Wednesday, October 8, 2014

«የማዕተብ ጉዳይ ሰሞነኛ ወሬ»


 
ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ «የኦርቶዶክሱን ክር እናስበጥሳለን» ብለዋል በማለት ማስጮሁን የጀመረው አሉላ ጥላሁን የሚባለውና የማኅበረ ቅዱሳኑ አባል የሚነዳው «ሐራ ተዋሕዶ» መካነ ጦማር ነው።  ድርጅት እንጂ እምነት የሌለው ሁሉ ያንን ተቀብሎ አስተጋባ። በእርግጥ ዶ/ር ሽፈራው ብለውታል? ወይስ አላሉትም? የሚለው ጉዳይ ማረጋገጫ የሚያስፈልገው  ቢሆንም «ራስ ሲመለጥና አፍ ሲያመልጥ አይታወቅም» እንዲሉ ዶ/ሩ ብለው ሊሆን ይችላል ብለን ብንገምት እንኳን ይሄንን ያህል ማስጮህና ማጦዝ ያስፈለገው ለምንድነው? ብለን መጠየቅ ተገቢ ይመስለናል።

1/ ምክንያታዊነቱ፤

    አዲስ ይወጣል በተባለው የሴኩላሪዝም ደንብ በመንግሥት የሥራ ቦታዎች ውስጥ ሃይማኖታዊ የሆኑ ምልክቶች ማለትም ስዕል ማድረግ፤ በጠረጴዛም ይሁን በግድግዳ መስቀል ማንጠልጠል፤ የኮምፒውተር ስክሪን ሴቨር ማድረግ፤ መንፈሳዊ ጥቅሶችን፤ ሂጃብ፤ ኒቃብ፤ ቡርቃና ሌላ ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ ምልክቶች እንዳይኖሩ የመከልከል ደንብ እየወጣ መሆኑ ሲነገር ቆይቷል።

  እነዚህ ሃይማኖታዊ ምልክቶችን እንደፈለጉ መጠቀም ከዚህ ቀደም ባለፉ ሥርዓታት ዘመን ያልነበሩና አዲስ የፈጠራ ልምዶች እርግጥ ነው። ዲሞክራሲ ያሰፈናቸው ወይም ዘመን የፈጠራቸው ናቸው ወይ? ብለን አንከራከርም።  ነገር ግን ሁሉም ሃይማኖት ከማን አንሼ ሰበብ አጋጣሚውን ተጠቅሞ የሚያደርግ ከሆነ ወይም «እኔን ደስ የማይለኝ ነገር በሥራ ቦታዬ ላይ ተቀምጧል፤ ስለዚህ እንዲወገድ ይደረግልኝ» በማለት ቢቃወም ሰላማዊ የሥራ ሁኔታውን ወደሃይማኖታዊ ንትርክና ጭቅጭቅ ሊቀይር መቻሉ ሳይታለም የተፈታ ነው። ከዚህ በፊትም ይህ ክሰተት ተፈጽሞ «መብቴ ነው!»  «መብትህ አይደለም!»  ወደሚል አተካራ ማስገባቱን ያጋጣመቸው ሰዎች ሲናገሩ ተደምጧል። 

  ለመሆኑ ደመወዝ ሊከፈለው ውል ፈጽሞ በገባበት የሥራ ቦታ ሃይማኖታዊ ምልክቶችን ማስቀመጥ ለምን አስፈለገ? ነገሩን ስንመለከተው ብዙ ጊዜ ሃይማኖታዊ ምልክቶችን ባልተፈቀደ ቦታም ይሁን ተገቢ ባልሆነ ሥፍራ ለማሳየት የሚፈልጉ ሰዎች «እኔ እበልጣለሁ» ወይም «ሃይማኖቴን በጣም እወዳለሁ» በሚል ስሜት ሌላውን ለማሳነስና እነሱ በእምነታቸው የተሻሉ መሆናቸውን ለማሳየት የሚፈልጉ ሰዎች ይመስሉናል።  የዚህ ተቃራኒ ደግሞ «እኔም አላንስም» በማለት ሌላውን ለመቃወም የራሱን ምልክት በተደራቢነት ለመጠቀም የመፈለጉ አዝማሚያ ወይም «ይነሳልኝ» ሲል ክስ የማቅረቡ ሁኔታ ያለውን የእኔነት ውጥረት ለማርገብና አደብ ለማስያዝ መንግሥት መፈለጉ ከተገቢነቱ አኳያ አያጠያይቅም። በየቦታው እየሄዱ በስመ ስብከት ሰበብ «ኢየሱስ ጌታ ነው» እያሉ የግል ነጻነትን ሳያስፈቅዱ እንሰብካለን ሲሉ ከግለሰብ ጋር የሚጋጩትን ጨምሮ በሃይማኖት ሽፋን የሌላውን መብትና ነጻነት መጋፋት ተገቢ አለመሆኑም ትክክል ነው።

  «እኔ የተሻልኩ ነኝ» በሚል ራስን የማግዘፍና በፈጣሪ ፊት ያለውን ተመራጭነት ለማሳየት ካልሆነ በስተቀር ምልክትን መደርደር፤ አብዝቶ መናገር ወይም ራስን ለማሳየት መሞከርና የየትኛው ሃይማኖት ተከታይ እንደሆንክ ማስተዋወቅ በእግዚአብሔር ፊት የበለጠ ተወዳጅ መሆንን ሊያሳይ አይችልም። ስለዚህ የትኞቹም ምልክቶች የፊት ማሳያ እንጂ የልባችን ተግባር መግለጫዎች ስላይደሉ አስፈላጊነታቸው ምክንያታዊ አይደሉም። የክርስትና ወይም የእስልምና ምልክት አድርጎ የሚሰርቅ ወይም የሚያመነዝር ትውልድ ምልክት ስላደረገ እንደ እውነተኛ ሰው ሊቆጠር አይችልም። 

