Sunday, March 13, 2016

እነሆ ሁለቱ ኪዳናት!

መቅድም
 ‹‹እነሆ ሁለቱ ኪዳናት›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍ በ2002 ዓ.ም ‹‹ሁለቱ ኪዳናት›› በሚል ርዕስ በመሪጌታ ሃየሎም ተዘጋጅቶ በማኅበረ ቅዱሳን አሳታሚነትና አከፋፋይነት በተሠራጨው መጽሐፍ ውስጥ ለተላለፉት ኢ-ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮዎች መልስ ለመስጠት ቢሆንም በችግሮቹ ላይ ብቻ ከማትኮር ይልቅ አንባቢያን ሃሳቤን በቀላሉ እንዲረዳልኝ ያስችላሉ ያልኳቸውን መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስና የታሪክ እውነታዎች በማሰባጠር በማስረጃ አስደግፌ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ፡፡ የዚህን ጽሑፍ ረቂቅ ያሳየኋቸው አንዳንድ ወንድሞች የሁለቱ ኪዳናትን ጸሐፊ፣ አርታኢና አሳታሚ ማኅበር የእምነት አቋም ተወራራሽነት ለመግለጽ የተጠቀምኩባቸውን የወል ዐረፍተ ነገሮች ባስተካክላቸውና በጸሐፊው ላይ ብቻ አትኩሬ መልእክቴን ባስተላልፍ እንደሚሻል አስተያየት ሰጥተውኛል፡፡ ሃሳባቸውን በሃሳብነቱ ብቀበለውም እንዳሉት ሶስቱን አካላት ነጣጥዬ ማየት ግን አልሆነልኝም፡፡ ለዚህም ምክንያቴ አርታኢው ከአርትዖት ተግባሩ ባሻገር የመጽሐፉን መግቢያ በማዘጋጀትና በመጽሐፉ የተካተተውን አስተምህሮ ‹‹ትክክለኛነት›› አጽንኦት ሰጥቶ በማስተጋባት እንዲሁም ማኅበሩ በሐመረ ተዋሕዶ 2001 ዓ.ም ልዩ እትሙ‹‹እቅበተ እምነት (አፖሎጂ) በቅድስት ቤተ ክርስቲያን›› በተሰኘ አምድ ሥር ‹‹ሁለቱ ኪዳናት ማኅበረ ቅዱሳን በተለያየ ጊዜ በመጻሕፍትና በመጽሔት በቃል ትምህርትም መናፍቃን ለዘሩት የጥርጥር ትምህርት መልስ የሰጠበት መጽሐፍ›› ነው ብሎ መገለጹ በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኘው የእምነት አቋም የጸሐፊው ብቻ ሳይሆን የአርታኢውና የማኅበሩ ጭምር መሆኑን የሚያረጋግጥ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ በተገለጠው የትምህርት አቋማቸው ብርሃኑ፣ ሐየሎምና ማኅበረ ቅዱሳን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸውና ብርሃኑንም ሆነ ሐየሎምን ሳመሰግን ሶስቱንም ማመስገኔ፣ እንዲሁም የብርሃኑንም ሆነ የሐየሎምን ሃሳብ ስቃወም ሁሉንም መቃወሜ መሆኑን ማስገንዘብ ተገቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ በእኔ እምነት ብርሃኑ ስለማያምንበት ነገር መንደርደሪያ አልጻፈም፤ ማኅበረ ቅዱሳንም የእምነት አቋሙ ያልሆነን ትምህርት አሳትሞ አላሰራጨም፤ ለመናፍቃኑ የተሰጠ መልስ ነው እያለም አልፎከረምና ከምስጋናውም ሆነ ከወቀሳው ሊጎድሉ አይገባም ብዬ ሁሉንም ያለ ልዩነት እንዲጋሩት አድርጌያለሁ፡፡

