Saturday, November 19, 2011

የመላእክት ተፈጥሮና ተልእኰ



ቅዱሳን መላእክት ተፈጥሮአቸው ረቂቅ ነው። አይጨበጡም፣አይዳሰሱም። ዳዊትም በመዝሙሩ እንዲህ ሲል ገልጿቸዋል። መዝሙር 104መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል»
ስለዚህ መላእክቱ መንፈስና እሳት ናቸው ማለት ነው። ስጋዊ ደማዊ አይደሉም። እርጅናና ሞት አይስማማቸውም። ምንም እንኳን መላእክት መንፈስና እሳት ቢሆኑ፣ እርጅናና የዚህ ዓለም ሞት ባይስማማቸው በራሳቸው ኃይል ምንም ሊደርጉ አይችሉም። ምክንያቱም እሳትና መንፈስ ያደረጋቸው ፈጣሪያቸው ገዢያቸውና ኃይላቸው እሱ ስለሆነ ነው። መላእክት ፍጡራን ስለሆኑ በቦታ ውሱን ናቸው። በሁሉም ስፍራ በአንድ ጊዜ የመገኘት ችሎታ የላቸውም። መላእክት ፍጡርና ውሱን ስለመሆናቸው መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ በቃሉ ይነግረናል። ለምሳሌ ያህል ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ድንጋይ ተንተርሶ በተኛ ጊዜ ከምድር እስከሰማይ በተተከለ መሰላል ላይ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ በህልም አይቷል። «ሕልምም አለመ እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፥ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር» ዘፍ 2812 መላእክቱ ውሱን ፍጥረት ስለሆኑ በዚያ መሰላል ላይ ይወጣሉ፣ ይወርዳሉ። በሁሉም ስፍራ የመገኘት ብቃት የላቸውም። በራሳቸው ምንም ማድረግ የማይችሉ ስለሆነ ነው በዚያ መሰላል ላይ የሚወጡት የሚወርዱት። ያም መሰላል ኢየሱስ ክርስቶስ ነበረ።
«እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው» ዮሐ 152 መላእክት የሚወጡበትና የሚወርዱበት ለመላእክት ሰማያዊ የኃይላቸው መሰላል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንን ራሱ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የተናገረው!
አንዳንዶች ግን ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ መላእክት ሲወጡበትና ሲወርዱበት ያየውን መሰላል እመቤታችን ማርያም ናት ይላሉ። «አንቲ ውእቱ ስዋስዊሁ ለያዕቆብ» የያዕቆብ መሰላል አንቺ ነሽ። (ቅዳሴ ማርያም)ይህ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው። ቅድስት ማርያም በዘመነ ያዕቆብ አልተፈጠረችም። ማርያም ከሐናና ከኢያቄም በሥጋ ተወልዳለች ካልን ከዚያ ቀደም በመንፈስ ነበረች ማለት ክህደት ነው። ማርያም መንፈስ ሳትሆን የሰው ልጅ ናትና፣ ስጋ ሳትለብስ በዘመነ ያዕቆብ በሰማይ ወይም በምድር የነበረችና መላእክት ይወጡባት፤ይወርዱባት ነበር ማለት ክርስቶስ ከእሷ የለበሰውን ስጋ አለመቀበል ነው። ይህ ደግሞ አደገኛ ክህደት ነው። ደግሞም ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው»ያለውን ቃል በማርያም ስም መለወጥ ኃጢአት ነው። ቅድስት ማርያም አምላክን በስጋ ስለወለደች ወደአምላክነት አልተቀየረችም። ዘመን የማይቆጠርላት ረቂቅ መንፈስ አይደለችም። (ሎቱ ስብሐት እንላለን)
ወደ ተነሳንበት ርእስ ስንመጣ መላእክት ለመውጣትም ለመውረድም የክርስቶስ ኃይል የሚያስፈልጋቸው ፍጥረታት መሆናቸውን እንረዳለን።




