Showing posts with label ትምህርት. Show all posts
Showing posts with label ትምህርት. Show all posts

Sunday, April 24, 2016

ትንሣኤ አንድ ነው፣ ሕይወትም እሱ ነው!



ቀልጣፋ ሬስቶራንቶች በቀላሉ የሚስቡን የፈለግነውን ምግብ በምንወደው መንገድ እንድናዝ መንገድ ስለሚከፍቱልን ነው። ጥቂት ካፌዎች ደግሞ ከመቶ በላይ የተለያዩ የቡና ጣዕም እንደሚያቀርቡ በጉራ ይናገራሉ። መኖሪያ ቤቶችና መኪናዎችን ስንገዛ እንኳ የምንፈልገው ምርጫ እንዲያሟላ እንሻለን። በቼኮላት፣ በቫኒላና በእንጆሪ ዓለም ታጥረን መኖር አንፈልግም። ፍላጎት ንጉሥ ነው! እንደግላዊ ፍላጎትህና ምርጫህ የምታገኝበት ሁሉ የተሟላበት ዘመን ነው። የዓይን አምሮትና ፍላጎትን የሚያሟላው ዓለም የእምነት መንገድንም ለዘላለማዊ ሕይወት ይበጃል ያለውን በአማራጭ አቅርቧል።

ታዲያ ለአንተ /ለአንቺ/ ትክክለኛ እምነት የማግኘቱ ሁኔታስ ምን ይመስላል?

ወቀሳ አልባ፣ ብዙ ጫና የሌለውና ይህንን አድርግ አታድርግ እያለ የማያስቸግር ሐይማኖት ብታገኝስ? ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ያውና እዚያ አለ እንደሚሉት ነገር፣ ሃይማኖት እንደሚወዱት አይስክሬም የሚመረጥ ነው እንዴ?
እድሜው፣ ሥርዓቱና ደንቡ ስለሚስብህ ይሆን? ወይስ በባለብዙ መንገድ የሕይወትህ ቤዛ ቃል ስለተገባልህ በአንዱ ላይ ተስፋህን ለማኖር?

ትኩረታችንን ለመሳብ የሚሻሙ በርካታ ድምፆች ስላሉ ለምን? ብሎ ነው አንድ ሰው ኢየሱስን ከሌሎች ማለትም ከመሐመድ ወይም ከኮንፊሸየስ፣ ከቡድሐ ወይም ቻርለስ ቴዝ ራስል ወይም ከጆሴፍ እስሚዝ አስበልጦ የሚመርጠው? ዞሮ ዞሮ ሁሉም መንገዶች የሚያደርሱት ወደ መንግስተ ሰማይ አይደለም እንዴ?

 “በኢየሱስ እናምናለን” የሚሉቱ ራሳቸው የማዳኑን ተስፋ የሚገልጡበት መንገድ የተለያየ ስለሆነ እንደገበያ ላይ ሸቀጥ ገብተን ድነትን የምንሸምትባቸው አይደሉም።
 በመሰረቱ ሁሉም ሃይማኖቶች አንድ አይደሉምና። እንደ እውነቱ ከሆነ ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ መንግስተ ሰማይ አያመሩም። ሁሉም መንገዶች ወደ ኢንዲያና መቼም አያደርሱም። የእምነት ድርጅቶች ሳይሆኑ ወደመንግሥቱ የሚያስገባው ላመኑበት ሁሉ “ኢየሱስ ብቻ ነው” የምንለው ማለት ስለፈለግን ሳይሆን እንድንል የሚያስገድደን እውነት ያለው በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ስለተፈፀመ ነው።

ኢየሱስ ብቻውን በእግዚአብሔር ሥልጣን ይናገራል።

1/ ምክንያቱም ኢየሱስ ብቻ ነው ሞትን ያሸነፈው። እስካሁን ድረስ መሐመድ፣ ኮንፊሸየስና ሌሎች በመቃብር በስብሰው ይገኛሉ። ነገር ግን ኢየሱስ በራሱ ስልጣን በጨካኙ የሮማውያን መስቀል ከሞተና ከተቀበረ ከሦስት ቀን በኋለ መቃብሩን ፈንቅሎ ተነስቶአል። በሞት ላይ ስልጣን ያለው ማንኛውም ሰው ትኩረታችን ሊስብ ግድ ይላል። ማንም በሞት ላይ ስልጣን ያለው ግለሰብ ሲናገር ልናደምጠው አስፈላጊ ነው። ሞትን ማሸነፍ የቻለ ከፍጥረታት መካከል ማንም የለም። ከሰማይ የመጣው ብቻ ሞትን አሸንፎ ወደሰማይ ወጥቷል።ስለዚህ እንዲህ ያለው አሸናፊ የተናገረው የእምነት መሠረት መሆን አለበት። ሰው ሟች መሆኑን ያውቃል። ሟች ደግሞ ከሞት ለማምለጥ የሚችለው በሞት ላይ ባለሙሉ ሥልጣን በሆነ ክንድ ላይ ሲያርፍ ነውና ኢየሱስን ማመን የግድ ይለዋል። በሞት ላይ ሥልጣን ያለው፣ ለሞታችን ብቸኛ ዋስትና የመሆን ብቃት አለው። ሌላ መንገድ፣ ሌላ ቃል ኪዳን፣ ሌላ አዳኝ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ማንም የለም። ይህንን እውነት ያለምንም ድርድር ማወጅ ያልቻለ እምነት፣ ምድራዊ የሃይማኖት ድርጅት እንጂ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ምስክር አይደለም።

2/ የኢየሱስ ሕይወትና ትንሣዔ ምስክር ያለውና እውነት ነው።
የኢየሱስን ትንሣዔ የሚደግፈው መረጃ የሚያጥለቀልቅ ነው። ሮማውያንና ሰቃልያኑ ካህናት የኢየሱስን መቃብር ማስጠበቅ ያስፈለጋቸው «በሦስተኛው ቀን እነሳለሁ» ያለውን ቃሉን ይዘው እንጂ የሞተ ሰው መቃብር ስለሚጠበቅ አልነበረም። አዎ ትንሣኤውን ለመከላከል ወታደሮች ከመቃብሩ ማንም እንዳይወጣ፤ ወደመቃብሩም ማንም እንዳይደርስ አድርገው አስጠብቀው ነበር። ነገር ግን የመቃብሩ ቦታ ባዶ ሆኗል! እንደተናገረው አልተነሳም እንዳይሉ የኢየሱስ ጠላቶች ያን ሁሉ ስለትንሣኤው የተነዛውን ወሬ ለማክሸፍ የበሰበሰውን አካሉን በማቅረብ በቀላሉ ያስታግሱት ነበር። ግን አልቻሉም፤ መላው ሲጠፋባቸው ደቀመዛሙርቱ ሬሳውን ሰርቀውት ይሆን? አሉ። ከሐዋርያቱ መካከል ከዮሐንስ በስተቀር ሌሎቹ የሸሹት በጊዜ ነው። የሸሹ ሰዎች ተመልሰው ከሮማ ወታደሮች ጋር ተዋግተው ሰረቁት ማለት የማይመስል ነገር ነው። የመቃብሩ ባዶ መሆን ሳያንስ ሞቶ የተቀበረ ሰው ዳግም ተነስቶ በሰዎች ፊት ራሱን በመግለጥ ያረጋገጠ በታሪክ ማንም የለም። ኢየሱስ ብቻ ይህን ማድረግ ችሏል።
ትንሣዔውን ያለምስክር ያልተወ ኢየሱስ ግን በአንድና በሁለት ሰዎች ፊት ብቻ ሳይሆን በአምስት መቶ ሰዎች ፊት ትንሣዔውን አስመስክሯል።

«መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ» 1ኛ ቆሮ 15፤4-8

ስለዚህ ሰዎች ኢየሱስን ለማመን የሚያስችላቸው በቂ የእምነት ማስረጃ ስላላቸው ነው። በዚህ ምድር ላይ ካሉ ሃይማኖቶች ውስጥ እንደኢየሱስ ሞትን ያሸነፈ፤ ትንሣኤውን በምስክር ያረጋገጠ ማንም የለም። ስለዚህ በሞት ላይ ሥልጣን ያለው ማንም ሰው ሊደመጥ ይገባል። ኢየሱስ በሞት ላይ ያለውን ሥልጣን አረጋግጧል። ስለዚህ የሚናገረውን መስማት ይገባናል። ለድነት ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ መሆኑን ራሱ ይናገራል።(ዮሐንስ 14፡ 6)። ኢየሱስ ክርስቶስ ካሉትም ብዙ መንገዶች አንዱ አይደለም። ኢየሱስ ብቸኛ የድነት መንገድ ነው። ሌላ መንገድ ሁሉ በትንሣኤና በሕይወት ላይ ሥልጣን የሌለው የሞት መንገድ ነው። በሞትና በትንሣኤ ላይ ሥልጣን በሌለው ማንኛውም የመዳን ተስፋ ቃል ላይ አትታመኑ። እውነት የምትመስል ነገር ግን የጥፋት መንገድ ናት። “በዚህና በዚያም ትድናላችሁ” የሚሉ ድምጾች መጨረሻቸው ሞት ነው። ሟች ለሟች የተስፋ መንገድ መሆን አይችልም።

3/ ኢየሱስ ከሸክም ያሳርፋል።

በዚህ ምድር ላይ ከሸክም አሳርፋችኋለሁ ብሎ ቃል የገባ አንድም ሥጋ ለባሽ የለም። ይህ ብቸኛ ኢየሱስ እንዲህ ይላል “እናንተ ደካሞች፤ ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደእኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” (ማቴዎስ 11፡ 28)። ሕይወትም አስቸጋሪ ነው። ብዙዎቻችን ደምተናል፣ ቆስለናል፣ ጦርነትንም እንፈራለን። ዓለምም አስጨናቂ እየሆነች ነው። ስለዚህ የሚያሳርፈንን ብንፈልግ ተገቢ ነው። ነገር ግን ከኢየሱስ በቀር ሸክም የከበዳችሁ ወደእኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ ያለ ማንም ሌላ የለም። በትንሣኤውና በሕይወቱ የታመነ ኢየሱስ ይህንን የማለት ብቃት ስላለው በእርሱ ላይ ማረፍ ከአስጨናቂው ዓለም ለመዳናችን ዋስትናችን ነው። ከድካማችሁ በማያሳርፉ በማንም ላይ አትታመኑ። ትድኑበት ዘንድ ብቸኛው ቃል ኪዳን ኢየሱስ ለመሆኑ “ወደእኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” የሚል ቃል ነግሮናልና ነው። በዚህ ተራራ ወይም በዚያ ሸለቆ የሚያሳርፍ ቃል የለም። ቃል፣ ቀራንዮ ላይ ስለእኛ አንድ ጊዜ ተሰጥቷል። በሞቱ ሞታችንን ሽሮ፣ በትንሣኤው ሕይወት በሰጠን በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ብቻ እንድንታመን የሚያስፈልገን የሚያስተማምን ምስክርነት ስለተወልን ነው።
ስለዚህ ምን ትፈልጋላችሁ? ከኃጢአት፤ ከድካም፤ ከተስፋ መቁረጥ በንስሐ መታደስ ወይስ የአንዱ ሃይማኖት አባል በመሆን ብቻ መኖር? ሕያው የሆነ አዳኝ ወይስ “ከሞቱት በርካታ ነቢያት ወይም ጻድቅ” አንዱን ተስፋ ማድረግ? ትርጉም ያለው ግንኙነት ወይስ ተራ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት መከተል?