እንደማምነው ካራ፣ ቅባት እና ጸጋ ሁሉም የተዋሕዶ አማኞች ናቸው፡፡ እንግዳ አመለካከት ሊመስል ቢችልም እንኳ ንስጥሮስ፣ አቡሊናርየስ፣ አውጣኬና ፓፓ ሊዮም ሳይቀሩ የዚሁ የተዋሕዶ ጽንሰ ሃሳብ አራማጆች ናቸው፡፡ ልዩነቱ የተፈጠረው ተዋሕዶን ለመግለጽ በተጠቀሙበት ቃል ትንታኔ ላይ ነው፡፡ አውጣኬ ተዋሕዶውን ያስረዳበት መንገድ መለኮት የሥጋን ባሕርይ መጥጦታል የሚል በመሆኑ መጠፋፋትን እንጂ የሁለቱን ባሕርያት መገናዘብ አያስረዳም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትም የለውም ተብሎ ተወገዘ፡፡ አቡሊናርየስ ክርስቶስ የሰው ነፍስ የለውም፤ በነፍሱ ምትክ ነፍስ የሆነለት መለኮት ነው አለ፡፡ በዚህም የክርስቶስን ፍጹም ሰውነት አጎደለ ተብሎ ተተቸ፤ ተለየ፡፡ ንስጥሮስም በበኩሉ የቃልና የሥጋ ተዋሕዶ ሁለቱ አካላት የየግል አቋማቸውን ጠብቀው የየራሳቸውን ሥራ እየሠሩ የሚኖሩበት ስምምነት (moral union) ነው አለ፡፡ እንደ እርሱ አባባል መለኮት በሥጋ ውስጥ አደረ እንጂ ባሕርያዊም ሆነ አካላዊ ተዋሕዶን አላስከተለም፡፡ ታዲያ ይህም ቢሆን የክርስቶስን አሐዱነት በተገቢው መንገድ አይገልጥም ተብሎ ተነቀፈ፡፡ በግልጥ እንደሚታወቀው የፓፓ ሊዮ አቋም ሁለት ባሕርያት በአንድ አካል የሚል ነው፡፡ ይህም ቢሆን ተዋሕዶን ምሉዕ በሆነ መንገድ አይገልጥም፡፡ አካል ያለ ባሕርይ ባሕርይም ያለ አካል ሊኖሩ አይችሉምና አንዱ የክርስቶስ አካል የማን ነው? የሚል ውዝግብ አስነሳ፡፡ ይህም አስተምህሮው በኦርየንታሎቹ ዘንድ ጥያቄ ላይ ወደቀ፡፡ በዚህም እንደሚታየው ፓፓ ሊዮም በሁለቱ ባሕርያት መኖር ላይ ከማትኮሩና የክርስቶስ አካል የመለኮት ነው ከማለቱ በቀር ተዋሕዶን አልተቃወመም፡፡ በመጀመሪያው የኤፌሶን ጉባኤ ተቀባይነት ያገኘው የቅዱስ ቄርሎስ የ‹‹ተዋሕዶ›› አስተምህሮ (ምንም እንኳ ምዕራባውያኑ በትክክል ባይረዱትና ከፓፓ ሊዮ የአንድ አካል ሁለት ባሕርይ፣ አልፎ ተርፎም ከአውጣኬ የመጠፋፋት ትምህርት ጋር ሊያመሳስሉት ቢሞክሩም) ሁለቱ አካላትና ሁለቱ ባሕርያት ሳይጠፋፉ፣ ሳይነጣጠሉ፣ ሳይቀላቀሉ አንዱ የሌላውን አካልና ባሕርይ ገንዘብ የተደራረጉበትን ከሁለት አንድ የመሆን ምስጢር (አንድ አካል፣ አንድ ባሕርይ፣ አንድ ፈቃድ፣ አንድ ግብር) የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ይህም በተዋሕዶ የተገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ያከናወናቸው ተግባራት ሁሉ ይህ የሥጋ ነው ያኛው ደግሞ የመለኮት ነው ተብለው ሳይከፈሉ በአንዱ በክርስቶስ (ሥግው ቃል) የተከናወኑ ናቸው የሚል ነው፡፡ በዚህ አስተምህሮ መሠረት እንደ ንስጥሮሳውያንና እንደ ኬልቄዶናውያን (ፓፓ ሊዎ) ድካሙን ለሥጋ ብርታቱንና ማዳኑን ለመለኮት የመስጠት ሙከራ በብርቱ የተነቀፈ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ከአውጣኬያውያንና ከነፓፓ ሊዮ የተዋሕዶ ሃሳብ በእጅጉ ይለያል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም በአቋም ደረጃ ይህንን ትቀበላለች፡፡

እንግዲህ በቤተክርስቲያናችን የሚታወቁት ሶስት ቡድኖች ምንም እንኳ ‹‹ተዋሕዶ›› ነን ቢሉም የተዋሕዶ አስተምህሯቸው ከላይ ከተገለጹት ተዋሕዶ ነን ባዮች ከየትኛው ምንጭ እንደተቀዳ በጥንቃቄ መፈተሽ ቀዳሚውንና ትክክለኛውን የተዋሕዶ እምነት ተገንዝቦ ለመከተልና ያለ እውቀት ከሚሰነዘር ትችት ለመታቀብ ያስችላል፡፡ ከዚህ የተነሳ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን በመጀመሪያው የኤፌሶን ጉባኤ ያጸደቀችውን የተዋሕዶ ጽንሰ ሃሳብ ከነአውጣኬና ከነንስጥሮስ የተዋሕዶ ትርጓሜ ለመለየትና አንባቢያንን ከድንጋሬ ለመጠበቅ ‹‹ትክክለኛው›› የሚል ገላጭ ቃል ተጠቅሜያለሁ፡፡ በኢትዮጵያውያኑ የእምነት ጎራዎች (ካራ፣ ቅባት፣ ጸጋ) አስተምህሮዎች ላይ የመጻፉ ጉዳይ ብዙም አልታየኝ ነበር፡፡ ሆኖም የአንዳንድ ጊዜ የገጠማቸው ግለሰቦችና ቡድኖች አስተምህሮ ምንጭ በብዙሃኑ ስለማይታወቅ ከነሰባልዮስና ከነአውጣኬ ወገን ተሰልፈው የነቄርሎስን እምነት እንከተላለን እያሉ እውቀቱ የሌለውን ምእመን ከማደናገር አልፈው በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠውን የእግዚአብሔር ቃል በመቃወም ላይ ስላሉና የእነርሱን ፈለግ ያልተከተሉትን ሁሉ እያሳደዱ እውነተኛ መስለው ለመታየት ሌት ከቀን እየተጣጣሩ ስለሚገኙ የአሳዳጆቹም ሆነ ተሐድሶ ናቸው በሚል ሽፋን እየተሳደዱ ያሉት ወገኖች ማንነት በግልጽ ይታወቅ ዘንድ እንዳልኩት ብዙም ትኩረት ላደርግባቸው የማልፈልጋቸውን ሶስት ቡድኖች አስተምህሮ ከመረጃ መጻሕፍት አሰባስቤ ለማቅረብ ተገድጃለሁ፡፡ በተለይ ማኅበረ ቅዱሳን የነቄርሎስን የተዋሕዶ ለምድ ለብሶ የሚያቀነቅነው ‹‹ሰባልዮሳዊ›› እና ‹‹አውጣኬያዊ›› ተዋሕዶ ፍንትው ብሎ ይታይና ትክክለኛው ማንነቱ ይገለጥ ዘንድ ይህንን ማድረጌ ተገቢ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ በተረፈ ወደ መሠረታዊው ሃሳቤ ለመሸጋገር አንድ ጸሐፊ በተናገሩት ቁም ነገር ሃሳቤን ልቋጭ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህ ትውልድ የሚፈልገውን እውነት በውስጧ ይዛለች፡፡ ነገር ግን እውነቷን ባልተዛባና ትውልዱ በሚፈልገው መንገድ ገልጣ ልታቀርብ አልቻለችም አብዛኛዎቹ የስብከት መድረኮቿ የተሞሉት ሌላውን በመንቀፍ ወግና ሥርዓትን ታሪክን በመተረክ ላይ በተመሠረቱ ስብከቶች ነው፡፡ በማኅበርና በግል ደረጃ በጽሑፍ የሚተላለፉ መልእክቶችም ይኸው ገጽታ ነው ያላቸው፡፡ ያለባትን ችግር በመረዳት በሚፈለገው ሁኔታ ወንጌልን የሚሰብክ አንድ ሰው ቢነሳ እንኳ በጥርጣሬ መንፈስ እየታየ በተለያዩ ውንጀላዎች ከመድረክ የሚወገድበት መንገድ ይፈለጋል (አግዛቸው ቀ.አ፡5)፡፡

ለእኔም እውነታው ይኸው ነው፡፡ የዚህም ምክንያቱ የአውጣኬያዊውና የሰባልዮሳዊው ተዋሕዶ ትምህርት በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ሠርጎ መግባቱ ነው፡፡ እንደ ተባለው የከበረ እውነት አለን፤ ነገር ግን በዘመናት ሂደት ውስጥ ተቀብሯል፡፡ ስለዚህ የተቀበረው እውነት ተፈልፍሎ ሊወጣና ምእመኑ በግልጥ እንዲያውቀው ሌሎችም ቢሆኑ መሠረታዊውን የተዋሕዶ አስተምህሮ ተገንዝበው አጓጉል ነቀፋዎችን ከመሰንዘር እንዲቆጠቡ ማድረግ ይገባል፡፡ ለዚህም ብርቱ ትግል፣ ለመታገልም እውነቱን ከሃሰቱ መለየት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከጥላቻ በጸዳ መንፈስ ከማንበብና ከመወያየት የተሻለ መንገድ የለም፡፡ አለመደማመጥና ምን ያመጣሉ ለሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንም እንዳልበጃት ከታሪክ መማር ይገባል፡፡ ስለዚህ ንባብዎ እውነቱን ለመፈለግና በመመካከር መልካሙን መንገድ ለመከተል ይሆን ዘንድ ከልቤ እመኛለሁ፤ እጸልያለሁም፡፡ ሌላው ምናልባት ላሳውቀው የሚገባኝ መልሱ የዘገየበትን ምክንያት ነው፡፡ እንደ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ጊዜ እስኪደርስ ነው ብዬ ባስብም ይህ ጽሑፍ ከታሕሣስ 2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከዚህ ጊዜ ድረስ በእጄ ላይ እየተንከባለለ ድፍን አምስት ዓመታት ማስቆጠሩን ሳስበው በጥቂቱ አዝናለሁ፡፡ በሌላ መልኩ ምንም እንኳ እንዲታተም ብዙ ጊዜ ተመኝቼ ባይሳካልኝም እንደ ቀልድ ባለፉት በእነዚያ ዓመታት ውስጥ እኔ ባደግሁበት ዕድገት ልክ የማደግና የመብሰል ዕድል አግኝቷልና ደስ ይለኛል፡፡ ምናልባትም ቀድመውና ዘግይተው ከተጻፉ ጓደኞቹ ይልቅ የመታተሙን ቅድሚያ እንዲያገኝ የረዳው ይኸው ሳይሆን አይቀርም፡፡ እንዲህም ሲሆን ፍጹም ነው ማለቴ አይደለም፡፡ ይልቁንም ገና ‹‹ሁ›› ስለሆነ ከስህተትና ከችግር የጸዳ ላይሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ አንብባችሁ በምትሰጡኝ ምክርና ተግሳጽ ታግዤ ስህተቴን በማረም የተሻሉ ሥራዎቼን ይዤ እንደምቀርብ ተሥፋ አደርጋለሁ፡፡ እስከዚያው መልካም ንባብ!!!
                         ጸሐፊው