Monday, June 13, 2016

"ፓ" ይላል ምዕመኑ!!!



«በዘውድአለም ታደሰ»
ነብይ ነኝ ባዩ የቤተክርስቲያን ደላላ!

ይሄ ሰውዬ "ጎሳ" ይባላል። በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ቸርቾች ሲሰብክ አይቼዋለሁ። (ጎፋ መድሃኒአለም ፣ ዘፀአት ፣ FBI ፣ ወዘተ... ) የሚደክም አይነት ሰው አይደለም። ውሃ ሳይጎነጭ በተከታታይ ለሶስት ሰአታት የማውራት አቅም አለው! የምእመኑን ሳይኮ በልቶታል። ህዝቤን ምን እንደሚያስጮሀት ስለሚያውቅ አዳራሹን በጩኸት መናጥ ለነብይ ጎሣ ቀላል ነው!
ብዙ ግዜ ቸርቾች ይህን ሰውዬ ሚጋብዙት ገንዘብ ክፉኛ ሲያስፈልጋቸው ነው። ወይ መሬት ሊገዙ ሲያስቡ ... አሊያም የተሻለ አዳራሽ ሊከራዩ ሲፈልጉ ... ብቻ የሆነ የፈንድ ሬይዚንግ ጉዳይ ሲኖር ጎስሻን ይጠሩትና በዚያች ጮሌ ምላሱ የራሱንም ሆነ የሌሎች ሰዎችን ታሪክ እያጋነነ በመስበክ የዚህን ምስኪን ምእመን ኪስ ያራቁትላቸዋል!
«ነኝ ያልኩ ኮንትራክተር ነበርኩ፣ ነፍፍ መኪኖችና ብዙ ሰራተኞች ነበሩኝ፣ ጌታ ሲገባኝ ግን ንብረቶቼን ሸጬ ለቸርች ሰጠሁ» ብሎ ይጀምራል ተረት ተረቱን።
«ፓ» ይላል ምእመኑ!
«ከዛ ክፉኛ ተቸገርኩና፣ ምልስ ምቀምሰውን አጣሁ፣» ብሎ ለፅድቅ ሲል የከፈለውን መከራ እያጋነነ ያወራል!
«በከተማዋ ስሜ የተጠራ ኮንትራክተር እንዳልነበርኩ ምልስ ምቀምሰውን አጥቼ ተቸገርኩ» ሲል ረሃብን የሚያውቀው የዚህ ህዝብ አንጀት በሀዘኔታ ይላወሳል።
የሰዉን አቴንሽን ማግኘቱን ሲያረጋግጥ ታዲያ ... እንዴት ተአምራዊ በሆነ ሁኔታ እግዜር ሀብታም እንዳደረገው፣ እንዴት እንዳበለፀገው ትረካ በሚመስል ሁኔታ ያወራ ያወራና የህዝቡን አእምሮና ስሜት በሚገባ እንደተቆጣጠረ ሲረዳ እንዲህ ይላል ..
«ጌታ እንዲህ ሲል ተናግሮኛል» ብሎ ይጀምራል ነብይ ጎሳ። (ማን ነብይ እንዳረገው እንጃለቱ)
«ጌታ ዛሬ በዚህ አዳራሽ ውስጥ ያላችሁትን ሁላችሁን እባርካለሁ ብሎኛል» ሲል እቺ በረከቷን ከአርያም ሳይሆን መድረክ ላይ ከቆመው አረም የምትጠብቅ ምእመን አዳራሹን በጩኸት ታቀልጠዋለች! በጭብጨባው የሚሟሟቀው ጎሲሻም «አንዳንዶቻችሁ ከዚህ አዳራሽ ስትወጡ ከበረከታችሁ ጋር ትገናኛላችሁ» ሲል አዳራሹ በአንድ ድምፅ «አሜን» ይላል።
«አንዳንዶቻችሁ ደግሞ ቤታችሁ ስትገቡ በረከታችሁ ቁጭ ብሎ ይጠብቃችኋል»
«አሜን»
«አንዳንዶቻችሁ ስራ ቦታችሁ ላይ»
«አሜን»
«አንዳንዶቻችሁ የዛሬ ሳምንት»
«አሜን»
«አንዳንዶቻችሁ የዛሬ ወር»
«አሜን»
«እግዜር በተራራው ላይ ሙሴን ሲያገኘው በእጅህ ላይ ምን አለ? ብሎ ነው የጠየቀው ወገኖቼ። እግዜር እጃችን ላይ ባለ ነገር ነው ሚሰራው። ዛሬ በእጃችሁ ላይ ምን አለ?» ይላል ብልጣብልጡ ጎሳ!
ይሄ የዋህ ሁን ሲባል ሞኝ የሆነ ህዝብም እውነት መስሎት እጅና ኪሱን ያያል! ከዛማ በቃ አዋራው ይጨሳል .... ፒፕሉ በረከቱን በስጦታው ለመግዛት ይጋፋል! አዳሜ ወርቋን ከአንገቷ ላይ እየበጠሰች፣ ገንዘቧን ከቦርሳዋ እያራቆተች፣ ምንም የሌላት ደግሞ የእጅ ስልኳን ሳይቀር መባ እቃ ውስጥ እየጨመረች የማይፈፀም ትንቢት ታቅፋ እርቃኗን ከአዳራሹ ትወጣለች ... ልትባረክ ነዋ ሃሃሃሃ
ከላይ እንዳልኩት ነብይ ጎሳ ነብይነቱን ከየት እንዳገኘው ማንም አያውቅም። የሚያወራው ታሪክም እውነት ስለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለም። ይህን ሰውዬ የሚጋብዙት ስግብግብ የቤተክርስቲያን አገልጋዮችም የሰውየው ምስክርነት እውነት የተፈፀመ ይሁን አይሁን ለማረጋገጥ ምንም አይነት ጥረት አያደርጉም! እነሱ ሚፈልጉት በሱ ጅንጀና የሚዘንበውን የገንዘብ ዶፍ ነው። የስብከቱ መለኪያ በሱ ስብከት አማካኝነት የገባው የገንዘብ መጠን ነው እንጂ የእግዚአብሔር ቃል አይደለም!
አሁን ቤተክርስቲያን በጎሳና ጎሳን በሚመስሉ መንፈሳዊ ደላሎች እየታመሰች የምትገኝበት ሰአት ላይ ትገኛለች። መፅሀፉ ጎሳንና መሰል አገልጋዮችን «ለመንጋው የማይራሩ» ይላቸዋል!
እንዲጠብቁት የተሰጣቸውን ምእመንና እረኛ የሆኑለትን መንጋ ስጋ እየበሉ ሰብተው ቆዳውን ገፍፈው ይለብሳሉ! በአስራትና በበኩራት፣ በመባና በፍቅር ስጦታ ስም፣ ገንዘቡ ወደካዝናቸው ይጋዝ እንጂ የገንዘቡ አመጣጥ እነሱን አያስጨንቃቸውም። በምእመኑ ፍራንክ ትልልቅ እቅዶች ያቅዳሉ፣ የህዝቡን መሶብ አራቁተው ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን ይገነባሉ፣ በሊትር ሶስት ኪሎሜትር የሚሄዱ ላግዥሪ መኪኖችን ይነዳሉ። ይሄ ተስፈኛ ምእመን ግን ከሰማይ መና እየጠበቀ በደረቅ ምድረ በዳ ደረቅ ትንቢታቸው ታቅፎ ከቃዴስ ቃዴስ ሲንከራተት ይኖራል።
በአብዛኞቹ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያኖች ዘንድ ምድር ምድር የሚሸት ስብከት በዝቷል። ሰባኪው ሁሉ የ prosperity Gospel (የብልፅግና ወንጌል) አቀንቃኝ ሆኗል፣ ምእመኑም በረከቱን የሚለካው በምድራዊና ቁሳዊ ሀብት ብቻ ነው! «ሀገሬ በሰማይ ነው» አይነት ንግግሮች ከምእመኑ አንደበት መደመጥ አቁመዋል። ኢየሱስ የሞተው ለቼቭሮሌት መኪናና ለግራውንድ ፕላስ ስሪ ፎቅ ይመስል ወሬው ሁሉ ቤት ስለመስራትና ቤት ስለማፍረስ ሆኗል ... እንደ ዊነርስ ቻፕል አይነት ቸርቾችማ ወሬው ሁሉ ሱሪ ስለመቀየርና መኪና ስለመንዳት ከሆነ ቆየ። «በመንፈስ መኪና የመንዳት» ፕሮግራም ሁሉ ያካሂዳሉ አሉ! ሃሃሃ
ነብያቶች በዝተዋል። ነብይነት ግን ከሞተ ቆየ! ሰባኪዎችም አሸን ናቸው። ስብከት ግን ስልሳዎቹ ላይ ቆሟል! በየመድረኩ ተኳኩለው እንጣጥ እንጣጥ የሚሉ (ባለብዙ ሚስት ዘማሪዎች እልፍ ናቸው) መንፈሳዊ ማንነትን የሚያንፅ መዝሙር ግን ከመድረኩ ነጥፏል!
በፅድቅና በቅድስና የሚያገለግሉ አንዳንድ አገልጋዮች እንዳሉ አይጠፋኝም። ግን እነዚህ አገልጋዮች ከጎሳውያኑ ጋር ሲተያዩ በገምቦ ውስጥ እንዳሉ ጥቂት ጠብታዎች ናቸው! ስለዚህ ባህር ውስጥ እንዳሉ አይቆጠሩም። እኔ ማወራው ባህሩን ስለሞሉት የተበከሉ አሳዎች ነው!
 ቸርቾች በየመቶ ሜትሩ ከተማ ውስጥ ፈልተዋል። ደቀመዝሙር ማፍራት የማይችሉ ውሀ አልባ ምንጮች ናቸው እንጂ! ክርስቲያን ያልሆኑ የክርስቶስ ሰባኪዎችና ክርስቶስን የማያውቁ አገልጋዮች ይሄን ምስኪን ምእመን እንደአሻንጉሊት እየተጫወቱበት ነው! አገልግሎታቸው ያከበራቸውን ህዝብ በመናቅና በማስፈራራት ላይ የተመሰረተ ነው! «ለምን?» ብሎ ጥያቄ የሚያነሳ ሲመጣ «ጌታ በቀባው ላይ እጅህን አታንሳ» በማለት በጥቅስ ያስፈራሩታል። በፅድቅ ለማገልገል ከላይ እታች እያሉ የጅብ ድግሳቸው ላይ የማይሳተፉትን ንፁሀን ደግሞ የተለያየ ስም ጀርባቸው ላይ በመለጠፍ ከአገልግሎት ያግዷቸውና የሚከተላቸውን ምእመን ኑሮ እየቀሙ ይኖራሉ! ሳቁን መንትፈው ይስቃሉ! ደስታውን አራቁተው ይደሰታሉ! እውነትም ለመንጋው የማይራሩ ሆዳሞች!
ዘመኑ የባቢሎናውያኑን ዘመን ይመስላል። ትርምስ እንጂ መረጋጋት የለም! ጩኸት እንጂ መግባባት ጠፍቷል። ግራ የተጋቡ ባለራእዮችና ያልተማሩ አስተማሪዎች መሬት ባልረገጠ የትምህርት ወጀብ ህዝቡን እየናጡት ነው። በተቀየጠ ዶክትሪንና በስህተት አስተምህሮ ምእመኑን ከወንጌል አርቀው አይኑን በማሰር ወደቁልቁለት እየነዱት ነው! ነብያት ነን ባዮቹ ወንዝ በማያሻግር ትንቢት ሲወራጩ መድረኮቻችን ላይ ውለው ያድራሉ። ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች በተራ ፉከራና ሽለላ የተሞሉ ፍሬ አልባ ደረቅ መሬቶች ናቸው!
በተለያዩ ቤተክርስቲያኖች እየተጋበዘ ህዝቡን የሚያራቁተው ደላላው ነብይ .... «ነብይ ጎሳም» ከላይ ለጠቀስኳቸው ሆዳም አገልጋዮች እውነተኛ ምልክት ሊሆን ይችላል ባይ ነኝ!

