ከእውነቱ /ለውይይት የቀረበ/
1/ መግቢያ
በድሮ ጊዜ ሰው በሰው ሲበደልና ፍትሕ ሲጓደል ‘ያገር ያለህ’ ወይም ‘የዳኛ ያለህ’ በማለት ይጮህ ነበር፤ ይህ ዓይነቱ የተበዳይ ጮኸትም ለትውልድ መርገም እንዳይሆን ተብሎ በአካባቢው በሚኖሩ እድሜና ልምድ ጠገብ ሺማግሌዎች ገላጋይነት/ዳኝነት የበደለ እንዲክስ የተበደለ ደግሞ እንዲካስ በማድረግ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ይደረግ ነበር፤ እኔም ዛሬ በዲሞክራሲ ስም በምድራችን ውስጥ እየሆነ ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ /በተለይ ባለውለታ በሆነችው በኦርቶዶክስ ቤ/ክ ውስጥ/ ቀረብ ብየ ስመለከት ይህ እውነተኛ የፍትህ ፈላጊዎች ያገር ያለህ ጩኸት ትዝ ብሎኝ ለኢትዮጵያውን በሙሉ ለውይይትና ለመፍትሄው ፍለጋ ጭምር የሽማግሌ ዳኞች ያለህ በማለት ጮኸቴን ላቀርብ ተገደድኩ። መቸም ለተወሰኑ ዓመታት ከአገሩ ራቅ ብሎ ለኖረ ኢትዮጵያዊ የአዲስ አባባ ገጽታ ቀየር እንደምትልበት ይታመናል፤ በርካታ ሕንጻዎችና መንገዶች ተሠርተዋል፤ ባቡርም ተጀምሮ ሕዝቡ እየተጠቀመበት መሆኑን በግልጽ ማየት ይቻላል፤ ለራሴ ሕሊና ታማኝ መሆን ስላለብኝ የሚታዩትን መልካም ነገሮች እሰየው በማለት፣ ደስ የማይሉትንና ደካማ የሆኑትን ደግሞ ለእርምት በግልጽነት ብጠቁም ሰውነቱን የሸጠ ካልሆነ በስተቀር ቅር የሚሰኝ እውነተኛ ሰው የሚኖር አይመስለኝም። እዚህ ላይ የሕንጻዎችና የመንገዶች መገንባት መልካም ቢሆንም፤ በራሳቸው ግን ያንድ አገር እድገት ዋና መስፈርቶች ናቸው ብሎ መውሰዱ ተገቢ አይመስለኝም፤ ሕንጻ ያለሰው ከንቱ የድንጋይ ክምር ብቻ ስለሚሆን! በሌላ መልኩ ደግሞ አብዛኛው ሕዝብ በኑሮ ችግር እየተጠበሰና ያገሪቱ ሃብት በጥቂቶች እጅ ውስጥ ሆኖ እያለ ኢኮኖሚስቶች በነፍስ ወከፍ የገቢ ስሌት ተመስርተው አድገናል ማለታቸው በሕዝቡ አጠቃላይ የኑሮ ምጥ ላይ የሚታየውን የህይወት ማቃሰት በግልጽ መካድ ነው የሚሆነው፤ የተመጣጠነ የሃብት ክፍፍል በሌለበት አገር ውስጥ ይህ ዓይነቱ የሂሳብ ቀመር እንዴት ሆኖ እውነተኛ ሚዛን እንደሚሆን ፈጽሞ አይገባኝም። ማየት ከመስማት የበለጠ ጥሩ መረጃ እንደሆነ ይታመናል፤ በመሆኑም አገራችን ኢትዮጵያ ምን እየሆነችና ወዴት እየተጓዘች እንደሆነ ከዚህ በፊት በጆሮዬ የሰማሁትን ዛሬ በዓይኔ አይቼ ለራሴ ህሊና ያገኘሁትን መረዳት በሚከተሉት ርእሶች ላይ ያለኝን ስጋት በትንሹ ላካፍል፡
1. ፖለቲካውና ኢኮኖሚው በሕዝቡ ኑሮ ላይ ያስከተለው አውንታዊና አሉታዊ ተጽእኖ፣ /በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ይሆናል/
2. በሐይማኖታዊ ተቋማት /በተለይ አብዛኛው ሕዝብ ችግሩን ለፈጣሪው የሚያቀርብባትና ለመጽናናት የሚሞክርባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን/ ውስጥ እየሆነ ያለው መተራመስ፤ በምድራችን ውስጥ በርካታ የሃይማኖት ተቋማት ይገኛሉ፤ ሆኖም ግን ከአገሪቱ ታሪክ ጋር ከፍተኛ ትስስር ያላትና በበርካታ ጠንካራ ጎኗ ጉሉህ ስፍራውን ይዛ የምትገኘው ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስለመሆኗ የሚክድ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም፤ ካለ ግን ልሟገተውና ጣሊያንን በምስክርነት ጠርቸ ላስመሰክርበት እችላለሁ፤ ይህ የሚሆነውም በራሳቸው ሙያ የሚተማመኑ እውነተኛ ዳኞች ከተገኙ ብቻ ነው። ስለዚች ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ አጀማመር፣ ላገር ስላበረከተችው መልካም አስተዋጽኦ፣ በረጅም የታሪክ ሂደቷ ውስጥ ስለገጠሟት በርካታ ተግዳሮቶችና ስለከፈለችው ከፍተኛ መስዋትነት ማወቅ ለሚፈልግ /የራሱን ታሪክ ማወቅ ለሚፈልግ/ ወደ ኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ጎራ እንዲል እየጠቆምኩ፤ የዛሬውን መልእክቴን ግን በቤተ ክርስቲያኒቷ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በስፍራው ላይ ተገኝቼ ያየሁትን እውነት ብቻ ጥንቃቄ ባለው መልኩ በዚህ የመጀመሪያ ጽሑፌ ላይ ለማቅረብ እሞክራለሁ።
በዚች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከላይ ከፓትሪያሪኩ ጀምሮ በተዋረድ ወደታች የሚፈስ ያስተዳደር መዋቅር አለ፤ በተጨማሪ በርካታ መንፈሳዊ የትምህርት ማሰልጠኛዎች እያስመረቁ የሚያወጧቸው ወጣቶች ዐውደ ምህረቱን ሞልተውት የሰንበት ትምህርት የማስተማሩን ሥራ በሰፊው ተያይዘውታል፤ እኔን የገረመኝና የማላውቅበትን ብእር እንዳነሳ ያደረገኝ ግን በዚህ ግራና ቀኙን በማያውቅና እግዚአብሔርን በሚፈራ የዋህ ወገናችን መካከል በተለያየ መንፈሳዊ ስያሜ ተመስርተው የሚያካሂዱት የእርስ በርስ ጦርነት ነው፤ በዘመናት መካከል እኔ ‘አውቅልሃለሁ የሚልለት ተቆርቋሪ አጥቶ የማያውቅ’ አሳዛኝ ሕዝብ፤! በዚህ መሰረት ለዛሬ ማህበረ ቅዱሳንን እና ኦርቶዶክስ ተሐድሶ የሚባሉትን መንፈሳዊ ማህበራትን ከሥራቸውና ከሚያራምዱት ዓላማ አኳያ በማየት ፍርዱን ለእውነት ፈላጊዎችና ለወገን ተቆርቋሪ ወገኖች ስተወው፤ ለበለጠ መፍትሄ ፍለጋ ግን ቤተ ሰብ ከቤተሰብ፣ ጓደኛ ከጓደኛ፣ ባል ከሚስት፣ ጎረቢት ከጎረቢት፣ አንዳችን ከሌላው ጋር በእውቀትና በቅንነት ግልጽ ውይይት በማድረግ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅመውን መደገፍ ለሁላችንም ይበጃል።
1/ ማህበረ ቅዱሳን ማነው?
ከማሕበረ ቅዱሳን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ሁላችንም ልንማረው የሚገባ ቁምነገር እንዳለ አምናለሁ፤ ዋና ዓላማው ግልጽ ባይሆንልኝም የአባላቱ ስብጥር፣ አባላት ለማህበራቸው የሚከፍሉት ዋጋና የርስ በርስ መደጋገፍ ይበል የሚያሰኝ ነው። እንዲሁም በየደብሩና በየገዳማቱ ለወደቁ ምስኪን ወገኖቻችን ከሚያደርገው መልካም ሥራ ባሻገር /እውተኛው ክርስትና የመስቀሉ ሥራ ውጤት እንጂ የመልካም ሥራ ውጤት አይደለም ወይም በሌላ አባባል የጽድቅ ሥራ ለመሥራት በመጀመሪያ በጸጋው አምኖ መጽደቅ አለበት ይላሉ ተሐድሶዎች/ ለባህልና ለቅርስ ጥበቃው ሥራ የሚከፍለው ዋጋም በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። የዚህ ማህበር ሌላ መገለጫ ባህሪው የተለያየ የጉዞ ፕሮግራም በማዘጋጀት ሕዝቡ ገንዘቡን ከፍሎ በነጭ ልብስና በኢትዮጵያ ባንዲራ ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ የሕዝቡ ማህበራዊ ትስስር እንዲበረታታ ያደርጋል፤ ሌላው አብዛኛው ሕዝብ አዲስና ልዩ ፈዋሽ ጸበል ተገኘ በተባለበት ስፍራና በየገዳማቱ ሁሉ አብዝቶ እንዲንቀሳቀስ ያደርጋል።
ማህበሩ በተጨማሪ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ጥቂቶቹ፡- ሕንጻ መገንባትን፣ ንግድ መነገድን፣ የራሳቸውን አባላት ማሰልጠንን፣ አዳዲስ ታቦታት መትከልንና ስነጽሁፎችን በሰፊው አውጥቶ ማሰራጨት ሲሆኑ በእነዚህ ጽሁፎቻቸውም ላይ በዋናነት ተሐድሶን የሚያጥላላና የሚያወግዝ መልእክት በትኩረት ያወጣል። የማህበሩን እንቅስቃሴ ለማጠቃለልም፡ የውስጣቸውን/የልባቸውን ባላውቅም አለባበሳቸው በባንዲራ የታጀበ ነጭ ልብስ በመሆኑ የየዋሁን ሕዝባችንን ልብ ለዓላማቸው በቀላሉ ማማለል ይችላሉ፤ ችለዋልም፣ ለቅርስና ባህላዊ እሴቶቻችን ከፍተኛ ትኩረት በመስጠታቸውም ለአገር ብቸኛ ተቆርቋሪ ከነሱ ሌላ ፈጽሞ የሌለ አስመስሏቸዋል፣ ባህላዊ የቆሎ ትምህርት ቤቶች የበለጠ እንዲጠናከሩ ድጋፍ ያደርጋል፣ የገዳምና የምንኩስናን ኑሮ በማበረታት ምሁራን ሳይቀሩ ወደገዳም እንዲገቡ ያበረታታል፤ እንዲያውም ከውጭ አገር ኑሯቸው ተመልሰው ገዳም እንዲገቡ የተደረጉ እንዳሉ ይነገራል፣ ዘርዓ ያዕቆብን የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለወለታ በማድረግ ያወድሱታል፤ታሪኩንም ሕዝቡ እንዲያውቀው ለማድረግ የተደጋገመ ወርክሾፕ በስሙ አድርገውለታል/እያደረጉለትም ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የማያውቃቸውን አዳዲስ ቅዱሳንን ሳይቀር ሕዝቡ እንዲያውቃቸውና ጽላት/ታቦት እንዲቀረጽላቸው ያደርጋል፤ አድርጓልም /ምሳሌ አርሴማ የምትባልን ነጭ ሴት/፣ ለአባላቱ ሁለንታዊ ድጋፍና ስልጠና በትጋት ከማድረጉም ባሻገር በምረቃና በሰርግ ላይ ከበሮና ጸናጽን ይዞ በመገኘት በሚያደርገው ሞቅ ያለ የሽብሸባ አምልኮ ከጴንጤዎች ጋር ውድድር የገባ አስመስሎታል፣ ሕንጻ ይገነባል፣ ንግድ ይነግዳል፣ ገንዘብ ይሰበስባል፣ አባላትን ያደራጃል /ከቀን ሰራተኛ እስከ ምሁር ባለስልጣናት ድረስ/፣ በዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ውስጥ የሚማሩትን ተማሪዎች በማሰልጠንና በእረፍታቸው ወቅት ወደየቤተ ሰቦቻቸው በመላክ ዓላማቸውን በሰፊው እንዲያስተዋውቁላቸው ያደርጋል //ይህን በተመለከተ አንድ በመንፈሳዊም ሆነ በታሪክ በቂ እውቀት የሌለው /ከስሜታዊነት በስተቀር/ የወንድሜ ልጅ መሳተፉን አጫውቶኛል//፣ ማህበሩ በሚያደርገው አጠቃላይ እንቅስቃሴ አባላቶቹንና የዋሁን ሕዝብ ፍጹም የጉልበት ሃይማኖተኛ እያደረገው እንደሆነ በአንዳንድ ደብር በስሜታዊ አባላቱ በኩል የሚታዩት የደም መፋሰስ ግጭቶች ይመሰክራሉ፣ አዳዲስ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ሥራ ላይ በሙያተኞቹ በኩል በሰፊው ይሳተፋል፣ ጎልቶ የሚታየው ሌላው ሥራው በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ ከሚገኙ አገልጋዮች መካከል አንዳንዶችን በመክሰስና ከሥራ በማሳገድ እስከ ቤተሰባቸው ችግር ላይ እንዲወድቁ ያደርጋል /ይህ በደል የደረሰባቸውን አንድ ሊቅ ይህ ጸሐፊ አናግሯል/፣ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተሃድሶ ያስፈልጋታል የሚሉትን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መሪጌቶች፣ መነኮሳት፣ ዲያቆናትና አባላትን በሙሉ የፕሮቴስታንት ቅጥረኞችና ጸረ ኦርቶዶክስ ናቸው በማለት በመጽሄታቸው፣ በጋዜጣቸውና በአውደ ምህረት ላይ በማውጣት ከፍተኛ ዘመቻ ያደርጋል።
ይቀጥላል