በሌላ ቦታም መጽሐፍ ቅዱስ ስለመላእክት ውሱንነት በደንብ ይነግረናል። በትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ ላይ እንዲህ የሚል ተጽፎልናል። ዳንኤል በምድረ ፋርስ በሀዘን ላይ በጾምና በጸሎት ተወስኖ በነበረበት ወቅት ከእግዚአብሔር ዘንድ አንድ መልአክ ተልኮለት ወርዷል። ዳን 1011 «እርሱም፦ እጅግ የተወደድህ ሰው ዳንኤል ሆይ፥ እኔ ዛሬ ወደ አንተ ተልኬአለሁና የምነግርህን ቃል አስተውል፥ ቀጥ ብለህም ቁም አለኝ። ይህንም ቃል ባለኝ ጊዜ እየተንቀጠቀጥሁ ቆምሁ» ይላል። ይህ መልአክ ግን ዳንኤል ካለበት ዘንድ ከመድረሱ በፊት የፋርስ መንግሥት አለቃ ይለዋል( ንጉሱን የሚመራው የሰይጣን መንፈስ) ማለት ነው። የተላከውን መልአክ ከዳንኤል ዘንድ እንዳይደርስ 21 ቀን በአየር ላይ ተዋግቶታል። በኋላም የመላእክት አለቃ ሚካኤል መጥቶ ሲያግዘው እሱ ወደ ዳንኤል መምጣት ችሏል። «የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሀያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ እነሆም፥ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ እኔም ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ተውሁት» ዳን 1013
የዚህ ዓለም ገዢ(ዮሐ1430) የተባለው ሰይጣን የፋርስ መንግሥት ገዢ መንፈስ ሆኖ ለዳንኤል የተላከለትን መልአክ 21 ቀን እንደተቋቋመው መልአኩ ራሱ ለዳንኤል ሲነግረው እናነባለን። ያኔም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ደርሶለታል። ሰይጣን ደግሞ በሌላ ጊዜም ከቅዱስ ሚካኤል ጋር ሲከራከር እንደነበር በይሁዳ መልእክት ላይ እናገኛለን። (ይሁዳ19)ሰይጣን ጳውሎስንም ከሚሄድበት መንገድ አዘግይቶታል።
«ወደ እናንተ ልንመጣ ወደን ነበርና፥ እኔ ጳውሎስም አንድና ሁለት ጊዜ፥ ሰይጣን ግን አዘገየን»1 ተሰ218
እንግዲህ ከላይ የምንረዳው የመላእክት ኃይል ውሱን መሆኑን፤ ከአንዱ መልአክ የአንዱ ሊበልጥ እንደሚችል፤የሚያዘገያቸው ነገር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል፣ ሰይጣን የሚከራከራቸው መሆኑን፣ የሚያሸንፉትም የስድብን ቃል በመናገር ሳይሆን«እግዚአብሔር ይገስጽህ» በማለት ስመ እግዚአብሔርን መከታ በማድረግ ኃይል እንደሆነ ነው።

