ከመንጋ አድር ባይ ጳጳስ፣ ፓስተር፣ ቄስና ሼክ ተብዬ አንድ ሳበኬ ወንጌል ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ያቀረበው ማሳሰቢያ ይሻላል!


ለኢትዮጲያ የኢፌድሪ መንግስት ጠቅላይ ሚንስተር ለአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እና አመራሩ።

ከፀጋአብ በቀለ(የወንጌል ሰባኪ)

          የየትኛውም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አራማጅ አይደለሁም፡፡ ጥሪዬ ስላልሆነ፡፡ ለፖለቲከኞች ግን አክብሮቴ ትልቅ ነው፡፡ በግሌ በዚህ መንግሥት ከቀበሌ እስከ ፌደራል ስላሉት መሪዎች እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ ቃሉ፡-"ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው"(ሮሜ.13፡1) የሚለውን ቃል ስለማምን፡፡ እንዲሁም በእግዚአብሔር መንፈስ የተመራው ሐዋርያ "ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ"(1ጢሞ.2፡1) ስለሚል ሁለም እግዚአብሔር ማስተዋልና ጥበቡን እንድሰጣችሁ እፀልያለሁ፡፡ እግዚአብሔር መንግሥትን ያፈልሳል ደግሞም ሌላ ያስነሣል፡፡ እግዚአብሔር፡- "ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል ነገሥታትን ያፈልሳል፣ ነገሥታትንም ያስነሣል ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል"(ዳን.2፡21)፡፡
ለመንግሥት ያለኝ አድናቆት

      በዚህ ሥርዓት እውነተኛና ሚዛናዊ ሕሊና ያለው ዜጋ ቀርቶ ዓለም ሁሉ ያደነቀው በትምህርት፣ በጤና፣ በኢኮኖሚ፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የብሔርሰቦች እኩልነት፣ በኢንቪስትመንት፣ በሃይማኖት ነፃነት፣ ...ረገድ የተገኘው ድል ትልቅ በመሆኑ ለዚህ ሁሉ አቅምና ኃይል የሆነን እግዚአብሔርን በማመስገን ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ያለኝ ግላዊ አድናቆቴን ከልቤ መግለጥ እፈልጋለሁ፡፡ እግዚአብሔር የአገሬን ሕዝብና መንግሥት ይባርክ!

ለመንግሥታችን በትህትና የቀረበ ግልጽ መልዕክት                                                                                                                      
    በተቃራኒው ኃላፊነትና ሸክም እንደምሰማው እንደ አንድ የዚህች አገር ዜጋና የወንጌል አገልጋይ ስለዚህች አገር መጻኢ ሕይወት ሳስብና ስጸልይ ብሩህ ገጽታና ያን ለማጥፋት የሚታገል አሉታዊ ሁለት ገጽታዎች ይታዩኛል፡፡ በዚህም ይች አገር በመስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኗ ተገነዘብኩ፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች በትክክል ከተጠቀምንባቸው የሚበልጥ ዕድገትና ለውጥ ይዞ የመጣ ሲሆን ካልተጠንቀቅን በዚህች አገር ትልቅ ጥፋትም ሊያመጣ የሚችል አቅም እንዳለሁ ስገነዘብ ባልተለመደ መንገድ ያልተለመደ ድምፅ ግልጽ አሰተያየት በትልቅ ትህትናና አክብሮት በማኅበራዊ ሚዲያ ለማቅረብ ወሰንኩ፡፡

1. የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት በሕግ መደንገጉ፤ ራስን በራስ ማስተዳደሩ፣ የራስን ቋንቋ፣ ባሕልና እሴቶች ማሳደጉ መልካም ሆኖ ሳለ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ስለ ልዩነታችን፣ ስለመንደራችን፣ ስለብሔራችን፣ ስለጎጣችን እንድናስብ የተደረገውን ያህል ስለ አንድነታችንና ስለአገራችን እንድናስብና እንድንነጋገር አልተደረግንም የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
 ዓመታዊ የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ለአንድ ሳምንት ከማክበር ያለፈ፡፡ ዛሬ ከደቡብ ወደ ሰሜን፣ ከሰሜን ወደ ምዕራብ፣ ከምዕራብ ወደ ምስራቅ ሄዶ በነፃነት ከመሥራት ኢትዮጵያውያን ወደ ተለያዩ አገራት መሰደድን ይመርጣሉ፡፡ ለመገናኛ ብዙሀን ዜና ግብአት አንድነታችንን የሚያሳዩ ሰሞነኛ ዜናዎችና ትእይንቶች እንጂ ለእርስ በርሳችን ያለን እይታና ልብ እጅግ መጥበቡ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
 ለምሳሌ፡- በቅርቡ በተነሳው ግጭት አንዳንድ አካባቢዎች ሌላውን ብሔር ለይቶ የማጥቃትና ከአካባቢያችን ውጡ የሚሉ ግልጽ መልዕክቶች ሲተላለፉ አይተናል፡፡ ሌላው ከኦሮምያ ዩንቨርሲቲ የጨረሱ ወጣት ተማሪዎች ወደ ሌሎች ክልሎች ሄደው ሥራ መሥራት እየቻሉ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የአገሪቷን ብሔራዊ ቋንቋ አማርኛን ስለማይችሉ፡፡ በአብዛኛው የተማረ ኃይል ተምሮ እየተመለሰ ያለው ወደ መንደሩ ሲሆን ወደ ሌላ ስፍራ ሲሄዱ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ ከዚህም የተነሣ በብዙ ወረዳዎች ዩንቪርሲቲ የጨረሱ ወጣቶች ሥራ ፈተው ይቀመጣሉ፡፡ ሥራ የፈታ አዕምሮ ደግሞ አደገኛነቱ የታወቀ ነው፡፡
 ያ ሚዛናዊ ሥራ እንደሚገባው ባለ መሠራቱ አሁን የገባንበት አንዳንድ ተግዳሮቶች ተጨባጭ ማስረጃዎችና ገሃዳዊና ጊዜ የማይሰጣቸው የለውጥ ጥሪ ናቸው፡፡ ለዚህ ትክክለኛ ጥሪ መንግሥት የተቃዋሚዎች ድምፅ አድርጎ ከመደምደም ይልቅ ትክከለኛ ምላሽ ቢሰጥ የሚል የብዙዎች ጩኼት ነው፡፡
 መንግሥታችን ያለፈውን ድልና ስኬት ብቻ ሳይሆን በብዙዎች ልብ በቅሎ ምድሪቷ ወዳልተፈለገው አቅጣጫ ሊወስዳት እየታገለ ያለውን በብሔርና በቋንቋ ላይ ያውጠነጠነ አደገኛ ጽንፈኝነት ላይ በጥንቃቄ መሥራት አለበት፡፡ ተሐድሶ የግድ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ጠባብነት ታላቅቷን ሶቪየት ኅብረት፣ ዩጎዝላቪያ ...የሕዝብን ጭፍጨፋ፣ መፈናቅሎችና የአገር መፋራረስና የሩዋንዳውያን መተላለቅ ምክንያት መሆኑን ምሁራን ይጠቅሳሉ፡፡ በብዙ አስቸጋሪ መንገድ ውስጥ ሄዶ ለዚህ የበቃውና ሕዳሴን መለያው ያደረገ መንግሥት ይህን ማድረግ ቀላል ባይሆንም አይችልም የሚል ልብ ግን የለኝም፡፡ ይህን እውን ለማድረግ መንግሥት ብቻውን አይደለም፡፡ ዜጎች ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን መሥራት አለብን፡፡ መንግሥት በዚህ ላይ ለመሥራት ካልፈቀደ ግን መጪው መልካም እንዳልሆነ የማገለግለው የሕያው አምላክ መንፈስ አመልክቶኛል፡፡

ቤንጃሚን ፍራንከሊን የተባሉ ሊቅ ሲናገሩ፡- "የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ እንደ ሞት ሽረት የሚቆጥሩ መንግሥታት በተፈጠሩበት ቆዳ ተጠቅልለው የሚሞቱ ናቸው፡፡ አንድ አገር ወይም ሕዝብ የሚመራበት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂዎችና ርዕዮተ ዓለማዊ ፍልስፍናዎች እንደ ተጨባጭ ዓለማዊ ሁኔታ ወይም ሕዝቡ ከደረሰበት የግንዛቤና የውጤት ደረጃ አንፃር መቃኘት አለባቸው፡፡ ይህን ማድረግ አለመቻል ነው ጉዞን የሚያደናቅፈው፡፡"

