Friday, November 21, 2014

ፍሪማሰንሪ /freemasonry/ ምንድነው?




ከዚህ በፊት በአንድ ጽሁፍ «ስለኤርያ 51» አጭር ምስጢራዊ ጽሁፍ ማስነበባችን ይታወሳል። አሜሪካና ዲሞክራሲ፤ ሥልጣኔና አሜሪካ መሳ ለመሳ ናቸው። እንደዚሁ ሁሉ ሌላው ዓለም ይቅርና የሀገሪቱ ዜጋ የማያውቃቸው ብዙ ምሥጢሮችም ያሉባት ሀገር ናት። ላይ ላዩን በዲሞክራሲው ዕድገት ጫፍ ረግጫለሁ በማለቷና በሥልጣኔውም መጥቄአለሁ እያለች ከመለፈፏ ጀርባ ብዙ ጉድ እንዳዘለች ብዙው ሰው አያውቅም፤ ቢያውቅም ትኩረት አይሰጠውም።  በነገረ መለኮት የበሰሉና የትንቢቱ ፍጻሜ ሰዓት መድረሱን በደንብ ያጠኑ ምሁራን ግን አሜሪካንን «ታላቂቱ ባቢሎን» ይሏታል። ምክንያቱም በአደባባይ ከሚታወቅላት የዲሞክራሲውና የሥልጣኔው እርከን ባሻገር የተሸከመችው ጉድ የት የለሌ ነውና። ሁሉም ነገር ከብረት በጠነከረ ምስጢርና ከምስጢሩ አጠባበቅ ጋር ሕይወት በሚያስከፍል ዋጋ፤ የረቀቀ መዋቅር በተዘረጋበት ሥርዓት የምትመራ ሀገር በመሆኗ እያወቁ ወይም ሳያውቁ ታደነዝዛለች።  በህጋዊ ደረጃ ከ«Church of Satan” አንስቶ እስከመጨረሻው ክሂዶተ እግዚአብሔር  «Atheism” ድረስ በነጻ የሚንቀሳቀሱባትና ለዓለሙ ሁሉ ማዕከል ሆና የምታገለግለዋ አሜሪካ ጾታን በመቀየር እንዲሁም የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻንም በመፍቀድ መሪ በመሆን ታገለግላለች።

      ሌላው ቀርቶ በየዓመቱ የሚከበረውን የሀለዊን /Halloween/ በዓል ጥቅምት/31 ቀን ከጫፍ ጫፍ በማክበር አሜሪካንን የሚቀድማት የለም። ለነገሩ «ሀለዊን» የሞቱ ቅዱሳንን ለማሰብ በሚል ይጀመር እንጂ ድርጊቱ የሙት መንፈስ የሆነውን ሰይጣንን ለማሰብ የተሰራ ለመሆኑ የድርጊቱ ክንዋኔ ያስረዳል። የሚያስፈራ ምስልና ቅርጽ፤ ጥርሱ ያገጠጠ፤ ዓይኑ ያፈጠጠ፤ አጽሙ  የተቆጠረ ማስጠሎ ነገር ለብሶ ወይም አጥልቆ  ሰውን በማስደንገጥና በማስፈራራት ቅዱሳንን ማክበር ነው ቢባል እንዴት ሊሆን ይችላል? ለነገሩ ቅዱሳንን ተጠግቶ ይህንን ማድረጉ ራሱን የቻለ ሌላ ምስጢር ስላለው እንጂ ቅዱሳንን ስለሚወክል አይደለም። (የዚህን ምስጢር ፍቺ በዚህ ጽሁፍ ቀጣይ ክፍሎች ለመዳሰስ ይሞከራል) አሜሪካ ለመጨረሻው ዘመን የተዘጋጀችና ለጥፋት ነጋሪት የምትጎስም ሀገር በመሆንዋ ነገሩ ሁሉ እየተበላሸ ሄዷል። ባለፈው ጥቅምት 31/ 2014 ዓ/ም በሚዙሪ፤ ሴንት ሉዊስ ከተማ ዓለም አቀፍ የ«ሀሎዊን» በዓል እንደሚደረግ የተላለፈው የጥሪ ምስል እንደሚያሳየን የጨለማውን ኃይል ካልሆነ በስተቀር ሌላ ማንን ሊሆን ይችላል? እስኪ ምስሉን አይተው ግምትዎን ይስጡ!!
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነን አሜሪካ ከምታስተናግዳቸው እንግዳ ነገሮች አንዱ ክፍል ስለሆነው ስለ«ፍሪማሰንሪ»/freemasonry/ ውቅያኖስ ታሪክ ጥቂቱን በጭልፋ ልናካችላችሁ ፈልገን ነው። ምክንያቱም የአንድ ዓለም አገዛዝ /One World Order/ እንዴት እየሰራ እንዳለ በማወቅ ከሚመጣው የስህተት መንፈስ እንድንጠበቅ አበክረን ለማስገንዘብ ነው። በዚህ ዙሪያ ምሁራኑ በሀገርኛ ቋንቋ ጽፈው በሰፊው እስኪያስነብቡን ድረስ ለጥንቃቄ እንዲበጅ በጥቂቱ እንዲህ አቅርበነዋል። መልካም ንባብ!