«ራሳችሁን በሰው ፊት የምታጸድቁ እናንተ ናችሁ፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ልባችሁን ያውቃል፤ በሰው ዘንድ የከበረ በእግዚአብሔር ፊት ርኵሰት ነውና» ሉቃ 16፤15

የሃይማኖታዊ ምልክት ፉክክር የጥፋት መጀመሪያ ነው። አንድ ሰሞን «አንድ እምነት፤ አንዲት ጥምቀት፤ አንድ ጌታ» የሚለውን ጥቅስ በልብስ ላይ አትመው የለበሱ ሰዎችን ለመገዳደር በሚመስል መልኩ «ኢየሱስ፤ መሐመድና ሙሴ የአላህ ነብያት» የሚል ጥቅስ ለብሰው የሚዞሩ ወጣቶችን ማየቴን አልረሳውም። ሃይማኖቱን በተፈቀደለት ቦታና በሥፍራ እንደመጠቀም ከሌላው የተሻለ እውነተኛነት እንዳለው ለማሳወቅ በሚደረግ ሩጫ ጥፋት ለማስከተል መሞከር የነበረውን ሰላም ከማደፍረስ በስተቀር በዚህ አድራጎት የሚታነጽ ማንም የለም።

«እንዲሁ ደግሞ እናንተ መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የምትፈልጉ ከሆናችሁ ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ» 1ኛ ቆሮ 14፤12

2/ የክር እናስበጥሳለን ፉከራና የተቃውሞ ዘመቻ፤

ከላይ በመግቢያችን ላይ እንደጠቆምነው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ስልጠና ላይ «ሂጃብ እንዳስወለቅን ክርም እናስበጥሳለን» ብለዋል የተባለው ጉዳይ እውነት ነው ወይ?   
«ሃይማኖታዊ ምልክቶችን ከመንግሥት የሥራ ቦታዎች ውስጥ እናስቆማለን፤ ሴኩላር የሆነ የሥራ ቦታ እንፈጥራለን» በሚለው እሳቤ ዙሪያ ከአንገት ላይ ክርም እናስበጥሳለን» የሚለውን ፉከራ በምን መስፈርት እንደተመለከቱት ግልጽ አይደለም። እንደእውነቱ ከሆነ ክር አንገት ላይ ማሰር ሌላውን አማኝ አያውክም። ለጌጥ ብሎ ሀብል ከሚያስር ሰው የተለየ ነገር የለውም። መንግሥት እስከዚህ ድረስ የወረደ ተግባር ይፈጽማል ተብሎ አይታሰብም። ተብሎ ከሆነ መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው እንላለን።
 ዶ/ር ሽፈራው ብለዋል ከተባለ በኋላ የገቡበትን አጣብቂኝ ለመከላከል እንደሆነ ለጊዜው ባይገባንም የጉዳዩን ጡዘት በማርገብ ደረጃ  በመንግሥታዊው ሚዲያ «ፋና ብሮድ ካስቲንግ» ቀርበው አላልኩም በማለት አስተባብለዋል። «ቤን» የተባለው አፍቃሬ መንግሥት ድረ ገጽ አዘጋጅም ጥያቄ አቅርቦላቸው አለመናገራቸውን ገልጸዋል። «እንደዚህ አላልንም» ካሉት በላይ የምንጠብቀው ምላሽ አይኖርም።
 ነገር ግን በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ሃይማኖታዊ የሆኑ ምልክቶች ሁሉ እንዳይኖሩ እናደርጋለን ተብሎ ከተዘጋጀው ደንብ ውስጥ ከተዘረዙት ሁሉ በአራጋቢዎቹ ዘንድ የዚህ የክር ጉዳይ ብቻዋን ለምን ተነጥላ ወጣች? ነው ጥያቄያችን። ይህንን ጉዳይ አስቀድሞ ያስጮኸው የማኅበረ ቅዱሳኑ «ሐራ ተዋሕዶ» መካነ ጦማር ነው። ሐራ ደግሞ ጅራፏን የምታስጮኸው በማኅበረ ቅዱሳኑ አሉላ ጥላሁን በኩል ነው።

 ብዙ ጊዜ በአፍቃሬ ማኅበሩ ብሎጎች ስማቸው በክፉ የሚወሳው ዓባይ ፀሐዬ፤ ስብሐት ነጋና ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም ናቸው።  እነዚህን የፖለቲካ ሹማምንት ማኅበሩና ደጋፊዎቹ የሚቃወሟቸው ማኅበሩ የፖለቲካ ድርጅት ስለሆነ ሳይሆን የማኅበሩን አካሄድ በግልጽ ስለሚቃወሙ ብቻ ነው።  እዚህ ላይ በአንድ ወቅት አቶ ስብሐት ነጋ «ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን ሸክም» ማለታቸው ሳይዘነጋ ነው። 
በሌላ በኩል ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ማኅበር መሆኑም መታለፍ የለበትም። ማኅበሩ  በፓትርያርኩ ላይ ጫና በማሳደር በወዳጆቹ ሊቃነ ጳጳሳት በኩል ማስፈጸም ያቃተውን ቤተ ክርስቲያንን የመረከብ ዓላማ ለጊዜውም ቢሆን የተገታው በሃይማኖት ሽፋን ሀገሪቱን ወደቀውስ መውሰድ ከሚፈልጉ ተቋማት አንዱ ማኅበረ ቅዱሳን ነው ስለተባለና ስሙ ብዙ ጊዜ ብዙ ጊዜ መነሳቱም አንዱ ምክንያት ነው። በዚህ በኩል ዶ/ር ሽፈራው ብዙ ተጉዘዋል። 

