Friday, November 18, 2011

ቅዱሳን መላእክት ትእዛዝ ይጠብቃሉ!


መልአክ የሚለውን ለማየት የግስ ዘሮቹን መመልከት ይጠቅማል። ይህንን በተመለከተ ዓይናማው የቤተክርስቲያን ሊቅ የነበሩት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(በማቅ ተሃድሶ ተብለዋል) «መጽሐፈ፡ሰዋስው፡ወግስ፡ወመዝገበ፡ቃላት፡ሐዲስ» በተሰኘው መጽሐፋቸው ገጽ 549 ላይ እንዲህ ሲሉ አትተዋል። ልኢክ፤ ልኢኮት(ለአከ፤ይልእክ) መላክ፤መስደድ ማለት ሲሆን ባለቤቱን ሲያመልክት ለአኪ ማለት ላኪ፤ ሰዳጅ ማለት ነው። መልአክ ማለት በቁሙ ሹመኛ፣ አለቃ ሲሆን በረቂቃን ፍጥረታት አጠራር ደግሞ በእለተ እሁድ ተፈጥረዋል የሚባሉትን የእግዚአብሔር መላእክቶችን ስም ይወክላል። ከዚህ የትርጉም ጽንሰ ሃሳብ የምንረዳው መላእክት ማለት የሚላኩ፣ የሚታዘዙ ፍጥረታት ሲሆኑ ላኪያቸው ወይም ሰዳጃቸው የፈጠራቸው እግዚአብሔር ነው ማለት ነው። በእለተ እሁድ ተፈጥረዋል የተባሉት መላእክት ማለት እንግዲህ የወደቁትንም መላእክት ጨምሮ ነው። የወደቁት መላእክት ላኪያቸውንና ሰዳጃቸውን ለመታዘዝ ባለመፈለጋቸው ከእግዚአብሔር ቅዱሳን የመባል ሀገር ወጥተው በጭለማ ሀገርና አሰራር ወዲያና ወዲህ እያሉ የሚኖሩ መላእክት ሆነዋል። ቅዱሳኑ መላእክት ግን ትእዛዝ ሲደርሳቸው በጌታ ሲላኩ እናያለን። «ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ፦ ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ አለ» የሐዋ 12፣11 ጴጥሮስን ሄዶ እንዲያድን የላከው ጌታ ነው። መልአኩ የተላከውም ጴጥሮስን እንዲያድን ነው። ቅዱሳን መላእክት እንደስማቸው ለሚገዙለት ጌታ ይላካሉ። አድኑ የተባሉትን ያድናሉ። እንዲሁም በመጨረሻው ዘመንም ቅዱሳኑ መላእክት ይላካሉ። «በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል» ማር13፣27 በሌላ ስፍራም እንዲህ የሚል አለ፤ «በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ»ዘጸ23፣20
እንግዲህ ቅዱሳኑ መላእክት ከምስጋና ከተማቸው፤ ሊታዘዙና ሊገዙለት ከወደዱበት የአምላካቸው ቃል (ልኢክ፣ልኢኮት) ሲደርሳቸው ብቻ ይወጣሉ እንጂ እንደወደቁት መላእክት በገዛ ፈቃዳቸው ወዲያና ወዲህ አይዞሩም፤አይሄዱም።
የወደቁት መላእክት ግን የሚከሱትንና የሚወነጅሉትን ሲፈልጉ፣ ሲያሳስቱ በገዛ ፈቃዳቸው ሲዞሩ ይኖራሉ። ሲዞሩ ነበር፣ ማሸነፍ ያልቻሉትን የእግዚአብሔር ሰው ኢዮብን መልካም ስራ አይተው የቀኑበትና ክስ ያቀረቡበት። «እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም። ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ»ኢዮብ 1፣7 እንግዲህ ራሱ ሰይጣን እንደተናገረው ዟሪና ምድርን ለክፋት ስራው የሚያስሳት፣ በራሱ ፈቃድ የሚመላለስ ሲሆን ቅዱሳኑ መላእክት ግን ስራቸው ፈጣሪያቸውን ማመስገን«...ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም» ራእይ4፣8 እንዳለው ምስጋና መስጠት ነው። መልእክት ሲደርሳቸው ደግሞ በመላእክት አለቃ ሚካኤል በኩል (1ኛ ተሰ4፣16 እና በይሁዳ መልእክት 1፣9) እንደተመለከተው ትእዛዙ ተፈጻሚ ይሆናል።
