Friday, July 12, 2013

በቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ያለው ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል!

ቀደም ሲል ስንል እንደቆየነው ሁሉ አሁንም ደግመን እንለዋለን። የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደራዊና አካዳሚያዊ ችግሮች ይህንን ያህል እንኪያ ሰላንትያ ውስጥ የሚያስገባ አልነበረም። ቤተክርስቲያኒቱ ባላት አቅም፤ የሰጠችውን መክፈልተ ሲሳይ ለተማሪዎቹ በተገቢው መንገድ ማድረስ ለመቻል ባለሙያና ትጉህ አስተዳደር ለማስቀመጥ መሞከር ቀዳሚው ነጥብ ሲሆን፤ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ እንደመሆኑ መጠን ቀሚስ ለባሽ ሳይሆን ራሱን ለውጦ ሌላውን መለወጥ የሚችል የተማረ ኃይል ለማፍራት ደረጃውን የጠበቀ የምሁራን ስታፍ በመመደብ የነገይቱን ቤተ ክርስቲያን ይረከቡ ዘንድ ማስቻል ሁለት የተሰናሰሉ አስፈላጊ ኩነቶች ሆነው ሳሉ የአስተዳደርና ብቃትና አርቆ የማሰብ ርእይ በዞረበት ያልዞረው ቤተ ክህነት ጉዳዩን አጡዞ መውጫ ወደሌለው አዘቅት ውስጥ ኮሌጁን እየወረወረው ይገኛል።
መነሻ ምክንያቶቹም ሁለት ናቸው።
1/ የአባ ጢሞቴዎስ ደካማ አስተዳደርን ለማስወገድና ከእርሳቸው ጋር የተማማሉ መሰሪ የኮሌጁ ሹማምንት የሚፈትሉት ውል የለሽ የነገር ልቃቂት ጋር የፓትርያርክ ማትያስ « ከእርስዎ ጋር ሞቴን ያድርገው » ቃል ኪዳን ላይበጠስ መተሳሰሩ ቀዳሚው ነው።
2/ ከነዚሁ ወሳኝ ከሆኑና ነገር ግን ጉዳዩን እንደናዳ ድንጋይ እያንከባለሉ ተማሪዎቹ ላይ የሚመርጉት ትላልቅ ኃይሎች እንዳሉ ሆነው በተገኘው አጋጣሚና ክፍተት ተጠቅሞ ከኮሌጁ ድኩምና መዝባሪ አስተዳደሮች ጋር በፕሮቴስታንታዊ ተሓድሶ ዜማ እየታገዘ የሚጠላቸውን ሰዎች በመጥረግ ራሱ ባዘጋጃቸው ተላላኪዎች በመተካት የኮሌጁን የመተንፈሻ ሳንባ ለመቆጣጠር የሚፈልገው ያ መሰሪ ማኅበር ባሰማራቸው ጉዳዩ ፈጻሚዎቹ በኩል ከወዲህ ጠርዝ ከተማሪዎቹ ችግር ጋር እንደአዞ እያነባ ከጀርባ ሲጮህ መገኘቱ ነው።
ከእነዚህ ሁለት ስውርና ግልጽ ኃይሎች ማለትም አንዱ የተማሪዎቹን ጩኸት እየጮኸ ከጀርባ ሆኖ ግፋ በለው ቢልም  ሌላኛውን ኃይል የተማሪዎቹን ጩኸት ላለመስማት ምክንያቶችን እየደረደረ እነሆ ወራቶችን አስቆጥሯል። ከዚህ ቀደም እንዳልነው አዲሱ ፓትርያርክም የመጣ ደብዳቤ ከመፈረም ውጪ እርባና የሌለው ሥራ ሳይሰሩ፤ ይባስ ብለው በሰላም ሀገር ኮሌጁ ይዘጋ ወደሚል ምክንያት የለሽ ውሳኔ ደርሰዋል። በጣም አሳዛኝ ነገር ነው።
ማኅበረ ቅዱሳን በአባ ጢሞቴዎስ እጅ እንዳልበላና እንዳልጠጣ ( ስንት ደብዳቤ እንዳላስፈረማቸው) ዛሬ በማኅበሩ የተሐድሶ ጥቁር ፋይል ላይ የተመዘገቡና አልታዘዝ ያሉትን ሰዎች አባ ጢሞቴዎስ ከጎናቸው ስላቆሙና አባረው ወደማኅበሩ ጊሎቲናዊ ጥርስ ውስጥ ስላላስገቡ ብቻ «ሐራ ተዋሕዶ» በተባለ የመጮኺያ ማሽን በኩል በአባ ጢሞቴዎስ ላይ አንዲት ቅጠል የማይበጥስ እርግማኑን ይወረውራል።