ፍሪማሰንሪ ምንድነው?

     «ማሰን» የሚለው ቃል ከላቲኑ / machio/ ከሚለው ቃል የተወረሰ ነው።  ትርጉሙም «ድንጋይ ጠራቢ ፈላጭ ወይም ግንበኛ  ማለት ነው።  ቃሉም ከ1155 እ,ኤ,አ ጀምሮ አገልግሎት ላይ ውሏል። freestone-mason ማለት «ነጻ ድንጋይ ጠራቢ፤ ግንበኛ ሰው ማለት ሲሆን ይህም ስያሜ በዚህ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ሰዎች «free mason» ፍሪማሰን በሚል አኅጽሮት አገልግሎት ላይ እንደዋለ በ1908 ዓ/ም የታተመው የፍሪማሰን ዜና መዋዕል መጽሐፍ ያስረዳል።  የላቲኑን ውርስ ቃል ተከትሎ “free” እና “mason” ከሚለው የእንግሊዝኛ ጥምር ቃላት የተገኘው ይህ ስያሜ ድንጋይ የመጥረብ፤ የመቁረጥና የመገንባትን ድርጊት ሲያመለክት «ፍሪማሰንሪ» /freemasonry/ ይባላል።  ይህም በነጻ ፈቃድ፤ በራስ ውሳኔ ዓለቱን ጠርቦ የማይነቃነቅና የማይናወጥ መሠረት ያለው ግንብ የመገንባት ዓላማ ነው ማለት ነው።  

«ፍሪማሰን» የተባለው ስያሜ በግንበኝነት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ሰዎች በተናጠል ሲጠሩበት የቆየ ቢሆንም ከ14ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ጀምሮ በአውሮፓ የህንጻ ምህንድስና ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች በጥቂት ሰዎች ተደራጅተው ራሳቸውን የመጥራት እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር። ይሁን እንጂ የማሰን የተናጠል እንቅስቃሴ ቀደም ሲል እንደነበረ ቢሆንም ድርጅታዊ ሕግና ፒራሚዳዊ የብቃት የእርከን ደረጃ ወጥቶለት የተመሰረተው በ1717 ዓ/ም በለንደን ከተማ ነው።። በ1731 በአሜሪካ ፤ በ1736 በስኮትላንድ መሰረቱን አስፋፋ። ከዚያም በ1725 በአየር ላንድ እንደተጀመረ ይነገራል።  አሜሪካ ውስጥ የተቋቋመው በጣም ደርጅቶና ጎልብቶ ዓለም ዐቀፍ ቅርጽ ለመያዝ በቅቷል። 

      ይህ የፍሪማሰን ማኅበር የአውሮፓን የኢንዱስትሪ አብዮት ተጠግቶ የተመሰረተው የህንጻና የምህንድስና ባለሙያዎችን የያዘው እንቅስቃሴ ቅርጹንና መልኩን ለውጦ በሰው አእምሮና አስተሳሰብ ላይ እንደህንጻ የሚያድግ ግብረገብነትን፤ በጎ አድራጎትንና  መልካም ስብእና ያለው ሕብረተሰብን የመፍጠር ዓላማ ባለው መመሪያ ላይ ራሱን በማቆም ሕግና ደንብ አውጥቶ መሥራት መጀመሩን የተጻፈ ታሪኩ ያስረዳል። 

  ምንም እንኳን የፍሪማሰንሪ ማኅበር በኦፊሴል ከአምልኮና ከፖለቲካ አስተሳሰብ ነጻ ነኝ ቢልም በ1723 እና በ1738 ዓም ተሻሽሎ በወጣው የፍሪማሰንሪ ሕገ መንግሥት ላይ እንደተመለከተው የሁሉም ነገር ንድፍ / architect/ ባለቤት «እግዚአብሔር ነው ስለሚል እንቅስቃሴው ሃይማኖት ለበስ እንደሆነ ፍንጭ ከመስጠቱም በላይ ድርጅቱ የራሱ የሆነ ዶግማና መመሪያ ስላለው የእምነት ድርጅት አይደለሁም የሚለው አባባሉ ተቀባይነት እንዳይኖረው አድርጓል።  ድርጅቱ የአንድ ወጥ የሃይማኖት ተቋም ላለመሆኑ እንደመከራከሪያ የሚያቀርበው ጭብጥ የፍሪማሰንሪ አባል ለመሆን  የየትኛውንም ሃይማኖት ተከታይ ወይም የሃይማኖት መጽሐፍ ተቀባይ ወይም የትኛውንም የፖለቲካ መስመር የያዘ ሰው በአባልነት መቀበል መቻሉን በማስረጃነት ያቀርባል።  ድርጅቱ ይህንን ይበል እንጂ አባል የሚሆን ሰው ቀድሞ የነበረውን እምነቱን ይሁን አመለካከቱን እንዲጥል ሳይገደድ የፍሪማሰንን አስተምህሮና ሕግ በተከታታይ ተምሮ በድርጅቱ የረቀቀ አስተሳሰብ ውስጥ እንዲሰጥም ማድረግ በራሱ ቀድሞ የነበረውን የማስቀየር ዘዴ እንደሆነ በተሞክሮ ያዩት ሰዎች በተግባር ያረጋገጡት ሀቅ ነው።