  ማኅበሩ ከአባ እስጢፋኖስ ጀርባ ሆኖ ያረቀቀውና የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን የመረከብ ሕግ  ውድቅ ከሆነበት በኋላ የተወረወረበትን ቅዝምዝም ለማሳለፍ ባለፉት ወራቶች አንገቱን ዝቅ አድርጎ ጠብቋል። መጪው ወር የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ይካሄዳል።  በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ውስጥ ያጣውንና ለአባ እስጢፋኖስ መነሳት ምክንያት የሆነው የሕግ ማርቀቅን ጉዳይ ተከትሎ ማኅበሩን አደብ ለማስያዝ በፓትርያርኩ በኩል የቀረቡ ነጥቦች ነበሩ። 

ይህንን ተከትሎ በማኅበሩ ላይ ይጸና ዘንድ ከሚታሰበው ደንብ በፊት ጥቂት ነገር መጫር ሳያስፈልግ አልቀረም። በማኅበሩ ላይ በሴኩላሪዝም ደንብ ስዕልና ጥቅስ በመሥሪያ ቤቶች እንዳይገኙ ከሚከለክለው ጉዳይ ውስጥ ከኦርቶዶክሳውያን አንገት ላይ የሚታሰረውን ክር ነጥሎ በማውጣት ማስጮህ የፈለገው በአማኙ ስስ ስሜት ተጠግቶ ብዙ ተቃዋሚ በማስነሳት አቅጣጫ የማስቀየር ስልት መሆኑ ነው። በዚህም የማኅበሩ አመራር የሆነው አሉላ በተወሰነ መልኩ ተሳክቶለታል። በዶ/ሩ ላይ ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ድረ ገጾችና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሳይቀሩ ተቀባብለው ዘምተውባቸዋል። በዚህም ጫና ይመስላል፤ ዶ/ሩ ሳይወዱ ምላሽ ወደመስጠት የተገደዱት። ብለውም ከሆነ «ካፈርኩ አይመልሰኝ» መሆኑ ነው። ያላሉም ከሆነ አጋጣሚውን ጠብቆ ዱላውን ያሳረፋባቸው ማኅበር ምላሽ በመስጠት የማስገደድ አቅሙን እንዲያዩ አድርጓቸዋል። ወደፊት በማኅበሩ ላይ ተጽዕኖ የማሳደር እስትንፋሳቸውን የመከልከል ዘዴ መሆኑ ነው።  በእርግጥ እንዲያ ከሆነ አያዋጣም።

የሚገርመው ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ «ኦርቶዶክሶች ክር የማይበጥሱ ከሆነ እኛም እስላሞቹ ሂጃብ አናወልቅም፤ ቆባችንንም አንጥልም» የሚል ዘመቻ መጀመሩ ነው። ነገሩ አብረን እንጥፋ ነው። «ከኔ ኪስ መታወቂያ ከጠፋ፤ ያንተም መታወቂያ መጥፋት አለበት» ማለት ቅናት እንጂ ጤናማ ክርክር አይደለም። ቡርቃና ኒቃብ ከክር ጋር የሚነጻጸሩት በምን ስሌት እንደሆነ አይገባንም። ትክክልም አይመስለንም። ባለክሮች ስለክር ማሰር ሲጮሁ ባለኒቃቦች ባለክሮችን ተጠግተው ጩኸት አስነሱ። ስለክርም፤ ስለቆብም፤ ስለኒቃብም ማንሳት የማይፈልግ ነጻው ሰው በመንግሥት መሥሪያ ቤት ነጻ ሆኖ እንዴት ይስራ? መልሱ አጭር ነው። ሃይማኖተኞች ሃይማኖታችሁን በተፈቀደላችሁ ቦታ ብቻ ፈጽሙ ነው። ሴኩላሪዝም ማለት ይህ ነው። መንግሥታዊ ሃይማኖት የለም፤ ሃይማኖታዊ መንግሥትም የለም።

 ነገር ግን ባልተጋነነ መልኩ ሥርዓት ማስያዝ የመንግሥት ድርሻ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሃይማኖታዊ ነገሮችን በጥንቃቄ በመያዝና ከባለጉዳዮቹ ጋር በመነጋገር ማስተካከል እንደሚቻል ጽኑ እምነት አለን። ለምሳሌ ፈረንሳይ ኒቃብና ቡርቃን በሕግ አግዳለች። «ኒቃብ» ዓይን ብቻ የሚታይበት ሲሆን «ቡርቃ» ደግሞ ሙሉ በሙሉ የተሸፋፈነች ሴት አለባበስ ነው። ሳርኮዚ «ለእነዚህ ሰዎች መታወቂያ መስጠት ምን ይጠቅማል?» ሲሉ ጠይቀዋል።
መታወቂያ ማን መሆኑን መለያ ነውና አባባላቸው እውነት ነው። ስለዚህ ክርን ከቡርቃ ጋር ለማስተያየት የምትሞክሩ ጥቂት ተረጋጉ። ከጸጥታ ስጋት አንጻርም ቢያስፈራ አያስገርምም። በ2007 ዓ/ም ያሲን ዑመር የተባለ እንግሊዛዊ አሸባሪ ፈንጂ ታጥቆ እንደሴት ቡርቃ ለብሶ እንደነበር የቢርምንግሃም ፖሊስ ሲያከሽፍበት አይተናል።

