/ኤፍሬም ባለጊዜ/
ሁለት ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ክርክር ገጥመዋል። አንዱ አማኝ ሲሆን ሌላኛው ከሀዲ ነው፣ ያውም የፈጠረውን አምላክ የካደ። ክርክራቸው ወዲህ ነው። አማኙ እግዚአብሔር አለ ይላል። ከሀዲው ሰው ደሞ በፍጹም የለም ይላል። አማኙ ሰው የእግዚአብሔርን መኖር ለማስረዳት መጽሐፍ ቅዱሱንም፣ ሳይንሱንም እያጣቀሰ ብዙ ተናገረ። ነገር ግን ሰሚ አልነበረውም። ከብዙ ክርክር በኋላ ይህ አማኝ ሰው አንድ ጥበብ መጣለትና ከሀዲውን ሰው እንዲህ ሲል ጠየቀው። እግዚአብሔር ቢኖር ይሻላል ባይኖር? ይህን ጊዜ ከሀዲው ሰው ፈጠን ብሎ ባይኖር ይሻላል አለ። ልብ በሉ! እንግዲህ ከሀዲው ሰው እግዚአብሔር የለም ብሎ ሲከራከር የነበረው የመረጃ ችግር ስለነበረበት አልነበረም። እግዚአብሔር የለም የሚለው እግዚአብሔር እንዳይኖር ስለሚፈልግ ብቻ ነው። ጠላቶችሁ ያላችሁን የከበረ ነገር በፍጹም ማመን አይፈልጉም። ያ ማለት ግን የከበረ ነገር እንዳላችሁ አያውቁም ማለት አይደለም። አንዳንዶች ግልጡን እውነት በጭራሽ መስማት አይፈልጉም ወይም ቢያውቁም ለማመን አይፈልጉም።
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተፃፈው ዳዊት ለወንድሞቹ ምግብ ለማድረስ ወደ ጦሩ ሰፈር በመጣ ጊዜ የኤልያብ ቁጣ በዳዊት ላይ ነዶ " ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂት በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሀቸው? እኔ ጠማማነትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁ፣ ሰልፉን ለማየት መጥተሀልና" ነበር ያለው። አሁን ኤልያብ ለዳዊት መንገር የፈለገው ዋና ሀሳብ ግልጽ ነው። አንተ እረኛ ነህ፣ አርፈህ በጎች ጠብቅ የሚል ነው። ነገር ግን እረኝነት ለዳዊት የስልጠና ስፍራ እንጂ የህይወቱ ጥሪ ላለመሆኑ ከኤልያብ የተሻለ ምስክር የለም። ምክንያቱም ዳዊት ለንጉሥነት በተቀባ ጊዜ ኤልያብ እዚያው ቦታ ላይ ነበር። (ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። 1ኛ ሳሙ 16፥13)
ነገር ግን ኤልያብም እንደዚያ ከሀዲ ሰው ችግሩ የመረጃ ሳይሆን የፍላጎት ነበር። ፍላጎቱ ደግሞ ዳዊት በእረኝነት ዘመኑን እንዲጨርስ ነው። በሥራችሁ፣ በሙያችሁና በንግግራችሁ ሁሉ እውነተኞች ብትሆኑም የሚቃወሟችሁ ሰዎች ቁልቁል ሊደፍቋችሁ ይሞክራሉ። መንገዳችሁን በወጥመድ ያጥራሉ። የምትወድቁበትን ጉድጓድ ይቆፍራሉ። እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ከሆነ ማን ሊቃወማችሁ ይችላል?
በመጨረሻም ለማለት የምፈልገው በከንቱ በሚጠሏችሁና ሁልጊዜ ውድቀታችሁን በሚመኙ ሰዎች ልባችሁና መንገዳችሁ አይያዝ። ከዛሬ ነገ በእኔ ላይ ያላቸውን አቋም ይቀይራሉ ብላችሁም አታስቡ። እንዲህ አይነት ሰዎች የሕይወት ዘመን ቋሚ ጠላቶች ናቸው። ነገር ግን እንደ ክርስቲያን በብዙ ፍቅርና ጸሎት አስቧቸው። እኔም እናንተም እዚህ የደረስነው በሰው ፍቅር አይደለም፣ በእግዚአብሔር ምህረት እንጂ!