Saturday, June 4, 2016

ማኅበረ ቅዱሳን አሁን የቤተ ክርስቲያን፤ ቆይቶ የመንግሥት መጥበሻ ምድጃ ነው!


በታሪክ አጋጣሚ የደርግን መውደቅና ግርግርን ተተግኖ የተፈጠረው ማኅበረ ቅዱሳን የመጥበሻ ምድጃ ከሆነ እነሆ 23 ዓመታት አለፉት። ብዙዎችን በትኗን፤ አሳዷል። ዳግም እንዳይመለሱ በማድረግ እንደተዋጊ በሬ እየበጠበጠ ከበረት አስወጥቷል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አፋፍተው ያሳደጉትን አቡነ ጳውሎስን ሳይቀር በአድማ የመጥበሻ እሳት እየለበለበ እስከመቃብር ሸኝቷል። የአሁኑን ፓትርያርክ የአቡነ ማትያስን ወንበር በተሾሙ ሰሞን ለመረከብ ተፍ ተፍ ብሎ ሳይሳካለት ቢቀር በተለመደ የመጥበሻ ምድጃው ላይ አስቀምጦ ላለፉት 3 ዓመታት  በአድማው ግሪል / GRILL/ እየጠበሰ ይገኛል።

ፓትርያርክ ማትያስ ብቻቸውን ሆነው ይህንን መጥበሻ ምድጃ ሊያስወግዱ ብዙ ታግለዋል። ነውራም ጳጳሳቱ እዳ በደላቸው በዚህ ማኅበር የኃጢአት መዝገብ ላይ ስለሰፈረ ከፓትርያርኩ በተጻራሪ ቆመው ውግንናቸው ለማኅበሩ ሆኖ ታይቷል። የማኅበሩ ሥፍራ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የት ነው? በሚለው ነጥብ ላይ ጥያቄ ያላቸው ፓትርያርክ ማትያስ ድርሻውን፤ አቅሙንና ተጠሪነቱን የሚወስን አዲስ መተዳደሪያ ደንብ እንዲወጣለት ያደረጉት ተጋድሎ ላይ ውሃ በመቸለስ የሲኖዶስ ጉባዔ በመጣ ቁጥር የሚያጨቃጭቅ አጀንዳ እያስገባ ሲሾልክ ቆይቷል። ዘንድሮም ይህን የቤት ሥራ ሰጥቶ በአንድ አጀንዳ ላይ ለ4 ቀናት ካጨቃጨቀ በኋላ የሲኖዶስ አባል የሆነው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር መፍትሄ አስምጦ ሊገላግላቸው ችሏል። ይህ ሁሉ የሆነው በማኅበሩና በጉዳይ ፈጻሚ ጳጳሳቱ የተነሳ ነው።

የእንደራሴ መኖር አለመኖር ለማኅበረ ቅዱሳን አሳሳቢው አይደለም። ነገር ግን በዘንድሮው ጉባዔ ላይ ማንሳት ያስፈለገው የራሱ ስሌት ስላለው እንጂ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ድክመት ከሱ መኖር በላይ አስቸጋሪ ፍጡር ስለመጣ አይደለም። በዚህም የተነሳ በአቅም ማነስ ሰበብ ፓትርያርኩን አሸመድምዶ በማስቀመጥ ለ3 ዓመታት ያህል እሳት ካነደዱበት ሥጋት ነጻ ለመውጣት የተያዘ መላ ከመሆን አይዘልም። ከዚህም በፊት እንዳልነው ጳጳሳቱ በሀገረ ስብከታቸው መሥራት ያልቻሉትን የመንፈሳዊና ሥጋዊ የልማት ሥራዎች  እንደራሴው እየዞረ የሚሰራላቸው አለመሆኑንም በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ማኅበረ ቅዱሳን እስካለ ድረስ ታዛዥ ያልሆነ የትኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለሥልጣን  ማኅበሩ ባዘጋጀው መጥበሻ ላይ ይጣዳል። ምርጫቸው ከማኅበሩ ጋር መቆም አለያም በተጻራሪ ሆነው ለመጥበሻው ራሳቸውን ከማዘጋጀት የግድ ነው። አባ ሳዊሮስ ከአዲስ አበባ ማኅበረ ካህናት ጋር ቆመው ማኅበሩን ሲያጋልጡ ምድጃውን አዘጋጅቶ መጥበስ ሲጀምር እጃቸውን አንስተው ለማኅበሩ ለማስረከብ መገደዳቸውን አይተናል። አባ ፋኑኤል ማኅበሩ የሌለበት ቦታ የት ሄጄ ልሥራ? እንዳላሉ ሁሉ ምርኮኝነታቸውን ካረጋገጡ በኋላ ግን ከማኅበሩ መጥበሻ ግሪል ላይ ወርደው እረፍት ሊያገኙ ችለዋል። ሌሎቹ ግን የሚደርስባቸውን እሳት አስቀድመው ስለሚያውቁ ቃላቸውን አክብረው የጫናቸውን በማራገፍ ግንቦትና ጥቅምት በመጣ ቁጥር በማኅበሩ አጀንዳ አስፈጻሚነታቸው ቀጥለዋል።

 ማኅበረ ቅዱሳን በስመ ተሐድሶና ሙሰኛ ነጠላ ዜማው የፈጃቸውና ያቃጠላቸው ካህናት ቁጥራቸው ብዙ ነው። ስለቅድስናና መንፈሳዊ ንጽህና በዋለበት ያልዋለ የዋልጌዎች ስብስብ ይህ ማኅበር ስም እያጠፋ ያሳደዳቸው፤ ስለኃጢአታቸው ንስሐ የሚገቡበትን በር እየዘጋ ተስፋ በማስቆረጥ ያስወጣቸው የትየለሌ ናቸው። የሚገርመው ግን ነውራም ጳጳሳቱን በቅድስና ካባ ሸፍኖ ለአገልግሎቱ የሚጠቀምባቸው የከባቴ አበሳ ተፈጥሮ ስላለው ሳይሆን እስካለገለገሉት ድረስ ብቻ ነው። እያንዳንዱ የማኅበሩ አባል በተለይም አመራሩ እነአቡነ እገሌ እስከምን ድረስ የጉስቁልና ባሕር ውስጥ እንደሰጠሙ እያወቀ በስምምነት አብሮ ይሰራል። ነገር ግን ከማኅበሩ አቋም ካፈነገጡ ከዚህ በፊት እንዳደረገው የእዳ ደብዳቤአቸውን ከማንበብ አይመለስም። ይህ በተግባር የተረጋገጠ እውነት ነው።

አንዳንዶች ማኅበሩን የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ብቻ አድርገው ያያሉ። ነገር ግን ማኅበሩ  እንደግብጹ የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር በፖለቲካው መድረክም የረቀቀ ተልእኮ ያለው ማኅበር ነው። በአባልነት ያቀፋቸው ሚኒስትሮች፤ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች፤ ሥራ አስኪያጆች፤ ፖሊሶች፤ ዳኞች፤ የሕዝብ አገልግሎት ሠራተኞች፤ መምህራንና ተማሪዎች፤ የሙያ ማኅበራት፤ በ44 አኅጉረ ስብከት ውስጥ ያሉ ሚሊዮኖች የሰንበት ት/ቤት አባላት፤ የጥምቀት ተመላሽ ተጠባባቂ ጦር የመሳሰሉትን በአባልነት እየመለመለ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የራሱን ዶክትሪን በመጋት ማኅበረ ቅዱሳን፤ ማኅበረ ቅዱሳን ካሰኛቸው ውሎ አድሯል። ዛሬ ከሲኖዶስ ወይም ከፓትርያርኩ በላይ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተቆርቋሪና ጠባቂ ከማኅበሩ በላይ የለም የሚለው አስተሳሰብ በእያንዳንዱ ሰው አእምሮ ውስጥ እንዲሰርጽ በሰፊው ተሰርቷል። ዘመናዊ የክርስቲያን ብራዘር ሁድ ማለት ማኅበረ ቅዱሳን ነው።

ሌላው የማኅበሩ ተንኮል አሁን ካሉት ታማኝና ታዛዥ ጳጳሳት በተጨማሪ ከእንግዲህ የሚሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት በራሱ መስፈርት የተመለመሉና ወደፊት ችግር እንደማይፈጥሩ የተረጋገጠላቸው ብቻ እንዲሆኑ ይፈልጋል። እነዚህ የማኅበሩ እጩ ኤጲስቆጶሳት ያለፈ ታሪካቸው የቱንም ቢመስል አሳሳቢ አይደለም። ተቀባይነታቸው አርአያነት ባለው ሁኔታ ቢሆንም፤ ባይሆንም ለማኅበሩ አስጊ እስካልሆኑ ድረስ እንዲመረጡ አጥብቆ ይሰራል። ነገር ግን በተቃራኒ ማኅበሩን የሚፋለሙ ከሆነ እንደአባ ሠረቀብርሃን ወ/ሳሙኤልን የመሳሰሉት በልዩ ልዩ ስምና ወንጀል በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ እጃቸውን ካልሰጡ በስተቀር ለእጩነት ሊቀርቡ አይችሉም።

በአጠቃላይ ማኅበሩ በታሪክ አጋጣሚ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተገኘ መጥበሻ ምድጃ ነው። በዚህ ምድጃ ዲያቆናት፤ ቀሳውስት፤ መነኮሳት ተጠብሰዋል። ሰባኪያነ ወንጌልና አስተዳዳሪዎች ተጠብሰዋል። ጳጳሳትና ፓትርያርኮች ተጠብሰዋል። እውነቱን እያወቁ ከመናገር ብዙዎች የተቆጠቡት ማኅበሩ መጥበሻው ላይ ከጣዳቸው የሚያወርዳቸው ስለሌለ ነው። ልክ እንደ መንግሥታዊ የስለላ መዋቅር የማኅበሩን ስም በተቃውሞ በአውቶቡስ፤ በታክሲ፤ በሬስቶራንት፤ በየካፌውና በሕዝብ መሰብሰበቢያ ቦታዎች መጥራት ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። መንግሥት ላይ ምን ዓይነት የአንኮበር መድኃኒት እንደተረጨበት ባናውቅም እሱም በፍርሃት ይሁን በድንዛዜ ፈዞ ቀርቷል።  እውነታው ግን ማኅበሩ ለየትኛውም ወገን መጥበሻ ምድጃ መሆኑ በተግባር የተረጋገጠ ነው።