  በሌላ በኩል ደግሞ ክር ማሰር የተጀመረው መቼ ነው? ብለን ወደዝርዝር አንገባም። ታሪኩ ረጅም ነው። ነገር ግን «ማዕተብ» ማለት ምልክት ማለት እንደሆነ እንናገራለን። ከክርስቲያንም ኦርቶዶክስ የመሆን ምልክት!
 ክር ማሰር ምልክት እንጂ ሌላ ምንም አይደለም። በአዲስ ኪዳን ስለክር ማሰር የተነገረን ነገር የለም። ማኅበሩ እንደቀድሞ ዋሾዎች የሌለውን ጥቅስ እያቀረበ የወንጌል አስተምህሮ እንደሆነ አድርጎ ለማሳመን ቢሞክርም ከውሸትነቱ ፈቀቅ ብሎ እውነት ሊሆን አይችልም። ክርስትና እምነት እንጂ ምልክት አይደለም። በክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት በማመን የሚኖሩበት ሕይወት ነው። የሚገርመው ደግሞ ሚሊዮኖች ክርና መስቀል አንገታቸው ላይ እያለ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ይዘርፋሉ፤ ያመነዝራሉ፤ ይሰክራሉ፤ ይሰርቃሉ፤ ይዋሻሉ። የአንገት ላይ ምልክት እንጂ የልብ ላይ ክርስትና የላቸውምና ከዚህ ድርጊታቸው ክር ማሰራቸው በጭራሽ ሊያድናቸው አይችልም።
 እንዲያውም ሥነ ምግባር የሌላቸውን ብዙ ጫት በሊታዎች፤ ሴትኛ አዳሪዎች፤ አመንዝራዎች፤ ሰካራሞች፤ ተሳዳቢዎች፤ ዘፋኞች ሰዎች ልብ ብላችሁ ብታዩ አንገታቸው ላይ ክር ወይም መስቀል ታገኛላችሁ። አንገታቸውን ላይ ምንም ምልክት የሌላቸው ሰዎች በተመሳሳይ ጥፋት ብናገኛቸው ያላዳናቸው አለማሰራቸው ነው ብንል ምልክቱን አስረው ያጠፉትንስ ለምን አልታደጋቸውም? ብለን መጠየቁ ተገቢ ነው።


  ስለዚህ ከክር ማሰር ጀርባ የራሳቸውን ዓላማ ለማራገብ የሚፈልጉ ቡድኖች ክር ስላሰራችሁ ጻድቅ አትሆኑም፤ ስላላሰራችሁም አትኮነኑም እንላቸዋለን። ክርስትና በክርስቶስ በማመንና የሥጋ ሥራዎችን በመተው የሚጓዙበት ሕይወት እንጂ ክር በማሰር ክርስቲያን መሆንህን ለሰዎች የምታሳይበት የጎዳና ላይ ማስታወቂያ አይደለም። ባለክሮችም እንደባለቡርቃዎቹ ተረጋጉ።
ጥል፤ ክርክር፤ አድመኝነት፤ በወንጌል ቃል ያልሆነ የቃላት ስንጠቃ፤ እውነትን የተቀሙ ሰዎች ተግባር ነው። አንዲቱ ቤተ ክርስቲያን የተከፋፈለችውም በእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ስለተሞላች ነው። የሐራ ተዋሕዶው አሉላ ያልኖረበትን ክርስትና በክር ስር ቢፈልገው አያገኘውም። እንዲያውም ጥፋት በደጁ ታደባለች።
 ክርስትና ስለስዕል ስለመስቀል፤ አንገት ላይ ክር ስለማሰር አይደለም። ክርስቶስን ስለመምሰል እንጂ።
 
«እነዚህን አስተምርና ምከር። ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢሆን፥ በትዕቢት ተነፍቶአል አንዳችም አያውቅም፥ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፤ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም ክፉ አሳብም እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ፥ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ» 1ኛ ጢሞ 6፤3-5

Wednesday, October 1, 2014

በምድራችን ላይ በክፉ መንፈስ ተነድተው ሕዝብን ያሳሳቱ ሀሰተኛ ክርስቶሶችና ነብያት!



 ( ክፍል 3 ) 

ጂም ጆንስ (1931-1978)
በአሜሪካዋ ኢንዲያና ስቴት ህዳር 18, 1931 ተወለደ። እድሜው ለአቅመ ህውከት ሲደርስ በኢንዲያናፖሊስ ከተማ የኮሙኒስት ፓርቲ አባል በመሆን በህውከት ስራ ላይ መሰማራትን «ሀ» ብሎ ጀመረ። የኮሙኒስት ርእዮት አራማጅ የሆነው ጆንስ በሜቶዲስት፤ በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ውስጥ ብቅ ጥልቅ እያለ ከቆየ በኋላ ዓለም በኒውክለር ትጠፋለች ስለዚህ ሐዋርያዊ ሶሻሊዝም በዓለም ላይ መምጣት አስፈላጊነት ይሰብክ ነበር። ጆንስታውን ወደተባለች የጉያና ከተማ በማቅናት «የህዝቦች ቤተ መቅደስ» የተሰኘ ቤተክርስቲያን ከመሠረተና ከተደላደለ በኋላ የእርሻ ተቋም ከፈተ።  በዚህ የእርሻ ተቋም ውስጥ ሶሻሊስታዊ እኩልነት የሰፈነበት ማኅበረሰብ እመሰርታለሁ በማለት የራሱን «የቀይጦር ሠራዊት» አደራጀ። ይህ የቀይ ጦር ሠራዊት ዋና ዓላማው የእርሻውን ሜካናይዜሽንና የቤተ ክርስቲያኑን ህልውና የመጠበቅ ዓላማ ይዞ የተነሳ ቢመስልም በተግባር ግን የጂም ጆንስን አንባገነንነት መንከባከብ ነበር። ወደተቋሙ የገባ ማንም አባል መውጣት አይችልም በማለት ማገድ ጀመረ። በዚህም ሳቢያ በዚያ ማኅበረሰብ ውስጥ የፈለገውን ማድረግ የሚችል አንባ ገነን መሆን ቻለ። ከዚህ ተቋም ሸሽተውና አምልጠው ወደአሜሪካ የገቡ ሰዎች ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተርና ለምክርቤቱ አቤቱታቸውን ማቅረብ ቻሉ። በሰብአዊ መብት ጥሰት የተከሰሰው  የጆንስን ጉዳይ የሚያጣሩ በኮንገረስ ማን ሊዮ ሪያን የሚመራ ብዙ የሚዲያ ሰዎችን የያዘ ቡድን ወደጉያና አመራ። ቡድኑ ከቦታው እንደደረሰ ከጆንስ ቀይጦር አባላት የጠበቀው የሞቀ ሰላምታ ሳይሆን የደመቀ የጥይት ተኩስ ነበር። ኮንግረስ ማን ሪያንና ሌሎች ብዙዎቹ በተኩሱ ተገደሉ።  ከፊሎቹም ቆሰሉ። ህዳር 18, 1978 ዓ/ም ጥዋት ላይ ይህ ግድያ ከተፈጸመ በኋላ ጆንስ ወደተከታዮቹ በመመለስ ከሚመጣባችሁ ቁጣ ለመዳን ራሳችሁን አጥፉ፤ ልጆቻችሁንም ጭምር ለመፍጀት ለሚመጡ ጠላቶች አሳልፋችሁ አትስጡ፤ ስለዚህ አብራችሁ ሙቱ በማለት ትእዛዝ ሰጠ።
ሳይናድ መርዝ እየጠጡና እያጠጡ 300 ህጻናት ያሉበት 900 ሰዎች በጥቂት ሰዓት ውስጥ አለቁ።
እኔ ቡድሃን፤ ሌኒንን፤ኢየሱስን እና ሌሎችን ሆኜ ተገልጫለሁ እያለ ያታልል የነበረው ጂም ጆንስ በአውቶማቲክ ጥይት ግንባሩን ብትንትንን አድርጎ ራሱን በራሱ ገደለ።




