Monday, November 24, 2014

ኡጋንዳዊቷ የቤት ሠራተኛ ሕይወት ለማጥፋት በመሞከር ወንጀል ተከሠሠች!

( ዕድሜአቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ እንዲመለከቱ አይመከርም ) The film is not suitable for viewing by anyone under 18 years of age

ባለፉት ቅርብ ቀናት በኢትዮጵያ ውስጥ ሐና በተባለች ታዳጊ ወጣት ላይ አስነዋሪና እጅግ አሳሳቢ ድርጊት ተፈጽሞ የብዙዎችን ልብ እንደሰበረ ይታወቃል። ማኅበራዊ አኗኗራችን ከመተሳሰብ እያፈነገጠ፤ ሥነ ምግባራዊ አስተሳሰባችን እያደፈ የመሄዱ ምልክት ነው። ዓለም አንድ መንደር እየሆነች ነው ሲባል በመሰልጠኑ ብቻ ሳይሆን በመሰይጠኑም ጭምር በመሆኑ ስግብግብነት፤ ራስ ወዳድነት፤ ብልግናና ዐመፃንም ዓለማዊ መንደርተኝነት እያካፈለው ይገኛል። ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመው አስነዋሪ ድርጊት ትኩሳቱ ሳይበርድ አንድ መንደር የሆነችው ዓለም ከወደዑጋንዳ ሌላ ዜና ብቅ አለች። በአንዱ ጫፍ የተፈጸመው ወሬ ወደሌላ ጫፍ ለመድረስ ደቂቃ የማይፈጅባት ዓለማችን ካስተናገደቻቸው ብዙ ዜናዎች መካከል አንዱን አሳዛኝ ድርጊት አሰማችን። ጉዳዩ እንዲህ ነው።

  ድርጊቱ የተፈጸመው በዑጋንዳ፤ ኪዋቱሌ በተሰኘች አነሰተኛ ከተማ ነው። ድርጊቱን የፈጸመችው የ22 ዓመቷ ጆሊ ቱሙሂርዌ የተባለች የቤት ሠራተኛ ስትሆን በተቀጠረችበት ቤት ውስጥ እንድትንከባከብ ከአሰሪዎቿ አደራ የተሰጣትን ሕጻን በዘግናኝ ሁኔታ ስትደበድብ በቤት ውስጥ ስውር ካሜራ የተቀረጸ ቪዲዮ ያሳያል። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሠራጨው ይህ ቪዲዮ ብዙዎቹን አሳዝኗል። በጣም የሚረብሸው ይህ ምስል ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንደዋለ ዓለም ዐቀፍ ትኩረት ስቧል።  የሕጻኗ ወላጅ አባት የሆነው ኤሪክ ካማንዚ ቪዲዮውን እንደተመለከተ ለኪዋቱሌ  ፖሊስ ጣቢያ በማመልከቱ ፖሊስ ደብዳቢዋን የቤት ሠራተኛ በቁጥጥር ስር አውሎ «በማሰቃየትና ለመግደል ሙከራ በማድረግ» ወንጀል የክስ ፋይል ከፍቶ ለፍርድ ቤት እንዳቀረባት የተገኘው ዜና ያስረዳል።  የቤት ሰራተኛዋ ከተቀጠረች 26 ቀናት ብቻ ያስቆጠረች ቢሆንም የፈጸመችው ድርጊት በተመሳሳይ ሁኔታ የቆየች እንደሚመስል ፖሊስ ግምቱን የሰጠ ሲሆን  ስለሰራተኛዋ ማንነትና የቀደመ ተግባር ምርመራ ለማድረግ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ለፍርድ ቤቱ በማመልከቱ ለታህሳስ 8/2014 እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ አዟል። ሕጻኗ በደረሰባት ጭካኔ የተሞላበት ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ቢሆንም እስካሁን ህክምና እየተደረገላት በሕይወት እንደምትገኝ ታውቋል።
ሕጻናት የተለየ ክብካቤና ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም ዓለም በምታስተናግደው የሥነ ልቡና ማኅበራዊ ቀውስ የተነሳ ለጥቃት እየተጋለጡ ይገኛሉ። ፍሪሃ እግዚአብሔር የሌለው ትውልድ ከሥነ ምግባር ውጪ በመሆን ለማኅበራዊ ኑሮ የአስተሳሰብ ቀውስ መጋለጡ አይቀሬ ነው። አሳዛኝና አስነዋሪ ድርጊት የመፈጸሙ ምክንያትም ይህ ነው።  በየቤታችን ለሕጻናት፤ በየአካባቢው ለሴቶችና ለታዳጊ ወጣቶች፤ ለአረጋውያንና ረዳት ለሌላቸው የምናደርገውን ክትትልና ቀና ድጋፍ በማጎልበት «የአባቴ ብሩካን» ተብሎ የተነገረውን የሕይወት ዋጋ ለማግኘት ዛሬውኑ እንነሳ!!

«ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ» 1ኛ ጴጥ 2፤2