    እንደፍሪማሰንሪ አባባል የጥበቦች ሁሉ /Architect/ የንድፍ ባለቤት እግዚአብሔር ሲሆን ያገኙትን ጥበብ ወደተግባር የሚለውጡት ደግሞ የፍሪማሰንሪ እውቀት የተሰጣቸው ሰዎች ናቸው ይላሉ። ለምሳሌም የኖኅ መርከብ የተሰራቸው በኖኅ የፍሪማሰን እውቀት ነው። የባቢሎን ግንብ ይሁን የሰሎሞን ቤተ መቅደስ ያለፍሪማሰን እውቀት ፍጻሜ አያገኝም ነበር ባዮች ናቸው። የግብጽ ፒራሚዶች የፍሪማሰን ጥበብ ውጤት ነው። የኖስቲኮች እውቀት፤ የግሪክ ፍልስፍና፤ የፓይታጎረስ ስሌት፤ የዞሮአስተር ትምህርት፤ የቻይና ጥበብ፤ የአልኬሚስቶች ፈጠራ ሁሉ በፍሪማሰን እውቀት ጎልምሶ ወደተግባር የተለወጠ መሆኑን ያምናሉ። 

   ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የፍሪማሰንሪ ድርጅት አባል ሲመለመል የትኛውንም ሃይማኖት የሚከተል ወይም የትኛውንም የሃይማኖት መጽሐፍ የሚቀበል ሰው መሆኑ ችግር የለውም። እንዲተውም አይጠበቅም። ቁምነገሩ አንድ ጊዜ የፍሪማሰንሪ ድርጅት አባል ከሆኑ በኋላ ድርጅቱን መልቀቅ እንደማይቻል ወይም በምክንያት ከለቀቁ ደግሞ የቆዩበትን የድርጅቱን ምስጢር ማውጣት የሞት ዋጋ እንደሚያስከፍል አስቀድሞ ቃለመሃላ ይፈጽማል። ፍሪማሰንሪ በስብከትና በድለላ የአባልነት ምልመላ አያደርግም። አብዛኛው የዚህ ድርጅት አባላት ፕሬዚዳንቶች፤ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፤ ዶክተሮች፤ ፕሮፌሰሮች፤ ጀነራሎች፤ ዳኞች፤ የሴኔትና የምክር ቤት አባላት፤ ቢሊየነሮች፤ ታዋቂ ሰዎችና ከፍተኛ ነጋዴዎች ናቸው። ከአሜሪካ 44 ፕሬዚዳንቶች ውስጥ 14ቱ የፍሪማሰንሪ ድርጅት አባላት እንደነበሩ በግልጽ ሲታወቅ  ከተቀሩትም ውስጥ በምስጢራዊ አባልነት የነበሩ እንዳሉ ይነገራል።

ፍሪማሰንሪ ካሉት 330 (ሠላሳ ሦስት ድግሪ) ማእርጋት አንዱ በሆነው የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ የተወሰኑ ትምህርቶችን አስቀድሞ ከወሰደ በኋላ ወደድግሪ ትምህርቱ ሲገባ ይህንን መሃላ ይፈጽማል።

« ዛሬ የፍሪማሰንሪ አባል ከሆንኩ በኋላ አባል ለሆንኩበት ድርጅት ካልታመንኩ ወይም ብከዳ ወይም ምስጢር ባወጣ በጎሮሮዬ ላይ ስለት ይረፍ፤ ምሳሴ ከስሩ ተነቅሎ ይጣል፤ አጽሜ አመድ ሆኖ ከውቅያኖስ የጥልቁ አሸዋ ውስጥ የተሰወረ ይሁን» ይላል። ለምን?

የፍሪማሰንሪ ዓርማና ሌሎች ምልክቶች ምንድናቸው? ከኢሉሚናቲ ጋር ያላቸው ግንኙነት ምንድነው? ይህንንና ሌሎች ምስጢሮችን በቀጣይ ክፍል ለማቅረብ እንሞክራለን።