ማርሻል አፕልዋይት  (1931-1997)
ስፐር ፤ቴክሳስ ተወለደ። እድሜው ለአቅመ ማሳሳት ከመድረሱ በፊት የአሜሪካ ወታደር በመሆን አገልግሏል። በሂውስተንና ኮሎራዶ ትምህርቱን የተከታተለው አፕል ዋይት በአላባማ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሲሰራ በግብረ ሰዶም ተጠርጥሮ ከስራው ተባሯል። ይህንን ተግባሩን የመሰከረበት ደግሞ በስብከቱ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን አስፈላጊነት መናገሩ ነበር። አፕል ዋይት የሙዚቃ ባለሙያ ስለነበር በዚህ ሙያ ያገኘውን ችሎታ ተጠቅሞ «Heaven’s Gate» /የመንግሥተ ሰማይ በር/ የተሰኘ ሃይማኖታዊ ድርጅት መሠረተ።  አፕልዋይት በዩፎዎች መኖር የሚያምንና በነሱ ላይ ጥገኛ የሆነ ስብከት ያስተምር ነበር።
 በ1974  ዓ/ም የተከራያትን መኪና ባለመመለስ ወንጀል ተከሶ ስድስት ወር ተፈርዶበት ከርቸሌ ወረደ። ከዚያም እንደወጣ ጣዖታዊ ስብከቱን ቀጥሏል። መስከረም 25, 1995 ዓ/ም «እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ነኝ» በማለት ለተከታዮቹ አሳወቀ።
በመጋቢት 29/ 1997 ዓ/ም ዩፎዎች መጥተው ወደገነት ስለሚወስዱን ራሳችንን እናጥፋ ብለው በጅምላ ራሳቸውን ገደሉ። ከተከታዮቹ መካከል ማርሻል አፕል ዋይትን ጨምሮ 30 አባላቱ ሞተው ተገኙ። ነገር ግን ሁኔታው እንደተሰማ ከቦታው የተገኘ አንድም ዩፎ አልነበረም። ይልቁንም ፖሊስ ከቦታው ተገኝቶ እነአፕልዋይት ራሳቸውን በራሳቸው ማጥፋታቸውን አረጋግጦ የህዝብ መቃብር ውስጥ እንዲወርዱ አድርጓል።




ያህዌህ ቤን ያህዌህ (1935-2007) 

 ጥንተ ስሙ ኸሎን ሜሼል ጁንየር ይባል ነበር። ይህ ጥቁር አሜሪካዊ እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ለማለት ፈልጎ ስሙን  በ1979 ዓ/ም «ያህዌህ ቤን ያህዌህ» በማለት ቀየረ። ብዙዎቹም ተከታዮቹ ከክርስትናውና ከአይሁድነት ያፈነገጡ ሰዎች ነበሩ። በተለይም ጥቁር አሜሪካውያን ብዙ ቁጥር ያላቸው ሲሆን ትክክለኛው እስራኤላውያን እኛ ነን፤ ይሉ የነበረ ሲሆን በአሜሪካና በዓለም ላይ በ1300 ከተሞች ውስጥ አባላቱን ማደራጀት ችሏል። እግዚአብሔር ጥቁር ነው። እስራኤልውያንም ጥቁሮች ነበሩ። ነጮቹ ታሪካችንን ቀምተው ነው። ሰይጣን ማለት ነጮች ናቸው ይል ነበር። በዚህም ምክንያት ዓርብ ህዳር 13 ቀን አንገታቸው የተቀላ የነጮች ሬሳ በአቅራቢያው ዳዋ ውስጥ ተጥሎ በመገኘቱ ጥቁሩ መሲህ ቤንያህዌህ በ1992 ዓ/ም ሰው በመግደል ወንጀል ተጠርጥሮ ተያዘ። በፍርድ ቤትም በምስክሮች ስለተረጋገጠበት የ18 ዓመታት እስር ተበይኖበት ከርቸሌ ወረደ።  
በእስራቱም ነብይ በሀገሩ አይከበርም ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው ሲሉ ተከታዮቹ ለፈፉ። ከ8 ዓመት እስራቱም በኋላ በ2001 ዓ/ም በምህረት ተለቀቀ። በ2007 ዓ/ም በፕሮስቴት ካንሰር ሞተ። ከሱ ሞት በኋላ ተከታዮቹ በሥጋ የተገለጠው እግዚአብሔር ማለታቸውን አልተዉም። ልቡ የደነደነ ዓለም ዓይኑ ታውሮ ሰው ያመልካል። ለጣዖትና ስዕል ይሰግዳል።

(ይቀጥላል % )

Wednesday, September 24, 2014

ስለመላእክት ያለው አስተምህሮ ምን ይመስላል?


