Wednesday, October 1, 2014

በምድራችን ላይ በክፉ መንፈስ ተነድተው ሕዝብን ያሳሳቱ ሀሰተኛ ክርስቶሶችና ነብያት!



 ( ክፍል 3 ) 

ጂም ጆንስ (1931-1978)
በአሜሪካዋ ኢንዲያና ስቴት ህዳር 18, 1931 ተወለደ። እድሜው ለአቅመ ህውከት ሲደርስ በኢንዲያናፖሊስ ከተማ የኮሙኒስት ፓርቲ አባል በመሆን በህውከት ስራ ላይ መሰማራትን «ሀ» ብሎ ጀመረ። የኮሙኒስት ርእዮት አራማጅ የሆነው ጆንስ በሜቶዲስት፤ በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ውስጥ ብቅ ጥልቅ እያለ ከቆየ በኋላ ዓለም በኒውክለር ትጠፋለች ስለዚህ ሐዋርያዊ ሶሻሊዝም በዓለም ላይ መምጣት አስፈላጊነት ይሰብክ ነበር። ጆንስታውን ወደተባለች የጉያና ከተማ በማቅናት «የህዝቦች ቤተ መቅደስ» የተሰኘ ቤተክርስቲያን ከመሠረተና ከተደላደለ በኋላ የእርሻ ተቋም ከፈተ።  በዚህ የእርሻ ተቋም ውስጥ ሶሻሊስታዊ እኩልነት የሰፈነበት ማኅበረሰብ እመሰርታለሁ በማለት የራሱን «የቀይጦር ሠራዊት» አደራጀ። ይህ የቀይ ጦር ሠራዊት ዋና ዓላማው የእርሻውን ሜካናይዜሽንና የቤተ ክርስቲያኑን ህልውና የመጠበቅ ዓላማ ይዞ የተነሳ ቢመስልም በተግባር ግን የጂም ጆንስን አንባገነንነት መንከባከብ ነበር። ወደተቋሙ የገባ ማንም አባል መውጣት አይችልም በማለት ማገድ ጀመረ። በዚህም ሳቢያ በዚያ ማኅበረሰብ ውስጥ የፈለገውን ማድረግ የሚችል አንባ ገነን መሆን ቻለ። ከዚህ ተቋም ሸሽተውና አምልጠው ወደአሜሪካ የገቡ ሰዎች ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተርና ለምክርቤቱ አቤቱታቸውን ማቅረብ ቻሉ። በሰብአዊ መብት ጥሰት የተከሰሰው  የጆንስን ጉዳይ የሚያጣሩ በኮንገረስ ማን ሊዮ ሪያን የሚመራ ብዙ የሚዲያ ሰዎችን የያዘ ቡድን ወደጉያና አመራ። ቡድኑ ከቦታው እንደደረሰ ከጆንስ ቀይጦር አባላት የጠበቀው የሞቀ ሰላምታ ሳይሆን የደመቀ የጥይት ተኩስ ነበር። ኮንግረስ ማን ሪያንና ሌሎች ብዙዎቹ በተኩሱ ተገደሉ።  ከፊሎቹም ቆሰሉ። ህዳር 18, 1978 ዓ/ም ጥዋት ላይ ይህ ግድያ ከተፈጸመ በኋላ ጆንስ ወደተከታዮቹ በመመለስ ከሚመጣባችሁ ቁጣ ለመዳን ራሳችሁን አጥፉ፤ ልጆቻችሁንም ጭምር ለመፍጀት ለሚመጡ ጠላቶች አሳልፋችሁ አትስጡ፤ ስለዚህ አብራችሁ ሙቱ በማለት ትእዛዝ ሰጠ።
ሳይናድ መርዝ እየጠጡና እያጠጡ 300 ህጻናት ያሉበት 900 ሰዎች በጥቂት ሰዓት ውስጥ አለቁ።
እኔ ቡድሃን፤ ሌኒንን፤ኢየሱስን እና ሌሎችን ሆኜ ተገልጫለሁ እያለ ያታልል የነበረው ጂም ጆንስ በአውቶማቲክ ጥይት ግንባሩን ብትንትንን አድርጎ ራሱን በራሱ ገደለ።




ማርሻል አፕልዋይት  (1931-1997)
ስፐር ፤ቴክሳስ ተወለደ። እድሜው ለአቅመ ማሳሳት ከመድረሱ በፊት የአሜሪካ ወታደር በመሆን አገልግሏል። በሂውስተንና ኮሎራዶ ትምህርቱን የተከታተለው አፕል ዋይት በአላባማ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሲሰራ በግብረ ሰዶም ተጠርጥሮ ከስራው ተባሯል። ይህንን ተግባሩን የመሰከረበት ደግሞ በስብከቱ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን አስፈላጊነት መናገሩ ነበር። አፕል ዋይት የሙዚቃ ባለሙያ ስለነበር በዚህ ሙያ ያገኘውን ችሎታ ተጠቅሞ «Heaven’s Gate» /የመንግሥተ ሰማይ በር/ የተሰኘ ሃይማኖታዊ ድርጅት መሠረተ።  አፕልዋይት በዩፎዎች መኖር የሚያምንና በነሱ ላይ ጥገኛ የሆነ ስብከት ያስተምር ነበር።
 በ1974  ዓ/ም የተከራያትን መኪና ባለመመለስ ወንጀል ተከሶ ስድስት ወር ተፈርዶበት ከርቸሌ ወረደ። ከዚያም እንደወጣ ጣዖታዊ ስብከቱን ቀጥሏል። መስከረም 25, 1995 ዓ/ም «እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ነኝ» በማለት ለተከታዮቹ አሳወቀ።
በመጋቢት 29/ 1997 ዓ/ም ዩፎዎች መጥተው ወደገነት ስለሚወስዱን ራሳችንን እናጥፋ ብለው በጅምላ ራሳቸውን ገደሉ። ከተከታዮቹ መካከል ማርሻል አፕል ዋይትን ጨምሮ 30 አባላቱ ሞተው ተገኙ። ነገር ግን ሁኔታው እንደተሰማ ከቦታው የተገኘ አንድም ዩፎ አልነበረም። ይልቁንም ፖሊስ ከቦታው ተገኝቶ እነአፕልዋይት ራሳቸውን በራሳቸው ማጥፋታቸውን አረጋግጦ የህዝብ መቃብር ውስጥ እንዲወርዱ አድርጓል።




ያህዌህ ቤን ያህዌህ (1935-2007) 

 ጥንተ ስሙ ኸሎን ሜሼል ጁንየር ይባል ነበር። ይህ ጥቁር አሜሪካዊ እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ለማለት ፈልጎ ስሙን  በ1979 ዓ/ም «ያህዌህ ቤን ያህዌህ» በማለት ቀየረ። ብዙዎቹም ተከታዮቹ ከክርስትናውና ከአይሁድነት ያፈነገጡ ሰዎች ነበሩ። በተለይም ጥቁር አሜሪካውያን ብዙ ቁጥር ያላቸው ሲሆን ትክክለኛው እስራኤላውያን እኛ ነን፤ ይሉ የነበረ ሲሆን በአሜሪካና በዓለም ላይ በ1300 ከተሞች ውስጥ አባላቱን ማደራጀት ችሏል። እግዚአብሔር ጥቁር ነው። እስራኤልውያንም ጥቁሮች ነበሩ። ነጮቹ ታሪካችንን ቀምተው ነው። ሰይጣን ማለት ነጮች ናቸው ይል ነበር። በዚህም ምክንያት ዓርብ ህዳር 13 ቀን አንገታቸው የተቀላ የነጮች ሬሳ በአቅራቢያው ዳዋ ውስጥ ተጥሎ በመገኘቱ ጥቁሩ መሲህ ቤንያህዌህ በ1992 ዓ/ም ሰው በመግደል ወንጀል ተጠርጥሮ ተያዘ። በፍርድ ቤትም በምስክሮች ስለተረጋገጠበት የ18 ዓመታት እስር ተበይኖበት ከርቸሌ ወረደ።  
በእስራቱም ነብይ በሀገሩ አይከበርም ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው ሲሉ ተከታዮቹ ለፈፉ። ከ8 ዓመት እስራቱም በኋላ በ2001 ዓ/ም በምህረት ተለቀቀ። በ2007 ዓ/ም በፕሮስቴት ካንሰር ሞተ። ከሱ ሞት በኋላ ተከታዮቹ በሥጋ የተገለጠው እግዚአብሔር ማለታቸውን አልተዉም። ልቡ የደነደነ ዓለም ዓይኑ ታውሮ ሰው ያመልካል። ለጣዖትና ስዕል ይሰግዳል።

(ይቀጥላል % )