እውነት የአባ ጢሞቴዎስ አስተዳደራዊ ድኩምነትና ግትርነት ለማኅበሩ የታየው ዛሬ ነው? ነፍሳቸውን ይማርና ከአቡነ ጳውሎስ ጋር አባ ጢሞቴዎስ በነገር ሲፋጠጡ፤ ማኅበሩ ለአባ ጢሞቴዎስ እሳቱ፤ ቅባቱ፤ መርዙ፤ ብረቱ እያለ ሲያሞካሽ አልነበረምን? ያንን ሁሉ ዛሬ ምን ውሃ በላው? ነገሩ ወዲህ ነው። ፈረንጆቹ /Use and throw/ ይሉታል። አንዴ ተጠቅመህ ሲያበቃ ወርውረህ መጣል ማለት ነው። አባ ጢሞቴዎስ እኔ ያልኩት እንደሚሉ፤ ግትርነት እንደሚያጠቃቸው፤ ተላላና ተደላይ መሆናቸው የዋለ ያደረ ባህርያቸው ነው። ይሁን እንጂ ማኅበሩ ያስፈልጉት በነበረበት ወቅት አገልግለውታል። ዛሬ ደግሞ አስፈላጊው አይደሉምና ከግዙፉ የተማሪዎቹ ችግር ጀርባ የቀድሞውኑ የምናውቃቸውን አባ ጢሞቴዎስን ይራገማል።
በሌላ መልኩ አዲሱ ፓትርያርክ የቀድሞውን ፓትርያርክ በየሚዲያው ሲያብጠለጥሉ እንዳልነበር ያቺ ታስነቅፍ የነበረችው ሥልጣን ተሽከርክራ እጃቸው ላይ ስትወድቅ ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ ትንሹን የተማሪዎች ችግር መፍታት አቅቷቸው ታንክ የታጠቁ ያህል ቆጥረው ግቢያችን የሆነው ባድመን ልቀቁ የሚል አዋጅ ለማስነገር ሲበቁ ስናይ «ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር፤ ሲይዙት ይደናገር» የሚለውን ብሂለ አበው አስታወሰን። ለአባ ጢሞቴዎስ የሚከፈል ትንሹ ዋጋ መሆኑ ነው።
ተማሪዎቹም ራሳቸውን ማጥራት የሚገባቸው ማንም አፍና ምላስ ሆኖ የሚጮህላቸው ማኅበርና የማኅበሩ አቀንቃኝ ቀሚስ ለባሽ በመሃከል ተሰግስጎ መኖር እንደሌለበት ነው። ጥያቄያቸው አጭርና ግልጽ ነው። «አስተዳደራዊና የተማሪ ዕለታዊ ኑሮ ይስተካከል» የሚል ብቻ መሆኑን አበክሮ ማስረገጥ ይገባል። ከዚህ ውጪ ቤተ ክርስቲያኒቱ ራሷ መተኪያ የሌላትና ሁሉን የሰበሰበች ማኅበር ሆና ሳለ ሌላ የቀኝ ክንፍ ማኅበር አባል በመሆን ችግሩን የታከከና ለራስ መደላድል ሁኔታዎችን ማጽዳት የሚሉትን አንጥሮ አለመግፋት በራሱ ወንጀልም ኃጢአትም ነው።
ከዚህ የተነሳ ማለት የሚቻለው ነገር ቤተ ክህነቱም ራሱ ገርፎ ራሱ እየጮኸ ነው። ግቢውን ለቃችሁ ውጡልኝ ማለት ምን ማለት ነው? በሌላቸው ውክልናና እውቀት በአንድ በኩል የተሐድሶ አቀንቃኞች በኮሌጁ ተሰግስገዋል እያሉ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ የአስተዳደር በደል ተፈጽሟል በሚል ዲስኩር ከተማሪዎች ጋር የሚጮሁ የሰው አራዊቶች ድምጻቸውን ያቁሙ። እነዚህኞቹም ራሳቸው ገርፈው ራሳቸው የሚጮሁ ቀላማጆች ናቸው።
እኛ የምንለው ተማሪዎቹም መባረር የለባቸውም፤ ማኅበር የሚባል የወፍ ጉንፋን በሽታ ከግቢው ይውጣ! አባ ጢሞቴዎስም ሌላው ቢቀር ዓይናቸው ደክሟልና ከሥራው አሳርፏቸው። በሽታው እንዳይዛመት የማኅበሩ የወፍ ጉንፋን ቫይረስ ያልለከፈው አባት ይሾም። ለዚያውም ካለ!!!  ጅራፎች ሆይ፤ በመከራ በገረፋችሁት ተማሪ ላይ ራሳችሁ ገርፋችሁ፤ራሳችሁ እንደተበደለ ሰው አትጩሁ!!!!!!!!!!