መላእክት የተፈጠሩበትን ቀን የሚያመለክት ቁልጭ ያለነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተቀመጠም። ይሁን እንጂ መምህራን አባቶች በእለተ እሁድ(በመጀመሪያው ቀን) ስለመፈጠራቸው ያስተምሩናል። ሰይጣንም በዚሁ ቀን ብርሃን ከመገለጡ ቀደም ብሎ በትእቢቱና ስልጣንን በመሻቱ እንደወረደም ይነግሩናል። ይህንን የሚያጠናክር መረጃ ከትንቢተ ኢሳይያስ 1412-15« አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቈረጥህ! አንተም በልብህ ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ። ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ፣ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጕድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ» የሚለውን በማቅረብ ያስተምሩናል። አክሲማሮስ የተሰኘው የስነፍጥረት መጽሐፍንም በዋቢነት ያቀርባሉ። በጥቅሉ ግን ሰይጣን ከክብሩ የወደቀ መልአክ ነው።
ቅዱሳን መላእክት ግን ለእግዚአብሔር ተልእኮ ይፋጠናሉ። እግዚአብሔር ወደ ላካቸው ስፍራም ይሄዳሉ።«ያዕቆብም መንገዱን ሄደ፥ የእግዚአብሔር መላእክትም ተገናኙት።ያዕቆብም ባያቸው ጊዜ። እነዚህ የእግዚአብሔር ሠራዊት ናቸው አለ የዚያንም ስፍራ ስም መሃናይም ብሎ ጠራው» ዘፍ 321-2
ሎጥንም ቅዱሳን መላእክት ተልከው አድነውታል። «ጎህም በቀደደ ጊዜ መላእክት ሎጥን፦ ተነሣ፥ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ በከተማይቱ ኃጢአት እንዳትጠፋ እያሉ ያስቸኵሉት ነበር» ዘፍ 1915
መላእክት የምስራች ቃልን ያደርሳሉ። ለሶምሶን መወለድ ምስራች የተናገረው መልአኩ ነበር። «የእግዚአብሔርም መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ እንዲህ አላት፦ እነሆ፥ አንቺ መካን ነሽ፥ ልጅም አልወለድሽም ነገር ግን ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ» መሳ 133
መላእክት የተላኩበትን ፈጽመው ስማቸውን ሳይነግሩን ሊሄዱ ይችላሉ። «ሴቲቱም ወደ ባልዋ መጥታ። አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፥ መልኩም እንደ እግዚአብሔር መልአክ እጅግ የሚያስደነግጥ ነበረ ከወዴትም እንደ መጣ አልጠየቅሁትም፥ እርሱም ስሙን አልነገረኝም» መሳ 136
መላእክት የተራበውን ለማብላት የተጠማውን ለማጠጣት ሊላኩ ይችላሉ። «በክትክታውም ዛፍ በታች ተጋደመ እንቅልፍም አንቀላፋ እነሆም፥ መልአክ ዳሰሰውና። ተነሥተህ ብላ አለው፣ሲመለከትም፥ እነሆ፥ በራሱ አጠገብ የተጋገረ እንጎቻና በማሰሮ ውኃ አገኘ። በላም ጠጣም፥ ተመልሶም ተኛ። 1 ነገ 195-6
መላእክት ሰዎችን ለተልእኰ ያፋጥናሉ። የሐዋ 826 «የጌታም መልአክ ፊልጶስን።፣ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ አለው»
እግዚአብሔርን ለሚፈሩና ለሚታዘዙ መልአክ ይላክላቸዋል። « እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ። ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል፣ ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው» የሐዋ 102-3
የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱሳንን ለማበረታታት ይላካል።
የሐዋ 2723-25 «የእርሱ የምሆንና ደግሞ የማመልከው የእግዚአብሔር መልአክ በዚች ሌሊት በአጠገቤ ቆሞ ነበርና፥ እርሱም፦ ጳውሎስ ሆይ፥ አትፍራ፤ በቄሣር ፊት ልትቆም ይገባሃል፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር የሚሄዱትን ሁሉ ሰጥቶሃል አለኝ። ስለዚህ እናንተ ሰዎች ሆይ፥ አይዞአችሁ፤ እንደ ተናገረኝ እንዲሁ እንዲሆን እግዚአብሔርን አምናለሁና»
መላእክት የጌታ አገልጋዮች ናቸው።
«ያን ጊዜ ዲያብሎስ ተወው፥ እነሆም፥ መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር»ማቴ 411
የመጨረሻውን የዓለም መከር የሚያጭዱት መላእክት ናቸው። «እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፥ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፥ አጫጆችም መላእክት ናቸው» ማቴ1339
መላእክት የእግዚአብሔርን የምስጢር ቀን አያውቁም። «ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም»ማቴ2436
በጌታ ትእዛዝና በመላእክት አለቃ ድምጽ በክርስቶስ ለሞቱት ትንሳዔ ይሆናል።
«ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ» 1 ተሰሎ 416
ከላይ ያለተጨማሪ ማብራሪያ እያየነው የመጣነው በነጥብ የተቀመጡት ጥቅሶች ሲጠቃለሉ ቅዱሳን መላእክት ለማዳን፤ ለማስተማር፤ የምስራችን ቃል ለመንገር፤ ለማበርታት፤ ለማወጅ፣ ለማገልገልና ለማመስገን የተመረጡ መሆናቸውን ነው።
እነዚህ ቅዱሳን መላእክትን የተመለከተ ሲሆን የወደቁት መላእክትስ ምን ይሰራሉ? የሚለውን እንመልከት!
የወደቁ መላእክት
አለቃቸው ዲያብሎስ ነው፣


 ስራቸው

ዋና ዋና ስራዎቻቸው 5 መደብ ሊከፈል ይችላል።
1/የእግዚአብሔርን ዓላማ መቃወም። ለዳንኤል የተላከውን መልአክ 21 ቀን እንደተዋጉት ማለት ነው።
2/ የዚህ ዓለም ገዢ ሆኖ መንግሥታትን፣ ነገሥታትን አገልጋዩ ማድረግ (ዮሐ1231)(ራእ 1614)
3/ሰዎች አምነው እንዳይድኑ የወንጌልን ቃል ከሰው ልብ በመስረቅ። (ሉቃ 812)
4/ ኃጢአተኞችን በኃጢአታቸው፤ ቅዱሳንን በመልካም ስራቸው ዘወትር በመክሰስ። (ኢዮ17-8)
ዘካ 31-2 እርሱም ታላቁን ካህን ኢያሱን በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ቆሞ አሳየኝ፥ ሰይጣንም ይከስሰው ዘንድ በስተ ቀኙ ቆሞ ነበር። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ ሰይጣን ሆይ፥ እግዚአብሔር ይገሥጽህ ኢየሩሳሌምን የመረጠ እግዚአብሔር ይገሥጽህ በውኑ ይህ ከእሳት የተነጠቀ ትንታግ አይደለምን? አለው።
ራእ1210 ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦ አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፥ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።
5/ የእግዚአብሔርን ቃል በማጣመም። (የሐዋ 1310)(2 ጴጥ 316)(መዝ 565) ዘፍ 31 እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበረ። ሴቲቱንም፦ በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት። ብሎ እንደተናገረው ዛሬም እንዲሁ ይሰራል። ለሃይማኖቶች መበራከትና የየራሳቸውን ስም ይዘው ራሳቸው ብቻ ጻድቅ፣ ሌላው ግን የውሸት መሆኑን የሚያስተምሩት ባጣመመው ቃሉ የተነሳ ነው።
ሌላውን ዐመጻና ኃጢአት ሁሉ የሚሰራውና የሚያሰራው በእነዚህ ነጥቦች ላይ ተንተርሶ ነው።
ሰይጣን(ዲያብሎስ) አብረውት የወደቁ የአጋንንት ሰራዊት አሉት። እነሱን በማሰማራት ይዋጋል።
ከእግዚአብሔር ፈቃድ ሲያገኝ ሊፈትን ይችላል። ኢዮብን እንደፈተነው ማለት ነው። ከሰማይ እሳትን ሊወረውር፣ አውሎ ንፋስን አስነስቶ ሊያጠፋ፣ ጦረኞችን አስነስቶ እልቂት ሊያደርስ ይችላል። ከዚያም አልፎ ተርፎ ስጋን መግደልም ይችላል። ኢዮ 117 (ማቴ 1028)ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ» እንዳለው።
ሰይጣን ይህን ማድረግ የመቻል ብቃት ቢኖረውም የወደቀ መልአክና በክርስቶስ መስቀል ከቅድስና መንገዳችን ላይ የተወገደ ነው። ቆላስ 214 የምናሸንፍበትን ኃይል አግኝተናል። ኤፌ 320 «እንግዲህ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው»
«በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል»

ማጠቃለያ፣

ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔር አገዛዝና ሥልጣን ስር ያሉ፤ የሚታዘዙ፤ የሚላኩ፤ ፈቃዱን የሚፈጽሙና ዘወትር የሚያመሰግኑ ናቸው።
ውዱቃን መላእክት፤ ከእግዚአብሔር አገዛዝ ስር ያሉ ግን ከስልጣኑ ያፈነገጡ፤የማይታዘዙ፤ የማይላኩ ፈቃዱን የማይፈጽሙና የማያመሰግኑ ናቸው። በአገዛዙ ስር ስላሉ ያለፈቃዱና ያለእውቅናው አንዳች ማድረግ አይችሉም። ኤፌ 21 «አሁን ያሉት በአየር ላይ፣ በምድር ላይና በሲኦል ሲሆን በመጨረሻበበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው።ም በገሀነም ይኖራሉ»
ሉቃ833 አጋንንትም ከሰውዬው ወጥተው ወደ እሪያዎች ገቡ፥ መንጋውም ከአፋፉ ወደ ባሕር ተጣደፉና ሰጠሙ»
የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ቸርነትና ምሕረት የበዛለት በአርአያውና በአምሳሉ ስለፈጠረው ነው። ያም ጥልቅ በሆነው የእግዚአብሔር ፍቅር አማካይነት በአንድያ ልጁ እንዲድን አስችሎታል። «ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ፣ ወአብጽሖ እስከለሞት» የተባለውም ለዚህ ነው።
አምላካዊ ጥበቃውንና ድጋፉን በቅዱሳን መላእክቱ በኩል ያደርግልናል። ቅዱሳን መላእክቱም እግዚአብሔር በላካቸው ስፍራና ቦታ ተገኝተው ትእዛዛቱን ይፈጽማሉ። ቅዱሳኑ መላእክት ግን ትእዛዝ ሳይደርሳቸው የትም አይንቀሳቀሱም። የሰው ልጅ በሰው ሰውኛነት የመረጠውን መልአክ ስለጠራ ወይም ስለለመነ መልአኩ ስሜ ስለተነሳ ልሂድ፤ልውረድ አይልም። እንኳን ተጠርቶ፣ ሳይጠራ ከተፍ የሚለው ሰይጣን ብቻ ነው። ከቅዱሳን መላእክት ከተማ ውጪ ያለው እሱና ሰራዊቱ ናቸው። በእዚህ ምድር ያለውን የሰው ልጆች የሚንከባከበን የሁሉ መገኛ የእግዚአብሔር ጥበቃና መግቦት ነው። ነቢዩ ዳንኤልን በጾም በጸሎቱ ወቅት ይጠብቀውና ያጸናው የነበረው የእግዚአብሔር ኃይል ነበረች። መልአኩንማ 21 ቀን እንዳይደርስ ጠላት ሲዋጋ አቁሞት ነበር።
ስለዚህ ቅዱሳን መላእክትን እናከብራቸዋለን፤ ይራዱናል፤ ያግዙናል ስንል እነርሱን በተለየ ስም በምናደርግላቸው ጥሪና ልመና ሳይሆን ለእግዚአብሔር በምናቀርበው ጸሎት ተቀባይነት የተነሳ እኛ የማናውቀው መልአክ ሊላክልን ሲችል ብቻ መሆኑን እንረዳ!!
በተጨማሪ ገብሩ ወልዱ የተባሉ ጸሐፊ በሰይጣን ባህሪይ ላይ የጻፉትን መጽሐፍ ቢያነቡት ብዙ እንደሚጠቀሙ አምናለሁ።
ለሁሉም ነገር እግዚአብሔር አእምሮውን ለብዎውን ያሳድርብን፣አሜን።


Friday, November 18, 2011

ቅዱሳን መላእክት ትእዛዝ ይጠብቃሉ!


