Thursday, July 18, 2013

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለምን ተሐድሶ ያስፈልጋታል? ክፍል ሁለት፡-

      
              (www.tehadeso.com)
ላደግንባት፣ ቃሉን ላወቅንባት እና አሁንም እያገለገልንባት ላለችው ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ሁሉ ዐዲስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል በመደገፍ እንደ ቃሉ የሆነ እና የሰላም አለቃ የሚሰለጥንበት ተሐድሶ እንደሚያስፈልጋት፣ በሙሉ ልባችን እናምናለን፡፡ ቤተ ክርስቲያን ተዘፍቃበት ካለው ሁሉን አቀፍ ችግር ለመውጣት የሚያግዛት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የሚከናወን ተሐድሶ አስፈላጊ ነው፡፡
“…እንደ ምሕረቱ መጠን ለዐዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን..”  የሚለው ዐረፍተ ነገር፣ ተሐድሶ በእግዚአብሔር መንግሥት አስፈላጊው እና ፍሬያማው እውነት እንደሆነ ያሳያል፡፡ የእግዚአብሔር ምሕረት ከፍተኛነት በመንግሥቱ ውስጥ ለሚኖረን ቦታ የሚያበቃን፣ በመንፈስ ቅዱስ በኩል የሆነው መታደስ ነው፡፡ ይህ እውነት ለግለሰብም ለቤተ ክርስቲያንም በእኩልነት ይሠራል፡፡ አንድ ሰው ከጠፋው ማንነቱ ተመልሶ ለእግዚአብሔር መንግሥት ዜጋ እንዲሆን ከመንፈስ ቅዱስ የሆነው ተሐድሶ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ቤተክርስቲያንም የቀበረችውን እውነት ቆፍራ እንድታወጣ እና ለእግዚአብሔር ሐሳብ እሺ በጄ ብላ እንድትታዘዝ ከመንፈስ ቅዱስ የሆነው ተሐድሶ ያስፈልጋታል፡፡

ባለፈው በክፍል አንድ ጽሑፋችን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለምን ተሐድሶ አንደሚያስፈልጋት ሦስት መሠረታዊ ምክንያቶችን አንሥተን ማቅረባችን ይታወሳል፡፡  ዛሬ ደግሞ ቀጣይ ሐሳቦችን እናቀርባለን፡፡

•    የሥጋዊ  አሠራር ሥር መስደድ፡-


በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ሰውና መንፈሳዊ አሠራር ከጠፋ ሰነባብቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያን፣ ነገሮች ሁሉ በጸሎት የእግዚአብሔርን ምሪት በመፈለግ ሳይሆን የሚሠራባት፣ የሰውን ፊት በማየት የሚከናወኑባት የዓለማውያን ሸንጎ ሆናለች፡፡ ከሞላ ጎደል በማንኛውም ጉዳይ ለማለት ይቻላል ቤተ ክርስቲያኗ የእግዚአብሔርን ምሪት ጠይቃ አገልጋዮችዋንና ምእመናኗን አስተባብራ በአንድነት በጸሎት በፊቱ ወድቃ የምትከውናቸው ነገሮች የሏትም፡፡ ይልቁንም በአሠራርዋ ከእሷ የተሻለ እንቅስቃሴ ካለው ከመንግሥት ፖሊሲዎች እና ወቅታዊ አጀንዳዎች በመነሣት እነዚያን አጀንዳዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማስፈጸም ከመሯሯጥ ያለፈ ሥራ ተሠርቶ አይታወቅም፡፡ መንግሥት “አቅም ግንባታ” ሲል ቤተ ክህነትም አቅም