4/ ኢየሱስ አማራጭ ሳይሆን ምርጫ ነው!

ሃይማኖት ማለት አንድ መንፈሳዊ ድርጅት ወይም የአንዱ ተቋም ስያሜና የዚያ አባል ሆኖ መኖር ማለት አይደለም። ከእግዚአብሔር አብ ጋር ትርጉም ያለው ግንኙነት ትፈልግ እንደሆን ሃይማኖትህ ኢየሱስን ማመን ነው። «በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው» ይላል መጽሐፍ። (ዮሐንስ 3፡ 36) አንዳንዶች ይህንንማ እናምናለን ነገር ግን ትክክለኛው እምነት ያለው በኛ ሃይማኖት ውስጥ ስለሆነ አባል ሁነን ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በማኅበር ስለመጸለይ ይነግረናል እንጂ ኢየሱስን ለማመን የዚህ ወይም የዚያ ሃይማኖት ተቋም አባል የመሆን ትዕዛዝ የለውም። ኢየሱስ በሱ የሚያምኑ ሁሉ እንዲድኑ እንጂ የሃይማኖት ድርጅት ሊመሠረት አልመጣም። ለጸሎት በኅብረት መሆን ቢያስፈልግ መጀመሪያውም መጨረሻውም የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ብቻ የሚከብርበት እንጂ ሰው፣ ሰው የሚሸትበት፣ ብቃትና የሰዎች ማንነት የሚደሰኮርበት ከሆነ ድርጅትን ማምለክ ይሆናል። በዚህ ዘመን ብዙዎች ተሰነካክለዋል።
 በራሱ ሥልጣን ከሙታን የተነሳ ማን አለ? ወይም በዓለም ላይ ካሉ የተለያዩ የሃይማኖት ድርጅቶች መካከል ለሰው ልጆች ዘላለማዊ የሕይወት ተስፋ ለመስጠት አስተማማኝ ማን አለ? መሐመድ፣ ኮንፊሽየስ፣ ራስል፣ ስሚዝ፣ ሉተር፣ ካቶሊክ፣ ኦርቶዶክስ፣ ፕሮቴስታንት ወዘተ ማንም ቢሆን ይህን ማድረግ አይችሉም።
እምነት ከሞት በላይ በሆነ በትንሣኤው ምስክርነት ላይ ይታመናል። ሕይወት ከድርጅት ሥልጣንም ባለፈ ብቸኛ የድነት መንገድ በሆነው ኢየሱስ ላይ ይጸናል።

“እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው” ዮሐ 6:47 ያለን ኢየሱስ ብቻ ነው።

Thursday, April 14, 2016

ውስጤ መኖር ያለበት ቃና ቲቪ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ ነው!!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከወዳጅ ጓደኞቼ ጋር በተገናኘን ቁጥር የመወያያ አጀንዳችን የሆነው ጉዳይ የዛሬውን ፅሁፍ እንድፅፍ አስገደደኝ፡፡ ዋና መቀመጫውን በዱባይ አድርጎ በቅርብ ጊዜ በሀገራቸን ስርጭቱን የጀመረው ቃና ቴሌቪዥን በአማረኛ እየተረጎመ (dubbing) በሚያቀርባቸው የቱርክ፣ የጣሊያን፣ የህንድ፣ የጃፓን እና የመሳሰሉት ሀገሮች ተከታታይ ፊልሞቹ የበርካታ ሰወችን ቀልብ እንደገዛ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ በእጅጉ የሚገርመው ደግሞ በዙሪያየ ያሉና የማውቃቸው በርካታ ክርስቲያኖች ጭምር ለእነዚህ የባህር ማዶ ፊልሞች እጅ ሰጥተው በጉጉትና በከፍተኛ ናፍቆት ሲጠብቁ ማየት ነው፡፡ የቃና ቲቪ ፊልሞች የሚታዩበት ሰዓት ደግሞ ወላጆች ከስራ፣ ልጆች ከትምምርት ቤት፣ ወጣቶችም ከሚውሉበት ስፍራ በቤት በሚሰበሰቡበት፣ የእግዚአብሔርን ቃል በሚያጠኑበት፣ በጋራ በሚፀልዩበት ሰዓት ነው፡፡ እውነትም በስጋ አይን ለተመለከታቸው ፊልሞቹ በከፍተኛ ሁኔታ የሰውን ቀልብ የመግዛት አቅም እንዲኖራቸው ሆነው ተሰርተዋል፡፡ አንደኛው ፊልም ሲያልቅ በቅፅበት ሌላው ይቀጥላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከምሽት 12፡00 ሰዓት የተቀመጠ ሰው እስከ ምሽት 4፡00 ሰዓት ሌላ ስራ ሳይሰራ ያለምንም እንቅስቃሴ ይቀመጥ ዘንድ ግድ ይለዋል ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ልብ እንበል የተቀማነው ወትሮ ለፀሎትና ለእግዚአብሔር ቃል ጥናት በእጅጉ ይመቸን የነበረውን ሰዓት ነው፡፡ ከዛም ደክሞን እንተኛለን፡፡ እዚህ ጋር ግን እንደመንፈሳዊ ሰው ልንነቃ የሚገባን ይመስለኛል፡፡ ሰባት በየቀኑ ለየአንድ አንድ አዓት የሚታዩ መሳጭ የባህር ማዶ ፊልሞች እቤታችን ድረስ መጥተው በራሳችን ቋንቋ እየተመለከትናቸው ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ቀድሞ ለጌታ የምንሰጠውን ሰዓት እየተውን፣ በፀሎት የምናሳልፈውን ጊዜ እየሸረሸርን ከክርስትና በእጅጉ የራቁ ሐገሮች ሰርተው በሚልኩልን ነገር ስንጠመድ የእነሱን ባዕድ፣ አምልኮ ኢ-ክርስትናዊ ነገሮች በሙሉ ወደ ውስጣችን እየሰገሰግን ነው፡፡ ልጆቻችንም ከክርስትና በእጅጉ ያፈነገጠ ነገር በየቀኑ እየተመለከቱ እንዲያድጉ እየተፈረደባቸው ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን በቆላስይስ 2፥8 ላይ ‹‹ እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ›› ብሎ በዓለማዊ ነገር እንዳንጠመድ ያስጠነቅቀናል፡፡ ኢየሱስም በማርቆስ ወንጌል 4፥24 ‹‹ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ›› ብሎ ከምንሰማውና ከምናየው እንድንጠበቅ ያዘናል፡፡ ዓለማችን ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ኢየሱስ በማቴዎስ ወንጌል ስለመጨረሻው ዘመን የተናገራቸውን የዘመን መጨረሻ ምልክቶች አንድ በአንድ አስተናግዳ ወደ ማገባደደዱ ትገኛለች፡፡ ብዙ ነገሮች ሆነዋል ብዙ ነገሮች ተፈፅመዋል፡፡ ባጠቃላይ ሰይጣን ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው አውቆ ከመቸውም ጊዜ በላይ በኃይለኛ ቁጣ እየተጋ ያለበት ዘመን ነው፡፡ ዲያብሎስ በዚህ ዘመን በተለይም ወጣቱን ክፍል ከቤተክርስቲያን ለማራቅ ወደ እግዚአብሔር ቃል ትኩረት እንዳያደርግ ከሚጠቀምባቸው ዋና ነገሮች መሀል የፊልምና የሙዚቃው ኢንደስትሪ እጅግ ወሳኙን ድርሻ ይዟል፡፡በዘመናችን የሚሰሩ ፊልሞች በአብዛኞቹ ሰወችን ለዓለማዊ ምኞትና ለርኩሰት አብዝተው የሚጋብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህም እኛ ክርስቲያኖች እንንቃ። ሰይጣን በረቀቀ መንገድ በእኛ ላይ እንዲሰለጥን እድል አንስጠው፤ የቱርክና የህንድ ፊልሞችን እያሳየ ከእግዚአብሔር መንግስት የሚለየን ጣቢያ ውስጣችን "ቃና ውስጤ ነው" እያልን ውስጣችን ሊሆንብን አይገባም፡፡ ምክንያቱም እኛ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ነን፡፡ ውስጣችን እሱ ብቻ ነው መኖር ያለበት። ብናምንም ባናምንም ዘመኑ የመጨረሻ ነው፡፡ ያኛው መንግስት እኛን በመዝናኛ ነገር ጠምዶ ከጌታ መንግስት ሊለየን እየተጋ ነው። እኛ ታዲያ ነቅተን ብዙ ምርኮ ልንበዘበዝ ሲገባን በወጥመዱ ከገባንለት እጅግ ከባድ ይሆናል፡፡ ስለዚህም እንንቃ በኢንተርቴመንት ስም ውድ ጊዜያችንን እንዳናስበላ፤ ይልቀንስ የእግዚአብሔርን ዓለምን በልጁ የመጠቅለል አላማ ለማሳካት አብሮ ሰራተኞች እንሁን!ስለወንጌል ግድ ይበለን፡፡
እኛ "መንፈስ ቅዱስ ውስጣችን ነው!"

Thursday, March 10, 2016

የተሸጠ ብኩርና!

