳስበናል። ለሥልጣን ሲሉ ሰው እስከመግደል ሊደርሱ መቻላቸውን ይገልጻል። እንደዚያ ካልሆነ አባ ማቴዎስ እስከዕድሜ ማሳጠር እብደት ቀመስ ንግግር ባልደረሱም ነበር። ምንም እንኳን የሰው ልጅ ዕድሜ በእግዚአብሔር እጅ ያለ ስለሆነ ሁሉም ሰው መሞቱ ባይቀርም አሟሟቱ ግን ልዩ ልዩ ነው።

 በጎርፍ፤ በመሬት መንቀጥቀጥ፤ በመኪና አደጋ፤ ገደል በመውደቅ፤ ውሃ ውስጥ በመስመጥ፤ በሕመም፤ በሰው እጅ በመገደል ወዘተ መንገድ ሕይወቱ ሊያልፍ ይችላል። የአቡነ ማትያስ አሟሟት በእነ አባ ማቴዎስ እጅ ይፈጸም ዘንድ ከፈጣሪ የታዘዘ ካልሆነ በስተቀር ካልጠፋ ወቀሳና ሌላ የማሳሰቢያ ንግግር «እንደአቡነ ጳውሎስ ዕድሜዎት በዐሥር ዓመት ያጥራል» ባለሉም ነበር። እግዚአብሔር የነፍሳት ሁሉ ጌታ ስለሆነ  አሟሟታቸውን ልዩ ልዩ አድርጓል።  በእርግጥም የሰውን ነፍስና ሥጋ ይለዩ ዘንድ ምክንያት ከሚሆኑት መካከል ክፉ መናፍስቶች አንዱ ናቸው። አባ ማቴዎስን ከክፉው መንፈስ እንደአንዱ እንቁጠራቸው? ሞትን ያህል ዜና በአደባባይ ያወሩት የክፉው መንፈስ መልዕክት ቢደርሳቸው ይሆናል። እውነታው ግን እግዚአብሔር ለአባ ማቴዎስና ለማኅበራቸው ብቻ የቆመ አምላክ አይደለም። ኃጢአተኞችን ሁሉ በመታገስ ዕለትን በዕድሜአቸው ላይ የሚሰጥ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው።
ነገር ግን አባ ማቴዎስ እንደጻድቅ ራሳቸውን ቆጥረው በሌላው ሰው ላይ ሲፈርዱ ለዚህ ክፉ አሳባቸው የሞት መልአክ ቀድሞ ወደእርሳቸው ቢመጣስ?

«ክፉ ሰው ዓመፃን ብቻ ይሻል ስለዚህ ጨካኝ መልአክ ይላክበታል» መዝ 17፤11 ይላልና መጽሐፉ።

አቡነ ማትያስም ከክፉ ሰዎች እጅ እንዲድኑ አብዝተው መጸለይ የሚገባቸው ይመስለናል። ዳዊት በዝማሬው እንዳለው

 « አቤቱ፥ ከክፉ ሰው አድነኝ፥ በልባቸውም ክፉ ካሰቡ ከዓመፀኞች ሰዎች ጠብቀኝ ቀኑን ሁሉ ለሰልፍ ይከማቻሉ» መዝ 140፤1

የዕድሜ ወሰን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

«የሰው ዕድሜ የተወሰነ ነው፥ የወሩም ቍጥር በአንተ ዘንድ ነው፥ እርሱም ሊተላለፈው የማይችለውን ዳርቻ አደረግህለት» ኢዮ 14፤5
አባ ማቴዎስ ማኅበረ ቅዱሳንን የሚነካ ሁሉ ይሞታል እያሉ ይናገራሉ።  ታዲያ አባ ማቴዎስ ጠንቅ ዋይ ናቸው ወይስ የሞት መንፈስ???? የምታውቁ ንገሩን!!

Share this article :

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger