Friday, May 31, 2013

የግብጽ ኮፕቲክ ፓትርያርክ ታዋድሮስ 2ኛ በዓባይ ግድብ ጉዳይ ላይ ቤተክርስቲያናቸው የሽምግልና ሚና እንድትጫወት በመሐመድ ሞርሲ አልተጠየኩም አሉ»

 የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበራትን የብዙ ዘመናት የበላይነትና የጠነከረ ቅርርብ መሠረት አድርገው በፖፕ ታዋድሮስ 2ኛ በኩል የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ ግፊት ለማድረግና የግጭት መነሻ እንዳይሆን ጫና እንዲያሳድሩ በመሐመድ ሙርሲ በኩል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል የሚል ሰፊ ዘገባ ይዘው የወጡትን የግብጽ ጋዜጦች መነሻ በማድረግ የፓትርያርኩ ጽ/ቤት መግለጫ ሰጥቷል። አናዶሉ የተባለው የዜና ወኪልም በቀጥታ ፖፕ ታዋድሮስ ጉዳዩን ያውቁት እንደሆነ በስልክ አነጋግሮአቸው በሰጡት ምላሽ  እንደገለጹት «የግብጽ ጋዜጦች ይህንን ዜና ከየት እንዳገኙት አላውቅም፤ ለእኔ በግሌ ከፕሬዚዳንት ሞርሲ በኩል  የኢትዮጵያን ግድብ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ጋር የሽምግልና ድርድር እንዳደርግ የጠየቁኝ ምንም ዓይነት ነገር የለም» በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

  የፓትርያርኩ ጽ/ቤት ለዜና ወኪሉ በተጨማሪ እንደገለጸው ጥያቄው ቢቀርብላቸው የኮፕት ቤተ ክርስቲያን በጉዳዩ ላይ ለመሥራት ምንም ቅሬታ የሌላት ቢሆንም መታወቅ ያለበት ነገር ግን፤  የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በሀገሪቱ መንግሥት የውሳኔ ሰጪነት ሥልጣን ውስጥ ምንም ድርሻ የሌላት መሆኑን መረዳት እንደሚያስፈልግ በመግለጫው ተመልክቷል። ለግብጽና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ጥቅምና ሰላም በሚበጅ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ዝግጁ ነን፤ ይህንን በተመለከተም የኢትዮጵያው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ሐምሌ 19/2013 ግብጽ በሚመጡበት ወቅት ስለግድቡ ጉዳይ እናነሳላቸዋለን በማለት ጽ/ቤቱ ያለውን ሃሳብ በተጨማሪ አስረድቷል። የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቀድሞ በነበራት ተደማጭነት በመንግሥት ላይ የምታሳድረው ተጽእኖ ባለመኖሩ በግድቡ ጉዳይ ላይ የጎላ ሚና ይኖራታል ተብሎ አይጠበቅም ሲል በዜና ዘገባው ላይ «አናዶሉ» የዜና ወኪል ያገኘውን ማብራሪያ መነሻ አድርጎ የራሱን ትንታኔ በመስጠት ስለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የወቅቱ አቅም እስከየት ድረስ እንደሆነ በግልጽ አስቀምጧል።
     ከዚሁ ጋር ተያይዞ የደርግን የውድቀት ቀን ተጠግቶ ግንቦት 20 የመፍሰሻ አቅጣጫው መለወጡ ስለተነገረው ታላቁ ኅዳሴ ግድብ የግብጽ ሚዲያዎች የጩኸትና የጦርነት ዜማ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። የጃማአ አል ኢስላሚያ ሙፍቲ የሆኑት ሼክ አብደል አክሄር ሐማድ ለተከታዮቻቸው ባሰሙት ንግግር እንደተጠቆሙት «ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ አቅጣጫ መቀየሯ በግብጽ ሕዝብ ላይ ጦርነት እንዳወጀች ያህል ይቆጠራል» በማለት ጠጣር መልዕክት አስተላልፈዋል። «አል አረቢያ» ለተሰኘው ቴሌቪዥን ጣቢያም በቀጥታ ስርጭት ባደረጉት ንግግር «የኢትዮጵያን ድርጊት የግብጽ መንግሥት በትዕግስትና በዝምታ ሊመለከተው አይገባም፤ የኢትዮጵያ ድርጊት በግብጽ ላይ የተፈጸመ የጦርነት አዋጅ ነው፤ ይህንን ድርጊት በፍጹም አንታገስም፤ በሽምግልና  ብቻ የሚፈታ ጉዳይ ስላልሆነ መብታችንን በኃይል እስከማስከበር መሄዳችን የግድ ወደሚል ሁኔታ ውስጥ እየገባን ነው» በማለት አቋማቸውን ለአድማጭ፤ ተመልካቹ በግልጽ ተናግረዋል። ግብጾች የሚጠብቀንን ግዴታ ሳንዘነጋ የዲፕሎማሲውን ጉዳይ ጎን ለጎን በማካሄድ ትኩረት መስጠት ይገባናል ማለታቸውም ተወስቷል።