Sunday, July 7, 2013

እነ አርቲስት ጀማነሽ “የቅዱስ ኤልያስ”ን መልዕክት ለፓትሪያሪኩ እንዳናደርስ ተከለከልን አሉ


(አዲስ አድማስ )“የማህበረ ስላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ” አባላት፤ ከቅዱሳን አባቶች የተላክነውን የቅዱስ ኤልያስን መልዕክት ለአዲሱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን ፓትሪያሪክ አቡነ ማቲያስ እንዳናደርስ ተከለከልን አሉ፡፡ አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን የተካተተችበት መልዕክት አድራሽ ቡድን፤ ባለፈው ማክሰኞ ረፋዱ ላይ መልዕክታቸውን ጋዜጠኞች ባሉበት ለፓትርያርኩ ለማቅረብ ፓትሪያሪኩ ጽ/ቤት በር ላይ ተገኝተው የነበረ ቢሆንም የጥበቃ አባላት “ለማነጋገር ፍቃድ የላችሁም” ብለው መልሰዋቸዋል፡፡ ከማህበሩ አባላት መካከል አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን እና መ/ር ወልደመስቀል ፍቅረማርያም ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ለሁለት ጊዜያት ያህል 4 ኪሎ በሚገኘው መንበረ ፓትሪያሪክ ጽ/ቤት በመሄድ ከአባቶች የተላኩትን መልዕክት ለማድረስ ቢሞክሩም ከጽ/ቤቱ የጥበቃ ሃላፊዎች ማለፍ አልቻሉም።
“በመጀመሪያው ቀን ከማህበረ ስላሴ መልዕክት ይዘን መምጣታችንን ለጥበቃዎች በመንገር ወደ ውስጥ እንድንገባ ከተፈቀደልን በኋላ ሌሎች በግቢ ውስጥ የነበሩ ጥበቃዎች በድጋሚ አስቁመውን ከስላሴ ካቴድራል ማኅበር የመጣችሁ መስሎን ነው እንጂ እናንተ መግባት አትችሉም በማለት ፓትሪያሪኩን እንዳናገኝ ተደርገናል” የሚሉት መ/ር ወልደመስቀል፤ በተለይ አንዲት ሴት የጥበቃ አባል ከአግባብ ውጭ ጀማነሽን እየገፈታተረች እንድትወጣ ማድረጓን ገልፀዋል፡፡ በሚዲያ ሳይቀር ቅዱስ ፓትሪያሪኩ ማንም ሰው ያለከልካይ በአካል መጥቶ ሊያነጋግረኝ ይችላል ያሉትን መነሻ አድርገን በመጀመሪያ ቀን ያለቀጠሮ የሄድን ቢሆንም ለሁለተኛ ጊዜ ቀጠሮ ለማስያዝ ብንፈልግም የሚያስተናግደን አካል በማጣታችን ለመመለስ ተገደናል የሚሉት መ/ር ወልደመስቀል፤ ጥበቃዎቹ የሄድንበትን ጉዳይ ጠይቀውን ከተረዱ በኋላ ፈጽሞ መግባት አትችሉም፤ ቀጠሮ ማስያዝ ከፈለጋችሁ አንድ እማሆይ አሉ፤ እሣቸውን አነጋግሩ ተባልን፤ የተባሉት ግለሰብ ግን ፍቃድ ወጥተዋል የሚል ምላሽ አገኘን ብለዋል፡፡ “አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ ስንሄድ ጥበቃዎቹ ፈጽሞ መግባት አትችሉም፡፡ አካባቢውን ለቃችሁ ሂዱ አሉን” ብለዋል - የማህበሩ አባላት፡፡