እቀጥላለሁ!‎

Saturday, June 4, 2016

ማኅበረ ቅዱሳን አሁን የቤተ ክርስቲያን፤ ቆይቶ የመንግሥት መጥበሻ ምድጃ ነው!


በታሪክ አጋጣሚ የደርግን መውደቅና ግርግርን ተተግኖ የተፈጠረው ማኅበረ ቅዱሳን የመጥበሻ ምድጃ ከሆነ እነሆ 23 ዓመታት አለፉት። ብዙዎችን በትኗን፤ አሳዷል። ዳግም እንዳይመለሱ በማድረግ እንደተዋጊ በሬ እየበጠበጠ ከበረት አስወጥቷል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አፋፍተው ያሳደጉትን አቡነ ጳውሎስን ሳይቀር በአድማ የመጥበሻ እሳት እየለበለበ እስከመቃብር ሸኝቷል። የአሁኑን ፓትርያርክ የአቡነ ማትያስን ወንበር በተሾሙ ሰሞን ለመረከብ ተፍ ተፍ ብሎ ሳይሳካለት ቢቀር በተለመደ የመጥበሻ ምድጃው ላይ አስቀምጦ ላለፉት 3 ዓመታት  በአድማው ግሪል / GRILL/ እየጠበሰ ይገኛል።

ፓትርያርክ ማትያስ ብቻቸውን ሆነው ይህንን መጥበሻ ምድጃ ሊያስወግዱ ብዙ ታግለዋል። ነውራም ጳጳሳቱ እዳ በደላቸው በዚህ ማኅበር የኃጢአት መዝገብ ላይ ስለሰፈረ ከፓትርያርኩ በተጻራሪ ቆመው ውግንናቸው ለማኅበሩ ሆኖ ታይቷል። የማኅበሩ ሥፍራ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የት ነው? በሚለው ነጥብ ላይ ጥያቄ ያላቸው ፓትርያርክ ማትያስ ድርሻውን፤ አቅሙንና ተጠሪነቱን የሚወስን አዲስ መተዳደሪያ ደንብ እንዲወጣለት ያደረጉት ተጋድሎ ላይ ውሃ በመቸለስ የሲኖዶስ ጉባዔ በመጣ ቁጥር የሚያጨቃጭቅ አጀንዳ እያስገባ ሲሾልክ ቆይቷል። ዘንድሮም ይህን የቤት ሥራ ሰጥቶ በአንድ አጀንዳ ላይ ለ4 ቀናት ካጨቃጨቀ በኋላ የሲኖዶስ አባል የሆነው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር መፍትሄ አስምጦ ሊገላግላቸው ችሏል። ይህ ሁሉ የሆነው በማኅበሩና በጉዳይ ፈጻሚ ጳጳሳቱ የተነሳ ነው።

የእንደራሴ መኖር አለመኖር ለማኅበረ ቅዱሳን አሳሳቢው አይደለም። ነገር ግን በዘንድሮው ጉባዔ ላይ ማንሳት ያስፈለገው የራሱ ስሌት ስላለው እንጂ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ድክመት ከሱ መኖር በላይ አስቸጋሪ ፍጡር ስለመጣ አይደለም። በዚህም የተነሳ በአቅም ማነስ ሰበብ ፓትርያርኩን አሸመድምዶ በማስቀመጥ ለ3 ዓመታት ያህል እሳት ካነደዱበት ሥጋት ነጻ ለመውጣት የተያዘ መላ ከመሆን አይዘልም። ከዚህም በፊት እንዳልነው ጳጳሳቱ በሀገረ ስብከታቸው መሥራት ያልቻሉትን የመንፈሳዊና ሥጋዊ የልማት ሥራዎች  እንደራሴው እየዞረ የሚሰራላቸው አለመሆኑንም በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ማኅበረ ቅዱሳን እስካለ ድረስ ታዛዥ ያልሆነ የትኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለሥልጣን  ማኅበሩ ባዘጋጀው መጥበሻ ላይ ይጣዳል። ምርጫቸው ከማኅበሩ ጋር መቆም አለያም በተጻራሪ ሆነው ለመጥበሻው ራሳቸውን ከማዘጋጀት የግድ ነው። አባ ሳዊሮስ ከአዲስ አበባ ማኅበረ ካህናት ጋር ቆመው ማኅበሩን ሲያጋልጡ ምድጃውን አዘጋጅቶ መጥበስ ሲጀምር እጃቸውን አንስተው ለማኅበሩ ለማስረከብ መገደዳቸውን አይተናል። አባ ፋኑኤል ማኅበሩ የሌለበት ቦታ የት ሄጄ ልሥራ? እንዳላሉ ሁሉ ምርኮኝነታቸውን ካረጋገጡ በኋላ ግን ከማኅበሩ መጥበሻ ግሪል ላይ ወርደው እረፍት ሊያገኙ ችለዋል። ሌሎቹ ግን የሚደርስባቸውን እሳት አስቀድመው ስለሚያውቁ ቃላቸውን አክብረው የጫናቸውን በማራገፍ ግንቦትና ጥቅምት በመጣ ቁጥር በማኅበሩ አጀንዳ አስፈጻሚነታቸው ቀጥለዋል።

 ማኅበረ ቅዱሳን በስመ ተሐድሶና ሙሰኛ ነጠላ ዜማው የፈጃቸውና ያቃጠላቸው ካህናት ቁጥራቸው ብዙ ነው። ስለቅድስናና መንፈሳዊ ንጽህና በዋለበት ያልዋለ የዋልጌዎች ስብስብ ይህ ማኅበር ስም እያጠፋ ያሳደዳቸው፤ ስለኃጢአታቸው ንስሐ የሚገቡበትን በር እየዘጋ ተስፋ በማስቆረጥ ያስወጣቸው የትየለሌ ናቸው። የሚገርመው ግን ነውራም ጳጳሳቱን በቅድስና ካባ ሸፍኖ ለአገልግሎቱ የሚጠቀምባቸው የከባቴ አበሳ ተፈጥሮ ስላለው ሳይሆን እስካለገለገሉት ድረስ ብቻ ነው። እያንዳንዱ የማኅበሩ አባል በተለይም አመራሩ እነአቡነ እገሌ እስከምን ድረስ የጉስቁልና ባሕር ውስጥ እንደሰጠሙ እያወቀ በስምምነት አብሮ ይሰራል። ነገር ግን ከማኅበሩ አቋም ካፈነገጡ ከዚህ በፊት እንዳደረገው የእዳ ደብዳቤአቸውን ከማንበብ አይመለስም። ይህ በተግባር የተረጋገጠ እውነት ነው።

አንዳንዶች ማኅበሩን የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ብቻ አድርገው ያያሉ። ነገር ግን ማኅበሩ  እንደግብጹ የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር በፖለቲካው መድረክም የረቀቀ ተልእኮ ያለው ማኅበር ነው። በአባልነት ያቀፋቸው ሚኒስትሮች፤ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች፤ ሥራ አስኪያጆች፤ ፖሊሶች፤ ዳኞች፤ የሕዝብ አገልግሎት ሠራተኞች፤ መምህራንና ተማሪዎች፤ የሙያ ማኅበራት፤ በ44 አኅጉረ ስብከት ውስጥ ያሉ ሚሊዮኖች የሰንበት ት/ቤት አባላት፤ የጥምቀት ተመላሽ ተጠባባቂ ጦር የመሳሰሉትን በአባልነት እየመለመለ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የራሱን ዶክትሪን በመጋት ማኅበረ ቅዱሳን፤ ማኅበረ ቅዱሳን ካሰኛቸው ውሎ አድሯል። ዛሬ ከሲኖዶስ ወይም ከፓትርያርኩ በላይ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተቆርቋሪና ጠባቂ ከማኅበሩ በላይ የለም የሚለው አስተሳሰብ በእያንዳንዱ ሰው አእምሮ ውስጥ እንዲሰርጽ በሰፊው ተሰርቷል። ዘመናዊ የክርስቲያን ብራዘር ሁድ ማለት ማኅበረ ቅዱሳን ነው።