መልአክ የሚለውን ለማየት የግስ ዘሮቹን መመልከት ይጠቅማል። ይህንን በተመለከተ ዓይናማው የቤተክርስቲያን ሊቅ የነበሩት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(በማቅ ተሃድሶ ተብለዋል) «መጽሐፈ፡ሰዋስው፡ወግስ፡ወመዝገበ፡ቃላት፡ሐዲስ» በተሰኘው መጽሐፋቸው ገጽ 549 ላይ እንዲህ ሲሉ አትተዋል። ልኢክ፤ ልኢኮት(ለአከ፤ይልእክ) መላክ፤መስደድ ማለት ሲሆን ባለቤቱን ሲያመልክት ለአኪ ማለት ላኪ፤ ሰዳጅ ማለት ነው። መልአክ ማለት በቁሙ ሹመኛ፣ አለቃ ሲሆን በረቂቃን ፍጥረታት አጠራር ደግሞ በእለተ እሁድ ተፈጥረዋል የሚባሉትን የእግዚአብሔር መላእክቶችን ስም ይወክላል። ከዚህ የትርጉም ጽንሰ ሃሳብ የምንረዳው መላእክት ማለት የሚላኩ፣ የሚታዘዙ ፍጥረታት ሲሆኑ ላኪያቸው ወይም ሰዳጃቸው የፈጠራቸው እግዚአብሔር ነው ማለት ነው። በእለተ እሁድ ተፈጥረዋል የተባሉት መላእክት ማለት እንግዲህ የወደቁትንም መላእክት ጨምሮ ነው። የወደቁት መላእክት ላኪያቸውንና ሰዳጃቸውን ለመታዘዝ ባለመፈለጋቸው ከእግዚአብሔር ቅዱሳን የመባል ሀገር ወጥተው በጭለማ ሀገርና አሰራር ወዲያና ወዲህ እያሉ የሚኖሩ መላእክት ሆነዋል። ቅዱሳኑ መላእክት ግን ትእዛዝ ሲደርሳቸው በጌታ ሲላኩ እናያለን። «ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ፦ ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ አለ» የሐዋ 12፣11 ጴጥሮስን ሄዶ እንዲያድን የላከው ጌታ ነው። መልአኩ የተላከውም ጴጥሮስን እንዲያድን ነው። ቅዱሳን መላእክት እንደስማቸው ለሚገዙለት ጌታ ይላካሉ። አድኑ የተባሉትን ያድናሉ። እንዲሁም በመጨረሻው ዘመንም ቅዱሳኑ መላእክት ይላካሉ። «በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል» ማር13፣27 በሌላ ስፍራም እንዲህ የሚል አለ፤ «በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ»ዘጸ23፣20
እንግዲህ ቅዱሳኑ መላእክት ከምስጋና ከተማቸው፤ ሊታዘዙና ሊገዙለት ከወደዱበት የአምላካቸው ቃል (ልኢክ፣ልኢኮት) ሲደርሳቸው ብቻ ይወጣሉ እንጂ እንደወደቁት መላእክት በገዛ ፈቃዳቸው ወዲያና ወዲህ አይዞሩም፤አይሄዱም።
የወደቁት መላእክት ግን የሚከሱትንና የሚወነጅሉትን ሲፈልጉ፣ ሲያሳስቱ በገዛ ፈቃዳቸው ሲዞሩ ይኖራሉ። ሲዞሩ ነበር፣ ማሸነፍ ያልቻሉትን የእግዚአብሔር ሰው ኢዮብን መልካም ስራ አይተው የቀኑበትና ክስ ያቀረቡበት። «እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም። ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ»ኢዮብ 1፣7 እንግዲህ ራሱ ሰይጣን እንደተናገረው ዟሪና ምድርን ለክፋት ስራው የሚያስሳት፣ በራሱ ፈቃድ የሚመላለስ ሲሆን ቅዱሳኑ መላእክት ግን ስራቸው ፈጣሪያቸውን ማመስገን«...ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም» ራእይ4፣8 እንዳለው ምስጋና መስጠት ነው። መልእክት ሲደርሳቸው ደግሞ በመላእክት አለቃ ሚካኤል በኩል (1ኛ ተሰ4፣16 እና በይሁዳ መልእክት 1፣9) እንደተመለከተው ትእዛዙ ተፈጻሚ ይሆናል።
እንግዲህ ይህ ያለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ ነው። ቅዱሳኑ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ትእዛዝ ሲኖር ሰዎችን ያድናሉ፤ይረዳሉ፤ይታደጋሉ፤ይነግራሉ፤ ያስተምራሉ፣ በቅዱሳንና ንስሃ በሚገቡ ሰዎችም ይደሰታሉ። ያለእግዚአብሔር ትእዛዝ ግን የትም አይሄዱም፤ አይዞሩም። ይህንን የሚያደርግ ሰይጣን ብቻ ነው። ራሱ ምድርን አሰስኳት፣ዞርኩባት እንዳለው በኢዮብ 1፣7 ላይ። ምክንያቱም ከአገዛዙ ውጭ ለመሆን ባይችልም ከአገልግሎቱ ቁጥጥር ውጭ ያለው እሱ ስለሆነ ነው። በዚህ ዓለም እንኳን ከቤተሰብ ቁጥጥር ውጭ በመጥፎ ስነምግባሩ የተባረረ ልጅ ውሎና አደሩ እንደልቡ ሲሆን በስርዓት ያደገው ግን ቤተሰቡ ከሚያሰማራውና ከፈቀደለት ወይም ከሚገባው ቦታ ውጭ አይዞርም።