( ክፍል ሁለት )
 


3/የቅዱሳን መላእክት አገልግሎት


በክፍል አንድ ጽሁፋችን ስለመላእክት ስያሜ ትርጉም፤ ስለአፈጣጠራቸው፤ ስለፈቃዳቸውና ተልእኰአቸው በጥቂቱ ለማየት ሞክረን ነበር። በክፍል ሁለት ጽሁፋችን ደግሞ ቀሪውን ነጥብ እግዚአብሔርን እንደፈቀደ መጠን ለማየት እንሞክራለን።
ቅዱሳን መላእክት የፈጣሪያቸውን ትእዛዝ ሳይጠብቁ  የትም እንደማይንቀሳቀሱ እርግጥ ነው። በዚህም የተነሳ እግዚአብሔር በወደደውና በፈቃደው ቦታ ቅዱሳኑን መላእክት ለእርዳታና ለትድግና ይልካቸዋል። 

«የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል» መዝ 34፤7

እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ሰዎች የእግዚአብሔር ጥበቃና እርዳታ ዘወትር ይደረግላቸዋል ማለት መላእክቱ በራሳቸው ፈቃድ ይንቀሳቀሳሉ ማለት አይደለም። አንዳንዶች ይህንን ጥቅስ በመጠቀም «መላእክት በተጠሩ ጊዜ በተናጠል መጥተው ያድኑናል» ወደሚል ድምዳሜ በመድረስ ከመላእክት አማላጅነት ጋር ለማያያዝ የሚፈልጉ ወገኖች አሉ። ነገር ግን ዳዊት በመዝሙሩ በግልጽ እንደተናገረው
 «በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል» ካለ በኋላ ሰው ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ፈቃድ ስር ካደረገ «እግዚአብሔርን፦ አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው» በማለት እግዚአብሔር ታዳጊ አምላክ እንደሆነ በማሳየት፤  ከእግዚአብሔር ዘንድ ደግሞ ለእንደዚህ ዓይነቱ አማኝ የተሰጠው የጥበቃ ተስፋ በቅዱሳን መላእክቱ በኩል መሆኑን ከታች ባለው ጥቅስ ይነግረናል።

«ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና» 
 ይላል በዝማሬው። መዝ 91፤ 1-16 (ሙሉውን ያንብቡ)
በተመሳሳይ መልኩ እግዚአብሔርን መታመኛቸው ላደረጉ ሰዎች የእግዚአብሔር ጥበቃ በመላእክቱ በኩል ሲፈጸም እንመለከታለን።

«ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ፦ ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ አለ» የሐዋ 12፣11

 ጴጥሮስን ሄዶ እንዲያድን የላከው ጌታ ነው። መልአኩ የተላከውም ጴጥሮስን እንዲያድን ነው። ቅዱሳን መላእክት እንደስማቸው ለሚገዙለት ጌታ ይላካሉ። አድኑ የተባሉትን ያድናሉ። ለመዓትም ይሁን ለምህረት መላእክቱ የሚላኩት በእግዚአብሔር ትእዛዝ እንጂ ሰዎች ስለጠሯቸው ወይም ስለፈለጓቸው አይደለም።
 በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ ወደቴስቢያዊው ኤልያስ መልአኩ በተላከ ጊዜም  አካዝያስ ስለህመሙ ምክንያት እግዚአብሔርን በጸሎት ከመጠየቅ ፈንታ ወደአቃሮን ብዔል ዜቡል ፊቱን ባዞረ ጊዜ መልአኩ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» በማለት የመጣበት ጉዳይ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ትእዛዝ ለመፈጸም እንደሆነ አስረግጦ ሲናገር፤

 «የእግዚአብሔርም መልአክ ቴስብያዊውን ኤልያስን፦ ተነሣ፥ የሰማርያን ንጉሥ መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣና። የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቁ ዘንድ የምትሄዱት በእስራኤል ዘንድ አምላክ ስለሌለ ነውን? ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም በላቸው አለው። ኤልያስም ሄደ» 1ኛ ነገ 1፤3-4

«እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» ማለቱ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተቀብሎ ለመፈጸም መምጣቱን ያስረዳል። ወደኤልያስ መልእክቱ ይመጣ ዘንድ ያስፈለገውም ኤልያስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይከተል ስለነበር መሆኑ እርግጥ ነው። በሌላ ቦታም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይፈጽሙ ከነበሩ ደጋግ ሰዎች መካከል አንዱ ወደሆነው ወደቆርኔሌዎስም ዘንድ ሲልክ  እንመለከታለን።

«ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፦ በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና። ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ»  የሐዋ 10፤ 30-31

