Showing posts with label ስብከት. Show all posts
Showing posts with label ስብከት. Show all posts

Sunday, September 10, 2017

በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ!



እኛ ነን ወደአዲሱ ዓመት የደረስነው ወይስ ዘመኑም እንደእኛው እየሄደ ነው?

  ቆሞ የሚጠብቅ ዘመን የለም። ዘመኑም እኛም በዘመኑ ውስጥ እየሄድን ነው። እግዚአብሔር በዓመት፤ በዓመቱ የሚሰራው አዲስ ዘመን የለም። እግዚአብሔር ዘመናትን የሠራው አንድ ጊዜ ነው።  በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተሠራው ዘመን በራሳችን እድሜ ላይ ሲቆጠር «አዲስ ዘመን» ከማለታችን በስተቀር ዘመኑም ለማለቅ ራሱ ወደእርጅና እየተጓዘ ነው።  ሰውም ዘመናትም የማለቂያ እድሜ አላቸው። ዘመናት የተሠሩት፤ ለሰው ልጆች አገልግሎትና የእግዚአብሔርን ፈቃድ አውቀው መልካሙን ሁሉ ይሠሩባቸው ዘንድ ነው። እንኳን «ለአዲሱ ዘመን አደረሰን!» ስንል እኛ በዘመን ውስጥ መታደሳችንንና መለወጣችንን መናገራችን ነው። እንደዚያ ካልሆነማ ዘመናት የተሠጣቸውን ግዳጅ እየፈጸሙ ወደተሰጣቸው እርጅና እየሄዱ እንጂ መቼ ቆመው ይጠብቁናል? ክረምትና በጋ፤ ብርሃንና ጨለማ፣ ዘርና ማዕረርን ዘመናት ከመስጠት አለማቆማቸውና በዘመን ስሌት መፈራረቃቸው እስከጊዜው የተሰጣቸውን ግዳጅ እየተወጡ መሆናቸውን ልብ ልንል ይገባል። እድሜአቸው አልቆ እስኪጠቀለሉም ይህንኑ ግዳጃቸውን ይወጣሉ።

  መዝ 102፤25-26 «አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል»

ሐዋርያው ጴጥሮስም በመልዕክቱ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደምንጠባበቅ መናገሩ አሁን ያለን ሰማይና የምንኖርባት ምድር አርጅተው እንደሚለወጡ በግልጽ ያስረዳናል።

2ኛ ጴጥ 3፥13 «ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን»

 ስለዚህ በዘመን ውስጥ በእድሜ ጣሪያ የምንጓዝ እኛ የሰው ልጆች ምን ማድረግ ይገባናል?
በጎ መመኘት በጎ ነው። በጎ መመኘት ብቻውን በጎ ነገር አያመጣም። የተመኘነውን በጎ ነገር ለመሥራት በጎ ጥረት ያስፈልገናል። አዲስነት ከእኛነታችን ውጪ የሚገኝ አይደለም። ዘመን በተቆጠረ ቁጥር «እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ» መባባሉ ጥሩ ቢሆንም ባልተለወጠ ማንነታችን ውስጥ ምን አዲስ ለውጥ አይመጣም። መታደስ፤ መለወጥ ለሰው ልጆች ማንነት ልዩ ግኝት ስለሆነ መለወጥ ያለብን እኛ ነን።

 ቁጡና ቂመኛ ሆነን ስለአዲሱ ዘመን ማውራት ምን ይጠቅማል? በውሸትና በቅድስና ጉድለት እየኖርን ከጉዞው ጨብጠን ልናስቀረው ስለማንችለው አዲስ ዘመን መልካምነት መመኘት በራሱ የሚጨምርልን አንዳች ነገር የለም።
ይልቁንስ ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውንና ሁልጊዜ እያነበብን ለመተግበር የተቸገርነውን በጎ ነገር እየፈጸምን ስለአዲስ ዘመን በጎ ምኞት እናስብ።

 «በእርግጥ ሰምታችሁታልና፥ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤ ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ»  ኤፌ 4፤21-32

አለበለዚያ ዘመን ካልሰራንበት «እንኳን አደረሳችሁ ሲባባሉብኝ ጊዜያቸውን በከንቱ ፈጸሙ\ ብሎ በኋለኛው ቀን እንዳልሰራንበት ይመሰክራል።
«ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል» ስለዚህ ንስሐ እንግባ፤ በልባችንም መታደስ እንለወጥ! ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን!

Friday, July 15, 2016

ትወደኛለህን?


(ከነገ ድል አለ)
ምላሽ የሚያሻው የክርስቶስ ጥያቄ - ትወደኛለህን? (ዮሐንስ 21)
ይህን ጥያቄ ስናነብ ወደ አእምሮአችን በቶሎ የሚመጣው ምንድን ነው? ምናልባት ምን ዐይነት ጥያቄ ነው? ብለን እናስብ ይሆናል፤ ወይም ጥያቄው የአፍቃሪ ጥያቄ አንደሚሆን ልንገምት እንችላለን። አሊያ እንደዚህ ተብሎ ይጠየቃል ወይ? ብለን ልንጠይቅም እንችላለን። ጥያቄው ረጅም ጊዜ ዐብሮን ከኖረ ሰው፥ በጣም ከሚያውቀንና ከምናውቀው ሰው፥ ለምሳሌ፥ ከባለቤታችን ወይም ከጓደኛችን ቢመጣስ ምን ይሰማናል? ያለ ጥርጥር ምን አይቶብኝ ይሆን? ወይም ምን አይታብኝ ይሆን? ምን ሰምቶብኝ/ምን ሰምታብኝ ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎችን ሊያጭርብን ይችላል።
ጥያቄው “አዎን እወድሃለሁ” የሚል ምላሽን ለማግኘት ወይም መወደድን ለማወቅ የተጠየቀ ጥያቄ አይደለም። ጥያቄው ከፍቅረኛ፥ ከትዳር አጋር ወይም ከጓደኛ የመጣ ሳይሆን ከጌታችንና ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ በተለይም ለጴጥሮስ የቀረበ ጥያቄ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ በ21ኛው ምዕራፍ አንደ ዘገበልን፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ያህል “ትወደኛለህን?” ሲል ጠይቆታል።

እወድሃለሁ
“ትወደኛለህን?” የሚለው ጥያቄ ፍቅርን ለማወቅ ወይም ለማረጋገጥ የሚጠየቅ ጥያቄ ቢሆንም፥ ዮሐንስ እንደ ጻፈው ጥያቄው ከዚያ የሚያልፍ መልእክት አለው። በርግጥ ትወደኛለህን? ተብሎ ሲጠየቅ ምላሹ አልወድህም የሚል አይሆንም። በክርስቶስና በጴጥሮስ መካከል የነበረውን ግንኙነት መለስ ብለን ስናስታውስ፥ ጌታ ደቀ መዛሙርቱን በሥጋ ልለያችሁ ነው፤ ልሄድ ነው ብሎ በነገራቸው ጊዜ፥ ጴጥሮስ ‘ተለይተኸን ወዴት ትሄዳለህ? የትም ብትሄድ ዐብሬህ እሄዳለሁ፤ ሞት እንኳ ቢመጣ ከአንተ አልለይም’ ያለው ሰው ነበር (ዮሐ. 13፥36-38)። ጌታ ለጴጥሮስ ንግግር የሰጠው ምላሽ፥ ‘እንኳ ነፍስህን ልትስጠኝ፥ ዶሮ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ’ የሚል ነበር።

ፍቅር እንዴት ይገለጣል?
እንደሚታወቀው በዓለም ላይ የፍቅር መገለጫ አንድ ዐይነት አይደለም፤ ከማኅበረሰብ ማኅበረሰብ፥ ከባህል ባህል ይለያያል። የፍቅር መግለጫ ቋንቋ፥ የጋለ ጭብጨባ፥ እንባ፥ የቃል ንግግር፥ አበባ ማበርከት፥ መተቃቀፍ፥ መጨባበጥ፥ መሳሳም ሊሆን ይችላል። ከእነዚህ በአንዱ ወይም በሌሎች መንገዶች ፍቅር ይገለጣል። ጌታ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ መላልሶ ሲጠይቀው፥ ጴጥሮስም ሦሰት ጊዜ መላልሶ እወድሃለሁ ብሎታል። እንዲሁም በኋላ ላይ ግራ የገባው በሚመስል መልክ፥ በማዘንም ጭምር እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ ብሎታል።

ፍቅርና ተግባር
በአጠቃላይ በወንጌል በተለይም በጌታችን ትምህርትና ሕይወት ውስጥ እንደምንመለከተው፥ የፍቅር ዋና መገለጫ ቃላት ሳይሆኑ ተግባር ነው። ጴጥሮስ “እወድሃለሁ” ቢልም በተግባር ግን ይህን ፍቅር ማሳየት አልቻለም፤ እወድሃለሁ ያለውን ጌታውን ክዶታል። ጌታችን ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል 15፥13 ላይ ነፍሱን ለወዳጆቹ ከመስጠት የበለጠ ፍቅር እንደሌለና ነፍስን መስጠት የፍቅር ጣሪያ መሆኑን እንዳስተማረ፥ በተግባርም ነፍሱን በመስጠት ፍቅሩን አሳይቷል። ከዚህ በኋላ ነው ጌታ ጴጥሮስን “ትወደኛለህን?” ሲል መላልሶ የጠየቀው። ጴጥሮስም እንደ ቀድሞው፥ “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም” (ማቴ. 26፥35) አላለም። የራሱን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ “እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” ነበር ያለው። ጴጥሮስ ፍቅሩን በተግባር መግለጽ ባይችልም፥ ኢየሱስ ፍቅሩን በተግባር ከገለጠና፥ የካደውን ጴጥሮስን በዚህ ፍቅር እንደ ገና ከመለሰው በኋላ አልከሰሰውም። ይልቁንም ሲመልሰውና ወይም እንደ ገና ሲያድሰው፥ ኀላፊነትንም ሲሰጠው እንመለከታለን።

መልእክቱ

“ትወደኛለህን?” የሚለው የጌታ ጥያቄ “አዎን እወድሃለሁ” ከሚል ምላሽ ያለፈ ቀጥተኛ መልእክት አለው። መልእክቱም የምትወደኝ ከሆነ አደራዬን ተወጣ የሚል ነው። ጌታ ሦስት ጊዜ፥ “ትወደኛለህን?” ሲል ከጠየቀው በኋላ ጴጥሮስ “አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” የሚል ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ፥ ግልግሎቼን አሰማራ፤ ጠቦቶቼን ጠብቅ፤ በጎቼን አሰማራ የሚል ግልጽ አደራ ሰጥቶታል (ዮሐ 21፥15-17)። ይህ ኀላፊነት ወይም አደራ የሕይወት መሥዋዕትነትን የሚጨምር እንደሚሆን ቀጥሎ በተጻፈው ቃል ውስጥ እናነባለን። “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ አንተ ጒልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፥ ሌላውም ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም ይወስድሃል አለው። በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ።” የዚህ ክፍል መልእክት በእኛም ሕይወት ሊተገበር የሚገባው ነው። ምክንያቱም ክርስቶስ በዕለታዊ ሕይወታችን ተግባራዊ ምላሽን ይጠብቃል። ትወደኛለህን? ለሚለው ጥያቄ በቃል “እወድሃለሁ!!” የሚለውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፥ ራሳችንን መልሰን መጠየቅ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም። በርግጥ ጌታን እንወደዋለን ወይ?

Tuesday, January 6, 2015

እንኳን ለአምላካችን፤ ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ክብር አደረሳችሁ!

ኢሳይያስ 9፥6 «ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል»
 ታህሣሥ 29/2007 ዓ/ም




Monday, August 11, 2014

ትክክለኛው ሃይማኖት የቱ ነው?