ባለፈው ማክሰኞ 10 የሚደርሱ ሴቶችና ወንዶች የማህበሩ መገለጫ የሆነውን ነጭ ባለቀስተ ደመና ጥለት ልብስ ለብሰው ፓትሪያርኩ ጽ/ቤት በሩ ላይ ቆመው ነበር፡፡ የነብዩ ኤልያስ መልዕክት ምንድነው ብለን የጠየቅናት አርቲስት ጀማነሽ ሠለሞን “መልዕክቱ ለፓትሪያሪኩ ስለሆነ እሳቸው ከሰሙ በኋላ ለህዝብ እንድታደርሱ ይነገራችኋል” ብላለች፡፡ የመንበረ ፓትሪያሪክ ልዩ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምሩ አበራ ከአዲስ አድማስ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ተጠይቀው “እስካሁን ጥያቄ ያቀረበልን የለም፤ ቤተክርስቲያኒቷ የራሷ የቅሬታ አቀራረብ ሥርዓት አላት፡፡ ለቅሬታም ሆነ ለቡራኬ የሚመጡትን በቀጠሮ እናስተናግዳለን፡፡ እስከ ሀምሌ 21 ቅዱስ ፓትሪያሪኩን በስልክ ለማነጋገር የተያዙ ቀጠሮዎች አሉ” ብለዋል፡፡ ከነብዩ ኤልያስ መልዕክት አለን ያሉት ግለሰቦች “ኦርቶዶክስ” የሚለው ስያሜ “ለተንኮል” የገባ ስለሆነ የቤተክርስቲያኒቱ ስያሜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መባሉ ቀርቶ “የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን” መባል አለበት በሚል አላማ እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል፡፡

Saturday, July 6, 2013

የካህናቱ የ«እናውቃለን» እና «አናውቅም» እውቀት!



ካህናቱ ከተራው ሕዝብ በቃለ እግዚአብሔር የተሻለ እውቀት እንዳላቸው ይታመናል። ይጠበቃልም። ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ መጻሕፍቱ ላይ «እያዩ የማያስተውሉ» ተብሎ የተነገረባቸው ደግሞ እነዚህ የእውቀት ማዕድ ያካፍሉ ዘንድ በክህነት አገልግሎት የተሰለፉትን ሆኖ ስናይ እጅግ ያስገርመናል። ካህናቱ እያዩ የማያስተውሉ ከሆነ የሚመሩት ሕዝብ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም።
አይሁዳውያኑ ካህናትና የመጻሕፍቱ መምህራን ስለብሉያት መጻሕፍት በቂ እውቀት እንዳላቸው ከመገመቱም በላይ ራሳቸውም በቂ እውቀት እንዳላቸው ስለራሳቸው ሲመሰክሩ እናነባለን። ይሁን እንጂ እውቀታቸው ሲመዘን ብዙውን ጊዜ አውቀን ተናገረናል የሚሉት አንደበት እርስ በእርሱ ከመጋጨቱ አልፎ ተርፎም ሰዎቹ ራሳቸውም ጭምር እርስ በእርሳቸው የሚጋጩበትም አጋጣሚ ታይቷል።
ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነን ከላይ በርዕሱ ላይ ያስቀመጥነው ነጥብ ጥሩ መነሻ ይሆነናል። እነዚህ የእውቀት ማዕድ አደላዳዮች እንደሆኑ የሚታሰብላቸው ካህናት በአንድ ወቅት በአንድ ምላስ ሁለት ቃል በመናገር አንዴ «እናውቃለን» ያሉትን አንደበት ሽረው ወዲያው ደግሞ «አናውቅም» በማለት ሲናገሩ እናገኛቸዋለን።
ካህናቱ ይኸንን ቃል የተናገሩት ጌታ ኢየሱስ ከደብረ ዘይት ተራራ መልስ በቤተ መቅደስ ብዙ ካስተማረ በኋላ በድንጋይ ሊወግሩት በፈለጉና በመካከላቸው ተሰውሮ በወጣ ጊዜ ነበር።  ከዚያ አልፎ እንደወጣ ዘመኑን ሁሉ ዓይነ ስውር የነበረና በልመና የሚተዳደር አንድ ሰው ባገኘ ጊዜ «ደቀ መዛሙርቱም መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ? ብለው ጠየቁት» ዮሐ 9፤2
