Showing posts with label መረጃ. Show all posts
Showing posts with label መረጃ. Show all posts

Saturday, March 26, 2016

ቀሲስ የ“ክብረት ልጅ”፥ ምነው በስድብ ቃል በጣም ጮኸ?!


ምንጭ፦ የአቤኔዘር ተክሉ ገጽ http://abenezerteklu.blogspot.com/
የክብረት ልጅ እይታዎቹን በሚያቀርብበት ብሎጉ፥ “ፓትርያርኩ፦ ለኢትዮጲያ የደኅንነት ፣ ለምእመናን የድኅነት ሥጋት” በሚል አንድ ጽሁፍ፥ ዛሬ አስነብቦ ድንገት ያየ ሰው ጠቆመኝና ወደጡመራው መድረኩ ገብቼ አነበብኩት፡፡ ዳንኤል በዚህ ጽሁፉ “100% ማኅበረ ቅዱሳን ሊያዘጋጀው ከጫፍ የደረሰውን ዐውደ ርእይ የከለከሉት ፤ ያስከለከሉት ፓትርያርኩ ናቸው”፥ ብሎ ደምድሞ አስቀምጦታል፡፡ የዐውደ ርእዩ ባለቤት ማኅበረ ቅዱሳን ደግሞ፥ በዋናው ጸሐፊው አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ በኩል ትላንት ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ “መግለጫ”፥ “ለመታገዱ ፓትርያርኩ እንደሌሉበትና በመንግሥት አካላት መመሪያ መታገዱን”ይፋዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ዳንኤል ፓትርያርኩን ከሰይጣን እኩል ነበር የሳላቸው ፤ “... ፓትርያርክ ማለት በግሪክ “ታላቅ አባት” ማለት ነው፡፡ የታላቅ አባት ተግባር የልጆቹን ሥራ ማፍረስ አይደለም ፤ ለዚህማ አባት አያስፈልግም ሰይጣን እንጂ፤ ...” በማለት፡፡ እንደከዚህ ቀደም ልማዱ ዳንኤል ሌሎች ማስጮኺያዎችንም በዚህ ጽሁፍ ለማካተት ጥሯል፡፡ አዳዲስ ስድቦችንም ለፓትርያርኩ እንደእጅ መንሻ አቅርቦላቸዋል፡፡

ቅዱስ ቃሉ ግን እንዲህ ይላል፥ “ፈራጆችን አትስደብ፥ የሕዝብህንም አለቃ አትርገመው።” (ዘጸ.22፥28) የሕዝብ አለቃ ወይም መሪ የሆነ ገዥ በምድር ላይ የእግዚአብሔር ተወካይ ፤ እንደራሴም ነው፡፡ ስለዚህ ልናከብረው ፤ በመውደድም ከሁሉ በፊት ልንጸልይለት ይገባል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሳያስበው ይህን ቃል በመተላለፉ ምክንያት ወዲያው ተጸጽቶ ተመለሰ ፤ አለማስተዋሉንም ተናገረ፡፡ (ሐዋ.23፥4-5) ፍትሐ ነገሥቱም “በእነርሱ ላይ የተሾመውን ጳጳስ ... እንደትልቅ ወንድም ያክብሩት መሪና አስተዳዳሪ እንደመሆኑ መጠን ሊታዘዙለት ይገባል” ይላል፡፡ (አን.4 ቁ.53) ዳኒ! ይህ የሕግ ቃል አንተን አይመለከትም ይሆን?!

የቤተ ክርስቲያን የቀኖና መጽሐፍ ፍትሐ ነገሥት በአንቀጽ.6 ስለቀሳውስት ድርሻ ባሰፈረበትና ቀሳውስት ከማዕረገ ክህነታቸው ስለሚሻሩበት ሁኔታ ሲዘረዝር “... ሕግን አውቆ የማይሠራባት ... ቄስ ይሻር፡፡” በማለት በግልጥ ያስቀምጣል፡፡ ዳኒ! እንኳን መንፈሳዊውን ሥጋዊውን የዚህን አለም ምድራዊ ሕግ መጣስህን አውቀኸዋል? ማኅበሩ ፓትርያርኩ አልከለከሉኝም እያለ፥ አንተ ግን ለፓትርያርኩ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍተሃል፡፡ እንደቤተ ክርስቲያን ቀኖና ከቅስናህ ትሻር ይሆን? እውነታው ግን አይመስልም፡፡

ፓትርያርኩ ቢያጠፉ እንኳ የቤተ ክርስቲያን ቀኖና ምን ነበር የሚለው? ጅል ፣ ሰይጣን ፣ የክፋት አነሳሽ ... እያሉ በአደባባይ ፓትርያርክን መዘርጠጥ አለበት የሚል “ቀኖና” አለን?! ለመሆኑ ስድብ ከማን ነው? የሕዝብን አለቃ አለማክበርስ? ያንን ሁሉ መጽሐፍ የጻፈው “ደራሲና ተመራማሪ” ምነው ምራቅ እንዳልዋጠ “ፍንዳታ”(የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ቃል ናት) ደርሶ ቱግ አለ?! እንዴ ይህ ነበር እንዴ በውስጡ የነበረው?!

ውድ ወንድሜ ቀሲስ ዳንኤል፦ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና አላት ፤ በየትኛውም የቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ሽቅብ ፓትርያርክን እንዲህ መዘርጠጥ አይደለም ምእመንን መናገር አጸያፊ ነው፡፡ ተግሳጽ ነው ብትለኝ፥ ለመሆኑ ተግሳጽ መቼ ነው የሚመጣው? ደርሰህ ከመገሰጽህ በፊት ስንቴ ይሆን የመከርካቸው? ስንቴ ይሆን የወቀስካቸው? ስንቴ ይሆን ካሉበት ነቀፌታ እንዲርቁ በሚራራ ልብ አዝነህላቸው እንደእግዚአብሔር ቃል በጸሎት ቃል ወደጌታ የማለድክላቸው? ... ደጋፊ ስላገኙ ብቻ ብዙ ማለት፥ ከማያዳላ ኅሊና ጋር ያፋጥጣል፡፡ ወንድምን ሰባት ጊዜ ሰባ ይቅር ማለትና መቀበል እኮ ከአባት ባሻገር ወንድም ለሚሆነን ፓትርያርክንም ያካትታል ፤ ለመሆኑ ይህን ታውቀዋለህን?!

ፓትርያርኩ ቢያጠፉ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና አላት፡፡ “...የአገሩ ሁሉ ኤጲስ ቆጶሳት ስለእርሱ የሚገባውን ይመረምሩ ዘንድ እርሱንም ለማየት በየዓመቱ ሁለት ጊዜ ከጳጳሳቸው (ፓትርያርካቸው) ዘንድ ይሰብሰቡ፡፡ ስለተሰጣቸው ሥልጣን በምታስፈራዪቱ ቀን መልሳቸው የጸናች ትሆን ዘንድ፡፡” (አን.4 ቁ.55) የሚል፡፡ የሚያዩት ፊቱን ብቻ አይደለም ፤ ሥራውን በማየት ያመሰግኑታል ፤ ነቀፌታም ካለ ይነቅፉታል፡፡ ዳኒ! ይህችን አላነበብካት ይሆን?! ፓትርያርኩን መውቀስና መምከር ፤ መገሰጽም ካለብህ መንገዱን አልሳትከው ይሆን? ይህን ያህል ግን ለምን ይሆን የጠላሃቸው? ዳኒ! ወንድምን ስለመጥላት ቃሉ በትክክል ይወቅስሃል፡፡

በእርግጥ ዳንኤልና ማኅበሩ መንገድ ሲተላለፉ ይህ የመጀመርያው አይደለም፡፡ ግን እውነት ለመናገር ባልተጣራ ወሬ ፤ በተራ አሉባልታ ያውም ስንት ሽልማት ያግበሰበሰው ሰው ይቺን ትንሿን ነገር ከማጣራት ቸኩሎ “በሚቆረቆርላት” ቤተ ክርስቲያን መሪ ላይ የስድብ ናዳ ያወርዳል ብሎ ማን ይጠብቃል?! ከዚህ ስህተቱ ይማር ይሆን ዳንኤል? ወይስ ወደፊትም ሌላ የስድብና የመዘርጠጥ ጽሁፍ ያስነብበን ይሆን? ወይስ እንደጳውሎስ በግልጥ የይቅርታ ልብ ይዞ “የሕዝብን አለቃ” ስለተሳደበበት ስድቡ ንስሐ ይገባ ይሆን? የምናየው ይሆናል፡፡ ፈጥነህ ንስሐ ብትገባ ግን ማሰናከያን ታስወግዳለህና እስኪ ቀድመህ ወደራስህ እይ!!!

ጌታ ማስተዋሉን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡

Sunday, February 14, 2016

የቫላንታይን ዴይ ከክርስትና አንፃር!


ስንቶቻችን ይሆን የቫለንታይን ቀን (የፍቅረኞች ቀን ብለን የምናከብረው) የሚከበርበት ምክንያትና መነሻው የምናውቀው? ወይስ ሰው ስለ አከበረውና የስልጣኔ መገለጫ መስሎን ነው የምናከብረው? ክርስቶስ ከመወለዱ ከብዙ ክፍለ ዘመናት በፊት አረማዊ ሮማውያን የካቲት 14 ማታና የካቲት 15 "የተኩላ አዳኙ" ለሚሉት ሉፐርኩስ (Lupercus) ክብር በማለት በጣኦት አምልኮ ያከብሩት ነበር። ሮማውያን ይህ በዓል ሉፐርካልያ (Lupercalia) ይሉታል።
ንጉሥ ቆንጠንጢኖስ ክርስትና የሮማውያን ይፋዊ ሃይማኖት መሆኑ በማወጁ ማንኛውም የጣኦት አምልኮ እንዲቀር ቢያስጠነቅቅም የተወስኑ ሮማውያን ሰዎች ግን በዓሉን ማክበር አልተዉም።
ይህንን አረማዊ በዓል ማለትም ሉፐርካልያ የሮማው ጳጳስ ገላስዮስ ክርስትያናዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር አደረጉ። ጳጳስ ገላስዮስ ለካቲት 15 ሲከበር የነበረው በዓል የቅዱስ ቫለንታይን ቀን በሚል አዲስ ስያሜ የካቲት 14 እንዲከበር አደረጉ።
እንዴት ይህ አረማዊ በዓል የቅዱስ ቫለንታይን ቀን የሚል ስያሜ ተሰጠው?
ቫለንታይን የሚል ስም በሮማውያን ዘንድ የተለመደ ስያሜ ነው። ቫላንታይን ጥንታዊው ታዋቂው ሉፐርኩስ ነው። ሉፐርኩስ በግሪካውያን ፓን (pan) ተብሎ ይጠራል። በጥንታውያን አይሁድ ደግሞ ይህ ፓን በአል (Baal) በሚል ስያሜ ይታወቃል። በአል በመጽሓፍ ቅዱስ ዘፍጥረት 10-9 ላይ ታላቁ አዳኝ ተብሎ ለተገለጸው ኒምሮድ ሌላኛው መጠርያው ነው። ኒምሮድ የሮማውያን የተኩላ አዳኙ ሉፐርኩስ ነበር። በዚህ መሠረትም የቅዱስ ቫለንታይን ቀን የአረማውያን ለኒምሮድ ክብር የሚያከብሩት የጣኦት አምልኮ ነው።
ቫለንታይን የሚል ቃል ቫለንቲኑስ (valentinus) ቫለንስ ከሚል የላቲን ቃል የመጣ ነው። ቀጥተኛ ትርጉሙ ጠንካራ፣ሃይለኛ ታላቅ ማለት ነው። ዘፍጥረት10-9 ላይ እንደምናነበው " እርሱም በእግዚአብሔር ፊት አዳኝ ነበረ። ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት ሃያል አዳኝ እንደ ኒምሮድ ተባለ።  ኒምሮድ የሮማውያን ጀግና ሃይለኛ ሰው ቫለንታይን ነበር።
ሌላኛው የኒምሮድ ስም ሳንክቱስ (Sanctus) ወይ ሳንታ (santa) ነው። ሳይንት (saint) የሚል የእግሊዝኛ ትርጉም አለው ማለትም ቅዱስ። የሮማውያን ሉፐርካልያ በመጨረሻ ቅዱስ ቫለንታይን የሚል ስያሜ ያዘ ማለት ነው።
ጥንታውያን ሮማውያን ከባቢሎናውያን በቀዱት አረማዊ የልብ (heart) ምልክት ይጠቀማሉ። በባቢሎናውያን በአል (baal) ልብ የሚል ፍቺ ነው ያለው። በአሁኑ ጊዜ ይህ አረማዊ የልብ ምልክት ለቫለንታይን ቀን (የፍቅረኛሞች ቀን የምንለው) መገለጫ እንጠቀምበታለን። በአል የባቢሎናውያን የጣኦት ጌታ ነበር። በሌላ መንገድም ኒምሮድ ወይም ቅዱስ ቫለንታይን ሳተርን ተብሎ ይጠራል። ሳተርን የሮማ-ባቢሎን ከአባራሪዎቹ ለመሸሽ በምስጥራዊ ቦታ የሚደበቅ ጣኦት ነው። ሳተርን የሚል የላቲን ቃል ሴሜቲክ (አይሁድ) ቋንቋ ከሚናገሩ ባቢሎናውያን የተገኝ ነው። መደበቅ፣ ራስን መደበቅ የሚል ፍቺ አለው።
በጥንታዊ እምነትም ኒምሮድ (ሳተርን) ከአባራሪዎቹ በመሸሽ ወደ ጣልያን እንደተጓዘ ይነገራል። የአፐኒን ተራራ ስያሜው ወደ ኔምብሮድ ወይም ኒምሮድ ተቀየረ።ይህ ተራራ ኒምሮድ በጣልያን የተሸሸገበት ቦታ ነበር። ሮማም በዚህ ተራራ ላይ እንደ ተመሰረተች ይታወቃል። ሮም ፈርሳ እንደገና ከመሰራትዋ 753 ዓ/ዓ በፊት ሳቹርንያ (ሳተርን፡ኒምሮድ የተደበቀባት ቦታ) የሚል ስያሜ ነበራት። ኒምሮድ በዚህ ቦታ ተይዞ በፈጸመው ወንጀል ተገደለ። በንጉሥ ቆስንጠንጢኖስ ጊዜም ክርስቲያናዊ ሰማዕት የሚል የውሸት ክብር ተሰጥቶት በሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስትያን መዘከር ጀመረ። ኒምሮድ፣ ባል፣ ቫለንታይን፣ ታላቁ አዳኝ፣ ፋውኑስና ሉፐርክስ 31ኛ፣ 32ኛና 33ኛና ደረጃ (ዲግሪ) ላይ ያሉ ፍሪማሶኖሪዎች ከሚያመልኩት ባፎሜት (የሜንደዝ ፍየል) አምልኮ አጋንንት ጋር የሚስተካከል ነው።
እንግዲህ በሰላቢ እጆች (ኢሉሚናቲ) ሴራ ዘመናዊነት ተላብሶ ድብቅ ጣኦት የሚመለክበት የቅዱስ ቫለንታይን ቀን እኛ ደግሞ የፍቅረኛሞች ቀን በማለት እያከበርን ማለትም እያመለክን ነው። አንድ በአል የሚከበርበትን ምክንያትና አስፈላጊነት ሊኖረው ግድ ነው። ሆኖም የምናከብረውን በአል የምናከብርበትን ምክንያትና አስፈላጊነት ሳናውቅ ከሴረኞች ድብቅ አላማ ማስፈጸሚያ ከመሆን መቆጠብ ይበጀናል፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር ነዉ!