ሌላው የማኅበሩ ተንኮል አሁን ካሉት ታማኝና ታዛዥ ጳጳሳት በተጨማሪ ከእንግዲህ የሚሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት በራሱ መስፈርት የተመለመሉና ወደፊት ችግር እንደማይፈጥሩ የተረጋገጠላቸው ብቻ እንዲሆኑ ይፈልጋል። እነዚህ የማኅበሩ እጩ ኤጲስቆጶሳት ያለፈ ታሪካቸው የቱንም ቢመስል አሳሳቢ አይደለም። ተቀባይነታቸው አርአያነት ባለው ሁኔታ ቢሆንም፤ ባይሆንም ለማኅበሩ አስጊ እስካልሆኑ ድረስ እንዲመረጡ አጥብቆ ይሰራል። ነገር ግን በተቃራኒ ማኅበሩን የሚፋለሙ ከሆነ እንደአባ ሠረቀብርሃን ወ/ሳሙኤልን የመሳሰሉት በልዩ ልዩ ስምና ወንጀል በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ እጃቸውን ካልሰጡ በስተቀር ለእጩነት ሊቀርቡ አይችሉም።

በአጠቃላይ ማኅበሩ በታሪክ አጋጣሚ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተገኘ መጥበሻ ምድጃ ነው። በዚህ ምድጃ ዲያቆናት፤ ቀሳውስት፤ መነኮሳት ተጠብሰዋል። ሰባኪያነ ወንጌልና አስተዳዳሪዎች ተጠብሰዋል። ጳጳሳትና ፓትርያርኮች ተጠብሰዋል። እውነቱን እያወቁ ከመናገር ብዙዎች የተቆጠቡት ማኅበሩ መጥበሻው ላይ ከጣዳቸው የሚያወርዳቸው ስለሌለ ነው። ልክ እንደ መንግሥታዊ የስለላ መዋቅር የማኅበሩን ስም በተቃውሞ በአውቶቡስ፤ በታክሲ፤ በሬስቶራንት፤ በየካፌውና በሕዝብ መሰብሰበቢያ ቦታዎች መጥራት ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። መንግሥት ላይ ምን ዓይነት የአንኮበር መድኃኒት እንደተረጨበት ባናውቅም እሱም በፍርሃት ይሁን በድንዛዜ ፈዞ ቀርቷል።  እውነታው ግን ማኅበሩ ለየትኛውም ወገን መጥበሻ ምድጃ መሆኑ በተግባር የተረጋገጠ ነው።

Wednesday, June 1, 2016

«ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡት፤ ውሃ ቢያንቅ በምን ይውጡት?




አበው ዘይቤያዊ ምሳሌ ሲሰጡ፤ ፍሬ ነገሩን  ሊገልጥ የሚችል ጥሩ ኃይለ ቃል ይጠቀማሉ። በአንድ ዐረፍተ ነገር ብዙ ሐተታ ሊወጣው በሚችል መልኩ የጉዳዩን ብስለትና ጠጣርነት በደንብ ያሳዩበታል። ለዚህም ነው «ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡት፤ ውሃ ቢያንቅ በምን ይውጡት?» በማለት መሆን የማይገባው ነገር ሆኖ ቢገኝ መፍትሄው ግራ የሚያጋባ እንደሆነ ለማስረዳት ይፈለጉት። አዎ፤ በዘመነ አበው ምላጭ፤  እባጭ እንዲፈነዳ፤ የተቋጠረው መግል እንዲፈርጥ ይበጡበት ነበር። በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ዛሬም አልፎ፤ አልፎ ይሰራበታል።  ነገር ግን ምላጭ ራሱ ቢያብጥ በምን ይቆረጣል? ውሃስ ቢያንቅ በምን ማወራረድ ይቻላል? ግራ የሚያገባ ነገር ነው። መሆን የሌለበት ሆኖ ሲገኝ ያስገርማል፤ ያስደነግጣል፤ መፍትሄውም ሩቅ ይሆናል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታየ ያለው ድርጊት የዚሁ ምሳሌ ተመሳሳይ ነገር ነው። በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ የቅዱስ ሲኖዶስ መንበር ከተመሠረተ ከ50 ዓመታት እጅግም ያልዘለለ ጊዜን ያስቆጠረ ቢሆንም በዚህ አጭር እድሜው 50 ጉድ አሳልፏል። ፓትርያርኳን አሳልፋ በመስጠት ለደርግ ጭዳ ማቅረቧም በማስረጃ የተረጋገጠ እውነት ነው። ፓትርያርክ አውርዳ ፓትርያርክ ሾማለች። ለሁለት የተከፈለ ሲኖዶስም የያዘችው በዚሁ አጭር እድሜዋ ነው። የሐዋርያትን መንበር ተረክቤአለሁ የምትለዋ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያት እንዳደረጉትና የራሱን ሥፍራ በለቀቀው በይሁዳ ምትክ እንደሾመችው ሐዋርያ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ እጣ ማጣጣል ሲገባት እንደፖለቲካ የካድሬ ምርጫ በሰውኛ አሳብና እንደተሰጣቸው ተልእኮ በሚመለመሉ ሰዎች ምርጫ መሾሟም የዚሁ የአጭር ዘመን ታሪኳ አንዱ ክፍል ነው። 

ነውርና ነቀፋ የሌለበት፤ ራሱንና ቤተሰቡን በአግባቡ ስለመምራቱ በምእመናንና ምእመናት የተመሰከረለት አገልጋይ ሰው ኤጲስ ቆጶስ እንዲሾም ቃለ ወንጌሉ ቢናገርም ከንባብና ከአንድምታው በዘለለ ተግባር ዳገቷ ቤተ ክርስቲያን ሆና ለሰሚ የሚቀፍ፤ ለሚያውቁት የሚያሳፍር ሹመት እየፈጸመች በመገኘቷ እነሆ ጥቅምትና ግንቦት በመጣ ቁጥር የዘራችውን እያጨደች ትገኛለች።
   «መልካም ዘር መልካም ፍሬ ያፈራል» እንዲል ወንጌል የዚህ ተቃራኒ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ስለመዘራቱ ደግሞ ፍሬውን ሲኖዶስ በመጣ ቁጥር ጭቅጭቅ፤ ንትርክ፤ ሁከትና አድማ ሲያስተናግድ ማየት የተለመደ ሆኗል። ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ለትውልድ የፈውስና የምሕረት መልእክተኛ መሆን የሚገባው አካል ለራሱ ከፈውስም ሆነ ከምሕረት ስለራቀ መሆን በማይገባው ሁኔታ ውስጥ ይገኛል። 

«ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡታል፤ ውሃስ ቢያንቅ በምን ይውጡታል?» ማለት ይኼ ነው። ሰው በልቡ መታደስ ካልተለወጠና የማይሞተውን የሞት አሸናፊ ካልለበሰ አዲስ ፍጥረት እንደማይሆን ሐዋርያው በመልእክቱ ነግሮናል።  ካልተለወጠና የቀድሞ ግብሩን ካልተወ አሮጌነት ደግሞ አብሮት ያለው ማንነት በክፋትና በተንኮል ተግባር እየተገለጠ በዘመኑ ሁሉ ይቀጥላል። ዛሬም በሲኖዶስ ጉባዔ ላይ የሚታየው ችግር ሁሉ የውስጥ ማንነቱ ማሳያ መስታወት ነው። ሰው የሌለውን ውበት ከየትም ሊበደር አይችልም።
ሰሞኑን እየተካሄደ ባለው ሲኖዶስ (ቅዱስ ለማለት ይከብደኛል) ምክንያቱም ካልተወሻሸንና ሞራል እንጠብቅ ካልተባለ በስተቀር መንፈስ ቅዱስ የሁከትና የንትርክ አምላክ ስላይደለ ቅዱስ ለማለት ይከብዳል። በስብሰባው ላይ እየታየ ያለው ኢ-መንፈሳዊና ኢ-ሥነምግባራዊ ድርጊት ከስምና ከማዕርግ እድገት በስተቀር ያልተለወጠ ማንነት የተንጸባረቀበት እጅግ አሳፋሪና አሳዛኝ ክስተት የታየበት ስለሆነ ነው። 

 «ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን?» 1ኛ ቆሮ 6፤1-2

በቅዱስ ስም ተሰብስቦ፤ በዓለማውያን ምናልባትም እግዚአብሔርን በማያውቁ ዐመጸኞች ፊት የጉባዔ ዳኝነት ከመጠየቅ ወዲያ ለሲኖዶስ ምን ሞት አለ? አሁን እውነት ሕይወት ያለው ሲኖዶስ የሚባል አካል አለ ማለት ነው? ይህ ሁሉ የሆነውና እየሆነ ያለው በሞተ አካል ውስጥ ያለው የሙት መንፈስ ፍሬውን እያፈራ በመገኘቱ የተነሳ ነው።  ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ፤

 «በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ» በማለት የተናገረው። የሐዋ 20፤28-30