እንግዲህ ይህ ያለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ ነው። ቅዱሳኑ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ትእዛዝ ሲኖር ሰዎችን ያድናሉ፤ይረዳሉ፤ይታደጋሉ፤ይነግራሉ፤ ያስተምራሉ፣ በቅዱሳንና ንስሃ በሚገቡ ሰዎችም ይደሰታሉ። ያለእግዚአብሔር ትእዛዝ ግን የትም አይሄዱም፤ አይዞሩም። ይህንን የሚያደርግ ሰይጣን ብቻ ነው። ራሱ ምድርን አሰስኳት፣ዞርኩባት እንዳለው በኢዮብ 1፣7 ላይ። ምክንያቱም ከአገዛዙ ውጭ ለመሆን ባይችልም ከአገልግሎቱ ቁጥጥር ውጭ ያለው እሱ ስለሆነ ነው። በዚህ ዓለም እንኳን ከቤተሰብ ቁጥጥር ውጭ በመጥፎ ስነምግባሩ የተባረረ ልጅ ውሎና አደሩ እንደልቡ ሲሆን በስርዓት ያደገው ግን ቤተሰቡ ከሚያሰማራውና ከፈቀደለት ወይም ከሚገባው ቦታ ውጭ አይዞርም።
በመጨረሻም ሊሰመርበት የሚገባው ነገር እኛ የሰው ልጆች የትኛውንም መልዓክ ስለጠራነው ወይም ስለጨቀጨቅነው በምንፈልግበት ቦታ ሁሉ ስሙ ስለተጠራ አይመጣም። ለተልእኮ የተፋጠኑ ተላኪዎች እንጂ ከቁጥጥር ውጭ የወጡ ዟሪዎች አይደሉምና ነው። ምናልባት ዟሪውና ምድርን የሚያስሰው የክፉ መልአክ «የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና»2ኛ ቆሮ 11፣14 እንዳለው እኔ ሚካኤል ነኝ፤ እኔ ገብርኤል ነኝ ብሎ ሊመጣ ይችላል። ቅዱሳኑ መላእክት ግን ለሰዎች የሚደርሱት ጸሎታችን ወይም ጥያቄያችን ወይም ለቅሶአችንና ሀዘናችን በእግዚአብሔር ዘንድ ሲሰማና ምላሽ የሚሰጠን ሲሆንና ሲላኩ ይመጣሉ። ጸሎታችንና መልካም ስራችን በእግዚአብሔር ዘንድ ሲወደድ እንኳን ቅዱሳን መላእክት ቅዱሳን ሰዎችም ሊላኩልን ይችላሉ። ልክ ለቆርኔሌዎስ ጴጥሮስ እንደተላከለት ማለት ነው። «ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ»የሐዋ10፣31 እንዳለውና ጴጥሮስ እንደተላከለት ማለት ነው።
ከዚህ ውጭ ቅዱሳን መላእክትን ስንጠራ ከተፍ ይላሉ ማለት ስለቅዱሳን መላእክት ተፈጥሮና ተግባር ያለማወቅ ብቻ ሳይሆን ከተፍ የሚለው ብርሃንን የሚመስለውን ከተፎ ዟሪ ማንነት ያለመረዳትም ጭምር መሆኑ ያሳዝናል። ቅዱሳን መላእክት እኛ ለእግዚአብሔር በምናቀርበው ጸሎትና ልመና ከእግዚአብሔር ቃል በሚወጣ ትእዛዝ ብቻ ለዚያውም እኛ ይህኛው ጠንካራ ነው፤ ያኛው ሰይፍ አለው፤ያኛው ደግሞ ቁጡ ነው፣ይህኛው ርኅሩኅ ነው ብለን ስለመረጥን ሳይሆን እኛ የማናውቃቸው ከእልፍ አእላፍ መላእክቱ መካከል ለተልእኰ የተዘጋጁትን እሱ የፈቀደውን ይልካል። ያኔም ይራዱናል፤ያግዙናል፤ የታዘዙትን ሁሉ ለእኛ በደስታ ይፈጽሙልናል። ከዚህ ውጭ ግን ቁጡ ወይም ርኅሩኅ ወይም ዓለምን በእጁ ሊገለብጣት ነበር፤ የወረወረው ጦር እስከምጽዓት ይወርዳል ወዘተ የሚሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ድምጾች ቅዱሳን መላእክትን ከሚያውቁ ሰዎች የሚወጡ ድምጾች አይደሉም። ይልቁኑም ከዚያ ከተፍ ከሚልና የብርሃንን መልአክ ሊመስል ራሱን ከሚለውጠው ዟሪ የሚወጣ መሆን አለበት። ምክንያቱም ስማቸው ስለተጠራ የሚመጡ ወይም ስላልተጠራ የሚቀሩ ቅዱሳን መላእክት የሉምና ነው። እነሱ እንደሰይጣን ያለትእዛዝ ወዲያና ወዲህ አይዞሩም። የቅዱሳን መላእክትን ተልእኰና ተግባር የሚያውቅ ልቡናን ከላይ ይስጠን።አሜን።(በዚህ ርእስ ላይ በሰፊው እንመለስበታለን)

Wednesday, November 16, 2011

በትዳር መካከል ያለውን ችግር መፍታት



ባልና ሚስት ፍጹማን ባለመሆናቸው በዚህ ምድር ባሉበት ጊዜ በግልም ይሁን በጋራ ስህተት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ማሰብ አያዳግትም።ባለትዳሮች ሁሉ በሆነ ወቅትና ሁኔታ ውስጥ ይሳሳታሉ። መጠኑና ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ስህተት የማይሰሩ ባልና ሚስት የሉም። የአንዳንዶች በሰዎች ዘንድ ሲታወቅ የአንዳንዶች ደግሞ ሳይገለጥ ሊቀር ይጥላል።የአንዳንዶች ብዙ ኪሳራ የማያስከትል ሲሆን የአንዳንዶች ደግሞ ከእነርሱም አልፎ ትውልድን የሚጎዳ አሉታዊ ውጤት ያለው ይሆናል። ይህ ጽሑፍም መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ አድርጎ ይመለከታልና መልካም ንባብ ለባለትዳሮችና ትዳር ለመያዝ ላሰቡ ሁሉ!!

ሙሉውን ጽሑፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

Wednesday, November 9, 2011

ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ!



ሮሜ 13፣7 «ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ»

ክብር ለአንድ ነገር ዋጋ መስጠትን ይመለክታል። ዋጋው ደግሞ በዓይነት፣በገንዘብ፣በጉልበትና
በሃሳብ ወይም በመንፈስ ሊገለጥ ይችላል። የሰው ልጅ በሕይወቱ ዘመን ይህንን ዋጋ ሲከፍል ኖሯል፤ ይኖራልም። ሰው ለፈጣሪውና ለሚያመልከው፤ ለሚበልጠው፤ ለሚወደው፤ ለሚፈራው፤ ለሚመራው ክብርን ይሰጣል። ምናልባት የሚሰጥበት መንገድና የሚሰጥበት ምክንያት ይለያይ እንደሆነ እንጂ ክብርን ስለመስጠት ሃሳብ ጥያቄን የሚያስነሳ ጉዳይ እንዳልሆነ እንስማማለን።

ሰው ፈጣሪው ስላደረገለትና ስለሚያደርግለት ነገር ሁሉ ክብርንና ምሥጋናን ይሰጣል። ክብርን የሚሰጠው ስለተደረገለት ብቻ ሳይሆን ፈጣሪ በመሆኑ ክብር ስለሚገባውም ጭምር ነው።

ነቢዩ ሙሴና ሕዝቡ እግዚአብሔር ከጠላት እንዳዳናቸው ደስታቸውን በዝማሬ ገልጠው ክብር ሰጥተውታል።

«በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩ። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ» ዘጸ ፲፭፣፩

ክብሩ ከፍ ከፍ ያለ፣ ኃይልና ሥልጣን በእጁ የሚገኝ፣ ማድረግ የሚፈልገውን ከማድረግ የሚከለክለው ለሌለ ምስጋና ይገባዋል ሲሉ ተገቢውን ክብር ሲሰጡ እናያለን። ስለተደረገላቸው ብቻ ሳይሆን ክብሩ ፍጹማዊ በመሆኑ ለመለኰታዊነቱ ተገቢ ክብር እንደሆነም ሌላ ሥፍራም እንደዚሁ ምሥጋና ሲሰጡ እናገኛቸዋለን።

«በተራራው ራስ ላይ በእስራኤል ልጆች ፊት የእግዚአብሔር ክብር መታየት እንደሚያቃጥል እሳት ነበረ» ዘጸ ፳፬፣፲፯

ክብሩ ታላቅና ሰው ሊቀርበው የማይችል መለኮታዊ እሳት ስለሆነ ክብርና ምስጋና የተገባው ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር በቦታና በሥፍራ አይወሰንም፣ መለኮታዊ አገዛዙ ሁሉን የመላ ስለሆነም ጭምር ክብር ይገባዋል። ሁሉን በሙላት መሸፈን የሚችል ያለእሱ ማንም የለምና።