Saturday, January 30, 2016

ፓትርያርክ ማትያስ ስለማኅበረ ቅዱሳን የጻፉት ደብዳቤ ከመዘግየቱ በስተቀር ሀቅነቱ ጥያቄ የሚያስነሳ አይደለም!

ማኅበረ ቅዱሳን ማለት ለተረት፤ ለእንቆቅልሽ፤ ለልማድና ለባህል እምነት ጥብቅና የሚቆም፤ የወንጌል ቃል ጆሮውን የሚያሳክከው፤ በኢየሱስ ክርስቶስ የእውነት መንገድ ላይ ቆሞ እንዳይገለጥ መጋረጃ የሚጋርድ የጠላት መልእክተኛ ማለት ነው። ማኅበረ ቅዱሳን በሀገሪቱ ላይ የብርሃን ወንጌል እንዳይበራ የጭለማ ሥራ የሚሰራ፤ ሰዎች በእጃቸው ያለውን እውነት እንዳያዩ ወደገደል የሚመራ እውር መሪ ማለት ነው።
ማኅበረ ቅዱሳን ማለት በአንድ ወቅት የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባለው እስራኤል በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት ትቶ የራሱን የልብ መሻትና ምኞት በተከተለበት ወቅት እንደሆነው ዓይነት በተመሳሳይ መልኩ በሀገራችን በኢትዮጵያም ከፊት ሆኖ በሀሰት እየመራ በእውነት የሚፈርድ እንዲታጣ ያደረገ፤ በሀሰትም የሚያስተምር እንዲበዛ የፈለፈለ፤ ልቡን ያደነደነ ትውልድ እንዲበረከት ሚና የተጫወተ ማኅበር ነው።
ያንን የእስራኤል ዐመጽ ነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ሲል ተናግሮት ነበር።

«እናንተ ሰነፎች ልበ ቢሶች፥ ዓይን እያላችሁ የማታዩ፥ ጆሮም እያላችሁ የማትሰሙ ሕዝብ ሆይ፥ ይህን ስሙ። በውኑ እኔን አትፈሩምን? ከፊቴስ አትደነግጡምን? ይላል እግዚአብሔር፤ እንዳያልፍ አሸዋን በዘላለም ትእዛዝ ለባሕር ዳርቻ አድርጌአለሁ፤ ሞገዱም ቢናወጥ አያሸንፍም፥ ቢጮኽም አያልፍበትም። ለዚህ ሕዝብ ግን የሸፈተና ያመፀ ልብ አላቸው፤ ዐምፀዋል ሄደውማል። በልባቸውም፦ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ በጊዜው የሚሰጠውን፥ ለመከርም የተመደቡትን ወራት የሚጠብቅልንን አምላካችንን እግዚአብሔርን እንፍራ አላሉም። በደላችሁ እነዚህን አስቀርታለች፥ ኃጢአታችሁም መልካምን ነገር ከለከለቻችሁ። በሕዝቤ መካከል ክፉዎች ሰዎች ተገኝተዋል፤ እንደ አጥማጆችም ያደባሉ፥ ወጥመድንም ይዘረጋሉ ሰዎችንም ያጠምዳሉ»           ኤር 521-26

ማኅበረ ቅዱሳን በዘመናት ብዛት ማን እንደጻፋቸውና ማን እንዳስገባቸው የማይታወቁ የተረትና የእንቆቅልሽ መጻሕፍት እንዳይነኩ ዘብ የቆመ የጠላት ወታደር ነው። ብዙዎች እውነት በመናገራቸውም ያወገዘና ያስወገዘ ማኅበር ነው። ለምሳሌ አንድ አስረጂ እናንሳ!

መስተብቍእ ዘመስቀል በተባለው የቤተክርስቲያን የጸሎት ክፍል ውስጥ እንዲህ የሚል ክህደት ተሰንቅሮ ይገኛል። 
«ለእሉ ክልዔቱ ፍጡራን/ለማርያም ወለመስቀል/ ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ፤ እስመ ተዐረዮሙ በክብሮሙ»
ለነዚህ ሁለቱ ፍጡራን  (ለማርያምና ለመስቀል) ለፈጣሪ የሚሰጠው  ምስጋና ይገባቸዋል። በክብር ፈጣሪያቸውን ተካክለዋልና!

 እግዚአብሔር ቢከብር ክብር የባህርይው እንጂ አክባሪ የሚጨምርለትና የሚቀንስለት ነገር የለም። ማንም የቱንም ያህል ቢከበር ከእግአብሔር ፈቃድ አንጻር እንጂ በራሱ ብቃት በሚያመጣው ችሎታ አይደለም። ደግሞም በክብር እግዚአብሔርን የሚስል፤ የሚያክልና አቻ የሚሆን ፍጥረት ፈጽሞ የለም። «በልዑል እመሰላለሁ» ካለው ከሰይጣን በስተቀር ከፍጥረታት ውስጥ በክብር እግዚአብሔርን የሚተካከል የለም።
«ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ» ኢሳ 1414

ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚመስለው ማንም የለም? በማንም ልንመስለውና ከማንም ጋር ልናስተካክለው አይገባም። ራሱ እግዚአብሔር በነቢዩ አንደበት እንደዚህ ሲል ተናግሮናልና።

«እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ። ኢሳ 4025»
  
ማኅበረ ቅዱሳን ማለት እንደነዚህ ዓይነት ተረቶችና ክህደቶች እንዳይነኩ ለእውነት ሁሉ ጠላት ለሆነው ለሰይጣን ጥብቅና ቆሞ የሚከራከር ማኅበር ነው። መንፈሳዊ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የእውቀትና የማስተዋል ተቋማት እንደመሆናቸው መጠን ጥያቄ የሚጠይቁና ከእግዚአብሔር ቃል የተገናዘበ አሳማኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው የሚተጉትን በክህደትና በምንፍቅና እየወነጀለ መቆሚያና መቀመጫ የሚያሳጣ፤ ወይ ከእውቀቱ ወይ ከእውነቱ አንዱንም ያልያዘ ድርጅት በመሆኑ ነው።
ስለዚህ ፓትርያርክ ማትያስ ለመንፈሳዊ ኮሌጆች ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ደብዳቤ ለመጻፍ የተገደዱት ከኮሌጆቹ ተማሪዎች ጥያቄ አንጻር ብቻ ሳይሆን ፓትርያርኩ ለሚያደርጉት ትግል የሊቃነ ጳጳሳቱ ድጋፍ አናሳ ሆኖ በመገኘቱ ቢያንስ የትግላቸው አጋር የተማረውን ክፍል ለመያዝ ከመፈለግ የተነሳ ይመስላል።
በዚህ አጋጣሚ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎችና የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ ግድ የሚለው ሁሉ ከፓትርያርኩ ጋር በመቆም የያዙትን ትግል ከግብ ለማድረስ በጸሎትና በሃሳብ እንዲያግዝ ለማሳሰብ እንወዳለን።
ደብዳቤዎቹን ለማንበብ ሊንኩን ከከፈቱ በኋላ ለማስፋትና በደንብ ለማንበብ ጽሁፉን ይጫኑት!
እዚህ ይጫኑ 1

እዚህ ይጫኑ 2

እዚህ ይጫኑ 3

እዚህ ይጫኑ 4

Friday, January 1, 2016

ስለአንዳንድ በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ላይ…ከአንዳንድ የኦሮሞ ጸሐፍት የተሰነዘሩ…ያስቀየሙኝ ክታቦች!!


 (በአማን ነጸረ ክፍል 4)

(7.1) ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ በጻፉት በመጀመሪያው ‹‹ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ›› መጽሐፋቸው ገጽ-137 ይሕንኑ ሁኔታ (የቶፋ ሥርዓት) በጥቁምታ ያመላክቱናል፤እንዲህ ሲሉ ‹‹በኢትዮጵያ የካሕናት ቁጥር እጅግ ብዙ ነው፡፡ለነዚሁም ሁሉ መንግሥት ከያውራጃው ከግማሽ እስከ አንድ ጋሻ መሬት ለእያንዳንዱ ካሕን ርስት እያደረገ ሰጥቷቸዋል፡፡ይኸውም ርስት እየሆነ የተሰጠው መሬት ለልጅ ልጅ የሚያልፍ [በመሆኑ] ቤተክርስቲያን ልታዝዝበት አትችልም፡፡በዚህም ላይ ከንጉሠ-ነገሥቱ ዠምሮ መሳፍንቱ መኳንንቱም ሌላውም እነሱን የመሰለው ሁሉ ወይዛዝርት እንኳ ሳይቀሩ የቤተክርስቲያን ገበዞች እየሆኑ ከ200 እስከ 700 ጋሻ መሬት ንጉሠ-ነገሥቱ ርስት እያደረገ ይሰጣቸዋል...›› በማለት ይዞታው በወሬ የኢኦተቤክ እየተባለ ስመ-ንብረቱ (title deed) ግን በተግባር በንጉሡ፣በመሳፍንትና ወይዛዝርት እጅ እንደነበረ፤እነዚህ መሳፍንትና ወይዛዝርት ሲያልፉም ልጆቻቸው የቤ/ክ ትምህርት ባይማሩም ‹ገበዝ› በሚል መጠሪያ ርስቱን ወርሰው ደሃ ካሕናትን እያስቀደሱ በስመ ተዋሕዶ የሚያደርጉትን ብዝበዛ (የቶፋ ሥርዓት) ስሙን ሳይጠሩ ያብራሩልናል፡፡
(7.2) በ1967 ዓ.ም የመሬት-ላራሹ ዐዋጅ ሲታቀድ በካሕናት እጅ እንደዜጋ የነበረውን መሬት ሁሉ በነባሩ ‹‹የሲሶ መሬት ይዞታ›› ትረካ አጠቃሎ የመውረስ አዝማሚያ አስፈርቶ ነበር፡፡ሁኔታው ያሳሰባቸው የጊዜው የኢኦተቤክ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በ1967 ዓ.ም ለደርግ በጻፉት ደብዳቤ ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ ‹‹...ተጋኖ ሲነገር የኖረው ጨርሶ ያልነበረ የመንግሥት ሥልጣን ድርሻና የሀገሪቱ ሲሶ መሬት ወሬ ፈጽሞ ተረት ቢሆንም ያው ያለው መጠነኛ ድጋፍ እስካሁን ድረስ ከመንግሥት ሲሰጣት ቆይቷል›› በማለት ‹‹ያው ያለው መጠነኛ ድጋፍ›› እንዲቀጥል ተማጽነው ነበር፡፡ፓትርያርኩ ጥያቄያቸውን በ7 ነጥቦች አብራርተው ነበር ያቀረቡት፡፡2ቱን ብቻ ልጥቀስላቸው ‹‹1ኛ. የኢትዮጵያ ገዳማት መሬት ያንድነት ማኅበር እንደ መሆኑ መጠን ይኸው በይዞታቸው ያለው የንፍሮ መሬታቸው በይዞታቸው ስር እንዲቆይ እንዲፈቀድላቸው፣እንዲሁም ‹በርሷ (በኢኦተቤክ) ስም ተይዘው ሌሎች ወገኖች ሲጠቀሙባቸው የኖሩ መሬቶች ቢወሰዱ የምትጎዳበት ባይኖርም› እስከ ዛሬ በቀጥታ ስትረዳባቸው የቆዩ አንዳንድ መሬቶች በይዞታዋ ስር እንዲቆዩላት፤2ኛ. በግብርና ስራ የሚተዳደሩ ካሕናት ሁሉ ካሕንነታቸው ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን ስለማይሽረው እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የመሬት ድርሻቸውን የማግኘት መብታቸው እንዳይዘነጋባቸው››ብለው ጠይቀው ነበር (መምህር ኪዳነማርያም ጌታሁን፡ገ.102)፡፡
(7.3) በደስታ ተክለወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ገጽ 1267 ‹‹ወኪል፣ምትክ፣ተጠሪ፣ገባሪ›› ተብሎ ስለተተረጎመው ‹‹ቶፍነት›› ሌላ ዋቢ እንቁጠር፡፡‹‹የኢኦተቤክ አስተዳደር በየዘመናቱ››የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ ብፁዕ አቡነ ገሪማ (ዶ/ር) ስለዚህ ጉዳይ ሲተርኩ ‹‹ለቤተክርስቲያን መግባት የሚገባውን የግብር ገንዘብ መሳፍንቱ፣መኳንንቱ፣ባላባቶችና ወይዛዝርት በግብዝና በእልቅና፣በመሪጌትነት፣በድብትርና፣በቅስና፣በዲቁና እና በልዩ ልዩ [የ]ክሕነት [አገልግሎት] ስም ርስት እየያዙ በግል እየተጠቀሙ በተወሰነ ክፍያ ወይም በቶፍነት ካሕናትን ያስገለግሉ ነበር›› ይሉናል፡፡አቡነ ገሪማ ታሪኩን ሲቀጥሉ ‹‹…የቤ/ክ መተዳደሪያ ብዛት ጎልቶ ከመታየቱ በቀር ለካሕናቱ መተዳደሪያ ይሆን ዘንድ የተፈቀደው ርስተ - ጉልት የሚሰጠው ጥቅም የአገልጋዮች ካሕናትን ችግር ከመሸፈን አኳያ በቂ አልነበረም፡፡…ከሚያጋጥሙት ችግሮች መካከል፡- ያልቀናውንና በረሃማውን መሬት እየሰጡ የለማውን መሬት መቀማት፣ለም የሆነውን መሬት በጠፍ መሬት መለወጥ፣የኩታ ገጠም አቀማመጥ ያለውን ርስት ወደ ግል ይዞታ ማስገባት…ይገኙበታል›› ይላሉ (አቡነ ገሪማ፡ገ.64-70)፡፡
(7.4) ከላይ ያለችውን የ“ቶፍነት” ሥርዓት ጽንሰ - ሐሳብ ለመረዳት ከመርስዔኀዘን ‹‹ትዝታዬ›› መጽሐፍ ገጽ-92 ማሳያ እንጨምር፡፡የድጓ መምህር የነበሩት ኣባታቸው ሲሞቱ የአባታቸውን መሬት ወርሰው እንደ ባለርስት መገበራቸው ቀርቶ እንዴት ወደ ቶፍነት እንደተሸጋገሩ ሲተርኩ ‹‹…እንግዲህ የምትገብረው በአባትህ ሥም አይደለም፣መሬቱ ለፊታውራሪ ጥላሁን ስለተሰጠ ሥመ - ርስቱ ተዛውሯል፤ሆኖም ለፊታውራሪ ጥላሁን በቶፍነት ልትገብር ትችላለህ…›› እንደተባሉ ይገልጻሉ፡፡ከመርስዔኀዘን አባባል እንደምንረዳው የመንግሥት ሹም የነበሩት ፊ/ሪ ጥላሁን ለድብትርና ተብሎ ለይስሙላ የተመደበውን ርስት ወርሰው ይዘው ደብተራውን (መርስዔኀዘንን) ‹‹ቶፋ›› አድርገዋቸዋል፡፡ታሪክ ግን ፊታውራሪ የያዙት ርስት ለስሙ የኢኦተቤክ ስለተባለ ብቻ ‹‹ሲሶ የቤተክሕነት ድርሻ›› ብላ ያልበላነውን ልታስተፋን ትጥራለች!!ቆዩማ ይቺን ታሪክ የሚሏትን ጉድ በጎጃምኛ ልስደባት ‹‹ኧግ!ይቦጭቅሽ!››
