ሴቶች ከወንድ ጓደኛ ማንን ትወዱ? ማንንስ ትመርጡ? ከማንስ ጋር ጋብቻን ትፈፅሙ? እስኪ ራሳችሁን ጠይቁ።
በራስ መተማመን ያላት ሴት ለችግሮች ራሷን አሳልፋ አትሰጥም። በሁኔታዎች መለዋወጥ አትሸበርም። ራሷን ላጋጠማት ተግዳሮት ታዘጋጃለች እንጂ በሽንፈት ለቅሶን አታስተናግድም። ታዲያ ይህንን ኃይል ከየት ማግኘት ትችላለች?
✔ ✔✔
መልካም ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ሴት ስነምግባርን፣ እውቀትን፣ ችሎታና በራስ መተማመንን የምታዳብረው በቅርቧ ባለው ከቤተሰቧ ነው። በአስተዳደግና በልጅነት ሕይወት ጉድለት የደረሰባት፣ በብዙ ችግሮችና መከራ ውስጥ ያለፈች ሴት በስነልቦናዋ ላይ በሚደርሰው ጉዳት በራስ መተማመኗን በማጣት ችሎታዋን ለማውጣትና ችግሮችን ለመጋፈጥ ያላትን አቅም አውጥታ ለመጠቀም ሊያዳግታት ይችላል።
በተለይም በአስገድዶ መደፈር፣ በእናት ወይም በአባት ብቻ ወይም ከሁለቱም አሳዳጊ ውጪ ያደገች፣ የኑሮ ጫናና ድህነት፣ አካባቢያዊና ሀገራዊ ችግሮች ( ጦርነት፣ ረሃብ፣ ስደት) በሴቷ ስነልቦና ላይ የሚያደርሱት ተጽእኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በቃላትም መግለፅ ከሚቻለው በላይ የስነልቡና ተጠቂ ልትሆን ትችላለች።
በዚህም የተነሳ ሴቶች ለአካለ መጠን ከደረሱ በኋላ ቤተሰባዊ ሕይወትን ለመመስረት በሚያስችላቸው ሁኔታ ላይ ያሳለፉት ቁስል የሚያደርስባቸው የአእምሮ ፈተናና ትግል እጅግ ውስብስብ ነው።
የመጠራጠር፣ ያለማመን፣ አንዳንዴም በቀላሉ የመታለል ወይም የመሸወድ ክስተት ሲያጋጥማቸው ያታያል። ሴቶች በፈገግታና በሳቅ ሸፍነው በማህበራዊ ኑሮው ቶሎ የመቀላቀል ተፈጥሮአዊ ችሮታ አላቸው እንጂ በኋላቸው የተሸከሙት ህመም በጣም ብዙ ነው። ሲስቁና ሲጫወቱ ዘመናቸውን ሁሉ እድለኞች የነበሩ ሊመስለን ይችላል። እውነቱ ግን እሱ አይደሉም። ሴቶች መከራቸውን እንደወንድ እያመነዠኩ ስለማይኖሩ ከሰው ለመቀላቀል ብዙም አይቸገሩም። ያ ደግሞ ሴትን ልዩ ፍጥረትና የተወደደች ያደርጋታል። ሴት ለወንድ ሚስት ብቻ ሳትሆን የጉድለቱ ሙላት የመሆኗም ምስጢር ሁሉን መከራ መሸከም መቻሏ ነው። 6 ልጆቿን ያለአባት አሳድጋ ለቁምነገር ያበቃች እናት አውቃለሁ።
✔✔✔
ክርስቲያን ሴቶች ምንም እንኳን ያለፈ ሕይወታቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ባለ አዲስ የእምነት ልምምድ የተለወጠ ቢሆንም ያሳለፉት ስነልቦና በቀላሉ የሚፋቅ ባለመሆኑ አልፎ አልፎ መቸገራቸው አይቀርም። ከጋብቻ በፊት የመንፈሳዊ ጋብቻ ትምህርትና የምክር አገልግሎት ማግኘት የበለጠ ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው ስለሚችል በዚሁ መልኩ አስቀድመው ቢገለገሉ የተሻለ ግንዛቤ ይኖራቸዋል።
በኛ በኩል ያሉንን ምክሮች ጥቂት እንበል።
✔✔✔
ባለፈ ስህተትሽ አትቆጪ። የዛሬውን ሃሳብሽን እንዲቆጣጠረውም አትፍቀጂ። ያለፈው ላይመለስ አልፏል። ያለፈው ለዛሬው ያለው እድል አስተማሪ መሆኑ ብቻ ነው። ጎበዝ ሰው በሌላ ሰው ስህተት ይማራል፣ ሰነፍ ሰው ደግሞ ከራሱ ስህተት ይማራል። ያለፈው ስህተትሽ ለዛሬው ማንነትሽ ትምህርት ከሆነሽ፣ አንቺ የዛሬዋ ጎበዝ ነሽ። ካለፈችው ሰነፏ አንቺነትሽ በልጠሻል ማለት ነው። ስህተት አንዴ ከበዛ ደግሞ ሁለቴ ቢሆን ነው። ከደጋገመሽ ግን ስህተቱ ከጎዳሽ ነገር ሳይሆን ካንቺ አለመለወጥ የመጣ ነው።
ፈረንጆች እንዲህ የሚል አባባል አላቸው። "ስትሄድ የመታህ የድንጋይ እንቅፋት ስትመለስም ከደገመህ ስህተቱ የእንቅፋቱ ሳይሆን ድንጋዩ አንተው ነህ" ይላሉ።
ፍርሃትን በራስ መተማመን፣ ስህተትሽን በመታረም ማሸነፍ ትችያለሽ።
አብዛኛው ወንድ ሴትን የሚወደው በአይኑ ነው። የውስጧን ማንነት ሳያይ ውጫዊውን አይቶ ማድነቅም፣ መውደድም ይቻላል። ብቻውን ግን ለፍቅር ግንኙነት አያበቃም።
የደም አይነት ልዩ ልዩ ነው። ሁሉም ደም ለሁሉም ሰው አይሆንም። በአይን የመጣ መውደድም በሁሉም ሴት ላይ ፍቅርን ሊመሰርት አይችልም። ለምርጫ የሚያበቃ ጥናት ያስፈልገዋል። የወደዱን ሁሉ ያፈቅሩናል ማለት አይደለም። ይህን ለማወቅ ጊዜ ወስዶ ማጥናት ተገቢ ነው። ለኛ የተሰጠ ሰው ከሆነ ለማጥናት በምንወስደው ጊዜ ያመልጠናል ብለን መስጋት አይገባም። እንዲያውም ሳናውቀው ዘው ከምንል ቢያመልጠን ይሻላል። ለኛ የተሰጠን እንዳይዘገይ ቶሎ መሄዱ ይሻላል። የከረመ ወይን ሲጠጡት ሆድ አይነፋም።
በአይን የወደደ የአይኑን አምሮት በአካል ባገኘው ጊዜ ቶሎ ይረካል። ከዚያም የማያርፈው አይኑ ወደሌላ ይሄዳል። ሴት ሆይ፣ የሚወድሽን ወንድ አይኑን ብቻ ሳይሆን ልቡን እዪው። ምን ይልሻል? ስሚው። አንቺን አይቶ ለልቡ አምሮት የሚቅበዘበዝ ከሆነ ችግር አለ። በአፉ እወድሻለሁ እያለ ፍቅሩን በተግባር የማያሳይ ከሆነ ችግር አለ። እንጋባ ሳይሆን እስክንጋባ አልጋ ላይ እንውጣ የሚልሽ ከሆነ ችግር አለ። የሚሰጥሽን ጊዜ ቀስ በቀስ የሚቀንስ ከሆነ ችግር አለ።
ታማኝ ወንዶችን ከአስመሳዮች ለመለየት ጊዜ ውሰጂ። አትቸኩዪ። በምላስ ብልጠት አትሸነፊ። ልቡን ለማወቅ አንቺ አምላክ አይደለሽም። ምላሱን በተግባሩ ፈትኚ። ከትዳር በፊት የተደጋገመ ውሸት በትዳር ውስጥም ይቀጥላልና ተጠንቀቂ።
በሰውኛ ሚዛን መልክና ውበት ጥሩ ነው። ነገር ግን ለእግዚአብሔር መንግስት በተመረጠ ትዳር ውስጥ ሁሉም ከንቱ ነው። ቅን እንጂ ቅንቅን አትሁኚ። ገንዘብ፣ ጌጥና ምቾት አያታልሽ። ዝሙት ኃጢአት ነው። ፍፃሜውም ሞት ነው። ስለዚህ በታማኝነት ለእግዚአብሔር መንግስት ራስሽን አስገዢ።
ጠቢቡ በመጽሐፉ እንዳለው መክብብ 6፣12
"ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው? ወይስ ለሰው ከፀሐይ በታች ከእርሱ በኋላ የሚሆነውን ማን ይነግረዋል?" ነውና ለጊዜው ለእግዚአብሔር ክብር ለሚሆን ሕይወት እንጂ ይህ ቋሚ መኖሪያችን አይደለምና ራስን መግዛት አትርሺ።
✔✔✔
"ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ"
ፊልጵ 4:6