በፒዲኤፍ ለማንበብ ( እዚህ ላይ ይጫኑ )
ብዙዎቹ የማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊዎች ድጋፋቸውን
የሚገልጹት በሃይማኖታዊ እውቀት ላይ ተመስርተው ሳይሆን ስሙን በቀባበት
የቅዱሳን መጠሪያ ስር ክርስቲያን በሚመስል ባህሪው ካጠመዳቸው ሱስ የተነሳ ነው።
ማኅበረ ቅዱሳንን ለማወቅ ውልደቱንና እድገቱን
መረዳት በጣም አስፈላጊው ነገር ነው። በዚያም ውስጥ የኖረበትን ውስጠ
ምስጢር ቀረብ ብሎ ማጥናትም በለበሰው ክርስቲያናዊ ካፖርቱ ስር ያለውን ማንነቱን ለመረዳት እጅግ አስፈላጊው ነገር ነው። ምክንያቱም
«መጽሐፍን በልባሱ፤ ሰውን በልብሱ አታድንቀው» የሚለውን ብሂል በመቀበል
ገቢር ላይ አውለን ለማድነቅም ይሁን ለመንቀፍ የሚያስችል ሙሉ እውቀት እንዲኖረን ስለሚያስችለን ነው። ካገኘናቸው ጭብጦች ተነስተን
ወደመንቀፉ ጥግ ስንደርስ በማኅበሩ ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ምልከታ ከጭፍን ጥላቻና ምሬት የራቀ እንዲሆን ያደርገዋል። ስንደግፈውና
ከፍ ከፍ ስናደርገውም ለመደገፍ የሚበቃን በጭብጥ ላይ የተመሰረተ እውቀታችን ከጭፍን ደጋፊነትና ከማኅበር አምላኪነት እንድንርቅ
ያግዘናል። ስለዚህ የማኅበሩን አዎንታዊና አሉታዊ ማንነት በይፋ ለመናገር ምን ጊዜም በተሟላ መረዳት ላይ በተመሰረተ እውቀት መሆን
እንዳለበት ለጥያቄ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። እኛን የሚነቅፉና የሚሳደቡ የማኅበሩ ደጋፊዎች እኛ ስለማኅበሩ ያለንን መረዳትና እውቀት
ለማወቅ ከመፈለግ ይልቅ ለደጋፊነት ያበቃቸውን መረዳት በእኛ ላይ ለመጫን እጃቸውን ሲወራጩ ይስተዋላሉ። የማኅበሩ ደጋፊዎች እንደሚያዩን
ሁሉ እኛም እነሱን የምናይበት ምልከታ ያለን ስለሆነ ልዩነቱ ከጭፍን ደጋፊነትና ከጭፍን ጥላቻ የወጣና የማኅበሩን ማንነት በማወቅ
ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከሁለታችን ይጠበቃል።
ማኅበረ ቅዱሳን እንዴት እንደተመሰረተ፤ እንዴት
እንዳደገ፤በዘመኑ ምን እንዳደረገ ብዙ ተነግሯል። ከልደት እስከ ጉርምስናው ብዙ ተጽፏል። በማኅበሩ የተሰለሉና የሕይወት ታሪካቸው
የተጠና ብዙ ሰዎችን በአስረጂነት ማቅረብ ይቻላል። በማኅበሩ አቅራቢነት በፖሊስ የተደበደቡ፤ ከስራ የተባረሩ፤ ሀገር ጥለው የተሰደዱ
ሰዎች ዛሬም በሕይወት ስላሉ የሚመሰክሩት ሐቅ ነው። የአንዳንዶቹንም ኃጢአትና በሥጋ ድካም የሰሩትን አበሳ ማኅበሩ በኃጢአት መዝገቡ ስምዓ ጽድቅ ጋዜጣ አስፍሮ ለሕዝብ በሽያጭ አቅርቦ
አስነብቦናል። ከዚህም በላይ የማኅበሩ መስራችና አባል ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ማኅበሩ ስላደረሰበት መገለልና ገፍትሮ ወደዳር የማስወጣት
የስውር አመራሩን ጡንቻ በተነተነበት ረጅም ጽሁፉ ያለውን የቅርብ እውቀት ምስክርነቱን ሲነግረን ስለማኅበሩ ያለንን እውቀት የበለጠ ያሳደገልን መረዳት ነው። እዚህ
ላይ ሳንጠቅሰው የማናልፈው ነገር ዳንኤል ከማንም ደጋፊ በላይ ስለማኅበሩ ያለውን እውቀት በጽሁፍ በገለጠ ጊዜ እርግማን ያዘነቡ
የማኅበሩ ደጋፊዎች፤ ውጥረቱ በእርቅ ፍጻሜ አግኝቷል ሲባል ደግሞ ምርቃት ለማዥጎድጎድ ጊዜ ያልወሰደባቸው መሆኑን ስናይ ደጋፊዎቹ
በማኅበሩ ላይ ያላቸው ድጋፍ በእውቀት ላይ በተመሰረተ መረዳት ሳይሆን በሱስ ፍቅር መጠመዳቸውን እንድረዳ ጋብዞናል። ዳንኤል የማኅበሩን ማንነት በጽሁፍ
ሲገልጥ፤ ማኅበሩ ያልነበረውን ማንነት ያን ጊዜ ከሰማይ ቧጥጦ የመጣ እንዳልነበረ ሁሉ ሲታረቅም ማኅበሩ የተገለጠበት ማንነት ወዲያውኑ
ብን ብሎ የሚጠፋ ሆኖ አይደለም። ታዲያ ለእርግማንና ለምርቃት ለምን ተጣደፉ ስንል የምናገኘው መልስ ድሮውንም ድጋፋቸው በስሜት
ስካር የተቃኘ መሆኑን ነው። ዳንኤልም ሲጣላም ይሁን ሲታረቅ ያሳደገውን ማኅበር ማንነት ጠንቅቆ ያውቀዋል። ምንም እንኳን ዳንኤል
ራሱ የችግሩ አካል መሆኑን ብናምንም ዳንኤል ከእርቅም በፊት ይሁን ከእርቅ በኋላ በማኅበሩ ላይ ስላለው ውስጥ አወቅ እውቀት ዛሬም
ቢሆን አብሮት አለ። በደንብ አውቆት የጻፈው መረዳት ቢታረቅም ባይታረቅም ከማኅበሩ ባህርይ አንጻር ማኅበሩ ያው ነው። እኛም ይህንን
ጠንቅቀን እንረዳለታለን። እንግዲህ ስለማኅበረ ቅዱሳን የሚኖረን ዙሪያ ገባ እውቀት የማኅበሩን ማንነት የበለጠ እንድንረዳ ስእል
የሚሰጠንና ይህም፤ ይህም አለ! እንድንል የሚያደርጉን ነጥቦች ከላይ የጠቃቀስናቸውና ሌሎችም ነገሮች ተደማምረው ነው።