«በዘውድአለም ታደሰ»
ነብይ ነኝ ባዩ የቤተክርስቲያን ደላላ!
ይሄ ሰውዬ "ጎሳ" ይባላል። በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ቸርቾች ሲሰብክ አይቼዋለሁ። (ጎፋ መድሃኒአለም ፣ ዘፀአት ፣ FBI ፣ ወዘተ... ) የሚደክም አይነት ሰው አይደለም። ውሃ ሳይጎነጭ በተከታታይ ለሶስት ሰአታት የማውራት አቅም አለው! የምእመኑን ሳይኮ በልቶታል። ህዝቤን ምን እንደሚያስጮሀት ስለሚያውቅ አዳራሹን በጩኸት መናጥ ለነብይ ጎሣ ቀላል ነው!
ብዙ ግዜ ቸርቾች ይህን ሰውዬ ሚጋብዙት ገንዘብ ክፉኛ ሲያስፈልጋቸው ነው። ወይ መሬት ሊገዙ ሲያስቡ ... አሊያም የተሻለ አዳራሽ ሊከራዩ ሲፈልጉ ... ብቻ የሆነ የፈንድ ሬይዚንግ ጉዳይ ሲኖር ጎስሻን ይጠሩትና በዚያች ጮሌ ምላሱ የራሱንም ሆነ የሌሎች ሰዎችን ታሪክ እያጋነነ በመስበክ የዚህን ምስኪን ምእመን ኪስ ያራቁትላቸዋል!
«ነኝ ያልኩ ኮንትራክተር ነበርኩ፣ ነፍፍ መኪኖችና ብዙ ሰራተኞች ነበሩኝ፣ ጌታ ሲገባኝ ግን ንብረቶቼን ሸጬ ለቸርች ሰጠሁ» ብሎ ይጀምራል ተረት ተረቱን።
«ፓ» ይላል ምእመኑ!
«ከዛ ክፉኛ ተቸገርኩና፣ ምልስ ምቀምሰውን አጣሁ፣» ብሎ ለፅድቅ ሲል የከፈለውን መከራ እያጋነነ ያወራል!
«በከተማዋ ስሜ የተጠራ ኮንትራክተር እንዳልነበርኩ ምልስ ምቀምሰውን አጥቼ ተቸገርኩ» ሲል ረሃብን የሚያውቀው የዚህ ህዝብ አንጀት በሀዘኔታ ይላወሳል።
የሰዉን አቴንሽን ማግኘቱን ሲያረጋግጥ ታዲያ ... እንዴት ተአምራዊ በሆነ ሁኔታ እግዜር ሀብታም እንዳደረገው፣ እንዴት እንዳበለፀገው ትረካ በሚመስል ሁኔታ ያወራ ያወራና የህዝቡን አእምሮና ስሜት በሚገባ እንደተቆጣጠረ ሲረዳ እንዲህ ይላል ..
«ጌታ እንዲህ ሲል ተናግሮኛል» ብሎ ይጀምራል ነብይ ጎሳ። (ማን ነብይ እንዳረገው እንጃለቱ)
«ጌታ ዛሬ በዚህ አዳራሽ ውስጥ ያላችሁትን ሁላችሁን እባርካለሁ ብሎኛል» ሲል እቺ በረከቷን ከአርያም ሳይሆን መድረክ ላይ ከቆመው አረም የምትጠብቅ ምእመን አዳራሹን በጩኸት ታቀልጠዋለች! በጭብጨባው የሚሟሟቀው ጎሲሻም «አንዳንዶቻችሁ ከዚህ አዳራሽ ስትወጡ ከበረከታችሁ ጋር ትገናኛላችሁ» ሲል አዳራሹ በአንድ ድምፅ «አሜን» ይላል።
«አንዳንዶቻችሁ ደግሞ ቤታችሁ ስትገቡ በረከታችሁ ቁጭ ብሎ ይጠብቃችኋል»
«አሜን»
«አንዳንዶቻችሁ ስራ ቦታችሁ ላይ»
«አሜን»
«አንዳንዶቻችሁ የዛሬ ሳምንት»
«አሜን»
«አንዳንዶቻችሁ የዛሬ ወር»
«አሜን»
«እግዜር በተራራው ላይ ሙሴን ሲያገኘው በእጅህ ላይ ምን አለ? ብሎ ነው የጠየቀው ወገኖቼ። እግዜር እጃችን ላይ ባለ ነገር ነው ሚሰራው። ዛሬ በእጃችሁ ላይ ምን አለ?» ይላል ብልጣብልጡ ጎሳ!