    በሌላ በኩልም በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ወቅት የግብጽ ጦር አዛዥ የነበሩት ጀነራል ሞሐመድ አሊ ቢላል እንዳስገነዘቡት ግብጽ በዓባይ ግድብ ላይ የጥቃት እርምጃ ብትወሰድ  ቀጣናውን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚቀይረው ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ የጋራ ጥቅም ያላት ቻይናና የግብጽ ባላንጣ የሆነችው እስራኤልን ወደጉዳዩ እንዲገቡ ሊያደርጋቸው ስለሚችል ግብጽ በምትወስደው  የጥቃት እርምጃ ምንም ትርፍ አታገኝም ሲሉ ለአል አረቢያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ የረቡዕ 30/ 5/2013 ዕለት ስርጭት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
      የሰሞኑ የግብጽ ሚዲያዎች እያራገቡ የሚገኙበትን ዘገባ ስንቃኝ  ጦር፤ ጦር የሚሸት መንፈስን ባዘለ መልኩ መሆኑ  ምናልባትም አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ ባላቸው ዝቅተኛ ግምትና  ለራሳቸው ጥቅም አብልጦ የማሰብ ራስ ወዳድነት ሲሆን አንዳንዶቹም በከፍተኛ ፖለቲከኞች በኩል ሆን ተብሎ በማስፈራሪያ ሰበብ  የሚሰራጭና የግብጽ እርምጃ የት ድረስ ሊሄድ እንደሚችል ለኢትዮጵያ መንግሥት መልዕክት ለማስተላለፍ ተፈልጎ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። 
በዚህም ተባለ በዚያ «አስቀድሞ ነበር መጥኖ መደቆስ፤ አሁን ምን ያደርጋል ድስትን ጥዶ ማልቀስ» እንዳይሆን  አንዴ የገቡበትን ሥራ ቀድሞ ባልጀመርነው ኖሮ ከማለት የኢትዮጵያ መንግሥት ከዲፕሎማሲው ጎን ለጎን ራሱን ማዘጋጀት ይገባዋል እንላለን። መንግሥት ልቡን ሰፊና እጁን ረጅም አድርጎ በፖለቲካ ያኮረፉትን በመጥራት በሀገር የጋራ ጉዳይ ላይ ማግባባት ወደሚችል የግል ሁኔታ ለመግባት የመድብለ ፓርቲውን ሥርዓት በር ከፈት ማድረግ አለበት።  እንደኢትዮጵያ ባለና ውጥንቅጡ በወጣ አመለካከት ውስጥ ልማት ብቻውን ሀገር አይገነባም። አሸባሪ የተባለ ማንም ተነስቶ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው ቢል አያስገርምም። ባራቅነውና በረገምነው ቁጥር መራቁ ባህሪያዊ ነውና። አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን በልማት ዜማ የማዳፈን ጉዳይ አኩራፊ ማበራከቱና ለጠላት በር መክፈቱ አይቀሬ ይሆናል። ግብጾች ራሳቸው መሥራት ያልቻሉትን የውጪ ሥራ በሌሎች እጅ ከማሰራት ይመለሳሉ ማለት የዋህነት ነው። 
ዓለማችን በአየር ለውጥ የተነሳ ሙቀቷ እየጨመረና በረሃማነትም እየተስፋፋ እንደመሄዱ መጠን አንድ ዓባይን ብቻ በተስፋ የምትጠብቅ ግብጽ በሆነ አጋጣሚ አንድ ክረምት ዝናብ በበቂ ባይጥልና ወንዙ ጎድሎ በትነት መጠኑን ከቀድሞው ቢቀንስባት ወደአጥፍቶ መጥፋት አትገባም ማለት አይቻልም። ረጅም እሳቤ ያለው እቅድ ለዓባይ የዛሬው ግድብ አስፈላጊው ነው እንላለን። 
እንዲያውም ስለዓባይ የተነገረው  የግብጽ ሸክም የሚራገፍበት ዘመን ደርሶም ይሆን? የሚል የትንቢት ጥያቄም እናነሳለን።
«ግብጻውያንንም በጨካኝ ጌታ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ ጨካኝ ንጉሥም ይገዛቸዋል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፦ ውኆችም ከባሕር ይደርቃሉ፥ ወንዙም ያንሳል ደረቅም ይሆናል። ወንዞቹም ይገማሉ፥ የግብጽም መስኖች ያንሳሉ ይደርቃሉም ደንገልና ቄጤማ ይጠወልጋሉ።  በዓባይ ወንዝ ዳር ያለው መስክ በዓባይም ወንዝ አጠገብ የተዘራ እርሻ ሁሉ ይደርቃል፥ ይበተንማል፥ አይገኝምም። ዓሣ አጥማጆቹ ያዝናሉ፥ በዓባይም ወንዝ መቃጥን የሚጥሉት ሁሉ ያለቅሳሉ፥ በውኆችም ላይ መረብ የሚዘረጉት ይዝላሉ» 
ኢሳ 19፤ 4-8

Thursday, May 30, 2013

በሰማንያ ወአሀዱ መጽሐፍ ሽፋን የተፈጸመው የጠላት ሴራ ሲገለጥ


(ክፍል ፩ )

መግቢያ፤

ሰይጣን የሰውን ልጅ ከሚያሳስትበት  አንዱ መንገድ የእግዚአብሔርን ቃል በማጣመም መተርጎም ነው። እግዚአብሔር አዳምን ከገነት ዛፎች መካከል አንዱን ሲከለክለው እንዲህ ብሎት ነበር። «ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና» ዘፍ 2፤17  ሰይጣን  ደግሞ ለዚህ ትዕዛዝ በመጀመሪያ የጥርጣሬ መንፈሱን በመርጨት «ሴቲቱንም፦ በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን?» ዘፍ 3፣1 ብሎ ከጠየቀ በኋላ ስለማይበላው የዕጽ ፍሬ አስፈላጊነት ራሱ መልሱን ሲሰጥ እናገኘዋለን። የምንጊዜም ምላሹ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል በተቃረነ መልኩ መሆኑ ነው። «እባብም ለሴቲቱ አላት። ሞትን አትሞቱም» ዘፍ 3፤4 እግዚአብሔር አምላክ ሞትን ትሞታላችሁ ሲል ሰይጣን ደግሞ ሞትን አትሞቱም ማለቱ የሀሰት አባት ያሰኘዋል። ከራሱ አመንጭቶ የሚናገር፤ ያመነጨውንም እውነት አስመስሎ የሚያቀርብ የክፋት ሁሉ ስር በመሆኑም ጭምር ነው። ሰይጣን እሱ ያመነጨውን ሀሰት አስቀድሞ ልበ ድኩም ፈልጎ  ይጭንና ሥራው ሁሉ በዚያ ሰው በኩል እየተላለፈ ለዓለሙ ሁሉ እንዲዳረስ ያደፋፍራል። ልክ የዘመኑ ትሮጃን ፈረስ የተባለው አንዱ ቫይረስ እየተራባ ኮምፒውተሮችን ሁሉ እንደሚያጠቃው ሰይጣን እውነተኛ ቃል አጣምሞ ሰዎችን ሁሉ ያጠቃል። ልዩነቱ የሰይጣን የጥቃት መሠረት የሰው ልጆችን ከእግዚአብሔር መንግሥት መለየት መቻሉ ስለሆነ ጥቃቱን የከፋ ያደርገዋል። ሰይጣን የጥርጣሬና የሞትን አትሞቱም መርዙን በቅድሚያ የረጨው በሔዋን ልቦና ውስጥ ሲሆን ስራው በትክክል ተቀባይነት ማግኘቱን ሲያረጋግጥ ትቷቸው ሄዷል። አዳምም የሞትን [ትሮጃን ሆርስ] ሃሳብ ከሚስቱ ተቀብሎ ተግባር ላይ ካዋለ በኋላ ውድቀቱን በማየቱ ረዳት የሰጠው እግዚአብሔርን በመክሰስ ለዚህ ሁሉ ውድቀቴ ምክንያቱ አንተ የሰጠኸኝ ሴት ናት በሚል ወቀሳ ሲያቀርብ እንመለከታለን።
« አዳምም አለ፦ ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ» ዘፍ 3፤12  ሔዋንም በተራዋ ጣቷን ወደእባብ ስታመለክት ማየታችን(ዘፍ 3፤13) የሰው ልጅ የራሱን ስህተት ባለመመልከት ሌላውን ስሁት አድርጎ የማቅረብ የዳበረ ልምድ እንዳለው ያረጋግጥልናል። ሰይጣን እስካለ ድረስ ድረስ ውጤታማ የሆነበትን ይህንን የማሳሳት ልምዱን ወደጥልቁ እስኪወረወር ድረስ ገቢራዊ ከማድረግ ለአፍታም እንደማያርፍ የቀደመ ሥራው ለዚህ ዘመንም አረጋጋጭ ነው። ሰይጣን ራሱ ሲጠየቅ በዓለሙ ሁሉ ለማሳሳት ያለዕረፍት እንደሚዞር መናገሩ በቂ ማስረጃ ነው።
«እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም። ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ» ኢዮብ 1፤7
ሰይጣን ምድርን ሁሉ የሚዞረው ስለአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ጥናት ለማካሄድ አለያም የተፈጥሮ ሀብት ክብካቤ ወይም የሰላምና ጸጥታ ሁኔታን መርምሮ ለማረጋጋት እንዳልሆነ እርግጥ ነው። መልካምነት ባህርይው ስላልሆነ ሰይጣን ዙረቱ ሁሉ ማጥፋት፤ ማሳሳት፤ መፈተንና መግደል ብቻ ነውና አሁን ድረስ እንደዞረ ነው። በዚህም ዘመን የሰው ልጆችን ዋና የሚያጠቃበት መሣሪያው ሰዎች እግዚአብሔርን ወደማወቅ እንዳይደርሱ፤ እውነቱን አውቀው ንስሐ እንዳይገቡ፤ የእግዚአብሔርን ቃል በመጋረድና በመከለል የስህተት መንገድ እንዲፈጠር በማድረግ ነው። ምክንያቱም ይህ ትውልድ የያዕቆብን አምላክ የሚፈልግ ነውና። «ይህች ትውልድ እርሱን የምትፈልግ ናት፥ የያዕቆብን አምላክ ፊት የምትፈልግ» መዝ 24፤6  በመጨረሻው ዘመን የመንግሥትም ወንጌል በዓለሙ ሁሉ እንደሚሰበክ አስቀድሞ ተነግሮ ነበርና። (ማቴ 24፤14) የቀረለት  ጊዜ  ጥቂት እንደሆነ ስለሚያውቅ እየዞረ ቃሉን በማጣመም እግዚአብሔር እንዳይመለክ ይጋርዳል፤ እውነት የሚመስል የስህተት ቃል እየፈጠረ ይከራከራል።
«ስለዚህ፥ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፥ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቍጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና» ራእይ 12፣12