ግንባታ፣ መንግሥት “ደን ልማት” ሲል ቤተ ክርስቲያንም ደን ልማት፣ መንግሥት የፀረ ሙስና ርምጃ ሲወስድ ቤተ ክርስቲያንም ያውም ላትተገብረው ስለ ሙስና ማውራትን እንደ ትልቅ ቁም ነገር ወስዳ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ የአሠራርም ሆነ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ምንም  ዝግጅትና ርምጃ ሳታደርግ የሰሞኑ ነጠላ ዜማዋ አድርገዋለች፡፡
እውነተኛው ባለ ራእይና የምሪት አለቃ እግዚአብሔር ተረስቶ፣ ትልቁ ሕገ መንግሥት መጽሐፍ ቅዱስ ተዘንግቶ “ምን ተባለ” እያሉ ሥራ ለመሥራት መሞከር በእስካሁን እንቀስቃሴዋ እንደታየው የተሻለ ለውጥ አላመጣላትም፡፡ መንግሥት የሚያወጣቸው ሕጎችና አፈጻጸሞች የተሳሳቱ ናቸው ባንልም፣ ቤተ ክርስቲያን ግን በእግዚአብሔር መንግሥት አሠራር ውስጥ የዓለማዊውን መንግሥት አሠራር ሙሉ በሙሉ ያውም ምን እንደሆነ እንኳ ሐሳቡ ሳይገባት ለመፈጸም ከሞከረች የሥጋዊነት መገለጫዋ ነው፡፡
በሌሎችም በቤተ ክርስቲያን በሚሠሩ ሥራዎች፣ የእግዚአብሔርን ቤት እንደ መንደር እድር በዘፈቀደ የመምራት እንቅስቃሴዎች ስለምታደርግ፣ ይበልጥ ከእግዘአብሔር ሐሳብ ሲያርቃት እንጂ ወደ ዘላለማዊ አምላኳ ሲያስጠጋት አላየንም፡፡ የሚደረጉት ማንኛቸውም ነገሮች ሥጋ ሥጋ ከመሽተት ያለፈ አንዳች መንፈሳዊነት አይታዩባቸውም፡፡ ከነጭራሹም መጽሐፍ ቅዱስ ተነብቦ የማይታወቅ እስኪመስል ድረስ ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ አሠራር ጠፍቷል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሲኖዶስ ጉባኤ እንደሚገኝ ለማሳየት  በጉባኤው አንድ ባዶ ወንበር ቢቀመጥም፣ መንፈስ ቅዱስ ከሲኖዶስና ከቤተ ክርስቲያን ሥፍራ ካጣ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ የማናውቃቸውን ብዙ “ቅዱሳትና ቅዱሳን” እንድንቀበል አድርጋ በስማቸው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ስታስገነባላቸው ለመንፈስ ቅዱስ ግን ሥፍራ አልተገኘለትም፤ በርግጥ በሚያምኑበት ልብ ውስጥ ያድራል እንጂ የሰው እጅ በሚሠራው ሕንፃ አይኖርም፡፡
ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ሥጋዊነትም፣ ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ቤት ገፍቶ ሲያስወጣው እንጂ ወደ ንጉሥ ክርስቶስ ቤት ሲመልሰው አልታየም፡፡ ያደጉባትን ቤተክርስቲያንንም፣ በዚህ ሥጋዊነትዋ ምክንያት “አይንሽን ለአፈር” እያሉ ጥለዋት የሚሄዱ ምእመናን ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ሥጋዊነትዋን ጥላ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራች ለብዙዎች ፈውስ ትሆን ዘንድ ተሐድሶ ያስፈልጋታልና “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ” እንላለን ፡፡


•    አስተዳደራዊ ብልሽቷ አገልጋዮቿንና ሕዝቧን ስላስጨነቀ


ስለ ኦርቶዶክሳዊቷ ቤተ ክርስቲያናችን ሲነሣ፣ አብሮ ሳይነሣ የማይታለፍ ነገር አስተዳደራዊ ብልሽቷ ነው፡፡ ይህ ርእስ፣ ቤተ ክርስቲያናችን በመንፈስ ቅዱስና በእግዚአብሔር ቃል የተመሠረተ ሁለንተናዊ ተሐድሶ አግኝታ ወደ ጥንተ ቅድስናዋና ክብሯ መመለስ ይገባታል የምንለውን እኛን እና ቤተ ክርስቲያን ከቶውንም ለውጥ አያስፈልጋትም “ስንዱ እመቤት ናት” የሚሉትን ወገኖች ያስማማናል፡፡ አስተዳደራዊ ብልሽቱን ሰዎች የሚያነሡበት መንገድ ይለያይ እንጂ  “የቤተ ክርስቲያኗ ህልውና ያሳስበኛል” የሚል ወገን ሁሉ ያለ ልዩነት የሚያነሣው ርእስ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያንዋ ከተቋማዊ እንቅስቃሴ ይልቅ የግለሰቦች ጠንካራ እና ደካማ ጎን ተገዢ መሆኗ በርግጥ ያሳስባል፡፡ ባለፈው ዓመት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ካረፉ በኋላ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አካባቢ የነበረው የአሠራር ዝርክርክነት ከእሳቸው ጋር ጠቅላይ ቤተክህነቱም የሞተ አስመስሎት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ በሰው ላይ የተደገፈ አስተዳደራዊ ሥርዓት ፍጻሜው ይሄ ነው ለማለት፣ የብፁዕነታቸውን እንደ ምሣሌ አነሣን እንጂ፣ ከእሳቸው በፊት የነበሩትም አሁንም ያሉት ፓትርያርኮች አሠራር ተመሳሳይ ነው፡፡ በዙርያቸው የሚሰበሰቡ ሰዎችም እነርሱ የሚፈልጉት እስከተሳካ ድረስ ለሌላ ነገር ግድ የሚላቸው አይደሉም፡፡
የደብር አስተደደር ሹመት እንኳ በጥንት ዘመን ከነበረው አውቀት ተኮር ሹመት፣ አሁን ወደ ዝምድና እና ጉቦ ተኮር ወደ መሆን ተሸጋግሯል፡፡ እንዲህ ያለው ሹመት፣ አንድን የደብር አስተዳዳሪ፣ በደብሩ ውስጥ ከሚገኙት በእውቀት ሻል ካሉ አገልጋዮች ይቅርና ከአንድ ዲያቆን ጋር እንኳ የሚስተካከል  ክብር ስለማያሰጠው መናናቁና ጥላቸው፣ ቡድናዊነቱና ወገንተኝነቱ ሥር የሰደደ ነው፡፡ በእውነትና በእውቀት ማስተዳደር ስላልተቻለ፣ ሊቃውንቱ ተገፍተው ጨዋና ወሬ አመላላሹ ተከብሮ እና ተፈርቶ ይገኛል፡፡  የሥራ ድርሻውን የሚያውቅና ሥራውን በአግባቡ የሚሠራ ሰውም ስለጠፋ ምእመኑ የክርስትና ካርድ እንኳ ለማውጣት ጉቦ እየተጠየቀ ይገኛል፡፡ የአገልጋዮች ቅጥር፣ ዝውውር እና የደመወዝ ጭማሪን በተመለከተ ወጥ የሆነ ሕግ ስለሌለ በአስተዳዳሪው እና በሀገረ ስብከት ሹመኞች ይሁንታና ተጠቃሚነት፣ ነገሮች እንደፈለጉ የሚደረጉበት ደብር እጅግ ብዙ ነው፡፡ በብዙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ መሪጌቶች ከዲያቆን ያነሰ ደመወዝ ስለሚከፈላቸው፣ ተስፋ የሚቆርጡበት ሁኔታ የተለመደ ነው፡፡ ከተማ አቀፍ የደመወዝ አከፋፈል እስኬል ስለሌለ የተሻለ ደመወዝ የሚከፍል ደብር ለመቀጠር እና ለመዘዋወር ያለው ሹክቻና የሚጠየቀው መደለያ ገንዘብ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ የአስተዳደር ችግር ውጤት ነው፡፡
በአስተዳደር ችግር ውስጥ እንደገና ሊታይ የሚገባው ቤተ ክርስቲያንዋ የፋይናንስ አያያዝ ነው፡፡ ከገንዘብ አሰባሰቡ ጀምሮ በዐፄ ምኒልክ ጊዜ ከነበረው የገንዘብ አስተዳደር የተሻለ ነገር ምንም  የላትም፡፡ በገንዘብ አቆጣጠር ላይ ያለውን አካሄድ ስንመለከተው፣ ለአታላይ በጣም የተመቸ ነው፡፡ ምንም ዐይነት ዘመናዊ የሂሳብ አያያዝ መንገድ የማይታይበት፣ ዘመናዊውን የሂሳብ አያያዝ ዘዴ የተማረ ሰው የማይቀጠርበት፣ የደመ ነፍስ መድረክ ሆናለች፡፡ ሌላው የሂሳብ አያያዙ ከፍተኛው ድክመቷ፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነት ተረስቶ  “ወነአምን በአሀቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን” የሚለው የአባቶች ትምህርት ተዘንገቶ፣ ደብሮች  እንደ ፌደራል መንግሥት፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚፈለግባቸውን ብር ከሰጡ በኋላ፣  ገንዘቡን በገዛ ፈቃዳቸው የፈለጉትን ማድረግ የሚችሉበት መሆኑ ነው፡፡ ገጠር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በደመወዝና በንዋየ ቅዱሳት እጦት እየተዘጉ በአዲስ አበባ ግን ሰባ እና ሰማንያ ሚሊየን ብር በዝግ አካውንት የሚያስቀምጡ ደብሮች መኖራቸው የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡
ቤተ ክርስቲያን አንድ እንደሆነች ከንግግር ባለፈ በቃሉ የሚታመን ከሆነ፣ የኑሮ ድካም ትከሻቸውን አጉቡጧቸው ወደ ከተማ የሚሰደዱትን የገጠር አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችን ለመታደግና ባሉበት ቦታ በቂ ገንዘብ ከፍሎ ለማኖር ይቻል ነበር፡፡ ምእመኑ ከቤተ ክርስቲያን የሚፈልገውን አገልግሎት ለማግኘት ሲመጣ ቀድሞ የሚታየው ኪሱ እንጂ ልቡ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የድሆች መጠጊያ መሆንዋ ከቀረ ሰንብቷል፡፡ እንደ መንግሥት ቢሮ  ገንዘብ ያለው ከፍሎ የሚስተናገድባት የሌለው ተገፍቶ የሚወጣባት ቤት መሆንዋ ለብዙዎች የልብ ስብራት ምንጭ አድርጓታል፡፡
እንደዚህም በእጅጉ የሚያሳዝነው የአስተዳደር ብልሹነት መገለጫ በገጠር ያሉ እና ሊዘጉ የተቃረቡ አብያተ ክርስቲያናትን ለሀገረ ስብከት የተመደበባችሁን ብር አልላካችሁም በመባል የሚደርስባቸው ማስፈራራት እና “ቤተክርስቲያኑን እንዘጋዋለን” ቁጣ ነው፡፡ ለእነዚህ የገጠር ካህናት፣ በነጻ የሚያገለግሏት ቤተ ክርስቲያን የበላይ ኃላፊዎች የአባትነት ፍቅርና ምስጋና ማቅረብ ቢያቅታቸው እንኳ የኑሯቸውን ሁኔታ እያወቁ ማስጨነቅ ባልተገባቸው ነበር፡፡ ዲታዎቹን የአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናትን፣ የእስፖንሰር ገንዘብ እየጠየቁ ለቅንጦት ነገሮች ከማዋል፣ በጭንቅ በሬ ሸጠው ዓመታዊ መዋጯቸውን እንዲከፍሉ የሚገደዱትን የገጠር አብያተ ክርስቲያናት አባቶች መታደግ ይገባ ነበር፡፡
ይህንን የአስተዳደር ብልሹነት በቤተክህነት ሥር የሰደደውን ሙስና ባለፈው ሰኔ 29/2005 ዓ. ም.  ቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት፣ የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ምረቃ ላይ መምህር ልዑል የተባሉ ሰው በዘይእሴ ቅኔ እንዲህ ሲሉ ገልጠውታል፡፡
ቤታችን ሆኗል ቤተ ወንበዴ፣ እጅግ ያሣዝናል በእውነት የሚፈጸመው ግፍ ተግባሩ፡፡
ሊቃነ ጳጳሳት ፍቀዱና፣  ቢ. ፒ. አር. ወፀረ- ሙስና ገብተው ይመርምሩ፡፡
ብዙዎች ስላሉ በግል መዝብረው የከበሩ፡፡
ዘረፉኝ እያለች በቀን ምንም ሳይፈሩ፡፡
ሙዳየ ምፅዋት ምስኪን ትጮኻለችና በበሩ
ዘረፉኝ እያለች በቀን ምንም ሳይፈሩ፡፡

እንዲህ ያለውን የውስጥ ብሶት በአደባባይ ሲቀርብ ሰምቶ ከማጨብጨብ እና ይበል ብለናል ከማለት ያለፈ የተደረገ ነገር የለም፡፡
ባለፉት ብዙ ወራት ሊፈታ ያልቻለውና ይልቁንም እየተባባሰ ያለው፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ጉዳይ ሌላው በቤተክርስቲያን የተንሰራፋውን አስተዳደራዊ ችግር አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ ተማሪዎች ችግር አለብን ሲሉ ሰምቶ የሚያስተናግድ እና ችግሩን የሚፈታ አባት አልተገኘም፡፡ በየአቅጣጫው ከእውነታ ይልቅ ለሁኔታ እና ለቀረቤታ የሚያደሉ አሠራሮች ቤተክርስቲያኗን ይጎዳል እንጂ አይጠቅምም፡፡ ደቀመዛሙርቱን በግፍ ለማባረርና አስተዳደራዊ ጥያቄያቸውን ላለመመለስ፣ ፖለቲካዊ መልክ እንዳለው በማስመሰል ከመንግሥት ጋር ለማጋጨት በመሪዎች እየተወሰደ ያለው ርምጃ አስተዳደራዊ ብልሽቱን ከማጋለጡም በላይ ጉዳዩን በንቀት እየተመለከቱት መሆኑን ማሳያ ነው፡፡  
ሌላው የአስተዳደር ብልሹነቱ ገጽታ የሆነው በሐዋሳ፣ በክብረ መንግሥት፣ በዲላ፣ በሐረርና በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈጠሩት ችግሮች እና የምእመናን መንገላታት ነው፡፡  ለችግሮቹ “ይህ ነው” የሚባል መፍትሔ ሳይሰጠው አሁንም እንደ ቀጠለ መሆኑን ስናስብ በተለይ አሁንም ተስፋ ሳይቆርጥ፣ ሲኖዶሱን እየተማጠነ ላለው ሕዝብ በእጅጉ እናዝናለን፡፡ የዚህ ችግር ፈጣሪዎች ከሆኑት መካከል አንዳንዶቹም መንፈስ ቅዱስ ይመራዋል የሚባለው ሲኖዶስ አባላት የሆኑ ጳጳሳት መሆናቸውን ማሰብ ልብን ያደማል፡፡ የመፍትሔ አመንጪ መሆን የሚገባቸው አባቶች የችግሩ ፈጣሪዎችና አባባሾች መሆናቸው የሚያስገርም እውነት ነው፡፡
በቤተ ክርስቲያን ያለው የአስተዳደር በደል እና የሥራ ዝርክርክርነት ከመነገር በላይ ነው፡፡ አገልጋዩም ሆነ ሕዝቡ በቤተ ክርስቲያን ባለው አስተዳደራዊ በደል ተስፋ ቆርጦ እና አዝኖ ይገኛል፡፡ እንዲህ ያለው ችግር በቶሎ መስተካከል ካልቻለ እንደደነበረ በግ እየበረረ የሌሎችን በረት በመሙላት ላይ ያለውን የምእመናን ፍልሰት በእጅጉ ያባብሰዋል፡፡ ከዚህ እና ከሌች አስተዳደራዊ ችግሮች ለወውጣት ተሐድሶ አማራጭ የሌለው መንገድ ነውና ደግመን መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ ልንል እንወዳለን፡፡
ይቀጥላል! …