(7.5) ይሄን ሀቅ ጠጋ ብለው ያላዩልን እነ መኩሪያ ቡልቻ እና አባስ ሐጂም ነዋሪ ነባሪውን ስሑት የወሬ ጫፍ ይዘው <<...the clergy were....landlords,they owned Oromo peasants as Gabbars...>> ይሉናል!እርግጥ ይሕ በነአቶ አጽሜ ጸረ-ካሕናተ-ኦርቶዶክስ ጥላቻ ተከትቦ እስካሁን የሚናፈስ የታሪክ አረዳድ ኢህአዴጋውያንን ጨምሮ የብዙኃኑ ልሂቅ አረዳድ ስለሆነ እነ መኩሪያ ቡልቻንና አባስ ሐጂን ነጥሎ መውቀስ ኢ-ፍትሐዊ ሊሆን ይችላል፡፡በቁሳዊ ሀብትና በካሕናት ኑሮ ረገድ የዛሬዋ የኢኦተቤክ ያለችበትን ከቅድመ-1967 ዓ.ም የመሬት ዐዋጅ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ አቅም ያስተዋለ ሰውማ በእርግጥም አቡነ ቴዎፍሎስ እንዳሉት በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚተረከው ‹‹የሲሶ መሬት›› ድርሻ ‹‹ፈጽሞ ተረት›› እንደነበረ ይገለጽለታል፡፡እኛማ ትናንት በተወረሱባት ሕንጻዎች ምትክ ከደርግ የ5 ሚሊዮን ብር ምጽዋት ትጠብቅ የነበረች ቤ/ክ ዛሬ ገንዘብ አያያዟ ባያስደስተንም እንኳ በጀቷ ቢሊዮን መሻገሩን አይተናል፡፡እናም የትናቱ የተረት ተረት ‹‹ሲሶ ግዛት›› ከቶም አያቃዠንም!!አባቴ እንዲህ ይል ነበር ‹‹ድሮ ካሕን ስሙና ማዕረጉ ብዙ ነው፤በቤቱ ግን ሙሉ እንጀራ ቆርሶ የሚበላ ከስንት አንድ ነው፤በነገሥታቱ ከባቢ ካሉት በቀር ድሆችን ካሕናት የሚፈቅድ የለም፤ከነተረቱም ‹የካሕን ልጅ ስም ይጠግባል፤እንጀራ ግን አይጠግብም› ይባል ነበር፤መምህራኖቻችን የኖሩት ተማሪ ለምኖ እያበላቸው ነው፤አየ!፤ተውኝማ ልጄ!››
(7.6) ትውልዱ ባይገለጽለትም እኛ መከራና ስቃይ ከካሕናት ወላጆቻችን የወረስነው ‹ምድጃ የላቀን፤አመድ የወረሰን፤ደሃ የድሃ ልጆች› ወላጆቻችንን ዘበናይ ሁላ ተማርኩ ብሎ ‹‹ሲሶ-ሲሶ!›› እያለ በእንግሊዝኛ ሲዘባነንባቸው እንገረማለን፡፡በተሳልቆ ‹‹ኡኡቴ!ድንቄም ሲሶ!›› እንላለን፡፡ትናንት በነበሩ ብዙኃን ካሕናት ወላጆቻችን ያልተጠገበ ጥጋብ የዛሬዎቹ ሕያዋን ልጆቻቸው እንድንሸማቀቅ የሚሹትን የባለቅኔውን ድንቅ አባባል ተውሰን፡-
‹‹እስመ-እንዘ-ቦ፡ሕያወ፡እሞተ-ሥጋ፡ግዙፍ፣
ሞተ-ዮሴፍ፡አኃዊሁ፡ነገርዎ፡ለዮሴፍ፡፡››እንላቸዋለን--ለቀባሪው ማርዳት!!ሁሉን ትተን የታላላቆቹን ሊቃውንት የነክፍለ ዮሐንስ መራብና መታረዝ የሚያመላክቱና ቅኔያዊ ቁዘማዎቻቸውን የገለጹባቸውን ቅኔያት እንጠቃቅሳለን፡፡እንዲህ፡-
‹‹...ልብስየሂ፡ምንንት፡መንጦላእተ-ርኅቅት፡ነፍስ፣
እስመ-አነ፡ከመ-ዶርሆ፡እምላእለ-አብራክየ፡እለብስ፡፡››
እያሉ እኒያን የመሰሉ ሊቃውንት እርቃናቸውን እንኳ በቅጡ መሸፈን አቅቷቸው እንደ ዶሮ ከጉልበት በላይ ተራቁተው በ‹‹ሲሶ ግዛት››ተረት አእጽምቶቻቸው እረፍት ሲያጡ ከማየት የሚደርስብንን ሕማም በቅኔያቱ እናስታምማለን፡፡ደግሞም የዋድላው የኔታ ሲራክ ራሳቸውን ከአህያና በቅሎ ጋር እያነጻጸሩ የ30 ብር ዓመታዊ ደሞዝ ሰቆቃዊ አኗኗራቸውን፡-
‹‹አእዱግ፡ወበቅል፡እንዘ-ያወጽኡ፡ስልሳ፣
ሲራክ፡አምላከ-ዋድላ፡ተሰይጠ፤ለሠላሳ፡፡››
እያሉ የገለጹባቸውን ቅኔያት እያስታወስን እንግሊዝኛ ተናጋሪ ደባትሮቻችን ወደ ልባቸው ተመልሰው ሚዛኑን የጠበቀ ጽሑፍ እንዲያቀርቡል እንጸልያለን፡፡አንዳንዴም እንጎተጉታለን፡፡አልፎ አልፎም ሕመማቸው ሕመማችን መሆኑን ሳንስት በተጋነነ ቅሬታና ፍረጃ መስመር ሲለቅቁብን ከወዲህ የላላውን ለመወጠር ከወዲያ የተወጠረውን እንጎትታለን--እንዲህ እንዳሁኑ!
የላላው ይወጠር፤የተወጠረው ይርገብ፡፡ወይኩን ማዕከላዌ!አሜን!ይኹን፤ይደረግ!
፡፡፡፡፡፡፡፡በአማን ነጸረ፡፡መስከረም 2008 ዓ.ም፡፡፡፡፡፡፡፡
ማጣቀሻዎቼ!
ሀ. መጻሕፍት(ሃርድ ኮፒ)
1. ብፁዕ አቡነ ገሪማ (ዶ/ር)፣የኢኦተቤክ አስተዳደር በየዘመናቱ፣ጥቅምት 2000 ዓ.ም፣ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት
2. ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ(M.A)፣የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ፣1986 ዓ.ም፣2ኛ እትም፣ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት
3. በኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንትና ጳጳሳት፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻(2000 ዓ.ም)፣በ2000 ዓ.ም፣ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት
4. አባ አንጦንዮስ አልቤርቶ (ዶ/ር) (ካፑቺን)፣የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ታሪክ በኢትዮጵያ፡ከብፁዕ አቡነ ጉሊየልሞ ማስያስ እስከ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ጃሮሶ (1841-1941 ዓ.ም)፣1993 ዓ.ም፣ንግድ ማተሚያ ድርጅት
5. ታቦር ዋሚ፣የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፣በ2007 ዓ.ም፣3ኛ እትም፣አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት
6. መርስዔኀዘን ወልደቂርቆስ፣ትዝታዬ፡ስለራሴ የማስታውሰው፣2002 ዓ.ም፣አስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅት፤ሮኆቦት አታሚዎች
7. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ (1ኛ መጽሐፍ)፣1965 ዓ.ም፣ብርሃንና ሰላም ወዳማዊ ኃይለሥላሴ ማተሚያ ቤት
8. አለቃ ተክለኢሱስ ዋቅጀራ (ሐተታ በዶ/ር ስርግው ገላው)፣የኢትዮጵያ ታሪክ፣2000ዓ.ም፣ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት
9. በቀለ ወልደማርያም አዴሎ፣የካፋ ሕዝቦችና መንግሥታት አጭር ታሪክ፣1996 ዓ.ም፣ሜጋ ማተሚያ ድርጅት
10. ዶናልድ ሌቪን (ትርጉም በሚሊዮን ነቅንቅ)፣ትልቋ ኢትዮጵያ፣2007 ዓ.ም፣አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ
11. ቅዱስ ያሬድ፣መጽሐፈ-ድጓ፣1988 ዓ.ም፣ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት
12. ከአባቶች ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ፣የውዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጉም፣1990 ዓ.ም፣ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት
13. የእጅ ጽሕፈት የግእዝ መማሪያ ግስ/መዝገበ-ቃላት(በራሴ ተቀድቶ የተማርኩበት)፡፡
14. እነ አለቃ አፈወርቅ ዘውዴ፣የግእዝ ቅኔያት የስነጥበብ ቅርስ-2፣1980 ዓ.ም፣ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት
15. መምህር ኪዳነማርያም ጌታሁን፣የሐሰት ምስክርነት፣1994 ዓ.ም፣ንግድ ማተሚያ ድርጅት
16. ሰሎሞን ጥላሁንና ሥምረት ገ/ማርያም፣ደማቆቹ፣2000ዓ.ም፣
17. ደስታ ተክለወልድ፣ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፣1962 ዓ.ም፣አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት
18. የኢትዮጵያ መጽሐፍቅዱስ ማኅበር፣የመጽሐፍቅዱስ መዝገበቃላት፣1992 ዓ.ም፣6ኛ እትም፣ባናዊ ማተሚያ ቤት
19. ላጵሶ ጌ.ድሌቦ (ዶ/ር)፣የኢትዮጵያ ረጅም ሕዝብና ታሪክ አንደኛ መጽሐፍ፣1982 ዓ.ም፣ንግድ ማተሚያ ድርጅት
ለ. የኢንተርኔት መጻሕፍት(ሶፍት ኮፒ) እና መጣጥፎች!
1. የመኩሪያ ቡልቻ፣የገመቹ መገርሳ እና የቶማስ ዚትልማንን ጽሑፎች ለማግኘት http://www.diva-portal.org/…/get/diva2:277262/FULLTEXT01.pdf
2. የመሐመድ ሐሰንን ጽሑፍ https://zelalemkibret.files.wordpress.com/…/jos-volume-7-nu…
3. የአባስ ሐጂን http://69.162.74.242/~iprenewi/r.php… ወይም http://69.162.74.242/~iprenewi/r.php…
4. በወለጋ ስለነበረው የሚሽኖች እንቅስቃሴ GILCHRIST, HORACE ERIC የጻፈው የ2ኛ ዲግሪ ማሙያ http://repository.lib.ncsu.edu/…/bits…/1840.16/844/1/etd.pdf
5. ፕ/ር ታምራት አማኑኤል የአለቃ ዐጽመጊዮርጊስን እና የነአለቃ ታዬ ታሪክ ጨምሮ የቀደምት ጸሐፍያንን ስራዎች ባጭሩ የዳሰሱበት መጽሐፍ http://www.ethioreaders.com/…/About-Ethiopian-Authors-Prof-…
6. ስለኦሮሞ ሕዝብ የሃይማኖት ተዋጽኦ https://en.wikipedia.org/wiki/Oromo_people#Religion
7. ‹‹ጋላ›› የሚለው ቃል በሶማሌ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ያለው የተለያየ ትርጉም https://www.yumpu.com/…/the-galla-myth-on-somali-history-or…
8. ስለ Krapf ሚሲዮናዊ ሕይወት https://en.wikipedia.org/wiki/Johann_Ludwig_Krapf
9. ‹‹ጋላ›› የሚለው ቃል ኬንያም ውስጥ በታሪክ መጻሕፍት ጥቅም ላይ ሲውል ስለመኖሩ የሚያሳይ ደብዳቤ http://yassinjumanotes.blogspot.com/…/stop-use-of-word-gall…
10. በዚች መዝሙር ላሳርግ Ethiopian Orthodox Mezmur in Afaan Oromo- Waldaa Qulqullootaa - Galanni Waaqayyoof haa ta'u https://www.youtube.com/watch?v=tER05f165A8
http://www.diva-portal.org/…/get/diva2:277262/FULLTEXT01.pdf