ይሄ የዋህ ሁን ሲባል ሞኝ የሆነ ህዝብም እውነት መስሎት እጅና ኪሱን ያያል! ከዛማ በቃ አዋራው ይጨሳል .... ፒፕሉ በረከቱን በስጦታው ለመግዛት ይጋፋል! አዳሜ ወርቋን ከአንገቷ ላይ እየበጠሰች፣ ገንዘቧን ከቦርሳዋ እያራቆተች፣ ምንም የሌላት ደግሞ የእጅ ስልኳን ሳይቀር መባ እቃ ውስጥ እየጨመረች የማይፈፀም ትንቢት ታቅፋ እርቃኗን ከአዳራሹ ትወጣለች ... ልትባረክ ነዋ ሃሃሃሃ
ከላይ እንዳልኩት ነብይ ጎሳ ነብይነቱን ከየት እንዳገኘው ማንም አያውቅም። የሚያወራው ታሪክም እውነት ስለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለም። ይህን ሰውዬ የሚጋብዙት ስግብግብ የቤተክርስቲያን አገልጋዮችም የሰውየው ምስክርነት እውነት የተፈፀመ ይሁን አይሁን ለማረጋገጥ ምንም አይነት ጥረት አያደርጉም! እነሱ ሚፈልጉት በሱ ጅንጀና የሚዘንበውን የገንዘብ ዶፍ ነው። የስብከቱ መለኪያ በሱ ስብከት አማካኝነት የገባው የገንዘብ መጠን ነው እንጂ የእግዚአብሔር ቃል አይደለም!
አሁን ቤተክርስቲያን በጎሳና ጎሳን በሚመስሉ መንፈሳዊ ደላሎች እየታመሰች የምትገኝበት ሰአት ላይ ትገኛለች። መፅሀፉ ጎሳንና መሰል አገልጋዮችን «ለመንጋው የማይራሩ» ይላቸዋል!
እንዲጠብቁት የተሰጣቸውን ምእመንና እረኛ የሆኑለትን መንጋ ስጋ እየበሉ ሰብተው ቆዳውን ገፍፈው ይለብሳሉ! በአስራትና በበኩራት፣ በመባና በፍቅር ስጦታ ስም፣ ገንዘቡ ወደካዝናቸው ይጋዝ እንጂ የገንዘቡ አመጣጥ እነሱን አያስጨንቃቸውም። በምእመኑ ፍራንክ ትልልቅ እቅዶች ያቅዳሉ፣ የህዝቡን መሶብ አራቁተው ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን ይገነባሉ፣ በሊትር ሶስት ኪሎሜትር የሚሄዱ ላግዥሪ መኪኖችን ይነዳሉ። ይሄ ተስፈኛ ምእመን ግን ከሰማይ መና እየጠበቀ በደረቅ ምድረ በዳ ደረቅ ትንቢታቸው ታቅፎ ከቃዴስ ቃዴስ ሲንከራተት ይኖራል።
በአብዛኞቹ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያኖች ዘንድ ምድር ምድር የሚሸት ስብከት በዝቷል። ሰባኪው ሁሉ የ prosperity Gospel (የብልፅግና ወንጌል) አቀንቃኝ ሆኗል፣ ምእመኑም በረከቱን የሚለካው በምድራዊና ቁሳዊ ሀብት ብቻ ነው! «ሀገሬ በሰማይ ነው» አይነት ንግግሮች ከምእመኑ አንደበት መደመጥ አቁመዋል። ኢየሱስ የሞተው ለቼቭሮሌት መኪናና ለግራውንድ ፕላስ ስሪ ፎቅ ይመስል ወሬው ሁሉ ቤት ስለመስራትና ቤት ስለማፍረስ ሆኗል ... እንደ ዊነርስ ቻፕል አይነት ቸርቾችማ ወሬው ሁሉ ሱሪ ስለመቀየርና መኪና ስለመንዳት ከሆነ ቆየ። «በመንፈስ መኪና የመንዳት» ፕሮግራም ሁሉ ያካሂዳሉ አሉ! ሃሃሃ
ነብያቶች በዝተዋል። ነብይነት ግን ከሞተ ቆየ! ሰባኪዎችም አሸን ናቸው። ስብከት ግን ስልሳዎቹ ላይ ቆሟል! በየመድረኩ ተኳኩለው እንጣጥ እንጣጥ የሚሉ (ባለብዙ ሚስት ዘማሪዎች እልፍ ናቸው) መንፈሳዊ ማንነትን የሚያንፅ መዝሙር ግን ከመድረኩ ነጥፏል!
በፅድቅና በቅድስና የሚያገለግሉ አንዳንድ አገልጋዮች እንዳሉ አይጠፋኝም። ግን እነዚህ አገልጋዮች ከጎሳውያኑ ጋር ሲተያዩ በገምቦ ውስጥ እንዳሉ ጥቂት ጠብታዎች ናቸው! ስለዚህ ባህር ውስጥ እንዳሉ አይቆጠሩም። እኔ ማወራው ባህሩን ስለሞሉት የተበከሉ አሳዎች ነው!
ቸርቾች በየመቶ ሜትሩ ከተማ ውስጥ ፈልተዋል። ደቀመዝሙር ማፍራት የማይችሉ ውሀ አልባ ምንጮች ናቸው እንጂ! ክርስቲያን ያልሆኑ የክርስቶስ ሰባኪዎችና ክርስቶስን የማያውቁ አገልጋዮች ይሄን ምስኪን ምእመን እንደአሻንጉሊት እየተጫወቱበት ነው! አገልግሎታቸው ያከበራቸውን ህዝብ በመናቅና በማስፈራራት ላይ የተመሰረተ ነው! «ለምን?» ብሎ ጥያቄ የሚያነሳ ሲመጣ «ጌታ በቀባው ላይ እጅህን አታንሳ» በማለት በጥቅስ ያስፈራሩታል። በፅድቅ ለማገልገል ከላይ እታች እያሉ የጅብ ድግሳቸው ላይ የማይሳተፉትን ንፁሀን ደግሞ የተለያየ ስም ጀርባቸው ላይ በመለጠፍ ከአገልግሎት ያግዷቸውና የሚከተላቸውን ምእመን ኑሮ እየቀሙ ይኖራሉ! ሳቁን መንትፈው ይስቃሉ! ደስታውን አራቁተው ይደሰታሉ! እውነትም ለመንጋው የማይራሩ ሆዳሞች!
ዘመኑ የባቢሎናውያኑን ዘመን ይመስላል። ትርምስ እንጂ መረጋጋት የለም! ጩኸት እንጂ መግባባት ጠፍቷል። ግራ የተጋቡ ባለራእዮችና ያልተማሩ አስተማሪዎች መሬት ባልረገጠ የትምህርት ወጀብ ህዝቡን እየናጡት ነው። በተቀየጠ ዶክትሪንና በስህተት አስተምህሮ ምእመኑን ከወንጌል አርቀው አይኑን በማሰር ወደቁልቁለት እየነዱት ነው! ነብያት ነን ባዮቹ ወንዝ በማያሻግር ትንቢት ሲወራጩ መድረኮቻችን ላይ ውለው ያድራሉ። ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች በተራ ፉከራና ሽለላ የተሞሉ ፍሬ አልባ ደረቅ መሬቶች ናቸው!
በተለያዩ ቤተክርስቲያኖች እየተጋበዘ ህዝቡን የሚያራቁተው ደላላው ነብይ .... «ነብይ ጎሳም» ከላይ ለጠቀስኳቸው ሆዳም አገልጋዮች እውነተኛ ምልክት ሊሆን ይችላል ባይ ነኝ!
እቀጥላለሁ!