በመጨረሻም ሊሰመርበት የሚገባው ነገር እኛ የሰው ልጆች የትኛውንም መልዓክ ስለጠራነው ወይም ስለጨቀጨቅነው በምንፈልግበት ቦታ ሁሉ ስሙ ስለተጠራ አይመጣም። ለተልእኮ የተፋጠኑ ተላኪዎች እንጂ ከቁጥጥር ውጭ የወጡ ዟሪዎች አይደሉምና ነው። ምናልባት ዟሪውና ምድርን የሚያስሰው የክፉ መልአክ «የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና»2ኛ ቆሮ 11፣14 እንዳለው እኔ ሚካኤል ነኝ፤ እኔ ገብርኤል ነኝ ብሎ ሊመጣ ይችላል። ቅዱሳኑ መላእክት ግን ለሰዎች የሚደርሱት ጸሎታችን ወይም ጥያቄያችን ወይም ለቅሶአችንና ሀዘናችን በእግዚአብሔር ዘንድ ሲሰማና ምላሽ የሚሰጠን ሲሆንና ሲላኩ ይመጣሉ። ጸሎታችንና መልካም ስራችን በእግዚአብሔር ዘንድ ሲወደድ እንኳን ቅዱሳን መላእክት ቅዱሳን ሰዎችም ሊላኩልን ይችላሉ። ልክ ለቆርኔሌዎስ ጴጥሮስ እንደተላከለት ማለት ነው። «ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ»የሐዋ10፣31 እንዳለውና ጴጥሮስ እንደተላከለት ማለት ነው።
ከዚህ ውጭ ቅዱሳን መላእክትን ስንጠራ ከተፍ ይላሉ ማለት ስለቅዱሳን መላእክት ተፈጥሮና ተግባር ያለማወቅ ብቻ ሳይሆን ከተፍ የሚለው ብርሃንን የሚመስለውን ከተፎ ዟሪ ማንነት ያለመረዳትም ጭምር መሆኑ ያሳዝናል። ቅዱሳን መላእክት እኛ ለእግዚአብሔር በምናቀርበው ጸሎትና ልመና ከእግዚአብሔር ቃል በሚወጣ ትእዛዝ ብቻ ለዚያውም እኛ ይህኛው ጠንካራ ነው፤ ያኛው ሰይፍ አለው፤ያኛው ደግሞ ቁጡ ነው፣ይህኛው ርኅሩኅ ነው ብለን ስለመረጥን ሳይሆን እኛ የማናውቃቸው ከእልፍ አእላፍ መላእክቱ መካከል ለተልእኰ የተዘጋጁትን እሱ የፈቀደውን ይልካል። ያኔም ይራዱናል፤ያግዙናል፤ የታዘዙትን ሁሉ ለእኛ በደስታ ይፈጽሙልናል። ከዚህ ውጭ ግን ቁጡ ወይም ርኅሩኅ ወይም ዓለምን በእጁ ሊገለብጣት ነበር፤ የወረወረው ጦር እስከምጽዓት ይወርዳል ወዘተ የሚሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ድምጾች ቅዱሳን መላእክትን ከሚያውቁ ሰዎች የሚወጡ ድምጾች አይደሉም። ይልቁኑም ከዚያ ከተፍ ከሚልና የብርሃንን መልአክ ሊመስል ራሱን ከሚለውጠው ዟሪ የሚወጣ መሆን አለበት። ምክንያቱም ስማቸው ስለተጠራ የሚመጡ ወይም ስላልተጠራ የሚቀሩ ቅዱሳን መላእክት የሉምና ነው። እነሱ እንደሰይጣን ያለትእዛዝ ወዲያና ወዲህ አይዞሩም። የቅዱሳን መላእክትን ተልእኰና ተግባር የሚያውቅ ልቡናን ከላይ ይስጠን።አሜን።(በዚህ ርእስ ላይ በሰፊው እንመለስበታለን)

Wednesday, November 16, 2011

በትዳር መካከል ያለውን ችግር መፍታት



ባልና ሚስት ፍጹማን ባለመሆናቸው በዚህ ምድር ባሉበት ጊዜ በግልም ይሁን በጋራ ስህተት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ማሰብ አያዳግትም።ባለትዳሮች ሁሉ በሆነ ወቅትና ሁኔታ ውስጥ ይሳሳታሉ። መጠኑና ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ስህተት የማይሰሩ ባልና ሚስት የሉም። የአንዳንዶች በሰዎች ዘንድ ሲታወቅ የአንዳንዶች ደግሞ ሳይገለጥ ሊቀር ይጥላል።የአንዳንዶች ብዙ ኪሳራ የማያስከትል ሲሆን የአንዳንዶች ደግሞ ከእነርሱም አልፎ ትውልድን የሚጎዳ አሉታዊ ውጤት ያለው ይሆናል። ይህ ጽሑፍም መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ አድርጎ ይመለከታልና መልካም ንባብ ለባለትዳሮችና ትዳር ለመያዝ ላሰቡ ሁሉ!!

ሙሉውን ጽሑፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