ሐራ ተዋሕዶ የተባለው የማኅበረ ቅዱሳን ቀኝ ክንፍ መካነ ጦማር ቅዱስ ፓትርያርኩ በሲኖዶሱ መክፈቻ ላይ ባቀረቡት ንግግር ተወገዙ፤ ውሳኔም ተላለፈባቸው ሲል ከብራዘር ሁድ ጳጳሳቱ ጋር ያለውን የምስጢር ትስስር በሚያሳብቅ መልኩ ዘገባውን አቅርቧል። ማኅበሩ የሲኖዶስ አባል ሆኖ በጉባዔው ላይ በመገኘት የጉባዔው ተካፋይ መሆን አይጠበቅበትም። በሱ ምትክ የጉባዔውን እስትንፋስ እየለኩ ምስጢር የሚያካፍሉ አባላት የሆኑ ጳጳሳት እንዳሉት ይታወቃል። ማኅበሩን ያናደደውና ደረጃውን ያልጠበቀ የፓትርያርኩ የመክፈቻ ንግግር ያሰኘው ነገር ቅዱስ ፓትርያርኩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ስለማኅበሩ ቀጥተኛ አቋም ይዘው በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ አበክረው ስላሳሰቡ ከደረሰበት ጭንቀት የተነሳ መሆኑ ይገባናል። የፓትርያርኩን ንግግር ደረጃ የሚያወጣና ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ እሱ ማነው? አባ ሉቃስ? አባ ማቴዎስ?
በዚህ ዓመት ስለማኅበረ ቅዱሳን አቅምና ጡንቻ የመጨረሻ ገደብ ካልተደረገበት የነብርን ጅራት ይዞ እንደመልቀቅ ይቆጠራል። ጳጳሳቱም ቢሆን ክብራቸውን ካልጠበቁና ለማኅበሩ በአድማ ተሰልፈው ከቆሙ በተመዘገበ ግለ ታሪካቸው ቦታ ቦታቸውን እንዲይዙ ሊደረግ ይገባል። በአጭር ቃል ባለትዳሮቹና የልጅ አባቶቹ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ማዕረግ ወርደው ከምዕመናን አንድነት ሊቀላቀሉ የሚገባው ዓመትም ይህ ዓመት ነው። ሳይገባቸው ከፍታ ላይ የተቀመጡ ሰዎች ባለበት አስተዳደር ምን ጊዜም ሁከት፤ ክፍፍልና እርስ በእርስ መለያየት መኖሩ እርግጥ ነው።
ይህ ዓመት ቤተ ክርስቲያንን የሚያምሱ፤ በአድማ የሚወስኑ ሰዎች ሰልፍ የሚሰበርበት እንዲሆን እንመኛለን።