ልክ እንደተወርዋሪ ኮከብ በዘመናት ውስጥ ብቅ ብለው (በቀደሙት ዘመናት፤ እንደአባ እስጢፋኖስ ፤በኋላም እንደአለቃ ታዬና አቡነ ፊልጶስ ጳጳስ ዘኢየሩሳሌም ወዘተ) ዓይነቶቹ ብርሃናቸውን አብርተው ሳይጨርሱ እልም ብለው የጠፉት ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ጠላት ባስቀመጠው እንቅፋት እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። ለዚህም ዋናው ነጥብ ጠላት ቤተክርስቲያኒቱ ጥንት ከምትቀበለውና በሐዋርያት መሰረት ላይ ከታነጸችበት አለት ላይ እያንሸራተተ በመከራ ወጀብ እንድትናጥ የሚያደርጋት የክፉ መንፈስ አሰራር በመንገሱ ነው። ወደዋናው የሰማንያ አሀዱ ገመና ከመግባታችን በፊት እስኪ አንዱንና  ፈጣሪን  ከፍጡራን ጋር አዳብሎ  በአምሳለ አምላክ የማስመለክ የጠላትን አሰራር አስቀድመን እንመልከት። ይህንን ቃል የማቅ አገልጋይ ዲ/ን ኅብረት የሺጥላ ከዚህ ቀደም እርሱ ከሚፈልገው መንገድ በመተርጎም የበለሱን ውበት እንዲያስጎመጅ አድርጎ አቅርቦት ነበር። ብዙዎችም ይህንን በለስ እየተቀባበሉ በማማሩ ተስበው ሲመገቡት ቆይተዋል። እስኪ ከዚያ እንጀምር።
1/ ፍጡርና ፈጣሪ አንድ ምስጋና ይገባቸዋልን?
«"ለእሉ ክሌቱ ፍጡራን ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ»  «ለእነዚህ ሁለት ፍጡራን/ለማርያምና ለመስቀል/ የፈጣሪ ምስጋና ይገባቸዋል፤ በክብራቸው ተካክለውታልና» የሚለውን ትርጉም ዲ/ን ኅብረት የሺጥላ እንዲህ ሲል በመተርጎም ዓይናችሁን  ግለጡና የበለሱን ውበት ተመልክቱ በማለት ያባብለናል።
«ይህ መጽሐፍ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጸሎት መጽሐፍ ነው፡፡ ለበርካታ መቶ አመታት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በተሐድሶ መናፍቃን ጠንካራ ትችትና ነቀፋ ቢደርስበትም አሁንም አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ስለቅዱስ መስቀል በተጓዳኝ አንሥቶ ይናገራል፡፡ ካለ በኋላ ዲ/ኑ በመቀጠል ፤በመስተብቁዕ ዘመስቀል ላይ የሚገኘው ‹‹እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ›› የሚለው የግዕዝ ዐረፍተ ነገር ወደ አማርኛ ‹‹በክብር ተመሳስለዋልና›› ተብሎ መተርጎም ሲኖርበት ወደ አማርኛ የመለሰው ክፍል ‹‹በክብር ተካክለዋልና›› ብሎ ስለተረጎመው አንባቢን የሚያሳስት ሊሆን ችሏል፡፡ ስለዚህ ዋናው ችግር የመጽሐፉ ሳይሆን ከግዕዝ ወደ አማርኛ የመለሰው ሰው ነው፡፡በዚህ ዐረፍተ ነገር ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው ቃል ‹‹ዐረየ›› የሚለው ግሥ ነው፡፡ ‹‹ዐረየ›› ሁለት ፍቺ አለው፡፡ አንደኛው ‹‹ተካከለ›› ማለት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ‹‹ተመሳሰለ›› የሚል ነው፡፡ «ዐረየ» በመለኮት «ተካከለ» እንደሚባል ነግሮን «ዐረየ« የሚለው «ተመሳሰለ» ተብሎ የሚተረጎምበትን ምክንያታዊ ጭብጥ ሳይነግረን ዝም ብሎ አልፎታል። «ማርያምና መስቀል፤ ከፈጣሪ ጋር ተመሳስለዋል » ተብሎ ቢፈታ ትንሽ የላላ መስሎት ከሆነ ፍጡርና ፈጣሪ በምን ሊመሳሰሉ እንደሚችሉ ሊነግረን የግድ ይሆናል። ያለበለዚያ «ለእሉ ክልዔቱ ፍጡራን ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ» ለእነዚህ ሁለቱ ፍጡራን የፈጣሪ ምስጋና ይገባቸዋል» በማለት የስህተት ቃል በቀደመችው ቤተክርስቲያን ውስጥ ጠላት የተከለውን ስህተት ዲያቆኑ ደግሞ  የዘርዓ ያዕቆብን  ሌጋሲ ለማስቀጠል ካለው ፍላጎት የመነጨ ከመሆን አይዘልም።
እንግዲህ ይህ ሰው መስተብቁዕን አይቶ አያውቅም ወይም ግሱን ከመጻሕፍት አላገላበጠም። ካልሆነም ደግሞ እባብ ያሳየውን የበለሱን መልክና ውበት ተቀብሎ እያገለገለ ነው ማለት ነው። «ተዐረዩ በክብሮሙ» በክብር ተካክለዋልና የሚለውን ቃል «በክብር ተመሳስለዋል እንጂ ተካክለዋል ማለት አይደለም በማለት ሊያዘነጋን ይሞክራል። ስሁት መንገዱን ከፍቶ ኑ በዚህ ሂዱ እያለ የሞትን በለስ ጎዳና ያመላክተናል። ትርጉሙን ስንመለከት «ዐርይ» ማለት በገቢር መምሰል፤ መተካከል፤ ትክክል መሆን ሲሆን በተገብሮ ደግሞ ተካከለ፤ ተመሳሰለ ማለት ነው።  በፈጣሪነት ባህርይ፤ በሥራው ካልተስተካከለው ወይም ካልመሰለው፤ አከለው፤ መሰለው ማለት አንችልም። አለበለዚያም መመሳሰልን ወደምድራዊ የሰዎች ሚዛን በማውረድ «መስቀልን፤ማርያምንና ክርስቶስን» ወደመለካት ክህደት ውስጥ የባሰ መውረድ ይሆናል። ዲያቆኑ በዚያ መንገድ ተመልከቱ እያለ መገኘቱ ከማይወጣው ድቅድቅ ውስጥ እየገባ ነውና የምታውቁት እባካችሁ ምከሩት። ንስሐም ይግባ!
ስለመለኮት  ዕሪና ስንናገር አንዱ ከሌላው ጋር የተካከለ/እኩል የሆነ/፤ የተስተካከለ/ከፍታና ዝቅታ የሌለው/፤ ምንም ያልተለየ ፤ፍጹም አንድ የሆነ ማለት ነው። አምላክ፤ ወልደ አምላክ ኢየሱስን ከማርያምና ከመስቀል ጋር ማመሳሰልም ሆነ ማስተካከል አይቻልም። «ለእሉ ክልዔቱ ፍጡራን ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ» ለእነዚህ ሁለቱ ፍጡራን የአምላክ ምስጋና ይገባቸዋል» ማለት የአምላክነት ባህርይን ይጋራሉ ማለት ሲሆን ምክንያታዊ ንጽጽሩን ሲያቀርብ ደግሞ «እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ» በክብር ተካክለውታልና በማለት ያመጣዋል። የፈጣሪነት ክብር ከፍጡርነት ክብር ጋር ሊተካከልም ሆነ ሊመሳሰል በፍጹም አይችልም። ቅድስት ማርያም ኢየሱስን በመውለዷ ወደአምላክነት አልተቀየረችም። መስቀሉም ኢየሱስ ስለሞተበት አምላክ ወደመሆን አልተለወጠም። ፍጡር በፈጣሪ ይከብራል እንጂ ከማንም የማይቀበልና ማንም ሊወስድበት የማይችል ክብር ያለውን አምላክ ከፈጣሪ ጋር ተመሳሳይ ምስጋና ይገባቸዋል ማለት ትልቅ ክህደት ነው። ጸጋ ተቀባይ ቢከብር ከሰጪው ቸርነት እንጂ  ራሱ ባለው አምላካዊ የመሆን ብቃት አይደለም።
«ጸጋን የተመላሽ ክብርት ሆይ ደስ ይበልሽ» ብለን ማርያምን ስናመሰግናት ጸጋውን የመላት አንድያ ልጇ መሆኑን እንረዳለን። ብጽእት ማርያም እያለ ትውልድ ማመስገኑ ከአምላክ ጋር ስለተካከለች ወይም ስለተመሳሰለች ሳይሆን ከሴቶች ሁሉ ተመርጣ የአብ አንድያ ልጅ ኢየሱስን በሥጋ ስለወለደችው ነው።  ማርያም መውደድና ማክበር ወደአምላክነት እስክንቀይራት ድረስ እንድንሄድ  ሊያደርገን አይገባም። « ነፍስየሰ ትትሐሰይ፤ በአምላኪየ ወበመድኃኒትየ» ነፍሴ በአምላኬና በመድኃኒቴ ሀሴት ታደርጋለች ማለቷን ስንመለከት ድንግል ማርያም የትህትናና የእውነት እናት መሆኗን ነው። እኛ እውነቱን ስንናገር ማርያምን አትወዷትም በማሰኘት ሰይጣን በሌሎች አፍ ሊከሰን ይፈልጋል። ዝም ስንል ደግሞ በሌሎች አፍ አድሮ  እሷ እኮ ለአምላክ የሚሰጠው ምስጋናና አምልኮ ይገባታል እያለ ያታልላል። «ይህንን ዕፅ ብትበሉ ዓይናችሁ ይከፈታል» በማለት ለሔዋን ሹክ እንዳለው ዛሬም  ቅን በምትመስል ቃለ እግዚአብሔር ስር ተከልሎ አምላክ ብቻውን እንዳይመሰገን ለማስቀናት ሥራውን ይሰራል። እግዚአብሔር ራሱ ሁሉን የሰራ፤ ሁሉን የተሸከመና ከማንም ጋር እንደማይመሳሰል በቃሉ እንዲህ ሲል ይነግረናል።
«እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ፥ እስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለሁ እኔ ሠርቻለሁ እኔም አነሣለሁ እኔ እሸከማለሁ እኔም አድናለሁ።በማን ትመስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ? እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ?» ኢሳ 46፤5
ይቀጥላል…………….

Monday, May 27, 2013

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለምን ተሐድሶ ያስፈልጋታል?


ምንጭ፡-http://www.tehadeso.com/
ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር እና በክርስቶስ ደም የታደሱና የተቀደሱ የምእመናን ጉባኤ ናት፡፡ ይህቺን አማናዊት ቤተ ክርስቲያን ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ታሪኳን ስናጠና በእግዚአብሔር ሐሳብ ውስጥ የሰው ሐሳብ እየተቀላቀለ እና ጤናማውንና ርቱዕ የሆነውን አስተምህሮ የሚያደፈርሱ ሰብኣዊ፣ አጋንንታዊና ዓለማዊ ሐሳቦች በተለያየ ሁኔታና መንገድ ወደ አማናዊቷ ቤተ ክርስቲያን ዘልቀው እየገቡ እውነተኛ የሆነውን መንፈሳዊ ትምህርትም ሲያደፈርሱ እናያለን፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ያሉ ለእውነተኛው የእግዚአብሔር ሐሳብ ቀናዕያን የሆኑ ቅዱሳን የእግዚአብሔርን ሐሳብ በሚያደፈርሱ አስተሳሰቦች እና ግለሶቦች ላይ ጠንከር ያለ ተግሣጽ ሲሰጡና አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ ሲወስዱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናነባለን፡፡ ምክንያቱም ተሐድሶ አዲስን ነገር አፍልቆ ማምጣትና በነበረ እውነት ላይ መጨመር ሳይሆን ከጌታችንና ከሐዋርያት የተቀበልነውን የሚያድነውን መለኮታዊ መገለጥ (አስተርእዮ) የሚጋርድ ትምህርትና ድርጊት ሲከሠት መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ትምህርት ለመጠበቅ የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ስለሆነ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያናችንም ሐዋርያዊት በመሆኗ የተመሠረተችበት የእምነት መሠረት አማናዊ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን በየጊዜው ምንጫቸው የማይታወቅ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ዲያብሎስንና ሰብእን ከእውነት ይልቅ ሐሰትን የሚያገለግሉ አስተሳሰቦች እና አስተምህሮዎች በመስኮት እውነተኛው የእግዚአብሔር ሐሳብ ወደ ጎን ተትቶ መንፈሳዊ ሕይወታችን ታውኮ በእውነተኛው ትምህርት ላይ ሐሰት ተቀላቅሎበት መንፈሳዊ ቁመናዋ ተበላሽቶ እንመለከታለን፡፡
ይህንን መንፈሳዊ ዝቅጠት የተመለከቱ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና መምህራን በየዘመናቱ እርምት እንዲወሰድበት ሲታገሉና ሲያስተምሩ ቢኖሩም ከእግዚአብሔር ያልሆነው ከቅዱሳት መጻሕፍት (ከአሥራው መጽሐፍት) የሚቃረነው አዲስ ትምህርት እንዳይታረም በነገሥታቱ ተደግፎና ታግለውለት ሲቆይና ሌላ ጊዜ ደግሞ ጨዋው ከአባቶቼ የተቀበልኩት ትምህርት ስለሆነ በማለት በእውነተኛ የክርስትና ትምህርት ላይ እንደ እራፊ የተለጠፈውን ባዕድ ትምህርት ለማስጠበቅ ሊቃውንቱንና መምህራኑን አፉን ሞልቶ “መናፍቃን ናችሁ” ብሎ መከራና ስደት እንዲነሣባቸው በማድረጉ በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ብዙዎች ስለቤተ ክርስቲያንና ስለእግዚአብሔር እውነት በብዙ መከራ ሕይወታቸውን መሥዋዕት አድርገዋል፡፡ ሌሎችም ተሰድደዋል፤ ተደብድበዋል፤ ታስረዋል፤ ተራቁተዋል፡፡
ይህ በመሆኑና ዛሬም በወንጌል ትምህርት ላይ የተጨመረ አሳሳች ትምህርትን እንደ ዶግማ የሚቆጥሩ የተደራጁ የእውነት ጠላቶች በመኖራቸው ብዙ የማስፈራሪያ ድምፅ ስለሚያሰሙ መምህራኑ አፋቸው ተለጉሞ በመከራ አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ይህ አደጋ ክፉውን መንፈስ ሊያገለግሉ በቆረጡ ደጋፊዎቹ ታጅቦ ሙሉ በሙሉ የመንፈስ ቅዱስን ሐሳብ የሚዋጋ የዲያብሎስ ጦር ሆኖ ይታያል፡፡ እንዲህ ያለውን አደጋ ገልጦ ማሳየት እና ቤተ ክርስቲያን ወደ አማናዊው የክርስቶስ ሐሳብ እንድትመለስ ማድረግ የማንኛውም ጤናማ አእምሮ ያለው ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ግዴታ ነው፡፡ ከዚህም በመነሣት ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር ሐሳብ በመቅናት፣ ሰውን ሳይሆን እግዚአብሔርን በመስማት ቤተ ክርስቲያናችን ለምን ተሐድሶ እንደሚያስፈልጋት አስረጅ የሆኑ ምክንያቶችን እናቀርባለን፡፡
1.    በቤተ ክርስቲያኒቱ እንግዳ ትምህርቶች ስለበዙ
ክርስትናን በተመለከተ ከመሥራቹ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትና ከእርሱም ቀጥሎ ከእግሩ ሥር ቁጭ ብለው ከተማሩ ሐዋርያት ትምህርት የበለጠና የተሻለ ትምህርት አይገኝም፡፡ እነዚህ ትምህርቶች ለክርስትናችን ቋሚ መሠረት ሆነው የሚታዩና በምንም ሌላ እንግዳ ትምህርት ሊተኩ የማይችሉ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “እኛም ብንሆን ወይም የሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን” ብሎ በጻፈልን አምላካዊ ቃል ሙሉ በሙሉ መስማማት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው (ገላ. 1÷8)፡፡ ወደ ፊት በስፋት እና ነጥብ በነጥብ የምንተችበት ቢሆንም በአንዳንድ ገድላት፣ ድርሳናት እና ተአምራት ላይ ተጽፈው የሚገኙ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በቀጥታ የሚጋጩ እንግዳ ትምህርቶችን ቤተ ክርስቲያኒቱ በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ራስዋ ተመልክታ ልታስተካክላቸው ስለሚገባ ወደ እውነተኛውና ከአምላኳ ወደተቀበችው ትምህርት እንድትመለስ ተሐድሶ ያስፈልጋታል፡፡
እንግዳ ትምህርቶቹ መወገድ የሚገባቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህች ምድር ወርዶ የሰው ልጆችን ለማዳን በመስቀል ላይ የሠራውን ሥራ ስለሚያቃልሉ እና እነዚህን ትምህርቶች እውነት ናቸው ብለው የተቀበሉት ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ባለመቻላቸው አንዳንዶች እነዚህን እንግዳ ትምህርቶች የኢትዮጵያዊነት መለያ አድርገው ቢወስዱዋቸውም፣ እንደ እውነት ቢከራከሩላቸውም፣ የሰው ልጆችን ከኀጢአት እስር ፈትቶ የዘላለም ርስታቸውን መንግሥተ ሰማያትን እንዲወርሱ ያደረገው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው እንጂ ሌላ ምንም ነገር ስላይደለ ከሲኦል እስር ከዲያብሎስ ቁራኛነት ለመላቀቅ ከቃሉ ውጭ የሆኑ ሐሳቦችን ሽረን ለወንጌሉ እንግዳ የሆኑ ትምህርቶችን ትተን በጠራው የመስቀል መንገድ ላይ በእምነት መጓዝ በዚህ ዘመን ለቤተ ክርስቲያን ወሳኝ ጊዜ ስለሆነ ይህን ውድቀቷን በቃለ እግዚአብሔርና በመንፈስ ቅዱስ ምርመራ ከእንግዳ ትምህርቶች ልትለይ ይገባልና ተሐድሶ ያስፈልጋታል፡፡
2.    የእግዚአብሔር ቃል ተገቢውን ስፍራ ስላጣ
ሌላው ቤተ ክርስቲኒቱ ተሐድሶ እንደሚያስፈልጋት አስረጅ የሆነው እውነት ቅዱስ ወንጌል በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ተገቢውን ስፍራ ማጣቱ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉን መጽሐፍ ይመረምራል፣ ይመዝናል፤ እርሱ ግን  በየትኛውም መጽሐፍ አይመረመርም፤ አይመዘንም፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የተለየ ሐሳብ ያለው ማንኛውም በቤተ ክርስቲያን የምንገለገልበት  መጽሐፍ ሌላ ምንም አይነት አንድምታ ሳያስፈልገው ከስህተት ትምህርት ጎራ ሊካተት ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የሁሉ ዳኛ በሆነው በእግዚአብሔር መንፈስ በመጻፉና የእግዚአብሔርን እውነት በመያዙ ነው፡፡ አሁን  ግን ምንጫቸው የማይታወቅ እና በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃረኑ መጻሕፍት ከመጽሐፍ ቅዱስ እኩል መሳ ለመሳ በመቀመጣቸው እና መጽሐፍ ቅዱስን በመገዳደራቸው በእውርነት ልምራችሁ የሚሉንን መጽሐፎች ተገቢውን ስፍራቸውን ማሳወቁ አግባብ ስለሆነ ተሐድሶ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስፈላጊ ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ በስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር ወቅት ንጹሑን ወንጌል መስበክ እንደ መናፍቅነት እየተቆጠረ ስለመጣ አገልጋዮች የግድ የእግዚአብሔርን እውነት የሚጋፉ መጻሕፍትን እየጠቀሱ እነርሱም አገልግሎታቸውም የእግዚአብሔርን መንግሥት እውነተኛ ሐሳብ የሚቃረኑ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ የእውነተኛ ኦርቶዶክሳዊነት መሠረቱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እና በሐዋርያት አባቶች የተሰበከውን ቃል በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ማብራራት መሆኑ እየቀረ ድርሳነ ባልቴትን መተረክ እየሆነ ይገኛል፡፡