Tuesday, October 27, 2015

ስለአንዳንድ በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ላይ…ከአንዳንድ የኦሮሞ ጸሐፍት የተሰነዘሩ…ያስቀየሙኝ ክታቦች!!

ከአማን ነጸረ (ክፍል 3)
(6.6) እስኪ እነዚህ ምዕራባውያን ሚሽነሪዎች ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ባሕል የነበራቸው አመለካከት ከኢኦተቤክ ሊሻል ይቅርና ምን ያህል የዘቀጠ እንደነበረ በራሳቸው መነጽር እንፈትሽ፡፡ Eric Gilchist የተባለ አሜሪካዊ በነመኩሪያ ቡልቻ ‹‹የአቢሲኒያ ትርክት›› ተጽእኖ ስር ሆኖ እንኳ በሠራው የ2ኛ ዲግሪ (ማስትሬት) ማሙያ ጥናት <<....as a result of their fundamental beliefs, SIM [Sudan Interior Missonary] missionaries viewed all non-Chiristean religious practices as evil and they demanded that their converts compeletly change their life style, with no compromise to accommodate local customs....>> በማለት ሚሲዮናውያኑ ለነባሩ የኦሮሞ ባሕል የነበራቸውን የተዛባ አመለካከት ካሳየን በኋላ Dough Priest የተባለውን በወለጋ ከ10 ዓመታት በላይ የሚሲዮናውያን መሪ የነበርን ትምክተኛ ሰው ጽሑፍ በመጥቀስ <<...the lives of the Galla people in general were one round after another of drunkness,adultery,thievery,lying,fighting,cheating,and worshiping false gods....today,many of the lives in our area have changed greatly....>> እያሉ (ሚሽኖቹ) ራሳቸውን ወለጋን የታደገ መሲኅ አድርገው ይመጻደቁ እንደነበር ጽፏል--ይቅርና ባሕሉን እንደ ባሕል ሊቀበሉ ( Eric Gilchist፡p.74)፡፡አናሲሞስ ነሲብም ቢሆን ሁሉንም የኦሮሞ አኗኗርና ባሕል ‹‹ቅዱስ›› ብሎ የተቀበለ አይመስልም፡፡በአንድ ደብዳቤው ላይ በስብከታቸው ስላመጡት ለውጥ ሲገልጽ ‹‹...በጋብቻ ላይ የሚፈጸም ጋብቻን እና በአካባቢው የሚታዩ ጎጂ ልማዶችን አጥብቀን ተፋልመናል፤እናም በዚህ በኩል ተሳክቶልናል፡፡ከዚህ ሌላ በኅብረተሰቡ መካከል ይዘወተር የነበረው የጥንቆላ፣የድግምት፣ለክፉ መናፍስት መሥዋዕት የማቅረብ ልማድ፣ሐሰተኛ ምስክርነት፣ውሸትና ሌላም ጎጂ ልምዶች ከዓመት ወደ ዓመት እየቀነሱ መጥተዋል›› ብሎ ነበር (ደማቆቹ፡ገ.35)፡፡እዚህ ላይ አንድ ሀቅ ላስታውስ፡፡በሰሜን ኢትዮጵያም ቢሆን አናሲሞስ ያነሳቸው ከክርስትና ጋር የሚቃረኑ ባሕላዊ ጎጂ ልማዶችና አምልኮዎች ነበሩ፡፡ዛሬም ርዝራዣቸው አለ፡፡ችግሩ በኦሮሚያ ብቻ የነበረ/ያለ አይደለም፡፡ስለሆነም ማንም በማንም ላይ ሊመጻደቅ አይችልም፡፡
(6.7) እስልምና የኦሮሞን ባሕል በምልዓት ይቀበላል የሚል ካለም እስኪ እንፈትሽ!! ‹‹Islamic Front for Liberation of Oromia›› የሚል ሃይማኖት ጠቀስ የኦሪሚያ ነጻ አውጪ ሽምቅ ተዋጊ በሼክ አብዱል ከሪም (ሼክ ጃራ አባ ገዳ) መፈጠሩን፣በባሌ አካባቤ ‹‹የሶማሌ አቦ...›› የሚባል አፍቃሬ-ሶማሊያ የኦሮሞ ሙስሊሞች የፖለቲካ ቡድን በታሪክ መታየቱን፣ይኸው ቡድን በ1969 ዓ.ም ከዚያድ ባሬዋ ሶማሊያ በእስልምና ስም ተቃቅፎ ኢትዮጵያን ያውም ሐረርጌን መውጋቱን፣ከሽግግር መንግስቱ ምስረታ ጀምሮ በተደጋጋሚ በምድረ-ኦሮሚያ እየተንቀሳቀሱ በወሐቢያና በሃዋርጃ ስም ብሔር ሳይለዩ ኦርቶዶክሳውያንና ለዘብተኛ ሙስሊሞችን እንዲሁም ፕሮቴስታንቶችን በተለይ ደግሞ የመካነ-ኢየሱስ ሉተራውያንን ያጠቁ የሙስሊም አክራሪዎችን ድርጊት እንደቀላል የእኩልነት ጥያቄ ብቻ እንድናየው እነ አባስ ሀጂ ስለመከሩን እንዳላየ እንለፈው፡፡ነገር ግን ከአክስት ልጅ ጀምሮ መጋባትን የሚፈቅደው የእስልምና ስብከት እንኳንስ ከአክስት ልጅ ጋር ከጎሳ አባል ጋርም ጋብቻን ከሚከለክለው የኦሮሞ ብሉይ ልማዳዊ ሕግ ያለው ተቃርኖ፣ኦሮሙማን በምድረ-ኦሮሚያ ለመገንባት ከሚታገለው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ጋር ‹ድንበር-ለምኔ› የሚለው ዘመናዊው እስልምና ያለው አለመጣጣም፣እንዲሁም ወደ ድሬ ሼክ ሁሴን መሄድን ወደ አባ ሙዳ እንደሚደረግ ምትክ መንፈሳዊ ጉዞ (ጂላ) የማይመለከተው የዘመኑ እስልምና (ወሀቢዝም) በነአባስ ሐጂ (Abas Haji:p.110-113) ቀደም ሲል ለስላሳ ትችት ሲደርስበት የነበረ ቢሆንም አሁን አሁን ግን እስልምና በኦሮሚያ ኤሊቶች ዙሪያ ኃይል እየተሰማው ስለመጣ ነው መሰለኝ ትንፍሽ የሚል የለም፡፡በነገራችን ላይ የልሂቁን ኦሮሞ ድምጽ የሚቃኙት በዋናነት ሙስሊም የመደብ ጀርባ ያላቸው ኦሮሞ ልሂቃን ሲሆኑ በተከታይነት የምዕራብ ኦሮሚያ ፕሮቴስታንቶች ያጅቧቸዋል፡፡ለሃይማኖት ልዩነት ልበ-ሰፊ ከነበረው ሜጫ እና ቱለማ መፍረስ በኋላ ባሉ ኦሮሞ-ተኮር አደረጃጀቶች ኦርቶዶክሳውያን ኦሮሞዎች በኅቡዕና በገሀድ ክፉኛ እንዲሸማቀቁና ከኦሮሞነት እንደወረዱ እንዲሰማቸው ሰፊ አግላይ ፕሮፖጋንዳ ተሰርቷል፤እየተሰራ ነው፡፡
(6.8) ካቶሊክስ ለምን ይቅርባት?!ትፈተሸ::የካቶሊክ ሚሽነሪዎች ገና ወደ ክርስትና ያልገባችውን ምድረ-ኦረሚያ (ፊንፊኔ) እንዴት ይመለከቷት እንደነበር አባ አንጦንዮስ ሲጽፍ ‹‹...የፊንፊኔና የአካባቢው ሕዝብ በጨለማ ውስጥ በሞት ጥላ ስር ይኖር ስለነበር የወንጌል ስርጭት በእርግጥ አስፈላጊ እንደነበር አባ ቶረን ሻኽኝ አስረድተው በአካባቢው የወንጌል ትምህርት ለማድረስ ቢያንስ አራት ወይም አምስት ተጨማሪ ሚሲዮናውያን እንደሚያስፈልጉዋቸው ኣሳስበው ነበር››ይሉናል (አባ አንጦንዮስ፡ገ.126) የአባ ቶረን ሻኽኝን የጥቅምት 14 ቀን 1868 ዓ.ም ደብዳቤ ጠቅሰው፡፡የባሪያ ንግድ፣ሴት ልጆችን ያለፈቃዳቸው መዳር፣በጋብቻ ላይ ጋብቻ የመሳሰሉ በኦሮሞና ሲዳማ ግዛቶች የሰፈኑ ልማዶች ለካቶሊካውያን ሚሽነሪዎች ፈተና ሆነው እንደነበርም አባ አንጦንዮስ በዚሁ መጽሐፍ ከገጽ 120 ጀምሮ ለስለስ ባለ የሚሲዮናውያን ቋንቋ በጊዜው የነበረውን ጎጂ ባሕል ተችተው ተርከውታል፡፡
(6.9) ከላይ የቀረቡት በኦሮሞ ባሕልና እምነት ላይ ያሉ አመለካከቶች ከራስ አስተሳሰብ/ሃይማኖት ውጭ ያለውን ባሕላዊ/ሃይማኖታዊ አመለካከት በራሱ በባሕሉ ዐይን ሳይሆን ‹‹በግል›› መለኪያ መለካት የሚያመጣውን የተዛነፈ ችግር ያንጸባርቃሉ፤ችግሩ ይብዛም ይነስም በሁሉም ወገን አለ--በሁሉም--የኢኦተቤክ ምዕመናንና የዋቄፈና አማንያንን ጨምሮ፡፡የዚህ አመለካከት አንጸባራቂ ከሆኑ ግለሰቦች አንዱ የሆነው Krapf የጻፈውን የኛው መሐመድ ሐሰን እንዳለ ገልብጦ በኦሮሞ ጥናት መጽሔት ቁጥር-7 ላይ በገጽ-118 ያሰፈረውን እንይ! <<...the Amhara Clergy were not sensitive to Oromo food habits in which milk, butter and meat were central>> ሲል አስቀምጦታል፡፡በKrapf ፕሮቴስታንታዊ እይታና በመሐመድ የከረረ ብሔርተኛ ምልከታ መሰረት የኢኦተቤክ የዐማራ ብቻ ናት፤የኢኦተቤክ ዶግማና ቆኖና አፈጻጸሙም ከብሔር-ብሔር እየተለያየ መተግበር አለበት!በነመሐመድ እምነት ለምሳሌ፡- የደብረብርሃን ዐማራ ኦሮቶዶክሳውያን በፍልሰታ ከሥጋና ቅቤ ሲታቀቡ የእነሱ ጎረቤት የሆኑት የልቼ እና የሸኖ ኦሮሞዎች ግን በፍልሰታ ስጋና ቅቤ የተከለከሉት በሃይማኖቱ ዶግማና ቀኖና ሳይሆን በዐማራ ቸልተኝነት ነው!!የደጀን (ጎጃም) አባይ ዳር ያሉ የቅ/ሩፋኤል ቤ/ክ አካባቢ ዐማራ ጸዋሚዎች በጾም ከስጋ ታቅበው፤በሌላ በኩል በሰ/ሸዋ ገርበ-ጉራቻ የፍልቅልቅ እና አካባቢዋ የቅ/ሩፋኤል የአባይ ዳር (የደራ?) ኦሮሞ ኦርቶዶክሳውያን ጾማቸውን ከስጋና ወተት ጋር ማከናወን ነበረባቸው!!ይሄ ያልሆነው የኢኦተቤክ ኋላቀር ስለሆነች ነው--በመሐመድና በKrapf አረዳድ!!እሺ!የኢኦተቤክ የጾም ስርዓትስ በነመሐመድ ጥልቅ የነገረ-ኦርቶዶክስ ጥናት የዐማራ ቀሳውስት ፈጠራ ነው ተብሏል!ሰው እንዴት ከግብጽ እስከ ሕንድ፣ከሶርያ እስከ አርመንያ፣ከአቴንስ እስከ ሞስኮ፣ከአስመራ እስከ አልባኒያ ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ በጾማቸው ወራት ጥሉላት ምግቦችን (የእንስሳት ተዋጽኦዎችን) እንደማይመገቡ ጎግልን ጎልጉሎ መረዳት ያዳግተዋል??መሐመድ ሐሰንን የሚያክል የታሪክ ባለሙያ ለጾም ያን ያህል የተደነገገ ዝርዝር ቀኖና ከሌለው የክርስትና ዘውግ (ፕሮቴስታንት) ሃይማኖታዊ ግንዱ የሚመዘዘውን (ፓስተር?) Krapf ምንጩ አድርጎ እንዴት ስለ ኢኦተቤክ የጾም ቀኖና ብይን ይሰጣል? ከሰጠስ ለምን የረመዳን አጽዋማት በኦሮሚያ ያላቸውን አቀባበል ጨምሮ መርምሮ በንጽጽር አይተነትንልንም?‹‹ሌሊት እየተመገቡ ቀን-ቀን መጾምን የሚደነግገው ረመዳን ከኦሮሞ ባሕል ጋር ያለው ተዛምዶ እንዴት ይታያል?በሙስሊምና በኦሮሞ ኦርቶዶክሳውያን መካከል ያለው የሃይማኖት ሕገጋት አቀባበል ከኦሮሞ ባሕል ጋር ያለው አንጻራዊ ውሕደትስ?›› ብለን ብንጠይቅስ?
7-- ክስ-ሰባት፡- የኢኦተቤክ እንደመሬት ከበርቴ (ባለ‹‹ሲሶ›› ግዛት)!!
በሁሉም የሀገራችን ጸሐፍያን የኢኦተቤክ ባለሲሶ ይዞታ የነበረች መሆኗ በስፋት ተጽፏል--በራሷ መጻሕፍት ሳይቀር፡፡እነ መኩሪያ ቡልቻም ይህንኑ ደጋግመው ጽፈውታል፡፡አባስ ሐጂም የቡልቻን ጽሑፍ ጠቅሶ <<...the clergy were given land that was confiscated from the Oromo peasants and become landlords, they owned Oromo peasants as Gabbars (serfs) and thrived upto their labour...>> በማለት ብሶቱን ያቀርባል (Mekuria cited in Abas Haji:p.104)፡፡ጥሩ፡፡እዚህ ላይ አንድ እውነት አለ::በኦሮሞም ሆነ በተቀሩት ብሔር-ብሔረሰቦች (ዐማሮችንና ትግራውያንን ጨምሮ) ‹የሰሞን መሬት› የሚባል የቤ/ክ ይዞታ አይነት ነበር፡፡ነገር ግን የዚህ መሬት ይዞታ ለስሙ የኢኦተቤክ ይባል እንጂ ባለቤቶቹ ተመልሰው መኳንንቱና መሳፍንቱ ነበሩ፤ያዙበታል፤ምርቱን ይቆጣጠራሉ፤እንዲሁም ሲሞቱ ለልጆቻቸው ያወርሱታል--መሳፍንቱ፡፡የካሕናቱ እጣ-ፈንታ በመሳፍንቱ ስር ቅጥረኛ ሆኖ በድርጎ (የእለት ምግብ) ብቻ ማገልገል ነው፡፡በሌላ አነጋገር ካሕናቱ የበላይነታቸው በመንፈሳዊ ጉዳዮች እንጂ በቤ/ክ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የማዘዝ መብት አልነበራቸውም፡፡ስለሆነም መሳፍንቱ በካሕናት ስም በተቆጣጠሩት ይዞታ መልሰው ካሕናቱን በእለት ምግብ ብቻ እየደለሉ በማስገልገል የተረፈውን ምርት ለግላቸው ይጠቀሙበታል፡፡ይሕ የባላባትና የደሃ ካሕናት ሥርዓታዊ የብዝበዛ ግንኙነት በተለምዶ ‹‹የቶፋ ሥርዓት›› ይባላል፡፡እንዲሕ ስር ሰድዶ የኖረው ሥርዓት ብዙም አይተረክም፡፡በቤተክሕነት ወገኖች የቀደሙ ነገሥታትንና ባላባቶችን አንዳንድ የማይካዱ ውለታዎች እንደማሳነስ ስለሚቆጠር ይመስለኛል የማይተረከው፡፡በዓለማዊ ጸሐፍት ደግሞ አንድም አሰራሩን በቅርብ ካለማወቅና ከቸልተኝነት፣ሁለትም ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት ተራማጆቻችን (ተራ-ማጆች!) የኢኦተቤክ’ንን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በጅምላ ፈርጆ ማሳቀል ቀላል ስራ ስለሆነላቸው ይመስለኛል፡፡እንጂማ የኛ ወላጆች (ወላጅ አባቴ ካሕን ነበር!) በልመና እንጀራ ተማሩ፤ከእጅ ወደ አፍ እንኳ ሊባል በማይችል የሰቆቃ ኑሮ እድሜያቸውን ገፉ፤የረባ ጥሪት ለልጆቻቸው ሳያኖሩ ድኅነትን አውርሰውን ያለእድሜያቸው ተንከራተው አለፉ፡፡ሞቱ፡፡‹‹ሕያዋን ለነገሥታት፤ሙታን ለካሕናት ይገብራሉ›› በሚለው ብሂል በሙታን ተዝካርና የሙት አልባሳት ሲደጎሙ ኖረው ሞቱ፡፡በዋናነት 5ቱ ቀዳስያንና በዙፋኑ ዙሪያ ያሉ ‹‹ካሕናተ-ደብተራ›› ብቻ ነበሩ የንጉሡና የምዕመኑ እርጥባን ተቋዳሾች፡፡የተቀረው ለማኝ ነው፡፡በካሕናቷ ‹ምንዳቤ ወረኀብ› የኢኦተቤክ ‹የልመና ሃይማኖት› ተብላ ትጠራ ነበር፤አሁንም ይሕ ስያሜ በከፊል አለ፡፡ይሄ ይታወቃል፡፡ታሪክ ሲጻፍ ግን ‹‹ባለሲሶ ግዛት›› ይባልልናል!!ግና እንዲያ እንዳልሆነ ይታወቅ ነበር፡፡ስለመታወቁ ማስረጃ እንቁጠር...