 ቀልጣፋ ሬስቶራንቶች በቀላሉ የሚስቡን የፈለግነውን ምግብ በምንወደው መንገድ እንድናዝ መንገድ ስለሚከፍቱልን ነው። ጥቂት ካፌዎች ደግሞ ከመቶ በላይ የተለያዩ የቡና ጣዕም እንደሚያቀርቡ በጉራ ይናገራሉ። መኖሪያ ቤቶችና መኪናዎችን ስንገዛ እንኳ የምንፈልገው ምርጫ እንዲያሟላ እንሻለን። በቼኮላት፣ በቫኒላና በእንጆሪ ዓለም ታጥረን መኖር አንፈልግም። ፍላጎት ንጉሥ ነው! እንደግላዊ ፍላጎትህና ምርጫህ የምታገኝበት ሁሉ የተሟላበት ዘመን ነው።
ለአንተ ብቻ ትክክለኛ ሃይማኖት የማግኘቱ ሁኔታስ ምን ይመስላል? ወቀሳ አልባ፣ ብዙ ጫና የሌለውና ይህንን አድርግ አታድርግ እያለ የማያስቸግር ሐይማኖት ብታገኝስ? ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ያውና እዚያ አለ ነገር ግን ሃይማኖት እንደሚወዱት አይስክሬም የሚመረጥ ነው እንዴ?
ትኩረታችንን ለመሳብ የሚሻሙ በርካታ ድምፆች ስላሉ ለምን ብሎ ነው አንድ ሰው ኢየሱስን ከሌሎች ማለትም ከመሐመድ ወይም ከኮንፊሸየስ፣ ከቡድሐ ወይም ቻርለስ ቴዝ ራስል ወይም ከጆሴፍ እስሚዝ አስበልጦ የሚመርጠው? ዞሮ ዞሮ ሁሉም መንገዶች የሚያደርሱት ወደ መንግስተ ሰማይ አይደለም እንዴ? በመሰረቱ ሁሉም ሃይማኖቶች አንድ አይደሉም እንዴ? እንደ እውነቱ ከሆነ ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ መንግስተ ሰማይ አያመሩም። ሁሉም መንገዶች ወደ ኢንዲያና መቼም አያደርሱም።
ኢየሱስ ብቻውን በእግዚአብሔር ሥልጣን ይናገራል።
1/  ምክንያቱም ኢየሱስ ብቻ ነው ሞትን ያሸነፈው። እስካሁን ድረስ መሐመድ፣ ኮንፊሸየስና ሌሎች በመቃብር በስብሰው ይገኛሉ። ነገር ግን ኢየሱስ በራሱ ስልጣን በጨካኙ የሮማውያን መስቀል ከሞተና ከተቀበረ ከሦስት ቀን በኋለ መቃብሩን ፈንቅሎ ተነስቶአል። በሞት ላይ ስልጣን ያለው ማንኛውም ሰው ትኩረታችን ሊስብ ግድ ይላል። ማንም በሞት ላይ ስልጣን ያለው ግለሰብ ሲናገር ልናደምጠው አስፈላጊ ነው። ሞትን ማሸነፍ የቻለ ከፍጥረታት መካከል ማንም የለም። ከሰማይ የመጣው ብቻ ሞትን አሸንፎ ወደሰማይ ወጥቷል።ስለዚህ እንዲህ ያለው አሸናፊ የተናገረው የእምነት መሠረት መሆን አለበት። ሰው ሟች መሆኑን ያውቃል። ሟች ደግሞ ከሞት ለማምለጥ የሚችለው በሞት ላይ ባለሙሉ ሥልጣን በሆነ ክንድ ላይ ሲያርፍ ነውና ኢየሱስን ማመን የግድ ይለዋል። ሌላ ማንም አዳኝ የለም።
2/ የኢየሱስ ሕይወትና ትንሣዔ ምስክር ያለውና እውነት ነው።  የኢየሱስን ትንሣዔ የሚደግፈው መረጃ የሚያጥለቀልቅ ነው።   ሮማውያንና ሰቃልያኑ ካህናት የኢየሱስን መቃብር ማስጠበቅ ያስፈለጋቸው «በሦስተኛው ቀን እነሳለሁ» ያለውን ቃሉን ይዘው እንጂ የሞተ ሰው መቃብር ስለሚጠበቅ አልነበረም።  አዎ ትንሣዔውን ለመከላከል ወታደሮች ከመቃብሩ ማንም እንዳይወጣ፤ ወደመቃብሩም ማንም እንዳይደርስ አድርገው አስጠብቀው ነበር። ነገር ግን የመቃብሩ ቦታ ባዶ ሆኗል!  እንደተናገረው አልተነሳም እንዳይሉ የኢየሱስ ጠላቶች ያን ሁሉ ስለትንሣዔው የተነዛውን ወሬ ለማክሸፍ የበሰበሰውን አካሉን በማቅረብ በቀላሉ ያስታግሱት ነበር። ግን አልቻሉም፤ መላው ሲጠፋባቸው ደቀመዛሙርቱ ሬሳውን ሰርቀውት ይሆን? አሉ።  ከሐዋርያቱ መካከል ከዮሐንስ በስተቀር ሌሎቹ የሸሹት በጊዜ ነው። የሸሹ ሰዎች ተመልሰው ከሮማ ወታደሮች ጋር ተዋግተው ሰረቁት ማለት የማይመስል ነገር ነው። ቀላሉ ሃቅ ግን የኢየሱስ ትንሳኤ እንዲሁ ተነግሮ ተገልፆ የሚያልቅ መች ሆነና! ትንሣዔውን ያለምስክር ያልተወ ኢየሱስ ግን በአንድና በሁለት ሰዎች ፊት ብቻ ሳይሆን በአምስት መቶ ሰዎች ፊት ትንሣዔውን አስመስክሯል።

«መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ» 1ኛ ቆሮ 15፤4-8

ስለዚህ ሰዎች ኢየሱስን ለማመን የሚያስችላቸው በቂ የእምነት ማስረጃ ስላላቸው ነው። በዚህ ምድር ላይ ካሉ ሃይማኖቶች ውስጥ እንደኢየሱስ ሞትን ያሸነፈ፤ ትንሣዔውን በምስክር ያረጋገጠ ማንም የለም። ስለዚህ በሞት ላይ ሥልጣን ያለው ማንም ሰው ሊደመጥ ይገባል። ኢየሱስ በሞት ላይ ያለውን ሥልጣን አረጋግጧል። ስለዚህ የሚናገረውን መስማት ይገባናል። ለድነት ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ መሆኑን ራሱ ይናገራል።(ዮሐንስ 14፡ 6)። ካሉትም ብዙ መንገዶች አንዱ አይደለም። ኢየሱስ ብቸኛ የድነት መንገድ ነው። ሌላ መንገድ ሁሉ በትንሣዔና በሕይወት ላይ ሥልጣን የሌለው የሞት መንገድ ነው።
3/ ኢየሱስ ከሸክም ያሳርፋል። በዚህ ምድር ላይ ከሸክም አሳርፋችኋለሁ ብሎ ቃል የገባ አንድም ሥጋ ለባሽ የለም። ይህ ብቸኛ ኢየሱስ እንዲህ ይላል “እናንተ ደካሞች፤ ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደእኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” (ማቴዎስ 11፡ 28)። ሕይወትም አስቸጋሪ ነው። ብዙዎቻችን ደምተናል፣ ቆስለናል፣ ጦርነትንም እንፈራለን። ዓለምም አስጨናቂ እየሆነች ነው። ስለዚህ የሚያሳርፈንን ብንፈልግ ተገቢ ነው። ነገር ግን ከኢየሱስ በቀር ሸክም የከበዳችሁ ወደእኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ ያለ ማንም ሌላ የለም። በትንሣዔውና በሕይወቱ የታመነ ኢየሱስ ይህንን የማለት ብቃት ስላለው በእርሱ ላይ ማረፍ ከአስጨናቂው ዓለም ለመዳናችን ዋስትናችን ነው።
ስለዚህ ምን ትፈልጋላችሁ? ከኃጢአት፤ ከድካም፤ ከተስፋ መቁረጥ በንስሐ መታደስ ወይስ  የአንዱ ሃይማኖት አባል በመሆን ብቻ መኖር? ሕያው የሆነ አዳኝ ወይስ “ከሞቱት በርካታ ነቢያት ወይም ጻድቅ” አንዱን ተስፋ ማድረግ? ትርጉም ያለው ግንኙነት ወይስ ተራ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት መከተል?
ኢየሱስ አማራጭ ሳይሆን ምርጫ ነው! ሃይማኖት ማለት አንድ መንፈሳዊ ድርጅት ወይም የአንዱ ተቋም ስያሜና የዚያ አባል ሆኖ መኖር ማለት አይደለም።  ከእግዚአብሔር  አብ ጋር ትርጉም ያለው ግንኙነት ትፈልግ እንደሆን ሃይማኖትህ ኢየሱስን ማመን ነው። «በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው»  ይላል መጽሐፍ። (ዮሐንስ 3፡ 36) አንዳንዶች ይህንንማ እናምናለን ነገር ግን ትክክለኛው እምነት ያለው በኛ ሃይማኖት ውስጥ ስለሆነ አባል ሁነን ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በማኅበር ስለመጸለይ ይነግረናል እንጂ ኢየሱስን ለማመን የዚህ ወይም የዚያ ሃይማኖት ተቋም አባል ሁን የሚል ትዕዛዝ የለውም። ኢየሱስ በሱ የሚያምኑ ሁሉ እንዲድኑ እንጂ የሃይማኖት ድርጅት ሊመሠረት አልመጣም።

«የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን» 1ኛ ዮሐ 5፤15

(www.Gotquestions.org)ተሻሽሎ የተወሰደ

Monday, May 5, 2014

«ኢየሱስ ለእኔ እንዲህ ነው፤ ለእናንተስ?»



የኦሪቱ የኃጢአት ማስተስርያ
ኢየሱስ በኔ ኃጢአት ምትክ ሞቶ ሕይወትን ይሰጠኝ ዘንድ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ህያው በግ ነው።
ዮሐንስ ወንጌላዊ እንዲህ ሲል እንደተናገረ;
 «በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ» ዮሐ 1፤29

እስራኤል ዘሥጋ የተባሉት የብሉይ ኪዳን ሕዝቦች እግዚአብሔር ከሰጣቸው ተስፋ መካከል አንዱ ኃጢአት ቢሰሩ ወይም ቢበድሉ ከዚህ መንጻት የሚችሉበትን መንገድ  አሳይቷቸው ነበር።  ይኼውም
 «ማናቸውም ሰው ቢበድል፥ ሳያውቅም ለእግዚአብሔር በተቀደሰው በማናቸውም ነገር ኃጢአትን ቢሠራ፥ ለበደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ከመንጋ ነውር የሌለበትን አውራ በግ ያቀርባል እንደ ግምጋሜህ መጠን በብር ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ለበደል መሥዋዕት ያቀርበዋል» ዘሌ 5፤15
ኃጢአተኛው ይህንን የኃጢአት ወይም የበደል መስዋዕት በታዘዘው ደንብ መሠረት ለሊቀ ካህናቱ ካቀረበ በኋላ እጁን በመስዋእቱ ላይ ጭኖ ከጸለየለት በኋላ ኃጢአተኛው ለሰራው ኃጢአት ምትክ ማስተሰርያ ሆኖ አንገቱን ይቆለምመዋል። ከደሙም የመሰዊያ ግድግዳው ላይ ይረጨዋል። ያን ጊዜም የኃጢአት መስዋዕት ሆኖ ኃጢአተኛው ከሰራው ኃጢአት ነጻ ሆኖ ይመለስ ነበር።
 ይህ ከኃጢአት ለመንጻት የሚደረግ የመስዋዕት ስርዓት ኃጢአት በሰሩ ቁጥር መቅረብ የሚገባውና ኃጢአተኞች ሁሉም ለየራሳቸው ያለማቋረጥ ለማቅረብ የሚገደዱበት የመንጻት ደንብ ነበር።  ይህን መስዋዕት ሁልጊዜ ለመፈጸም ያስገደደው ምክንያት ሊቀካህኑም ሆነ የሚሰዋው በግ  ዘላለማዊ ስላልነበሩና ብቃት ስለሚጎላቸው ነበር።   ሊቀካህኑ ለራሱ መስዋዕት እንዲያቀርብ ይገደዳል። በጉም  ነውር እንዳይኖርበት ጥንቃቄ ይደረግበታል።  እንደዚያም ሆኖ ፍጹም ማዳን አይችሉም።
  
«ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መስዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ፥ ላልተማሩትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፤በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መስዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል» ዕብ 5፤1-3

ስለዚህ ይህንን ኪዳን በማስቀረት እግዚአብሔር አዲስ ቃል ኪዳን ለመግባት ወዷል። በዚሁ መሠረት እነዚህን አምስት ነጥቦች የሚያሟላ ነው ፤
1/ ኃጢአትን የሚያስተሰርየው ሊቀ ካህን በሞት የሚሸነፍ መሆን የለበትም።

2/ ሊቀ ካህኑ በመሐላ የተሾመ መሆን አለበት።

3/ ለራሱ መስዋዕት ማቅረብ የማይገባው ንጹህ መሆን አለበት።

4/ ሊቀ ካህኑ እንደኦሪቱ በግ የሚያቀርብ ሳይሆን ራሱ ለኃጢአተኛው በግ ሆኖ መሰዋት አለበት።

5/ ኃጢአተኛው ወደሞተለት ሊቀካህን በመቅረብ መናዘዝ እንጂ ስለኃጢአቱ በግ ማቅረብ አይጠበቅበትም።
ስለዚህ ይህንን የሚያሟላ መስዋዕት እግዚአብሔር አብ ልጁን ወደምድር ልኳል። እሱም ሰው የሆነው ኢየሱስ ነው። 
«ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው» ዮሐ 3፤13 
ኢየሱስ በመሃላ የተሾመ ዘላለማዊ ሊቀካህን ስለሆነ ዛሬ ሌላ ሊቀካህን የለንም። የኦሪቱ የኃጢአት መስዋዕት በግ ከኃጢአት ያነጻ ነበር። የአዲስ ኪዳኑ የእግዚአብሔር በግ ደግሞ ላመኑበት ለዘለዓለም ያድናል። ከዚህ ውጪ የመዳን መንገድ ለሰው ልጅ አልተሰራም። ኢየሱስም «መንገዱ እኔ ነኝ» ያለውም ለዚህ ነው። ሌላ የመዳኛና የመጽናኛ መንገድ በጭራሽ በዚህ ምድር በሌላ በማንም የለም።

«እነርሱም ያለ መሐላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን፦ ጌታ። አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሐላ ካህን እንዳልሆነ መጠን፥እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል።እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።» ዕብ 7፤20-27
ስለዚህ ኢየሱስ በሞቱ ሞቴን ያሸነፈ፤ የሕይወቴ ቤዛና በሥጋ የተገለጠ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። በእርሱም አዳኝነት አምናለሁ። «በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው»  ዮሐ 3፤36 እንዳለው የዘላለምን ሕይወት በሞቱ በኩል አግኝቻለሁ። ከሌላ ከማንም የድኅነትን ተስፋ አልጠብቅም። በኃጢአት ብወድቅ የምነጻው፤ የምነሳው በእሱ ብቻ ነው። የምለምነው፤ የምጠይቀው፤ የምማጸነው እሱን ብቻ ነው። በሩ እሱ ስለሆነም «አንኳኩ ይከፈትላችኋል» በማለት የሰጠኝ የመዳን ተስፋ የማይለወጥ ነውና። ኢየሱስ ለእኔ እንዲህ ነው። እናንተስ የመዳናችሁን ተስፋ የምትጠባበቁት ከእነማን ነው?