Monday, July 22, 2013

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጉዞና ልምላሜ የተለየው ዛፍ አንድ ናቸው!

አዲስ አበባ የሀገሪቱ ርእሰ መዲና እንደመሆኗ መጠን የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በገንዘብ፤ በባለሙያና በሠራተኛ አቅም ትልቁ ሀገረ ስብከት ነው። በዚህ ሦስት ተቋማዊ አቅም በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ለሌሎች ሀገረ ስብከቶች የሚተርፍ በቂ ኃይል ያለው ሀ/ስብከት ነው። የርእሰ መዲናይቱ ሀ/ስብከት እንደመሆኑ መጠን የተሻለ ሥራ፤ ክፍያና ኑሮ ለማግኘት ከገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን የሚፈልሰው አገልጋይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። የሚያሳዝነው ግን አዲስ አበባ ከተማ ከተኛችበት እየነቃች እዚህም እዚያም ጉች ጉች ብለው የሚታዩት ግንባታዎችና የተዘረጉ መንገዶች ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለውጥ ምን እንደሚመስል ለማየት የሚያስችል ዐይን እንዲኖረው የፈየደለት ነገር አለመኖሩ ነው። የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አስተዳደር ወደኋላ መሄድ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ዛሬም የሚታይበት አንዳች እንቅስቃሴ የለም። ለውጥ የሂደት ክስተታዊ ግዴታ ቢሆንም ይህ አመክንዮ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ለምን እንዳልጎበኘው ግራ ያጋባናል። ምናልባት እንደ ቀንድ አውጣ የዐርባ ዓመት እንቅልፉን አልጨረሰ ይሆን? ጊዜ ደግሞ ታክሲ አይደለም። ጊዜ ሲሄድ ባለበት ከሚቆመው ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በስተቀር።
የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ተቋማዊ የኋሊዮሽ መንገድ ስንገመግም ቤተክርስቲያኒቱ የት እንዳለች ፍንጭ ሊሰጠን ይችላል። እነማን ቤተ ክርስቲያኒቱን እየመሯት እንዳሉ ያመላክተናልም። በሌላ ቋንቋ ቤተ ክርስቲያኒቱን የ40 ዓመት የቀንድ ዐውጣ እንቅልፍ ውስጥ እንደገባች የተቀመጡባት ሰዎች አመራር ይጠቁመናል። ዋልታ የሌለው ጣሪያ በአናቱ ዝናብ ማስገባቱ አይቀርምና ለጣሪያው መበስበስ የአናቱ ክፍተት ምክንያት ከመሆኑ ውጪ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት መበስበስ የላይኛው ጣሪያ የመበስበሱ ምልክት ተደርጎ ቢወሰድ አያስኬደንም ትላላችሁ?
የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን የበሰበሰ ጣሪያ ለመጠጋገን ብዙ ተሞክሯል። መጽሐፉ እንደተናገረው በአሮጌው አቁማዳ ላይ አዲስ ለመጣፍ እየተሞከረ መበጣጠሱን የከፋ አደረገው እንጂ የተቀየረ አንዳች ነገር የለም። በእነ እገሌ ዘመን የነበረው አስተዳደር ጥሩ ነበር እንዳንል የሁሉም ዘመን ችግር በመጠን ከሚበላለጥ በስተቀር በይዘቱ አንድ ነው። በእርግጥ ይዘቱ መጠኑንና ዓይነቱን ጨምሮ ዛሬ ሀ/ስብከት ሳይሆን «ኃላፊነቱ የተወሰነ የነጣቂዎች ማኅበር» ወደመሆን በመሸጋገሩ ከድሮዎቹ አስተዳደር ዛሬ የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱ እውነት ነው። አንዱን ሾሞ አምሮቱ ሲጠረቃ ሌላ ያልጠረቃ በመሾም ችግሩን በማባባስ በኩል ያ! ያልታደለው ሲኖዶስ ለሀ/ስብከቱ ውድቀት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ምክንያቱም ሲኖዶሱ ያልጠረቃውን በጠረቃው አመራር በማለዋወጥ ካልዘሩበት የሚያጭዱ ነጣቂዎችን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በማኅበር አደራጅቶ ባልለቀቃቸውም ነበር። 

ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን ንቡረ እድ መምህር ገ/ማርያም ገ/ሥላሴ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እያሉ አውድማውን ሳያሄዱ የተመረተውን ዝም ብለው የሚቅሙ አጋሰሶችን አፍ በመዝጋታቸው ብቻ በእህል በሎች ክስ ባላባረሯቸውም ነበር። የሆነው እውነታ ግን ጠርጎ በሎችን መረን ለቆ፤ «ሊሰራ የማይወድ አይብላ» ብለው የታገሉትን ጠንካራ ሰው ባላባረረም ነበር። ድሮስ ጠርጎ በልን ሊታደግ የሚችለው ከጠርጎ በል በቀር ማን ሊሆን ይችላል?