ጌታም ሲመልስ፤ «በራሱም ይሁን በቤተሰዎቹ ኃጢአት ሳይሆን የእግዚአብሔር ሥራ ይገለጽ ዘንድ» እንደዚያ መሆኑ ከገለጸላቸው በኋላ የመጣበትን የማዳን ስራ በማሳየት በምራቁ ጭቃ ለውሶ ዓይኑን በመቀባትና በሰሊሆም መታጠቢያ በመታጠብ ዓይነ ብርሃኑ እንዲመለስ እንዳደረገለት እናነባለን።
የሚገርመው አስደናቂ ነገር የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው። ዓይነ ብርሃኑ የጠፋው ይህ ሰው ዓይኑ ከበራለት በኋላ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ከመወለዱ አንስቶ እውር የሆነን ሰው ዓይን ያበራ ሰው ስለመኖሩ እንዳልተሰማ በመሰከረ ጊዜ ካህናቱ በተቃራኒው ሃሳቡን በመቃወም «ይህ ሰው ኃጢአተኛ እንደሆነ እናውቃለን» በማለት የመጀመሪያ ቃለ ጽርፈት ሲሰነዝሩ ታይተዋል። ዮሐ 9፤24
ዓይነ ስውር የነበረው ሰው የተደረገለትን ነገር አድንቆ ለካህናቱ ሲመልስ «ኃጢአተኛ መሆኑን አላውቅም፤ ዕውር እንደ ነበርሁ አሁንም እንዳይ ይህን አንድ ነገር አውቃለሁ አለ» ዮሐ 9፤25
ካህናቱ የማያውቁትን የብርሃን ጌታ እንደሚያውቁት አድርገው በላዩ ላይ የሀሰት አንደበት ሲከፍቱ፤ እውር ሆኖ መወለዱንና አሁን ግን ብርሃን እንደተሰጠው የተግባር ምስክር ሆኖ የራሱን ሕይወት ስለቀየረው ስለኢየሱስ ማንነት ከካህናቱ በተሻለ ማወቅ መቻሉ በእርግጥም አስገራሚ ነገር ነው። ምናልባትም ራሱ ባለቤቱ እንደተናገረው « የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ አለ» ያለው ቃል እንደተፈጸመባቸው የሚያስረዳን ነገር ይሆናል። ዓይነ ስውሩ የሥጋ ብርሃንም፤ የልቡና ዓይንም ሲገለጥለት የልቡናቸውን ብርሃን በእውቀት እንደሞሉ የሚያስቡና ዓይነ ሥጋቸውም ከልደታቸው ጀምሮ ምሉዕ እንደሆነ የሚተማመኑት ካህናት ግን በሁለቱም ወገን መጋረዳቸውን አንደበታቸው ያረጋግጣል። ይኸውም ከእናቱ ማኅጸን አንስቶ እውር ሆኖ የተወለደን ሰው ብርሃን መስጠት የቻለ ስለመኖሩ ከዚህ ቀደም እንዳልተሰማና ይህንን ለማድረግም ከእግዚአብሔር ካልሆነ በስተቀር ኃጢአተኛ ሰው ብርሃን መስጠት እንደማይችል ልቡናቸው እያወቀ የለም! ይህ ሰው «ኃጢአተኛ እንደሆነ እናውቃለን» ሲሉ በቃለ ሀሰት ምስክርነት እስከመስጠት ያደረሳቸው ነገር እያዩ የማያዩ ሰዎች ስለሆኑ ነበር።
 እነዚህ ልበ ዕውራን ካህናት የዕውርነታቸው መጠን የለሽነት የሚገለጸው ደግሞ የተነገራቸውን እውነት ለመቀበል አለመፈለጋቸው ብቻ ሳይሆን እየተነገራቸው የሰሙትን ለመሸከም የሚችል ልቡና የሌላቸው መሆናቸው ደግሞ ሌላው አስገራሚ ነገር ነው።
ካህናቱ ዓይኑ ስለበራለት ሰው በቅድሚያ ጥያቄ ያቀረቡት ለወላጆቹ ነበር። «እናንተ ዕውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታድያ አሁን እንዴት ያያል? ብለው ጠየቁአቸው» ዮሐ 9፤19
ወላጆቹም፤ ዓይነ ስውሩ ልጃቸው አሁን ዓይኑ እንደበራለት ከመሰከሩ በኋላ ማን እንዳበራለትና እንዴት እንደበራለት እንደማያውቁ በተናገሩ ጊዜ ካህናቱ ሁለተኛ ማረጋገጫ በመሻት ወደ ጉዳዩ ባለቤት በመሄድ ጥያቄያቸውን ዓይነ ስውር ለነበረው ሰው አቅርበዋል። እሱም ሲመልስ «ያበራለት ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እንደማያውቅ፤ ነገር ግን ዓይኑን እንዳበራለት እንደሚያውቅ ሊገባቸው በሚችል ቋንቋ በግልጽ ተናግሮ ሳለ መልሰው በጥያቄ ሲያደርቁት ይታያሉ። ዳኅጸ ልሳን በመፈለግ ለመክሰስና ሸንጎ አቁሞ ለማስወገዝ ወይም ለማስደብደብ ካልሆነ በስተቀር ወደእውነት ለመመለስ ለቀና ነገር ቀና ልብ መቼም የሌላቸው ናቸው።
«ደግመውም። ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዓይኖችህን ከፈተ? አሉት» ዮሐ 9፤26 ዓይኑ የበራለትም ሰው ነገረ ስራቸው ሁሉ አስገርሞትና እንደዚህ አብዝተው ጥያቄ መጠየቃቸው በተደረገው ተአምር ተስበውና በኢየሱስ የማዳን ፍቅር ተሸንፈው ደቀ መዛሙርቱ ለመሆን የፈለጉ መስሎት በመሰላቸት ስሜት እንዲህ ሲል መለሰላቸው።
«እርሱም መልሶ፦ አስቀድሜ ነገርኋችሁ አልሰማችሁምም፤ ስለ ምን ዳግመኛ ልትሰሙ ትወዳላችሁ? እናንተ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትወዳላችሁን? አላቸው» ዮሐ 9፤26
ካህናቱ ነገረ መጻሕፍትን አዋቂዎች ናቸው፤ እድሜአቸውን ሁሉ በመቅደሱ ሲያገለግሉ ኖረዋል፤ በዚያ ላይ ዓይናቸው አልታወረም። በእርግጥም መጠየቃቸው ደቀመዛሙርት ለመሆን ከመፈለግ የተነሳ ሊሆን እንደሚችል ቢገመት ስህተት ላይሆን ይችላል። ስህተቱ ግን ካህናቱ ክርስቶስን ለማወቅ አለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን ለማወቅም አለመፈለጋቸውን አለመረዳት ነው። ልበ ዕውራኑ ካህናትም ሲመልሱ እንዲህ አሉ።
«ተሳድበውም። አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ፥ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እኛ እናውቃለን፥ ይህ ሰው ግን ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም አሉት» ዮሐ 28-29
ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ዓይኑ ብርሃን ስለማግኘቱ ለማወቅ አንድም ቦታ መፈለጋቸውን አናነብም።  ዓይነ ብርሃኑ የተመለሰለትን ሰው በጥያቄ ከማሰለችታቸው በላይ ተመጣጣኝ መልስ ቢሰጣቸው ካህናት ሆነው ሳለ የምላሻቸው ማሟሺያ ስድብ ጭምር ማከላቸው በእርግጥም እውቀት በተለይም መንፈሳዊ እውቀት ከላይ ከሰማይ ካልተሰጠ በስተቀር በትምህርትና በክህነት ማዕርግ ሊገኝ እንደማይችል ያረጋግጥልናል። ይህንንም እውነት ጌታችን ራሱ እንዲህ ሲል መናገሩ የታሪኩን እውነታ ያሳያል። «የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም» ዮሐ 6፤44  ለሰው ልጅ ትምህርትና እውቀት አስፈላጊ የለውጥ መሣሪያዎቹ እንደሆኑ ባይካድም  ከላይ ካልተሰጠ በስተቀር ይህ በራሱ ወደእውነተኛ መገለጥ ሊያደርስ አይችልም። ብዙ አዋቂዎች ባለማወቅ ደመና ተሸፍነው መገኘታቸው ዘወትር የምንመለከተው ሐቅ ነው።
ካህናቱ ዓይነ ስውሩን ከሰደቡት በኋላ «አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ፤ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን» አሉት።  የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን የተናቀ ደረጃ ሲሆን የሙሴ ደቀ መዝሙር መሆን መቻል በካህናቱ ዘንድ ትልቅ እድገትና እውቀት መሆኑ ነው። ዛሬም «የእርቃችን መንገድና እውነት፤ መድኃኒትና በር ኢየሱስ ብቻ» ብሎ መጥራት ያስነቅፋል። በዚህ ላይ ልዩ ልዩ የመዳኛ መንገዶችን፤ ብዙ ብዙ አማላጆችን ካልያዝክ በስተቀር  «ኢየሱስ» በሚለው ስም ላይ ብቻ መታመን ዋስትና እንደሌለው የሚያስተምሩ ካህናት አሉ። «ፊት የማያስመልሱ፤ አንገት የማያስቀልሱ» ብዙ የቃል ኪዳን ባለቤቶችን ከፊትህ ካላደረክ ገነትን በኢየሱስ ይቅር ባይነት ላይ ብቻ ታምነህ እንዲህ በቀላሉ አታገኝም! የሚሉ መምህራንና ካህናት አሉ። «ስድስቱን ቃላተ ወንጌልንና ዐሠርቱ ቃላተ ኦሪትን» ለመፈጸም ከመፈለግ ይልቅ «ተአምሯን ለመስማት ተሽቀዳደሙ» የሚለውን ማደንዘዣ ዘወትር የሚያነበንቡ ልበ እውራን ካህናት አሉ። «ኢየሱስ ጌታ ነው»  (1ኛ ቆሮ 12፤3) ብሎ መጥራት ይህ የመናፍቅ አባባል ነው የሚሉና ይህንንም በመፍራት በአፋቸው የማስገቡ ካህናት አሉ።
ካህናተ ቤተ መቅደስ፤ ዓይነ ብርሃኑ የተመለሰለትን ሰው ከሰደቡ በኋላ «አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ» ብለው ለእነሱ ጸያፍ የመሰላቸው፤ ነገር ግን የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን ከመቻል የተሻለ እድል እንደሌለ ስለማያውቁ ራሳቸውን የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ከመሆን አግልለው «እኛ የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን» ማለታቸው ትልቁንና የተሻለው መጣላቸው መሆኑን አላወቁትም። እናውቃለን ይላሉ፤ አያውቁም፤ እናያለን ይላሉ እውራን ናቸው። አብ ስለወልድ ማንነት የገለጠላቸው ግን «ኢየሱስ ጌታ ነው» ሲሉ አያፍሩም። «በሩ እኔ ነኝ» ስላለ ዕለት ዕለት ያንን በር ብቻ ያንኳኳሉ። «አንኳኩ ይከፈትላችኋል» ያለው ቃል ስለማይታበል ተስፋቸው እሱ ነው።  የሌሎችን በር በመደብደብ፤ እባካችሁ ሂዱና ያንን «በሩ እኔ ነኝ» ያለውን ጌታ አስከፍቱልን ብለው በማስቸገር ባልተነገረ ድካም ውስጥ ራሳቸውን ሲያሽከረክሩ አይገኙም። እሱን በቀጥታ ለለመኑት አምላካችን የማያሳፍር በቃሉ የታመነ ተለማኝ ነውና።
«እኔም እላችኋለሁ። ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል»   ሉቃ 11፤9
የሚገርመውና የሚደንቀው ነገር ካህናተ ሌዋውያኑ «ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እናውቃለን» ሲሉ ቆይተው የደቀ መዝሙርነት ጉዳይ ሲነሳ የተናገሩትን ቃል ሸምጥጠው በመካድ «ይህ ሰው ከወዴት እንደሆነ አናውቅም» ሲሉ መገኘታቸው ነው። «እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እኛ እናውቃለን፥ ይህ ሰው ግን ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም አሉት» ዮሐ 9፤29  ከወዴት እንደሆነ ካላወቁት ከምን ተነስተው ነው « ይህ ሰው ኃጢአተኛ እንደሆነ እናውቃለን» ብለው ለመናገር ድፍረት ያገኙት?  ለዚህ ሁሉ ያላዋቂ ሳሚ ዓይነት ምላሻቸው ዋናው ምክንያት ካህናቱ ራሳቸውን የሚስሉት ከሌላው የተሻለ እውቀትና ማንም ያልደረሰበት ትምህርት እንዳላቸው ስለሚያስቡ ብቻ ነው። እውነትና ከአብ ዘንድ ስለወልድ ያለው መገለጥ ከሌላ ከማንም ዘንድ ሊኖር ይችላል ብለው በፍጹም አያስቡም። ቢኖር እንኳን ከእነሱ የተለየውን ሁሉ እንደኑፋቄና ክህደት ይቆጥሩታል።
በዘመናችን የወልድን መሲህነት፤ ብቸና አዳኝነትና ከምድር እስከሰማይ የተዘረጋውን ሕያው መሰላል በማንሳት ሌሎችን በምትክነት አበጅተው፤ ለምትክነቱም የሚጠቅም መከላከያ ምሽግ ቆፍረው የሚሟገቱ ካህናትና አዘጭዛጭ ማኅበራት አሉ።  «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው» ዮሐ 1፤52  የሚለውንና ከባለቤቱ ከራሱ የሰማነው ቃል አይበቃንም፤ የግብጻዊው መነኩሴ የህርያቆስም ይጨመርልን፤ አብሮም ይዳበል በማለት «አንቲ ውእቱ ሰዋስዊሁ ለያዕቆብ» መላእክት የሚወጡባትና የሚወርዱባት መሰላል አንቺ ነሽ (ቅዳሴ ማርያም) የሚሉ ካህናትና አዘጭዛጮች አሉ። ይህንን የቃል ልዩነት ለማስማማት ሲሉ አንዴ እናውቃለን፤ አንዴ ደግሞ አናውቅም የሚሉ ልበ እውራን አሉ። ራሳቸውን ከክርስቶስ ደቀ መዝሙርነት ሰልፍ አውጥተው እኔ የተክልዬ ልጅ፤ የሳማ ሰንበት፤ የዜና ማርቆስ፤ የአርሴማ፤ የሙሴ…………..የሚሉ አሉ። የአጵሎስና የኬፋ ዓይነት መሆኑ ነው።
«ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል። ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፥ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ። ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፥ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም። ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ስለዚህ አሽንክታባቸውን ያሰፋሉ ዘርፉንም ያስረዝማሉ፥ በምሳም የከበሬታ ስፍራ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥በገበያም ሰላምታና። መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ» ማቴ 23፤2-7 ዛሬም በተግባር አለ። ካህናቱ ያውቃሉ ግን እውነትን አያውቁም!!