እንዲህ ያለው አስተሳሰብ በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ትክክለኛውን ተሐድሶ ካላገኘ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ ሙሉ በሙሉ መመሪያዋ እንዲሆናት ወደ እግዚአብሔር ቃል ካልተመለሰች አሁንም ቢሆን በየዕለቱ እየጨመረ የመጣውን የምእመናን ፍልሰት ማስቆም ይቸግራታል፡፡ ሰውን በስፍራው ለማጽናት የተሻለው እና እግዚአብሔርም የሚደሰትበት ትክክለኛው መንገድ የእውነትን ቃል በእውነት ሳያፍሩ እና ሳይሸሽጉ እንደ ጥንት አባቶቻችን ለሕዝቡ መግለጥ ነው፡፡ ለዚህም ቤተ ክርስቲያን ጤነኛ በሆነ የተሐድሶ ኣስተሳሰብ ልትቃኝ ያስፈልጋታል፡፡
3. የመዳንን እውነት የሚገዳደሩ ትምህርቶችን ማስተናገድ ስለጀመረች
የልጅ ቡኮ ዕለቱን ነው
ቢጋግሩት ነቀፋ ነው
ቢቀምሱትም የከረፋ
ቢጨብጡት ወዮ አበሳ
እንደተባለው መንፈስ ቅዱስን ሳያማክሩ ለአሸናፊው የእግዚአብሔር ሐሳብ ብቻ መገዛትን ትተው የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምሮ በማያውቁ እና ለስሜታቸው ባሪያ በሆኑ ሰዎች እየተፈጠሩ ያሉት አዳዲስ አስተምህሮዎች ሀይ ባይ ከልካይ አጥተው የክርስቶስን መስቀል እየወጉ ይገኛሉ፡፡ እኛም እንደ ቤሪያ ምእመናን “ነገሩ እውነት ይሆንን?” በማለት ለመመርመር ከመሞከር ይልቅ “ከኛ ወገን ያለ ሁሉ የሚለው ሁልጊዜ እውነት ነው” በሚል በጨዋ ምእመን አመክንዮ ተይዘን ለስህተት ትምህርቶች ተገዝተን እንገኛለን፡፡ እነዚህ የስህተት ትምህርቶች የመዳንን እውነት ቀስ በቀስ እየሸረሸሩ አሁን ፊት ለፊት መዋጋት ጀምረዋል፡፡ “ያለ ድንግል ማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም” የሚለውና እርሱን የመሰሉ ጥንተ ተፈጥሮዋቸው አጋንንታዊ የሆኑ እና “መዳን በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” (የሐዋ.ሥራ 4÷12) የሚለውን የመንፈስ ቅዱስ አዋጅ የሚሽሩ እንግዳ ትምህርቶች በመጽሐፍ ደረጃ ታትመው እስከ መሰራጨት ደርሰዋል፡፡
በእግዚአብሔር ቃል የተገለጸውን “መዳን በሌላ በማንም የለም” ተብሎ የተዘጋውን የጽድቅ ማኅተም የሚከፍቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጸው እውነት ውጭ  ሌላ አማራጭ አለ ብለው የሚያስተምሩ ሁሉ ለሰው መዳን ሳይሆን መጥፋት በአጋዥነት የሚሠሩ ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር የተያያዙ እና በዝክር፣ ወንዝ በማቋረጥ፣ ገዳማት በመሳለም፣ በቀብር ቦታ እና በሌሎችም ብዙ መንገዶች ሰው ሊድን ይችላል፡፡ ብለው የሚያስተምሩ ደፋር ብዕር የገለበጣቸው አጋንንታዊ ሐሳቦች ያሉባቸው ገድላት እና ተአምራት በመኖራቸው ሕዝቡ ያዳነውን ጌታ በእውነተኛ ማንነቱ ሳይረዳ በዋል ፈሰስ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
መዳን የህልውና ጉዳይ ስለሆነ በቀላሉ ሊታይ የሚችል አይደለም፡፡ እናቶቻችን እንደሚሉት “እስቲ ይሁና!! ምን ይታወቃል የአንድዬ ሥራ” በማለትም በቀላሉ ሊታለፍ የሚችል ነገርም አይደለም፡፡ የአንድዬ ሥራ የሚታወቅ እና በአደባባይ በመስቀል ላይ የተከናወነ ነው፡፡ አንድዬ ለመዳናችን ከደሙ የተሻለ አማራጭ አልሰጠንም፡፡ በመስቀል ላይ የፈሰሰውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ደም ለኔ ስለኃጢአቴ የተከፈለ ቤዛነት ነው ብሎ አምኖ መቀበል ለመዳን ዋነኛውም ብቸኛውም አማራጭ ነው፡፡
ነገር ግን ህዝቡ ይህንን እውነት አምኖ እንዳይቀበል የሚከለክሉ ሌላም አማራጭ አለህ ብለው የሚያስተምሩ በክርስቶስ የተሰጠንን መዳን ቀብረው ማሳሳቻ የሚሰብኩ ስለበዙ ቤተክርስቲያናችን ወደ ሐዋርያት ትምህርት እንድትመለስ መታደስ አለባት፡፡ መዳን በክርስቶስና በመስዋዕታዊ ሞቱ በማመን መሆኑን መቀበልና ማስተማር አዲስ ትምህርት የሚመስላቸው አሉ ግን አይደለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እና በተደጋጋሚ የተቀመጠ፣ ሐዋርያት የሰበኩት እስከ ዘመናችን ድረስ እውነተኛውን መንገድ የተከተሉ እንደ እነ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ ያሉ አባቶቻችን መዳን በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ የሆነ እና በክርስቶስ በማመን ብቻ የምንቀበለው ነው፡፡ ብለው ያስተማሩት ትምህርት ነው፡፡(ትምህርተ ሀይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት )
ስለዚህ በእነዚህ እና በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች ተሐድሶ ለቤተክርስቲያኒቱ ያስፈልጋታል ብለን እናምናለን፡፡ ለእናት ቤተክርስቲያናችን መታደስም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ እናገለግላለን፡፡
ይቀጥላል