2. መንግሥት የደጋፊዎችን ድምፅ ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚዎችንም ድምፅ ከዚህ በበለጠ ቢሰማ መልካም ነው፡፡ (በስሜት የሚደገፍ የደጋፊዎች ድምፅ አንዳንዴም መንግስት እውነቱን ሊጋርደው ይችላል) የሚሰራው ፖለቲካ እንጂ የሃይማኖት ህግ አይደለም። ዴዝመንድ ቱቱ እንዳሉት፡" ሰላም ከፈለክ ከወዳጅ ጋር ሳይሆን ከጠላት ጋር መንጋገር ጀምር" እንዳሉት የተለያየ ርዕዮተ ዓለም መከተል ጠላትነት ባይሆንም እኛ ከሚንለው የተለየ ፍልስፍና ላላቸው ሰዎች ትክክለኛ ቦታ ልኖረን ይገባል፡፡ ሁለታችንም ለአንድ አገር ጥቅም እስከቆምን ድረስ፡፡ ይህን የሚንለው ብዙውን ጊዜ የፖለቲካው ምህዳር ከቀን ወደ ቀን እየጠበበ እንደመጣና አሳታፍ አይደለም በማለት አንዳንዶች በተስፋ ቁረጥ ስናገሩ ይሰማልና፡፡ ይህ ደግሞ ለዲሞክራሲያዊ ግንባታ አይበጅም፡፡

3. መንግሥት ቀርቶ መላዕክትም ይሳሳታሉ፤ ስለዚህ መንግሥት አንዳንዴ ገሃዳዊ ስህተት ሲፈጽም ይቅርታን ይጠይቅ፡፡  (እንደሚሳሳት አምኖ ለፈፀመው ስህተት ይቅርታ አለመጠየቅ ግብዝነት ነው)

መደምደሚያ
    መንግሥት ጠባብነት፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳሉ አምኖ ደጋግሞ በመገናኛ ብዙሃን ስናገር ይሰማል፡፡ ይህም ትልቅ ነገር ነው፡፡ ብርቱ አቋም፣ ጠንካራ እርምጃ ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል፡፡ ከላይ የተዘረዘሩ ሀሳቦች አዲስ ባይሆኑም አዲስ ትኩረት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ይፈልጋሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ የትላንቱ ታሪክ ታሪክ ነው፡፡ መጥፎም ይሁን ጥሩ፡፡ የእኛ ታሪክ ነው፡፡ ያለፈው ታሪክ አይለወጥም፤ አይከሰስም፡፡ ዛሬ የተሻለ ነገር ከሠራን ግን መልካም ታሪክ ሆኖ ነገ ይጻፋል፡፡ መልካም ታሪክ በሠራን መጠን የትላንቱ አሉታዊና የማንፈልገው ታሪካዊ ገጽታዎች እየተዋጡ ይመጣሉ፡፡ የትላንቱን አሉታዊ የታሪክ ክስተት ለበቀልና ለህቡዕ የጥፋት አጀንዳ እየመዘዝን ከተጠቀምንበት ግን የጥፋት ሠራተኞች እንሆናለን፤ ምድራችንን የደም መሬት እናደረጋታለን፡፡ ከመጥፎ ታሪክ ጋር ሁልጊዜ ስማችን እየተጠራ ይኖራል፡፡ ስለዚህ መልካም ታሪክ ለመሥራት መልካም አመለካከት ይኑረን፡፡

 ትልቁ ችግራችን ችግሮቻችንን ያየንበት ዓይን እንጂ ያለፉም ሆኑ አሁን ያለንበት ችግሮቻችን በራሳቸው ከአሉታዊ አመለካከቶቻችን በላይ አደገኞች አይደሉም፡፡ ችግሮቻችን ከእኛ በላይ ትልቅ አይደሉም፡፡ ችግሮቻችን አደገኛ መሆን የሚጀምሩት እኛ ፈጥረናቸው መፍትሔ በመስጠት ማስወገድ ሲገባን እኛን መፍጠር ወይም መምራት ሲጀምሩ ብቻ ነው፡፡

 
ሰላም፣ ብልጽግና፣ ዕድገት፣ ለውጥ፣ አንድነት፣ ፍቅር በአገራችን ለሚገኙት ብሔር ብሔረሰቦችና መንግሥት ይሁን፡፡


እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ፀጋአብ በቀለ/ሐዋሳ/ ነሐሴ 4/12/2008 ዓ.ም

ይህን ፅሁፍ ከጠቅላይ ሚንስተሩ እጅ ይደርስ ዘንድ ሼር በማድረግ የበኩሎን ይወጡ።
Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 1 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
September 2, 2016 at 3:24 PM

Tsega Ab, your thoughts are no bad. But, have you listened to Diakon Tariku Abera's interview with Esat? Check your u-tube. It is a masterpiece, very important message to all leaders and sebaki wengels, popes and chruch officials. Please read it!! He indicated that a Spade is a Spade.

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger