የቁልቁለት መንገድ ተጀምሯል!
ይህ ጽሑፍ በመጋቢት ወር 2004 በመካነ ጦማራችን ላይ የወጣ ነው። ደግመን ማውጣት ያስፈለገን፤ ሞት የሁሉም ሰው ጽዋ ቢሆንም ማኅበረ ቅዱሳን ፓትርያርክ ጳውሎስን በደጋፊ ጳጳሳቱ በኩል እስከሞት እያዋከበ መቆሚያና መቀመጫ እንዳያሳያቸው እነሆ ፓትርያርክ ማትያስን በተራቸው እስከሞት እየተዋጋ ለመቆየት መቁረጡ በዳበረ ልምዱ ሲሰራበት መቆየቱን ለማሳየት ነው። እንዲህ ብለናቸው ነበር። አንዳች ነገር ሳያደርጉ ሞት ወሰዳቸው፤ ማኅበሩም ሰፋለት። (አመኑንም አላመኑም ፓትርያርክ ጳውሎስ፤ አንድ ነገር አስረግጠን እንነግርዎታለን። በማኅበረ ቅዱሳንና በደጋፊዎቹ ጳጳሳት ግብዓተ መሬትዎ ሊፈጸም የቀረው ጥቂት ነው) ዛሬም ፓትርያርክ ማትያስን ለተመሳሳይ ጽዋ በወከባና በአድማ እያንደረደረ ይገኛል። ማኅበሩ የሚተዳደርበት አዲስ ሕግ ሳይጸድቅ፤ በዐቃቤ መንበርና በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የሥልጣን ነጠቃውን ጀምሯል። ወደፊትስ?
በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ማኅበረ ቅዱሳን ከተራ ማኅበርነት ወደ ሀገረ ስብከትነት አደገ። በዚህም የተነሳ ሲኖዶሱ ሙሉ በሙሉ በማኅበረ ቅዱሳን እጁን ተጠምዝዞ እንደሚሰራ አስመሰከረ። የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ሆኖ የየሀገረ ስብከቶቹ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሆኖ ያገለግላል። ይህ ጽ/ቤት ደግሞ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ በየ3 ዓመቱ በሚያደርገው ምርጫ በሚመድበው ሊቀጳጳስ ነው። እንግዲህ ማኅበረ ቅዱሳን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና አሥኪያጅ ሆነ ማለት ራሱን የቻለ ሀ/ስብከት ሆነ ማለት ነው። የጠቅላይ ቤተክህነቱ መምሪያዎች ሊያዙት አይችሉም። ከዚያም በላይ ቅዱስ ፓትርያርኩ ሊያዙት፤ ሊናገሩትና ሊቆጡት አይችሉም ማለት ነው። በቀጥታ በቅዱስ ሲኖዶስ በሚመደበው ሊቀጳጳስ በኩል ግንኙነቱ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋር ብቻ ይሆናል ማለት ነው። እንዲህ ነው እንጂ ሹመት፤ መሾም ካልቀረ!! አንድ ማኅበር ባንድ ጊዜ እመር ብሎ አናት ላይ ፊጢጥ ብሎ ከመቀመጥ ወዲያ ሹመት ከወደየት ይገኛል? ከእንግዲህ ከተቀመጠበት ደረጃ አንጻር ማኅበር መባሉ ዝቅ የሚያደርገው ስም ስለሆነ የቅዱሳን መምሪያ ወይም የወጣቶች ሀ/ስብከት እንዲባል ሲኖዶሱ በነካካው እጁ ስሙንም ማሻሻል ይገባዋል። ከዚያም አያይዞ ለዚሁ አዲስ ሀ/ስብከት አንድ ሊቀጳጳስ እንዲመድቡለትም ጥቆማውን እናቀርባለን። አንድ ነገር ታዘብን። ቤተክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ የሚባል አካል እንደሌላት ተረዳን። በአንድ ተራ ማኅበር እየተመሩ የእሱን ጉዳይ ብቻ ሲያነሱና ሲጥሉ ሦስትና አራት ቀናት ስብሰባ መወዘፍን ምን ይሉታል? ስንት ስራ መስራት እየቻሉ ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ማውረድ እስኪያቅታቸው ድረስ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን አጀንዳ ይዞ መከራከርን እውነት ሰዎቹ በመንፈስ ቅዱስ ነው የሚመሩት እንድንል ያደርገናል። ይህ ማኅበር ባይኖር ኖሮ ስለምን ጉዳይ ሊሰበሰቡ ነበር፤፤
ይህ ማኅበር እስካሁን እየታዘዘ እንዳልቆየ የተጻፉለት ደብዳቤዎች አረጋጋጮች ናቸው። እሱ ራሱ አልቀበልም ብሎ በደብዳቤ አረጋግጧል። አንዴ ከኢህአዴግ፤ አንዴ ደግሞ ከተቃዋሚ ነኝ እያለ፤ ሌላ ጊዜ ከሀገር ቤቱ ሲኖዶስ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ገለልተኛ እየመሰለ የተጓዘበትን ሁላችንም እናውቃለን። የወንድሞች ከሳሽና አሳዳጅ ስለመሆኑም ግፉን የቀመሱ ሁሉ ይመሰክራሉ። የተጓዘባቸውን ስልቶች ሁሉ ያጠናው መንግሥት ከሽብር አቀንቃኝ ከሰለፊያ ጋር በአንድ ረድፍ አንዳስቀመጠው ነግሮናል። ስለሆነም አቡነ ጳውሎስ ይህንን የአድማና በጥቅም የተሳሰረ ውሳኔ አልፈርምም በማለት ውድቅ ሊያደርጉት ይገባል። ማኅበሩ አስቀድሞ ከሰለፊያ ተግባር ነጻ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ማምጣት ይጠበቅበታል። ደጋፊዎቹ ጳጳሳትን በማስረጃና በሰው ምስክር ተጠንተው ብቁ ሆነው ያልተገኙ ካሉ ከማዕርጋቸው መሰናበት አለባቸው። ቄስ የነበሩ፤ ልጆች የወለዱ፤ ቅምጥ ያላቸው እንዳሉ ይወራል፤ የአንዳንዶቹም ይታወቃል። እየተሸፋፈነ መቀመጡ ለቤተክርስቲያን ጠንቅ የሆነ ውሳኔ ለማስወሰን ያልተመለሱ ሰዎች ስብስብ መሆኑ ከታየ ውሎ አድሯል። ነውራቸውን ለመሸፈን እንኳን ከድመት አንሰዋል።
በአንድ ወቅት አባ ገብርኤል፤ አቶ ኢያሱ ተብለው ከማዕርጋቸው ተገፈው እንደነበረው፤ ማንነታቸው እንደገና ተመርምሮ አስቸጋሪ በሆኑት ላይ ዛሬም ተመሳሳይ ውሳኔ ሊሰጥባቸው ይገባል። ጨከን ያለ የሥርዓት ማስከበር አካሄድ መውሰድ ካልተቻለ ሲኖዶሱን በነሱ በኩል እያወከ ነገ ፓትርያርክነቱን አስቀድሞ ከዚያም ቤተመንግሥቱን እንደሚረከብ የሚጠራጠር ካለ የማኅበሩን አካሄድ የማያውቅ ብቻ ነው። አመኑንም አላመኑም ፓትርያርክ ጳውሎስ፤ አንድ ነገር አስረግጠን እንነግርዎታለን። በማኅበረ ቅዱሳንና በደጋፊዎቹ ጳጳሳት ግብዓተ መሬትዎ ሊፈጸም የቀረው ጥቂት ነው። ከሆነለት ፓትርያርክነቱን ለሚታዘዝ ሰው ሰጥቶ ወደ ቤተመንግሥት ሰተት ብሎ ለመግባት ከጽዋ ማኅበርነት ወደ መምሪያ ተገዳዳሪነት፤ አሁን ደግሞ ወደ ሀገረ ስብከትነት ማደጉ ከምንም በላይ ማሳያ ነው። ታዲያ ከእንግዲህ የቀረው ምንድነው? ይህ ሁሉ ለጽድቅ ነው እንዳይትሉንና እንዳንስቅ ጥቂት እዘኑልን። ነጋዴና ሸቃጭ የሆነ ቅዱስ ማኅበር አራት ኪሎ የለም ። እያየነው በትንሽ በትንሹ የወጣው ይህ ሐረግ ቤተ ክህነቱን አንቆ ወዳሰበበት በመጓዝ ላይ ነው። እግዚአብሔር ለዚህ ክፉ ማኅበር አሳልፎ ከሰጠ በእውነትም ቤተክርስቲያኒቱ ለፈተናና ለውድቀት ተመርጣለች ማለት ነው። ተወደደም፤ ተጠላ ሲኖዶስ በየዓመቱ ያለህውከት ማለፍ አይችልም።
ሰውዬው «ሁሉን ለማየት መቆየት»እንዳለው የሚሆነውን ለማየት ከዕድሜው አይንፈገን!