(መነሻ ሃሳብ በደግፌ ጃክሰን)

  ነጠላ ያስረዘሙ ፈሪሳዊ ሰልፈኞች ከመጻሕፍቱ ጀርባ በኦርቶዶክሳዊ አቋቋም አደግድገው ቆመዋል። ከድንኳኑ ውጨኛው ክፍል "5ኛው የማኅበረ ቅዱሳን የመጻሕፍት ኤግዚቢሽን"የሚል ጽሑፍ በጉልህ ተጽፎ ተሰቅሏል። ሰይጣንም፣ ክፉውም፣ ጠማማውም፣ ነፍሰ ገዳዩም፣ ወንበዴውም፣ ሟርተኛውም ሰው "ቅዱስ ነኝ"ቢል በዚህ ዘመን የሚጠይቀው ስለሌለ (አሁን ጥያቄ የለም ማለት እስከመጨረሻው ጥያቄ የለም ማለት አይደለም) በቅድስና ማኅበር ስም የተጻፈውን ማስታወቂያ ካነበብኩ በኋላ ስለቅድስናው የሚመሰክር ፍንጭ ፍለጋ ወደድንኳኑ ጎራ አልኩ።  እዚህ ላይ አንባቢን ላስገነዝብ የምፈልገው ነገር እኛ ለራሳችን የምንሰጠው ስም ሳይሆን የምንሰራው ሥራ ነው የዋጋችንን ሚዛን ሊወስን የሚችለው። ጠንቋይ ቤት የሚካኤልና የማርያም ስዕል ተሰቅሎ መገኘቱ ወይም የገብርኤልን ዝክር እንድትደግስ በማለት ባለሀድራው በማጓራቱ ጠንቅ ዋይነቱን ወደቅድስና ማዕረግ አይለውጠውም።
ወደፍሬ ነገሩ ስመለስ፣ ከቅዱሳኑ ማኅበር ድንኳን ጎራ ብዬ የእግዚአብሔርን ቅድስና የሚያውጁ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን መድኃኒትነት የሚናገሩ፣ ዓይን ሁሉ ወደቀራንዮ እንዲመለከት የሚያሳስቡ መጻሕፍት ፍለጋ አማተርኩ። ጠላታችሁ ይፈር፣ አንድም መጽሐፍ በማጣቴ አፈርኩ። ይልቁንም እልክ የተጋቡ በሚመስል መልኩ ከዚህ በተቃራኒ የሰዎችን እይታ ከቀራንዮ በማስኮብለል ወዳልሆነ ቦታ የሚነዱ፣ ክርስቶስን በሰዎች ማንነትና ትልቅነት የሚጋርዱ ሆነው አገኘኋቸው። ካየሁት የመጻሕፍት ዐውደ ርእይ የተረዳሁት ነገር የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት፣ ብቸኛ አዳኝነት፣ መንገድና ሕይወትነት ከመስበክ ይልቅ ቅጠልም፣ አፈርም፣ ዳቦም፣ ንፍሮም፣ ጠላም፣ ቅራሪም፣ አተላም፣ ተራራ ለተራራ መዞርም ሳማ ሰንበትም፣ አርሴማም፣ የግሼኗ ማርያምም፣ ኩክየለሽ ማርያምም፣ ግንድ አንሳውም፣ ሺህፈጁም፣ ጭሱም፣ ጠበሉም፣አመዱም፣የባህር ዛፍ ቅጠሉም፣ ጥንጁቱም፣ ቅርንፉድ መታጠንም፣ ቅማልና አይጥ ስእለት ማድረስም ገነት፣ መንግሥተ ሰማያት ሰተት አድርገው ያስገባሉ ትባላለህ። በቃ ያስገባሉ ከተባልክ አሜን ብለህ መቀበል ነው።  የኢየሱስስ ማዳን ምን ሊሆን ነው? ብሎ መጠየቅ፣ ማጉረምረም አይቻልም። መናፍቅ፣ ተሀድሶ፣ ጴንጤ ገለመሌ ካልሆንክ በስተቀር በክርስቶስ ላይ ተጨማሪ ልዩ ልዩ ተስፋዎች ሲቀርቡልህ አልቀበልም ማለት አትችልም።  "መንፈስን ሁሉ አትመኑ፣ ነገር ግን መንፈስ ከእውነት እንደሆኑመርምሩ"  የሚለውን ትምህርት ከማንበብ ውጪ ወደተግባር መለወጥ ክህደት ነው። ይህንን በመቃወም ፉከራው የገፋው ሰይጣን፣ አሹልኮ ያስገባቸውና በዘመናት ሂደት ጠፍተውና ቁጥራቸው ተመናምኖ የቆዩ መጻሕፍትን ይኼ ቅዱስ ነኝ የሚለው ማኅበር በባትሪ ፈልጎ በማሰባሰብ አራብቶና አባዝቶ አገልግሎቱን ማጠናከሩን በአግራሞት ተመለከትኩ። ሰይጣን በዚህ አገልግሎት ከመቼውም በላይ ደስተኛ ሳይሆን አይቀርም።  ማንነቱን መርምረው እንዳያውቁ በዘመቻ እየደፈቀ፣ ክህደቱን ለማግነን የሰራባቸው እንደዚህ የሰራባቸው ዘመናት አልታዩም። ኢየሱስ ክርስቶስ የንፍሮ ውሃ የጠጣልህን እስከ ዐሥር ትውልድ እምርልሃለሁ የሚል ቃል በ33 ዘመነ መዋዕለ ሥጋዌው ለማንም አላስተማረም። ይልቁንም ሌላ የመዳኛ መንገድ እንደሌለ አስረግጦ መናገሩን እናውቃለን።
ዮሐንስ 14፣6
"ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም"
ማኅበረ ቅዱሳን ግን የለም፣ ወደአብ መግባት የሚቻልባቸውንና ሰዎች በቀላሉ ከፈፀሟቸው የሚድኑባቸው ልዩ ልዩ ብልሀቶች አሉኝ የሚሉ መጻሕፍትን በአደባባይ ይሸጣል።  በዚያ ኤግዚብሽን ላይ ከተደረደሩት መጻሕፍት መካከል  “ወናሁ ትመውት በሕማመ ብድብድ እኩይ ሞት፣ ወእሬሲ ለከ ኪያሃ ከመ ስቅለትየ ወከመ ደመ ሰማዕት እለ እምቅድሜከ አኮ ለባሕቲትከ አላ ደቂቅከኒ እለ ይወውቱ በሕማመ ብድብድ በውስተ ዛቲ ገዳም እኌልቆሙ ምስለ ሰማዕታት ወአወፍዮሙ ለከ መንግሥተ ሰማያት”
ትርጉም፦ “እነሆ በክፉ ሞት በተቅማጥ ትሞታለህ፣ እሷንም እንደ ስቅለቴና ከአንተ በፊት እንደነበሩት ሰማዕታት ደም እቆጥርልሃለሁ ነገር ግን ለብቻህ አይደለም በዚች ገዳም በተቅማጥ በሽታ የሚሞቱትን ልጆችህንም ቁጥራቸውን ከሰማዕታት ጋራ አደርጋለሁ፣ መንግሥተ ሰማያትንም እሰጣቸዋለሁ” የሚለው ገድለ ተክለ ሃይማኖትን ገለጥ አድርጌ እንደገዢ ሰው አየሁት። ስድስት ክንፍ እንደተተከለለት የተቆረጠ እግር አለፍ ብሎ ወድቆ በስዕል ይታይ ነበር።
አቡነ አረጋዊ በዘንዶ ሲንሸራሸሩ፣ ለማርያም ድግስ የተቆላ አሻሮ የሸተተው ገነት እንደገባ፣ የሴት ብልት ስሞ ማርያም አፈወርቅ እንዳለችው የሚያትት፣ እግዚአብሔርን ክዶ በማርያም እንደዳነ የሚተርክ፣ ሰይጣን መነኮሰ፣ 30 ትውልድ ተማረ፣ ሎጥን ያዳነችው ማርያም ናት፣ መርቆሬዎስ ፀሐይና ፈረቃን ፈጠረ፣ ገብርኤልና ሚካኤል ሠለስቱ ደቂቅን አዳኑ፣ ሲኦልን የሞሉት ጋላና ሻንቅላ፣ የአርሴማ ድንግል ድንጋይ መካን አስወለደ፣ የአድዋን ጦርነት ጊዮርጊስ አሸነፈ ወዘተ ወጎችን የሚጠርቁ መጻሕፍት እንደጉድ ሲቸበቸቡ ተመለከትኩ። የሆኖስ ሆኖ ጊዮርጊስ አድዋ ላይ ከተዋጋ ጀግኖች አርበኞች ምን ሰሩ ሊባል ነው? የሞቱትና የቆሰሉት ምን ሲያደርጉ ኖሯል? ነው ወይስ መቁሰልና መሞት አልነበረም?
"የጉድ አገር ገንፎ እያደር ይፋጃል" እንዲሉ ሰዎቹ ጊዮርጊስ ባይኖር ጣልያንን ባላሸነፍንም ነበር ይሉናል። ኢህአዴግ ደርግን ያሸነፈው ማንን ይዞ ይሆን?
ማኅበሩ እያራባ ከሚሸጣቸው መጻሕፍት አብዛኛዎቹ ወንጌልን የሚቃወሙ፣ ባዶ ተስፋ የሚሰጡ፣ ሰው ከወንጌል ይልቅ እነዚያን እንዲያነብ የሚገፋፉ፣ የክርስቶስ ኢየሱስን የማዳን ሥራ አስትተው በትርኪ ምርኪ ቃል ኪዳን ላይ እንዲታመኑ የሚያበረታቱ መጻሕፍት ብቻ ድንኳኑን ሞልተው አይቻለሁ። ታዲያ ይህንን የስሁታንን ሥራ የሚሸጠው ማኅበር ራሱን "የቅዱሳን" ሲል ያሞካሸዋል።
ሰይጣን አስርጾ ያስገባቸውና በዘመናት ብዛት ተቀዳደውና ተመናምነው የሚያባዛለት አጥቶ በደነገጠበትና ተስፋ በቆረጠበት ሰዓት ማኅበሩ ድንገት ደርሶ እንደታደገው ማረዳት አይከብድም። ሊወገዙ የሚገባቸው የባዶ ተስፋ መጻሕፍትን ከወንጌል በላይ አሳትሞ ማሰራጨት ከቶ ምን ይባላል?
ከኤግዚቢሽኑ መጻሕፍት እንዲህ የሚል ቃል ያለበት መጽሐፍም ነበር።
«ወሶቤሃ አውስአ  ወይቤላ ንስኢ ወሐብኩኪ ዐሥራተ ብዙኀ ነፍሳተ መጠነ ነጠብጣብ ዝናም ዘ፬ቱ አውራኅ ለእለ አሐዱ ዕለት»
ትርጉም «ጌታም እንዲህ አላት። በዐራት ወራት ውስጥ በየቀኑ የሚወርደውን የዝናም ነጠብጣብ ያህል ነፍሳትን ዐሥራት አድርጌ ሰጥቼሻለሁ» ገድለ ክርስቶስ ሰምራ
 በዓለም ላይ በየቀኑ የሚዘንበውን የአራት ወራት ያህል የዝናብ ነጠብጣብ ውሃ ያህል ሰው ከአዳም ጀምሮ አልተፈጠረም። ገድሉ የተፈጠረውንም፣ ያልተፈጠረውንም ክርስቶስ ሰምራ ታድን ዘንድ ቃል ተገብቶላታል ይለናል።  በዚህ ቃል መሠረት ኦርቶዶክስ በክርስቶስ ሰምራ በኩል የዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ናት ማለት ነው።
በሮሜ 10፣3 እንደተመለከተው
"የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም" የሚለው ቃል ከሚፈፀም በቀር እንኳን ለዓለሙ አዳኝ ልትሆን ቀርቶ ራሷም ከቆመችበት የአበው አስተምህሮ ተንሸራታ ተስፋ በሌለው ተረታ ተረት ተሸፍናለች።  ማኅበሩ የመጋረጃውን አገልግሎት በማስፋት ሰዎችን ወደጥፋት እንዳይነዳ  እንደሄሜዎስና እስክንድሮስ ለሰይጣን ተላልፎ የተሰጠ ይሁን! ብኩርናውን ለጥቅም፣ ትጋቱን ለስሁት አገልግሎት፣ ሐዋርያትም ከሰበኩት ስብከት የተለየውን የሰበከ የተረገመ ይሁን! አሜን።

Sunday, January 24, 2016

"ቅድስና ለእግዚአብሔር"


(ተረፈ አበራ)
ሰው በክርስቶስ ሲያምን ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል ።ሮሜ 4:25 ይህ ማለት በታረሰ መሬት ላይ ተተክሎ እንደ ጸደቀ ወይን ይሆናል።ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል እንደ ሊባኖስ ዝግባ ይለመልማል እንደሚል መጽሐፍ ፍሬ ያፈራል።መዝ 29:92 ፍሬው ቅድስና ይባላል።ጽድቅና ቅድስና እምነትና ሥራ ይባላሉ ።ያዕ 2:14 ቅድስና መለየት ማለት ሲሆን ሰው በክርስቶስ ጸጋ መጽደቁን የሚያረጋግጥበት የመንፈስ ፍሬ ነው ።ይህም ማለት ውስጣዊ ጤንነት እና ንጹህነት ወይም ከእንከን መራቅን ያመለክታል።እግዚአብሔር በባህሪው ቅዱስ ነው ።ሰዎችን በጸጋው ይቀድሳል።
  ቅድስና የሚያስፈልገን ነገር ግን ያልፈለግነው የሕይወት ውበት ነው።ደስታን፣ብልጽግናን፣ሰላምንና ስኬትን በምንፈልግበት መጠን ቅድስናን ፈልገን እናውቅ ይሆን? ቃሉ፦'ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።' ይላል።ዕብ.12፥14 ቅዱሱን ጌታ ለማየት የቅድስና ጥሪውን በመቀበል፣በደሙ በመታጠብ ከዓለም፣ ከኀጢአት፣ ከርኩሰትና ከሥጋ ሀሳብ በመለየት መኖር ያስፈልጋል።'እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።'1ኛ ጴጥ. 1፥15-16።ክርስትና ለእግዚአብሔር የመለየት ኑሮ ነው።ልዩነቱ የበጎ ተጽዕኖ አቅም ነው።በተራራው ጌታ የሰበከንን የአማኝ ኑሮ ብናጠና ብልጫችንን እንረዳለን። ለሚበልጠው ታጭተን በሚያንስ አኗኗር እንዳንገኝ እናስተውል። በቅዱሱ ፊት በተጣለ ማንንነት መቆም አይቻልም።በሰው ፊት እንኳ ቆሽሾ መቅረብ ምን ያህል ይከብዳል? 'እኔ ኤልሻዳይ ነኝ፤ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጹምም ሁን፤' ዘፍጥረት 17፥1 ያለውን ጌታ ነው የምናመልከው። እግዚአብሔር የምንቀደስበትን መስዋእት አዘጋጅቷል። የተዘጋጀው መስዋእት ልጁ ነው።ህሊናችንን ቀድሶ መንፈሳችንን አንጽቶ በደላችንን አጥቦ ሊያቆመን ወደሚችለው እንቅረብ።አሮጌ(ያደፈ ልብስ)አልብሶ የሚከሰንን በደሙ ኀይል በስሙ ስልጣን ጥሎአል።ራእይ 12፥11 ቀዳሹ እኛን መቀደስ ፈቃዱ ነው እኛ መቀደስ እንፈልጋለን?ብሉይ ኪዳን 'ቅዱሳን ሁኑ'(ዘሌ 19፥2) ያለን ቅዱሱን ልጁን ላከ።ቀዳሹ ጌታም እኛን ተቀዳሾቹን በደሙ አነፃ።ከኀጢአታችን አጠበን(ራእይ 1፥6) ቀደሰን(1ቆሮ 6፥11) ክብሩን እንድናበራ ለየን።በመሆኑም እኛ ለርስቱ የተለየን ቅዱስ ሕዝብ ነን።(1ጴጥ 2፥9)።ለለየን ተለይተን መኖር ይጠበቅብናል።ቅድስና የሕይወት ዘመን ኑሮ ነው፡፡ስለዚህ ሁልጊዜ ሀሳባችንን ልናነፃ፣ንግግራችንን ልንገራ፣ ሰውነታችንን ከርኩሰት በጸጋው ኀይል ልንጠብቅ ይገባል። ቅዱሳን ለመሆን መጠራታችንን አንርሳ።(ሮሜ 1፥7)። የተጠራነው ለርኩሰት አይደለም።'ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና።"1ኛ ተሰሎንቄ 4፥7። ስለዚህ አባታችንን ለመምሰል በአንደበት ብቻ ሳይሆን በሕይወትም በቅድስና ማደግ አለብን።አባታችን መልኩን በኛ ሕይወት ውስጥ የማየት ናፍቆት አለው።የጠራን በባሕርይው ቅዱስ እንደሆነ እኛም በኑሯችን ሁሉ ከአለም እድፍ ራሳችንን በመጠበቅ በቅድስና መኖር አለብን። የቀደሰንን እንድንመስል ተወስኗል።'ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና።'ሮሜ 8፥29።አስቀድሞ ወደታሰበልን ያድርሰን፤ካላደረሰን መድረስ የለምና። ይቀጥላል! እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን !!