መንጋው ተበትኗል፤ ለሚጠፋው በግ የሚራራ እረኛ የለም፤ ቤተመቅደሱ በርግብ ሻጮችና በለዋጮች ተሞልቷል፤ እርስ በእርሳቸው የሚነካከሱና የሚበላሉ ሆነዋል፤ ነገር ግን በሕይወት አለን ይላሉ። ለሥልጣን ሽሚያ፤ ለመፈንቅል፤ ለቡድን አሸናፊነት፤ ለማኅበር የበላይነት ይጋደላሉ።
 በየተመደቡበት ሀገረ ስብከት እንደነገሥታት የሚሰጣቸው ስግደት ሳይጎድል፤ እንደሰማያዊ ሹም ሆነው መታየታቸው ሳይጠፋ ምንም የሰሩትና ያለሙት በሌለበት ሁኔታ ዓይናቸው ሁል ጊዜ የሚያየው እዚያ ጣሪያ ላይ ነው። ጣሪያው ደካማ ይሁን ሰነፍ የሚያስቀምጠው አንድ ሰው ነው። ጣሪያው ላይ ሰው ሲቀመጥ ያልታገሉ ፈራህያን ዛሬ የሚያደቡት ምን ለማግኘት ነው? ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስበው? ተጨንቀው? በጭራሽ አይደለም።
 ጳጳሳቱ ሰው ከመቅጠርና ከማባረር ባለፈ ሚሊዮን ተከታዮቻቸውን አሰልፈው ትምህርት ቤት፤ ጤና ጣቢያ፤ የንጹህ መጠጥ ውሃ፤ የብሎኬት ማምረቻ፤ የእንጨት መሰንጠቂያ፤ የመስኖ ልማት፤ የልብስ ስፌት፤ የጧፍና ሻማ ማምረቻ፤ የአልባሳትና ቅርሳ ቅርስ ተቋም፤ የዶሮና የከብት እርባታ፤ የዳቦ መጋገሪያ፤ የካህናት ማሰልጠኛ፤ ኮሌጆች፤ ዩኒቨርሲቲዎች፤ የህጻናት ማሳደጊያ፤ የአረጋውያን መጦሪያ ለምን አያቋቁሙም? ለምን አይሰሩም? ማን ከለከላቸው?
ከ15 ሚሊዮን ያልበለጠ ተከታዮች ያሏት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት በረሃውን ገነት ያደረጉት፤ ምርትና ሃብታቸው የተትረፈረፈው እንደእኛ ጳጳሳት በፎጣ በመሸፋፈን ሳይሆን በአጭር ታጥቀው ከእስላም ሰይፈኞች ጋር በመታገልና ተግተው በመስራታቸውና በማሰራታቸው ነው። ከላይ ከተዘረዘሩት ውስጥ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ያልሰራችው የልማት ስራ የለም።  በጀት ተመድቦላቸው፤ ባለሙያ ተቀጥሮላቸው ሳይሆን መነኮሳቱን፤ ካህናቱን፤ ምእመናኑን በማስተማርና በማሰልጠን በራስ አገዝ የልማት ተሳትፎ የተመሰረተ ነው።
 የኛዎቹ ለግንቦቱ ጉባዔ ከጥቅምት ጀምሮ ከመዶለትና ለጥቅምቱ ጉባዔ ደግሞ ከግንቦት ጀምሮ ሴራ ከመጎንጎን በስተቀር በሀገረ ስብከታቸው የልማት ርእይ፤ እቅድና ግብ በጭራሽ የላቸውም። ከሐውልት ምርቃት፤ ከቀብር ክፍያ፤ ከክርስትና፤ ከጋብቻ፤ ከፍትሃት፤ ከጸበል፤ ከሰበካ ጉባዔ አባልነት ወዘተ የሚሰበስቡትን ሚሊዮኖች ብር ለደመወዝና ለስራ ማስኬጂያ ከማዋል ባለፈ ተመልሶ ለሕዝቡ ልማት የዋለው ምን ያህሉ ነው? በደቡብ ክልል አካባቢ ያሉ የኦርቶዶክስ ምእመናን «እናንተ አምጡ እንጂ እንደሌሎቹ እንኩ አታውቁም» ማለታቸውን ስንሰማ የኛዎቹ መስጠትን ሳይማሩ አምጡን ከየት ለመዱት ያሰኛል።

    በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውድቀትና ማሽቆልቆል ተጠያቂዎቹ ጳጳሳቱ ናቸው። ለመንጋው መበተን፤ ለስርቆትና ሥነ ምግባር ጉድለት ኃላፊነቱን መውሰድ አለባቸው። የታጣው መሪ እንጂ  ለመመራት ፈቃደኛ፤ ለመስጠት እጁን የማይዘረጋ  ምእመን የለም። ደግሞስ እንደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመን እጁን የሚዘረጋ አለ እንዴ?
 በሀገረ ስብከታቸው ልማት ሳያሳዩ ወደላይ መንጠራራት ስንፍናቸውን እንጂ አዋቂነታቸውን አያመለክትም። ጳጳሳቱ ለድክመታቸው ምክንያት ፓትርያርኩ ላይ አመልካች ጣታቸውን ከመቀሰራቸው በፊት እኔ በሀገረ ስብከቴ ምን ሰራሁ? ብለው ራሳቸውን ይጠይቁ። ብዙዎቹን ጳጳሳት ከምንኩስና ጀምሮ ስለምናውቃቸው ስለማንነታቸው ነጋሪ አያሻንም። ከታች ጀምሮ ያልተገነባ ስብእናና ችሎታ ደረጃቸው ስላደገ ባንዴ አብሮ አይመነደግም። ቁም ነገሩ እንደእኛው ችሎታ የሚያጥራቸው ሰዎች መሆናቸው ሲሆን አሁን አለቃቸውን ማስቸገር ቀደም ሲል በአለቅነታቸው ካዳበሩት ችግር የተማሩት ብቸኛ እውቀት ይመስለኛል።  ከዚያ ባሻገር በልማታቸው ለሕዝቡ የመኖር ተስፋ ወይም በጸሎታቸው ለሀገር የሚተርፉ ሆነው 15 ሚሊዮን ሕዝባችንን ከድርቅ ሲታደጉ አላየንም። ከመንጋ ጳጳስ እንዴት አንድ ኤልያስ ይጥፋ? ተግባር እንጂ ስም አላልኩም።

በግንቦቱ ሲኖዶስ ተሰብስበው በፓትርያርክ ማትያስ የችሎታ ማነስ ላይ ከመሳለቅ አስቀድመው በራሳቸው የአቅም ማነስ ላይ ቢወያዩ የተሻለ ነበር። ምሳሌ እንስጥ፤  ከ1985 ዓ/ም ጀምሮ 23 ዓመት በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው የቆዩት የአሁኑ አባ ጎርጎርዮስ፤ ሟቹ አቡነ ጎርጎርዮስ ከመሰረቱት የዝዋይ ካህናት ማሰልጠኛና የአትክልት ልማት ወዲህ ስንት ማሰልጠኛ አቋቋሙ? ስንት የልማት አውታር ተከሉ? እውነታው ምንም ነው። አባ ቄርሎስስ በሰሜን ወሎ ሀ/ስብከት ስንት የካህናት ማሰልጠኛ፤ ስንትስ የእደ ጥበብ ተቋም ተከሉ? ስንት የከብት ማድለቢና የዶሮ እርባታ አቋቋሙ? ማን እንዳያደርጉ ከለከላቸው? ሟቹ አባ ጳውሎስ ወይስ ሕያው አባ ማትያስ?

 በምሥራቅ ጎጃምና በምዕራብ ጎጃምስ ምን ተሰራ፤ በሰሜንና ደቡብ ጎንደር ሀ/ስብከትስ ምን ልማት ተቋቋመ? በአጭር ጊዜና በረጅም ጊዜ እቅዳችሁ ምን አሳካችሁ?  በደን ልማት ላይ ሕዝቡን በማስተባበር በዚህ ዓመት ስንት ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ተዘጋጅታችኋል?
እርግጥ ነው ጳጳሳቱ በሌላ የሥራ መስክ ላይ አልቦዘኑም። የግል ቤታቸውን ገንብተዋል፤ ዘመናዊ መኪና አስገዝተዋል። በባንክ ገንዘባቸውን አጭቀዋል። ዘመድ አዝማዳቸውን በየቤተ ክርስቲያናቱ ቀጥረዋል።  
በአንድ ወቅት መንግሥቱ ኃ/ማርያም ሚኒስትሮቹን ሰብስቦ « የምትነዱትን የመኪና ዓይነትና ብዛት፤ ያላችሁን ቤት፤ የምትውሉበትን፤ የምታድሩበትን ቦታና ጭምር ይኽ ሕዝብ ብታምኑም ፤ ባታምኑም አሳምሮ ያውቃል» ብሏቸው ነበር።  ሕዝብ ምን የማያውቀው አለ? ተከድኖ ይብሰል ብለነው እንጂ የኛዎቹን ስንቱን ጉድ እናውቃለን።
 አሁን እነሱ ምን ስለሆኑ ነው፤ እንደራሴ ይሾም የሚሉት?  እንደራሴ ምን ያድርግላቸው? መፈንቅለ ፓትርያርክ መሆኑ ነው ወይስ እንደራሴው በየሀገረ ስብከታቸው እየሄደ ት/ቤት ሊሰራላቸው ነው? ጉዳዩ ፓትርያርኩን ወደጎን አስቀምጦ ለጳጳሳቱና ለማኅበረ ቅዱሳን ያደረ ሰው ለማስቀመጥ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው። እቅዱም የኃጢአታቸው ዐቃቤ ኃጢአት ከሆነው ከማኅበረ ቅዱሳን ሴራነት የዘለለ አይደለም።  የሚያሳዝነውና የሚያስገርመው ነገር የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር እንደራሴ ለመሾም ይችሉ ዘንድ እንዲያግዛቸው መለመናቸው ነው።
 የፖለቲካ ሰው ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ቅዱስ በሚባለው ጉባዔያችሁ ተቀምጦ ሲነገራችሁ ከመስማት ሞት ይሻላችሁ ነበር። ዳሩ ግን የሞታችሁት ቀድሞ ነውና ይኼ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ውርደት ለእናንተ ግን ክብር ነው። ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በጠሩት ጉባዔ ላይ አንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ የተናገረውን ጠቅሼ ልቋጭ። «ፖለቲከኛው እጣን፤ እጣን ሲሸት፤ የሃይማኖት አባት ፖለቲካ፤ ፖለቲካ ሲሸት አስቸጋሪ ነው» ማለቱን አስታውሳለሁ።
አዎ፤«ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡት፤ ውሃ ቢያንቅ በምን ይውጡት?» እንዲሉ።