Thursday, January 24, 2013

“አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ጥምቀት” ማለት ምን ማለት ነው?

የእግዚአብሔር መንግሥት የምትወረሰው አንዱን ጌታ በማመንና የእምነት አዋጅ የሆነውን «አንዲት ጥምቀት» በመጠመቅ እንደሆነ ቅዱስ ወንጌል ያስተምረናል። ይሁን እንጂ ዓለምን ደግሞ ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከታት ብዙ ጌቶች፤ ብዙ ቤተ እምነቶችና ብዙ ጥምቀቶችን እያስተናገደች ትገኛለች። ይኼው የዓለሙ አንድ ዘርፍ የእምነት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያችን ውስጥም የሚታይ ሲሆን የየራሳቸው ጌታ ያላቸው፤ በየራሳቸው ጥምቀት የሚያምኑ፤ ልዩ ልዩ ሃይማኖቶች መኖራቸው እርግጥ ነው። ከዚህ አንጻር ከእኔ በቀር «አንድ ጌታ፤ አንድ ሃይማኖት፤ አንድ ጥምቀት» በማለት በአደባባይ ለማወጅ የመናገር መብቱና ብቸኛ ውክልና  ያለው ሃይማኖት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም ማለት ነው።  ምክንያቱም የሚያምነውን  እምነት በማይቀበሉ ሰዎች መካከል እኔ ነኝ እውነተኛው ብሎ ቢያውጅ አንድም ሌሎቹን ለማስቆጣት ወይም እነሱንም ለተመሳሳይ እንቅስቃሴ እንዲነሳሱ ከሚያደርግ በስተቀር የትክክለኛ እምነት ባለቤት መሆኑን በየትኛውም መልኩ አያረጋግጥምና ነው። «ጸብ ያለሽ በዳቦ ካልሆነ በስተቀር» ይህ ጥበብ ያለው የስብከት ዘዴም አይደለም። በአንድ የሙስሊም በዓል ላይ ታላላቆቹ የአላህ ነብያት መሐመድ፤ ዒሳ/ኢየሱስ/ እና ሙሴ (ሰዐወ) ናቸው የሚል ጽሁፍ ያለበት ቀይ ካናቴራ ሙስሊም ወጣቶች ለብሰው አይቻለሁ። ይህ እንግዲህ «ኢየሱስ ከነብይም በላይ አምላክ ነው» ለሚሉ አማኞች ስድብ  መሆኑ ነው።   በግሉ የሚያምንበትንና የራሱ ቤተ እምነት የሆነውን ዒሳ/ኢየሱስ/  ነብይ መሆኑን ካመነ በካናቴራ ላይ ጽፎ አደባባይ መውጣቱ ምን ለማምጣት ነው? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። «ይህንን የማትቀበሉ ካላችሁ ጸብ ይዛችሁ ኑልኝ!» ብሎ ሁከት መጋበዝ ካልሆነ በስተቀር ምንም ፋይዳ የለውም።

 በሌላ በኩልም በአሁን ዘመን ታቦት ስለመኖሩ የማይቀበል  ቤተ እምነት እንዳለ እርግጥ ነው። ይኼው ቤተ እምነት በተራው « የዘመኑ ታቦት ጣዖት ነው» ብሎ ቢጽፍና ይህንኑ ይዞ አደባባይ ቢወጣ ያለምንም ጥርጥር አንዲት እርምጃ ሳይሄድ ወይ ይገደላል፤ አለያም ደሙ ይፈሳል እንጂ የሚያምንበትን በመጻፉ መብቱ ነው ብሎ የሚቀበለው ሰው አደባባይ ላይ አይገኝም።

ብዙ ኦሮሞዎች የኢሬቻን በዓል ያከብራሉ፤ ወንጌል አምናለሁ ለሚል ለሌላ ሰው ግን ኢሬቻን ለማክበር ዛፍ ስር መስገድና መስዋእት ማቅረብ ጣዖት ከማምለክ ጋር ሊያያዝ ይችላል። ይህንን የኢሬቻ አክባሪዎችን ስሜት የሚያስቆጣ ጽሁፍ በማንጠልጠል አደባባይ መውጣት ለነገር ካልሆነ በስተቀር የትኛውንም ነገር የሚያንጽና በማስተማር ሌላውን ለመለወጥ የሚሰጠው ፋይዳ አይኖርም። በተመሳሳይ መልኩ እነማኅበረ ቅዱሳንና ጎጋ ደጋፊዎቹ፤ መናፍቃን የሚሏቸውን ክፍሎች ለመሳደብ/ አስተምሮ ለመመለስ አይደለም/ በአንድ ወቅት «ያለድንግል ማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም» እና በሌላ ጊዜም «አንዲት ጥምቀት፤ አንዲት ሃይማኖት» የሚል ሸሚዝ ለብሰው በአደባባይ ሲንጎራደዱ ታይተው ነበር። ይኼው ድርጊት ዛሬም መቀጠሉ እየተነገረ ነው። የሌላውን ስስ ስሜት ለመኮርኮርና አምንበታለሁ የሚሉትን ጽኑ አቋም በአደባባይ በማንጸባረቅ እንደተቃዋሚ የሚቆጥሩትን ክፍል ልብ ለማቁሰል ካልሆነ በስተቀር ኢ-አማኝ የሆነውን ማንንም ሊለውጥ የሚችል ድርጊት አይደለም። ዋናው ነጥብ ለአደባባይ ጽሁፍ የሚመረጡት ጥቅሶችና ጽሁፎች በቤተ እምነቱ ውስጥ ካለው አጠቃላይ አቋም ውስጥ የሌላኛውን ወገን እምነት የሚመለከትና ስሜቱን ሰቅዞ በመያዝ ጠጣር መልእክት የሚያስተላልፈውን መምረጡ የራሱ የሆነ ዓላማና ግብ እንዳለው ለማወቅ አስቸጋሪ አይደለም። ያንን ጥቅስ ይዞ አደባባይ መገኘት ያስፈለገው የእምነቱ ተከታዮች ስለተሰወረባቸው ለመግለጽ ነው ወይስ የእምነቱ ተከታዮች ላልሆኑ ለሌሎች ክፍሎች ብትወዱም ብትጠሉም እኔ እንደዚህ እላለሁ ብሎ ለመንገር? የሚል ጥያቄን ያስከትላልና ነው።


ወንጌል ማስተማር፤ ያላመኑትን ማሳመንና የእኔ እውነት ትክክል ነው ወደሚሉት እምነት ሌላውን ለመቀየር ጥበብ የሚያስፈልገው አገልግሎት መሆኑ እሙን ነው። ወንጌልን መስበክ እንደባለ አእምሮ እንጂ በመታበይ ወይም ማን እንደእኔ በሚል ትምክህት ሊሆን አይችልምና። በዚህች ዓለም የስብከት ጥበብ ሳይሆን  እንደባለ አእምሮ መንፈሳዊ ብስለትና ሌላውን ደስ አሰኝቶ ሊለውጥ በሚችል መታደስ እንጂ በትእቢት አስተሳሰብ የሚደረግ ስብከት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ወንጌልም አበክሮ የሚነግረን ይህንኑ ነው።

«እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው። የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ» ሮሜ 12፤1-3


ከዚህ ተነስተን በሰሞኑ የጥምቀት በዓል ላይ «አንድ ጌታ፤ አንድ ጥምቀት፤ አንዲት ሃይማኖት» የሚለውን ጥቅስ የለበሱ የጥምቀት ተመላሾች ማኅበር ወጣቶች ማንንም ሰብከው ሳይለውጡ /በእለቱ በዚህ ጥቅስ የተለወጡ አዲስ አማኞች ስለመኖራቸው አልሰማንም/ ወጣቶቹ የመታሰራቸው ዜና ተሰምቷል። ይህንን ተከትሎ የተለያዩ የድረ ገጽ ሚዲያዎች ዜናውን አስተጋብተዋል። በእርግጥ ጥቅሱ የወንጌል ቃል ነው። ቃሉም እውነት ነው። ነገር ግን ይህንን ጥቅስ ለብሰው አደባባይ የዋሉት ወጣቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው «አንድ ሃይማኖት ብቻ» መሆኑን ለማሳወቅ ወይስ ሌሎች ሃይማኖቶችን ለመስበክ? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። ነገሩ በዓለ ጥምቀትን አስታኮ እውነተኛይቱ ሃይማኖት የእኔ ስለሆነ ሌሎቻችሁ ዋጋ የላችሁም ለማለት ካልሆነ በስተቀር እንደ ወንጌል አስተምህሮና እንደ ባለአእምሮ የተለወጠ ሰው፤ ሌላውን ደስ በማሰኘት ወደእውነት እንዲመጣ በመርዳት ለሌላው የሚተርፍ አንዳችም ጥቅም ያለው  አካሄድ አልነበረም። ይልቁንም ሌላው ወገን የራሱን አጸፋዊ ጥቅስ በመልስ ምት ይዞ እንዲመጣ የሚያደፋፍረው ይሆናል። ሌላው የሚያምንበት የራሱ እውነት ለእኔ ውሸት እንደሆነው ሁሉ፤ እኔም የማምንበት እውነት ለእርሱ ውሸት ስለሚሆን የኔን ትክክል ብዬ የማምንበትን እውነት ለማስተላለፍ የምጠቀምበት መንገድ ሌላውን የሚያርቅ ሳይሆን በመረጃና ማስረጃ  የማሳምንበት ሊሆን ይገባል።ምክንያቱም ሃይማኖት የሰዎችን ስሜትና አእምሮ የመቆጣጠር ትልቅ ኃይል ያለው ስለሆነ ማንም ለማስተማር ሲፈልግ ጥበብና ስልት ያለውን መንገድ መከተሉ የግድ ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴና ከተማ አርዮስፋጎስ አደባባይ ላይ ከድንጋይ በተሰራና «የማይታወቅ አምላክ » የሚል ጽሁፍ ለሰፈረበት ጣዖቱ አምላኪ ሕዝብ ያስተላለፈው የትምህርት መንገድ ትልቅ ግንዛቤ ይሰጠናል። በስብከቱ መነሻ የማይታወቀውን አምላክ፤ ይህ ድንጋይ ነው ብሎ ክብሩን አዋርዶ አልጀመረም። እናንተ ጣዖት አምላኪ ሕዝቦች ወዮላቸሁ ብሎ በማስፈራራትና ጆሮአቸውን ጭው በሚያደርግ ቃል አላስበረገገም። ይልቁንም እንዲህ በማለት ለድርጊታቸው ግምት ሰጥቶ እያዋዛ ወደሚፈልገው ጎዳና መራቸው እንጂ!



«ጳውሎስም በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፦ የአቴና ሰዎች ሆይ፥ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ። የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ። ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ» የሐዋ  17፤22-23

ጳውሎስ ትምህርቱን የጀመረው የአቴናውያንን «የማይታወቀው አምላክ» በመዝለፍ ሳይሆን  አቴናውያን አማልክትን እጅግ እንደሚፈሩ ዋጋ በመስጠትና በዚህም ጽኑ ፍላጎት የተነሳ የማይታወቀውን አምላክ እንደሚያመልኩ በመግለጽ ነበር። ይህም ጆሮአቸውን ሰጥተው የሚናገረውን ሁሉ እንዲያዳምጡ የሚያበረታታቸውና አእምሮአቸውን ወደእርሱ ንግግር የሚጎትት ጥበብ ነበር። ከዚያም ስለአቴናውያን የማይታወቅ አምላክ ድክመትና ጉድለት ቅድሚያ ከመናገር ይልቅ ለጆሮ አዲስ ወደሆነውና ወደሚስብ አዲስ ትምህርት ሲያስገባቸው እናያለን። ይልቁንም ጳውሎስ የሚያመልከው አምላክ ሁሉን ቻይ/Almighty/ ፤ ምሉዕ በኩለሄ/ Omnipotent/ መሆኑንና ሰው በሰራው ቤት ተወስኖ እንደማይኖር፤ ሁሉን የፈጠረ፤ የሁሉ አስገኚ እንደሆነ በሰፊው በማብራራትና በማስተማር ያንን ሁሉን ቻይ አምላክ በአእምሮአቸው ውስጥ ሲስል ይታያል። ይህም  ሁሉን የፈጠረ አምላክ፤ በሁሉ ሥፍራ መገኘት የሚችልና ሰው በሰራው ቤት የማይኖር አምላክ የሁሉም ነገር የበላይ እንደሆነ እንዲቀበሉና እነሱ ከድንጋይ የሰሩትና የማይታወቅ አምላክ ብለው የሚጠሩት አምላክ፤ ጳውሎስ ከነገራቸው አምላክ ያነሰ እንደሆነ እንዲያሰላስሉ የሚያደርግ ስብከቱን በንጽጽር አቅርቦላቸው እንደነበር ወንጌል ይነግረናል። አቴናውያን የሚያመልኩት አምላክ የእጃቸው ስራ፤ መናገር የማይችል፤ መልስ የማይሰጥና ውሱን ከመሆኑ የተነሳ ከዚህ በላይ የሆነ ሉዓላዊ ስልጣኑ በሥፍራ የማይገደብ አምላክ  እንዳለ ሲነገራቸው ይህንን ኃያል አምላክ ለመቀበል ጊዜ የሚፈጁ እንደማይሆኑ ጳውሎስ አውቆ ነበር። ከትንሹ እምነታቸው ወደ ትልቁ ደረጃ ጳውሎስ ሲያሸጋግራቸው ወዲያውኑ ሲያምኑ እንመለከታለን። በዚህም ስብከት የተነሳ አንዳንዶች ተባብረው የማይታወቅ አምላካቸውን ትተው የጳውሎስን አምላክ በእምነት መቀበላቸውን ስናነብ በዚህ ዘመን ሊደረግ የሚገባውን የስብከት ዘዴ ጥበብም እንዴት ማስኬድ እንደሚገባን የሚያስረዳን ጥሩ መንገድ ነው።


ከዚህ ሃሳብ ተነስተን ርዕሰ ጉዳያችንን ስናጠቃልል «አንድ ጌታ፤ አንድ ጥምቀት፤ አንድ ሃይማኖት» የሚለውን የወንጌል ቃል ለማስተማርና ሌሎች ቤተ እምነቶች እኛ እውነት ብለን የያዝነውን እውቀት እንዲቀበሉ ለማስተማር ዘዴው ጥቅሱን በጨርቅ ላይ አትሞ በየጎዳናው ይዞ በመውጣት ሳይሆን ጌታን በማመን የሚገኘውን ዋጋ፤ ጥምቀት የሚያሰጠውን ጸጋና ሃይማኖት ያለውን ኃይል በማሳየት፤ ይህ ጥቅም እንዳያመልጣቸው ተስበው እንዲመጡ በጥበብና በብልሃት በማስተማር መሆን ይገባናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለአቴናውያን ያደረገው እንደዚህ ነውና። አንዲት ሃይማኖት የሚል መፈክር ማንንም አይለውጥም። ይልቁንም ሌላውን ለተመሳሳይ የምላሽ ነውጥ ያነሳሳ እንደሆን እንጂ።  ከዚህ አንጻር ራሳችን የምናውቀውንና የምናምንበትን ቃል በካናቴራ ላይ አትመን አደባባይ መውጣታችን  ራሳችንን ለመስበክ ሳይሆን ከእኛ በተቃራኒ ላለው እምነት «አንድ ሃይማኖት» የሚለው የወንጌል ቃል እኔን ብቻ ይመለከታል ለማለት ከመፈለግ የሚመጣ ራስን የተሻለ ክርስቲያን አድርጎ በማቅረብ መታበይ የፈጠረው ስሜት ከመሆን የዘለለ አይደለም።

ከዚያ ውጪ ክርስቲያን መሆኔን ለማሳወቅ «እኔ ክርስቲያን ነኝ» የሚል ጽሁፍ ግምባሬ ላይ ለጥፌ በመሄድ የክርስቲያንነት መገለጫዬ አድርጌ ባስብ ግብዝ መሆኔን እንጂ ክርስቲያን መሆኔን አያመለክትም። «የአንድ ጌታና የአንድ ሃይማኖትን» ጥቅስ አለቦታውና አለጊዜው መጠቀም የውጤታማ አስተምህሮ መለያ አይደለምና ለአስተምህሮአችን ጥንቃቄ እናድርግ!