Saturday, September 5, 2015

ባለቤቴን አፈቅረዋለሁ ትዳራችንም ፅኑ ነው !!


ከዚህ በፊት ስለተከስተ ጌትነት የአሜሪካው አማርኛ ድምጽ አየር ላይ ካዋለው መረጃ ተነስተን ዐመጻውን በንስሐ እንዲተው የሚያሳስብ ዘገባ አውጥተን ነበር። በንስሐ ስለመመለሱ እየተናገረ ባለበት ሁኔታ የባለቤቱን ጽናትና ያላትን የይቅርታ ልብ ተመልክተን ወደፍቺና የግድያ ተግባር ላለመሄድ የተጓዘችበትን የክርስትና አርአያነት «አሌክስ አብርሃም» የዘገበውን ልናስነብባችሁ ወደድን።
 


ባለቤቴን አፈቅረዋለሁ ትዳራችንም ፅኑ ነው !!
 (አሌክስ አብርሃም )

ይቅርታ መቸም እንደሚወራው ቀላል ነገር አይደለም !! በተለይም በባልና በሚስት ማሃል በአንድኛው ወገን ለትዳር አለመታመን ሲከሰት የተበደለው አጋር ይቅር ለማለት ይቸገራል …እንዲህ አይነቱ ነገር ሲከሰት ሚስት ባሏን በመፍለጫ …በተኛበት አቅምሳው እጇን ለመንግስት የሰጠችበት ዜና ሰምተናል ….ባልም በገጀራ ሚስቱን አመሳቅሎ ዘብጥያ የወረደባቸውን በርካታ ዜናዎች በቲቪ ተመልክተን አማትበናል ! የራሱ ጉዳይ ያሉም ትዳራቸውን በትነዋል !
ይህን ነገረ ካለነገር አላነሳሁትም …. በዚያ ሰሞን ከወደአሜሪካ የሰማነው ዜና የሚታወስ ነው …..ዘማሪ ተከስተ ጌትነት ሚስቴን አማግጦብኛል ያለ አንድ ሰው በየሚዲያዎቹ ቀርቦ ፍረዱኝ ሲል ሁላችንም ሰምተን ጉድ ጉድ ብለናል ! ማገጠች የተባለችውም ሴት በየሚዲያው እንዴት ካንድ አይሉ ሁለት ሶስት ጊዜ ወዳረፈበት ክፍል ጎራ እያለች ‹‹ሳትፈልግ ›› አብረው እንደተኙ በዝርዝር መግለፅዋ ይታወሳል ….ፓስተር ተከስተ ጌትነትም ይህንኑ አምኖ ይቅርታ መጠየቁ እንደዛው ..ሚዲያውም እስኪበቃው አናፍሶታል !ዘማሪ /ፓስተር ተከስተ በሚያገለግልበት ቤተክርስቲያንም አገልግሎቱን እንዳቆመ ተዘግቦ ነበር !!
ታዲያ ያኔ አገር ይያዝ ያለው ሚዲያ ለዚችኛዋ ዜና ጭጭ ማለቱ ስለገረመኝ …ያው ችግሩን ካወራን መጨረሻውስ ምን ሆነ የሚለውን ዝም ማለቱ ተገቢ አይደለም በሚል ይችን ፅሁፍ እነሆ አልኩ ……. ትላንት ‹‹የእውነት ቃል ጎስፕል ሚዲያ›› ‹‹የእንደገና አምላክ›› በሚል ርእስ እንደዘገበው ከሆነ ዘማሪ ጌትነት ባለፈው ቅዳሜ በምእመኑ ፊት ቁሞ ስለሁኔታው ምስክርነቱን ሰጥቷል … ባለቤቱ የምስራችም የሆነውን ሁሉ ይቅር እንዳለች በሚገልፅ አጭር ቃል እንዲህ ብላለች ‹‹ ባለቤቴን አፈቅረዋለሁ ትዳራችንም ፅኑ ነው ›› ፓስተር ጌትነትም ወደአገልግሎቱ ተመልሷል !! መቸስ ይቅርታ ጥሩ ነው … መልካም የትዳርና የአገልግሎት ጊዜ ይሁን እያልኩ ….ምንም እንኳን የመጀመሪያ ተጎጅዋ እርሷ ብትሆንም እንዲህ በችግር ጊዜ የራሷን ብሶት ትታ ከባሏ ጎን የምትቆም ሚስት ማግኘት መታደል ነው የሚል የግል አስተያየቴን ጨምሬ ላብቃ !!