የንቡረ እድ ገ/ማርያም ገ/ሥላሴ ወንጀል የቤተ ክርስቲያኒቱን ሙዳየ ምጽዋት ዘረፋ ማስቆም መቻላቸው ነበር። ከ200 ሺህ ብር በላይ ተቆጥሮ የማያውቀው የመንበረ መንግሥት ቅ/ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ  ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የተቆጠረው በንቡረ እድ ገ/ማርያም ክትትል መሆኑ ታሪክ መዝግቦታል። የሌሎቹም አድባራት ሙዳየ ምጽዋት ሣጥኖች እየተዘቀዘቁ ከመገልበጥ የተረፉት በኚሁ ሰው አስተዳደር ዘመን ስለመሆኑ ገልባጮቹ ሳይሆን አገልጋይ ካህናቱ የሚናገሩት እውነታ ነው። ምን ያደርጋል ታዲያ? እውነተኛና ሀቀኛ እርሟ የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ንብረ እድ ገ/ማርያምን ከአዲስ አበባ ወደሽሬ  በመወርወር ሲኖዶሱ ቁጭቱን ተወጣባቸው። ገልባጮችንም አስደስቷል። አባ ገ/ማርያም ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት መነሳታቸውን የሰሙ ምሽት ሙዳየ ምጽዋት ገልባጮች ሻምፓኝ ሲራጩ ማደራቸው ተሰምቷል። እንግዲህ ይህ ክፍል ነው በመበደሉ ምክንያት ሲኖዶሱ በነፍሱ የደረሰለት። አሳዛኝ ዘመን?
ዛሬ ደግሞ በፓትርያርክ ማትያስ ምርጫ ላይ የአንበሳውን ድርሻ የወሰዱት አባ እስጢፋኖስ ለፈጸሙት የታማኝነት አገልግሎት ከፓትርያርኩ በገጸበረከትነት የቀረበላቸው ስጦታ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሲሆን በፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስነት ሽፋን ተዝቆ የማያልቀውን ካዝና የድርሻቸውን እንዲናኙ  ተመድበው እነሆ ከመነሻው በስመ ሥልጠና ሽፋን ተረክበው እያመሱት ይገኛሉ። የሚያሳዝነው ደግሞ ገና ምኑንም ሳይጀምሩ አባ እስጢፋኖስ አድባራቱን ገንዘብ አዋጡና ወደ ሀገረ ስብከቱ ገቢ አድርጉ እያሉ ሥልጠና በተባለው አሰልቺ መድረክ ላይ ነጋ ጠባ መጮሃቸው ነው። አዋጡ ማለት ምን ማለት ነው? ፐርሰት ክፈሉ ነው? ወይስ የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት የሚጦራቸው ድኩማን አሉት? ጥያቄውን ለአቡኑ እንተውና ከአዋጡ ጭቅጨቃቸው የምንረዳው እውነታ ቢኖር ሀ/ስብከቱ ዛሬም ፈውስ የራቀው መሆኑን ነው። ሥልጠና በተባለው የጩኸት መድረክ ላይ ሥልጠናውን የሚካፈሉት እነዚያው የቤተ ክርስቲያንን ሙዳየ ምጽዋት የሚገለብጡ ሰዎች መሆናቸውን ስናይ አቡኑ አዲስ ነገር መጀመራቸውን በማሳየት በቀደመው ጎዳና ለመሄድ ያቀዱት ስላለመሆኑ የሚያሳምን አንዳች  ሥር ነቀል ተቋማዊ ለውጥ አለመኖሩ ቁልጭ ብሎ ይታየናል።  ስልጠና በተለወጠ ሰውና ለለውጥ በተዘጋጀ አእምሮ ላይ የሚዘራ ዘር እንጂ የለውጥ መንገድ እንቅፋት ሆኖ በቆየና በጨቀየ አእምሮ ላይ ሲሆን ስናይ ረዳት ሊቀጳጳሱ ወይ ስራውን አያውቁትም፤ ወይም ስራው አያውቃቸውም።
 አቡነ ቀውስጦስ የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሳሉ በተጠናወታቸው ዘረኝነት የጎጣቸውን ሰዎች እያመጡ ሲሰገስጉና ሲያሳድጉ ንቡረ እድ ገ/ማርያም በሩን ዘግተ አላሳልፍ ስላሏቸው ብቻ በሲኖዶስ ጉባዔ ላይ ከሳሽ ሆነው መገኘታቸውን አንዘነጋውም። ዛሬም አቡነ እስጢፋኖስ የንቡረ እድ ገ/ማርያምን ወደ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነት ዳግም የመመለስ የካህናት ጥያቄ አልቀበልም ያሉት ንቡረ እዱ እጅ ከወርች አስረው ረጅም እጆችን ሁሉ ስለሚያስቆሙ ከወዲሁ የተወሰደ መላ መሆኑ ይገባናል። አቡኑ ሙስናን የሚዋጉ ከሆነ ምነዋ! የሙስናውን በር ድርግም አድርገው የዘጉትን ንቡረ እድ በሥራ አስኪያጅነት ማስቀመጥ ፈሩ? በእርግጥ አቡኑ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሳሉ ጥንቱኑ በሩን የከፈቱት እሳቸው አይደሉ እንዴ? ስለሆነም ሙስናን የመዋጋት ብቃትም፤ ሞራልም የላቸውም። ስልጠና መልካም ቢሆንም ሙስና በስልጠና አይጠፋም። ሙስናን በሚጠየፍና ለመዋጋት በተዘጋጀ አመራር እንጂ በገንዘብ አዋጡ ስልጠና ሊሆን አይችልም። የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤትም ይሁን አድባራቶቹ በእነማንና በተደራጀ አዲስ አመራር ተዋቅሯል?
 ሙስናው ከዐለማውያኑ በዐይነቱ የከፋ ሆኗል። አፍኒንና ፊንሐሶች ተፈልፍለዋል። ሁሉም በዐመጻው ተካክሏል። ጠቅላላው ታማሚ በመሆኑ መድኃኒት የሚሆን ነገር ርቋል። ለዓለም ትተርፍ ዘንድ አደራ የተጣለባት ቤተ ክርስቲያን በባላንጣ ተወራለች።  አሳዛኝ ዘመን!
የሚገርመው ደግሞ ሰሞኑን ከጳጳሱ እግር ከሥር ሥራቸው ቱስ ቱስ የሚሉ የማኅበረ ቅዱሳን አሸርጋጆችን ስንመለከት  በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ውስጥ እንደፈለጉ ለመፋነን እድል ማግኘታቸው ጠቋሚ ሲሆን የሚፈሩትን ማኅበር ለማገልገል ግንባራቸውን እንደማያጥፉ  የሊቀ ጳጳሱ የቆየ ልምድ ደግሞ ያረጋግጥልናል። ከወዲያ ፓትርያርክ ማትያስ በቀጥታ መስመር በውዳሴና በተጠናው ደካማ ጎን በኩል በለስላሳ ጥበብ ተይዘዋል። ከወዲህ አቡነ እስጢፋኖስ በረዳት ሊቀ ጳጳስነት ተጠፍንገዋል። በመሀከል የሲኖዶስ ጸሐፊው የማቅ ታማኝ አባል አባ ሉቃስ ተቀምጠዋል። ጥሩ የመድረክ አዳማቂ የነበሩት አቡነ ጢሞቴዎስ ለማኅበሩ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለምርቃት ሳይበቃ በጎዶሎ ቀን ከኮሌጅ ተማሪዎች ጋር ተጋጭተው ከሥፍራ ተወግደዋል።  ያገለገሉትን መለስ ብሎ የማያየው ይህ ማኅበር ከአባ ጢሞቴዎስ ጋር ራሱ ተጣልቶ ከመለያየት የገላገለው የተማሪዎቹ ግርግር ሳያስበው መከሰቱ ነበር። ከጀርባም ሆኖ የተማሪዎቹን ችግር በማራገብ ነዳጅ ያርከፈክፍ የነበረው ይህ እድል ሳያልፈው ለመጠቀም ካለው ፍላጎት የመነጨ ነበር። ያሰበው በተማሪዎቹ ችግር ጀርባ ፍጻሜ አገኘ።  ከዚህ የተነሳ ማኅበሩ በትኩስ በትኩስ ምድብተኞች ለመገልገል እድል ያረግድለታል ወይም  አካሄዱን ያውቅበታል። ይኸው እንደ ሳሙና እየተሙለጨለጨ ዛሬ ላይ ደርሷል። ከዚህ በፊት ውጥረት ሲበዛበት የዐባይን ቦንድ እገዛለሁ እስከማለት መድረሱ እንደሳሙና በመሙለጭለጭ ላለመያዝ መሄድ የሚችልበት ስልት ረቂቅ መሆኑን ያሳያል።
ከላይ እያልነው እንደመጣነው በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ውስጥ  ዛሬም አዲስ ለውጥ የለም። በላተኞች ስልጠና እየወሰዱ ከመሆኑ በስተቀር አዲስ የሥራ ኃይል፤ አዲስ የመዋቅር ለውጥ የለም። አሁንም የታመነባቸው፤ የሚታወቁና የተመሰከረላቸው ሰዎች በለውጥ ሂደቱ ውስጥ የሉም። በአምናውና በካቻምናው በሬ አርሶ ምርት መጠበቅ ከቶ እንዴት ይቻላል? ካልዘሩበት ማጨድ ማለት ይህ ነው።
ሁለት ወገኖች ግን ተጠቃሚዎች ይሆናሉ። ሀ/ስብከቱ በፓትርያርክ ማትያስ የተሰጣቸው ሽልማት ሲሆን ከዚህ በሚገኘው ሲሳይ የሚናኙት አዲሱ ሊቀ ጳጳስና ከአባ ጳውሎስ ሞት በኋላ ታማኞቹ ብቻ ቦታ ቦታቸውን የያዙለት ማኅበረ ቅዱሳን ተጠቃሚዎች ናቸው።
ከዚህ በተረፈ ሀ/ስብከቱ ከሕመሙ ይድናል ብለን እንድንጠብቅ የሚያደርገን የሚታይ አዲስ መንፈስ፤ አዲስ መዋቅር፤ አዲስ የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት፤ አዲስ የውጤት ምዘና ስልት፤ አዲስ የልማት እቅድ የለም። ካህናቱ ከላይ የሚፈሰውን መመሪያ እንደቧንቧ ከሚጠጣ በስተቀር በሂደቱ ላይ ወሳኝ አካል ተደርጎ አልተወሰደም። ጉዞው ከየት ወደየት? ነው ብንል ከድጡ ወደማጡ ነው መልሳችን። ገንዘብ አዋጡ፤ ገንዘብ አዋጡ! ድሮም ዛሬም ከሀ/ስብከቱ ውስጥ ያልጠፋ የበላዮች ድምጽ አልቀረም። ዛሬ ላይ ይህንን እንደዘገብን አምላክ ቢፈቅድ የዛሬ ዐመትም እንዲሁ የለውጥ ያለህ ብለን እንዘግብበት ይሆናል። የዚያ ሰው ይበለን!