የቆርኔሌዎስ ስለጸሎቱ መሰማትና ስለምጽዋቱም በእግዚአብሔርን ዘንድ መታሰብ የሚናገር መልእክተኛ መላኩን ስንመለከት ዳዊት በዝማሬው እንዳመለከተው በልዑል መጠጊያ ለሚኖሩ ሁሉ መላእክቱ እንደሚላኩላቸው በግልጽ ያረጋግጥልናል። በዚሁ ተመሳሳይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስረጂ በማቅረብ የመላእክቱን ተራዳዒነትና አጋዥነት መግለጽ  ይቻላል። ነገር ግን አስረግጠን ማለፍ የሚገባን ቁም ነገር መላእክቱ የሚመጡት በእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ ስር ላሉ ሲሆን ሰዎች የፈለጉትን መልአክ ስለጠሩ ወይም በልባቸው አምሮት የመረጧቸውን  መላእክት ስም ስለተናገሩ አለመሆኑን መገንዘብ ይገባናል። በሰዎች ጥሪ እገሌ የተባለ መልአክ መጣልኝ የሚል አንዳችም አስረጂ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ አይገኝም። በተራዳዒነትና አጋዥነት እንደተላኩ የሚነገርላቸው አብዛኛዎቹ መላእክትም በስም ተለይተው አይታወቁም። ቁም ነገሩ የትኛው መልአክ በታላቅ ኃይል ትእዛዙን ይፈጽማል በማለት በኛ ምርጫ የሚወሰን ሳይሆን በስም የተገለጹም ይሁን ያልተገለጹትን እግዚአብሔር መላእክቱን ልኮ የወደዳቸውን እንዴት ይታደጋል? የሚለውን ከመረዳቱ ላይ ልናተኩር ይገባል። ስለዚህም ተልከው ስላገዙን መላእክት የምንሰጠው ክብር እግዚአብሔር ለኛ ያደረገውን ታላቅ ሥራ ቀንሰን የምናካፍለው መሆን የለበትም። በርናባስና ጳውሎስ ከእናቱ ማህጸን ጀምሮ እግሩ የሰለለውን ሰው በፈወሱበት ወቅት የሊቃኦንያ ከተማ ሰዎች «አማልክት ከሰማይ ወደእኛ ወርደዋል» በማለት መስዋዕት ሊያቀርቡላቸው በወደዱ ጊዜ እነጳውሎስ ያደረጉትን ማየቱ ተገቢ ነው።

«ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፥ እንዲህም አሉ። እናንተ ሰዎች፥ ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፥ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለ»                የሐዋ 14፤14-15

ጳውሎስና በርናባስ ቅዱሳን በአገልግሎታቸው ሐዋርያት ሆነው ብናከብራቸውና ብንወዳቸውም ቅሉ በእነሱ እጅ በተሰራው አምላካዊ  ድንቅ ሥራ ግን ምስጋናንና ክብርን በጋራ ሊቀበሉ አይችሉም። ክብርና ምስጋና ሁሉ ለእግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ራሳቸው እንደመሰከሩት የእግዚአብሔር  የብቻው የሆነውን ወደፍጡራን መስጠት ተገቢ እንዳልሆነ ማወቅ ይገባናል።

4/ የእግዚአብሔር መላእክት ሳይላኩ በሰዎች ጥሪ ሥፍራቸው ለቀው ይሄዳሉን?

ቅዱሳን መላእክትን ቅዱሳን ያሰኛቸው ዋናው ቁም ነገር የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ማክበር መቻላቸው ነው። ከእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ ውጪ የሆኑትማ  ከማዕርጋቸው ተሰናብተዋል። ስለዚህ ቅዱሳን መላእክቱ ሰዎች ስለጠሯቸው ወይም ስማቸው ነጋ ጠባ ስለተነሳ ተጠርተናል በሚል ሰበብ ወደየትም አይሄዱም። ከላይ በማስረጃ ለማስረዳት እንደተሞከረው ቅዱሳኑ መላእክት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለፈጸሙ ወይም እግዚአብሔር ፈቃዱ ይፈጸም ዘንድ በወደደበት ቦታ መላእክቱን ከሚልክ በስተቀር የትኛውም መልአክ ስሙ ስለተጠራ ወይም ስለተወሳ ተከብሬአለሁና ልሂድ፤ ልውረድ በማለት ከተማውን ለቆ የትም አይሄድም። አንዳንድ ሰዎች የመላእክቱን ስም ለይተው በመጥራት ናልኝ የሚሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካልሆነ ትምህርት የተገኘ ልምምድ ውጤት ነው።
 ስሙ ተጠርቶ ይቅርና ገና ሳይጠራ ስፍራውን ለቆ የትም የሚዞረው ሰይጣን ብቻ ነው። ሰይጣን ቦታውን ለቆ የትም የሚዞረው ከእግዚአሔር ፈቃድ ውጪ ያፈነገጠ ሽፍታ ስለሆነ ነው። ቅዱሳን መላእክቱ ያለእግዚአብሔር ትእዛዝ ስማቸው ስለተጠራ ብቻ ሥፍራቸውን ለቀው እንደማይንቀሳቀሱ የሚያውቀው ሰይጣን ራሱን የብርሃን መልአክ አስመስሎ ሊያታልል እንደሚችል ወንጌል ያስረዳናል።
«ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና» 2ኛ ቆሮ 11፤14

ሰይጣን በራሱ ፈቃድ የሚተዳደር ዐመጸኛ ስለሆነ በዓለሙ ሁሉ እየዞረ ሰዎችን ሲያሳስት ይውላል። በተለይም የእግዚአብሔርን ፊት በሚሹ ሰዎች ዙሪያ የጥፋት ወጥመዱን ሊዘረጋ አጥብቆ ይተጋል። ጻድቅ የሆነው ኢዮብንም ያገኘው በዚህ የጥፋት አደናው ወቅት ዓለምን ሲያስስ እንደነበር ከንግግሩ ታይቷል።

«እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም። ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ»ኢዮብ 1፣7

ስለዚህ ክርስቲያኖች እንደእግዚአብሔር ፈቃድ እየኖሩ ለትእዛዙ በተገዙ ጊዜ በመልካም ትሩፋታቸው ይሁን በችግራቸው ወይም በመከራቸው ወቅት እንዲራዷቸው ቅዱሳኑ መላእክት ከሚላኩ በስተቀር ሰዎች በቀጥታ መላእክቱን ስለጠሯቸው ወይም በስማቸው ስለተማጸኑ የሚመጡ ባለመሆናቸው ከመሰል ስህተት ልንጠነቀቅ ይገባል። ይልቁንም ከእግዚአብሔር ተልእኮ ውጪ ቅዱሳኑ እንደማይንቀሳቀሱ የሚያውቁት የሰይጣን ሠራዊት የብርሃን መልአክ በመምሰል ራሳቸውን ቀይረው ከሚፈጽሙብን ሽንገላ ልንጠነቀቅ ይገባል።

እንደማጠቃለያ፤

 ቅዱሳን መላእክት ሰዎችን ይራዳሉ፤ ያግዛሉ ማለት በሥልጣናቸው የራሳቸውን ክብር ስም ለማስጠበቅ ይሠራሉ ማለት አይደለም። በተፈጥሮአቸውም ውሱን ስለሆኑ በዓለም ላይ በአንድ ጊዜ በስፍሐትና በምልዓት የመገኘት ብቃት የላቸውም። በሁሉም ሥፍራ ተገኝተው ሰዎች ሰለጠሯቸው መልስ አይሰጡም።  ይሁን እንጂ በዓለም ላይ በስማቸው ተሠራ በሚባለው ቤተ ጸሎት በአንድ ጊዜ በስፍሐትና በምልዓት ተገኝተው ጸሎት እንደሚቀበሉ ተቆጥሮ ስማቸው ሲጠራ ይታያል። በቅዱሳን መላእክት ተራዳዒነት እናምናለን ማለት ቅዱሳን መላእክት በራሳቸው ፈቃድ ስለጠራናቸው ይደርሱልናል ማለት አይደለም። ቅዱሳን መላእክት ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ሳይደርሳቸው አይንቀሳቀሱም። የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማም ቅዱሳኑን መላእክት ስናከብራቸው አስተሳሰባችንን በመለጠጥ የምንጓዝበት የእምነት ጽንፍ ወደስህተት እንዳይጥለን ለማስገንዘብ ነው። ቅዱሳኑን ያለትእዛዝ ስለጠራናቸው ብቻ በማይመጡበት ሥፍራ ሰይጣን የብርሃን መልአክ መስሎ ከሚፈጽመው ማታለል ለመጠበቅ ነው።
በአንዳንድ የእምነት ተቋማት ዘንድ ስለመላእክት ያለው አስተምህሮ የተዛባ ምስልን እንደያዘ መገንዘብ ይቻላል። 

   በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አንዳንዶች የመላእክቱን ተፈጥሮ ዘንግተው ሁሉን የመስማት፤ የማወቅና በሁሉ ሥፍራ የመገኘት ችሎታ እንዳላቸው ሲቆጥሩ መታየቱ ተለምዷል። መላእክት በተጠሩ ጊዜ መልስ እንደሚሰጡና እንደሚራዱ የሚሰጠውም ግምት ያለትእዛዝ በራሳቸው ፈቃድ እንደሚንቀሳቀሱ ያደርጋቸዋል። ይህም ወደ እግዚአብሔር ሳይሆን በተራዳዒነት ሰበብ ወደ መላእክቱ ጸሎት የሚያደርሱ ሰዎችን አስገኝቷል። «እንደአናንያ፤ እንደአዛርያ፤ እንደሚሳኤል አድነን ገብርኤል» እያሉ መዘመር እንደተገቢ ከተቆጠረ ውሎ አድሯል። ሠለስቱ ደቂቅን ያዳነው ገብርኤል ነው ከሚለው የትርጉም ፍልሰት ጀምሮ «ገብርኤል አዳኝ ነው» ወደሚለው መልአኩን  ለይቶ የማመስገን የፍቺ ጽንፍ ድረስ ስለመላእክት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ምስል መስጠት ጉዳዩን አደገኛ ያደርገዋል። እኛ የሚያድኑን እግዚአብሔር ፈቃዱን የፈጸመባቸው መላእክቱ ወይስ የእግዚአብሔር ኃይል? በሚለው ሃሳብ ላይም መቀላቀል የታየበት ሁኔታ ሕዝቡ መላእክቱን በተናጠል ወደመጣራት ሲገፋው ይስተዋላል። ከሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ሚካኤል አንተ ታውቃለህ? ብሎ የመጸልይ ልምምድ ስለመላእክቱና ስለእግዚአብሔር ፈቃድ የተቀላቀለ ትምህርት ውጤት ነው።
አንድ ክርስቲያን በአንድ ጊዜ ወደእግዚአብሔርም፤ ወደመላእክቱም ጸሎት ማድረስ አይችልም። ይህ መተላለፍ ነው። እግዚአብሔር ደግሞ ከክብሩም፤ ከምስጋናውም ለማንም አያጋራም። ቀናተኛ አምላክ የሚባለውም ለዚህ ነው። ኢያሱ ወልደነዌ ለህዝቡ እንዲህ አለ።
«ኢያሱም ሕዝቡን፦ እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም መተላለፋችሁንና ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም» ኢያ 24፤19
ስለዚህ ስለመላእክት ተፈጥሮ፤ ተልዕኰና አገልግሎት በደንብ ማወቅ የሚገባን የእግዚአብሔርን ለመላእክት፤ የመላእክትንም ለእግዚአብሔር በመስጠት የእምነት ሥፍራውን  እንዳናቀላቅል ሲባል ነው። ተፈጥሮአቸውን፤ ተልእኰአቸውንና ተግባራቸውን ለይተን እንወቅ። ከስህተትም ላይ እንዳንወድቅ እንጠንቀቅ። ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን!