በንጽህናና በድንግልና እየኖሩ የክርስቶስን የማዳን ሥራ ዘወትር እያሰቡ መኖር የእውነተኛ ክርስቲያን አንዱ ገጽታ ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስም ይህንን ሲገልጸው «ነገር ግን ያለ አሳብ ልትኖሩ
እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባልና» በማለት ሳያገቡ የክርስቶስን መከራ ሞት እያሰቡና የሕይወታቸው መመሪያ አድርገው ለሚኖሩ ትልቅ ሥፍራ ሰጥቷቸው
ይገኛል። (1ኛ ቆሮ 7፤32)
ይህ ማለት ግን ያገቡ ሰዎች ክርስቶስን ማገልገል አይችሉም ማለት አይደለም። እንዲያውም የሌላቸውን ጸጋ ለማግኘት ሲሉ በትግልና በትልቅ ፈተና ስር ራሳቸውን ጥለው
ሥጋቸውን በመጨቆን የሚያሰቃዩትን ሰዎች በድንግልና ያለመቀጠል ብቃታቸውን እንዲህ ሲል ከፈተናቸው እንዲላቀቁ በጌታ መንፈስ ይመክራቸዋል።
«ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ» 1ኛ ቆሮ 7፤ 9
ክርስቲያን መኖር የሚገባው በተሰጠው ጸጋ እንጂ የሌለውንና ያልተጠራበትን ጸጋ በጥረቱ ለማግኘት በመፈለግ ባለመሆኑ አንዳንዶች
በድንግልና እንኖራለን ብለው ሲያበቁ አዳማዊ ማንነታቸው ከሔዋን ጋር የሚያጣምር ሲሆንባቸውና ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ምኞት ስር ሲጥላቸው
የሥጋ ብልቶቻቸውን በቢላዋ ጎምደው እስከመጣል ይደርሳሉ። ይሁን እንጂ የሥጋ ብልታቸው መቆረጡ የልብ ምኞታቸውም ቆርጦ ሊያስቀረው
የማይችል ስለሆነ ዘወትር እንደተቅበዘብዙ ይናራሉ።
«ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው፥ አንዱ እንደዚህ
ሁለተኛውም እንደዚያ» 1ኛ ቆሮ 7፤7
ሐዋርያው እንዳለው በድንግልና የጌታን ነገር ብቻ እያሰቡ መኖር የተሻለ መሆኑ አይካድም። ይህ ጸጋ ለሁሉም የሚሰጥ ባለመሆኑ አንዳንዶች ጸጋቸውን ሳያውቁ ሰዎች በደነገጉት
የድንግልና ሕግ ሥር ወድቀው የራሳቸውን የጽድቅ መንገድ ለማቆም እየታገሉና እየተቃጠሉ መኖራቸው እርግጥ ነው። የሥጋ ብልቶቻቸውን ከመቁረጥ አንስቶ አስገድዶ
እስከመድፈር ፤ እንስቶችን አባብሎ ከመዳራትና የስርቆሽ ዝሙት እስከመፈጸም መድረሳቸው የሰውኛ ጥረት ውጤት ነው። አንዳንዶቹ የሥጋው ፈተና የመጨረሻው ጣሪያ ላይ
ሲደርስባቸው ለክፉ መንፈስ ተጋልጠው ግብረ ሰዶም እስከመፈጸም ይደርሳሉ።
«የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም» ሮሜ 10፤3
የተባለው የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ ለመጽደቅና የራሳቸውን ጽድቅ ለማቆም ሲታገሉ ከጽድቁ ሥራ ወጥተው የቀሩትን ይህ ቃለ እግዚአብሔር ተፈጽሞባቸዋል
ማለት ይቻላል።
ከዓለማውያን ሰዎች ባልተሻለ መልኩ አባ እገሌ እገሊትን ደፍረው ተያዙ፤ አቡነ እገሌ ልጅ ወለዱ፤ እነአባ እገሌም ግብረ ሰዶም ፈጸሙ እየተባለ ለሰሚ የሚቀፍ ዜና የሚሰማው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ
የሌላቸውን ጸጋ ለማግኘት ሲታገሉ ቆይተው የጭናቸው እሳት እየፈጀ መቆሚያና መቀመጫ ስለሚያሳጣቸው ነው። በቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ
በሰው ሚስት ላይ የተያዙ፤ አስገድደው የደፈሩ፤ አልፎ ተርፎም ግብረ ሰዶም ፈጽመው የተገኙ የብዙ አባዎች ጉዳይ አሳሳቢነት ለሲኖዶስ
ጉባዔ መወያያ ሆኖ መቅረቡ አይዘነጋም።
ይህ እንግዲህ የምናውቃቸውንና የምንሰማቸውን አስጸያፊ ተግባራት ሳይጨምር መሆኑ ነው። ይህን ማንሳት በሥጋ ድካም መነኮሳት
የሰሩትን ኃጢአት ለማውራት ሳይሆን የጋብቻን ክቡርነት የሚናገረውን የእግዚአብሔርን ቃል በመጋፋት የራሳቸውን ሕግ ለማቆም በመታገል
መካከል በሚፈጠረው ሽንፈት የተነሳ ኢ-ሞራላዊ፤ ኢ- ምግባራዊና ጸረ ሃይማኖታዊ አድራጎት እየተስፋፋ በመገኘቱ ምክንያት እንደሆነ
መታወቅ አለበት። የማይቻለውን ለመቻል ሲታገሉ ሽንፈታቸው መረን የለሽ ወደመሆን አድርሷቸው የመገኘታቸው ነገር ግልጽ ወጥቶ በመነጋገር አንድ እልባት
ላይ መድረስ ካልተቻለ ድርጊቱ ማቆሚያ የሌለው ሆኖ ይቀጥላል። ይህም በተጎጂው ላይ፤ በእምነቱ ተከታይ ውስጥ እና በማኅበረሰቡ ውስጥ
አሉታዊ አስተሳሰብ እንዲኖር የማድረጉ ነገር ማብቂያ የለውም።
በተዘዋዋሪ መንገድ ለድርጊቱ መባባስ ሕብረተሰቡም የራሱ
የሆነ አሉታዊ ድጋፍ አለው። ይኸውም የጋብቻን ክቡርነት ውድቅ በማድረግ
በሌላቸው ጸጋ በድንግልና ለመኖር በመፈለግ ጦርነት መካከል በሚፈጠረው
የምኞት ቃጠሎ የተነሳ ሰዎች ለመፈጸም ወደተገደዱበት ሕገ ወጥ ወሲባዊ
ጎዳና የሚገቡበት ሌላው መንገድ፤ መነኮሳት በአንድም ይሁን በሌላ
ምክንያት በሰው ሰራሽ የምንኩስና ህግ ጥላ ስር ካደሩ በኋላ ከምኞት ቃጠሎው በመውጣት ሴት ማግባት እንዳይችሉ በሕብረተሰቡ ዘንድ
የሚኖራቸው ተቀባይነት ዜሮ ስለሚሆን ይህንንም ሽሽት ነው። ሕብረተሰቡ
ጋብቻ የፈጸመውን መነኩሴ ፈረ’ስ፤ ውድቅ፤ ስንኩል፤ቆብ ጣይ የሚል
ስም በመለጠፉና ከጋብቻ በኋላ አገልጋይ ሆኖ ለመቀጠል እንደማይችል
በሚደርስበት ተጽእኖ የተነሳ በሰው ሰራሽ የምንኩስና ቀንበር ስር ለመኖር ይገደዳል። በዚህም የተነሳ ድብቁን ኃጢአት በመለማመድ
በስውር ለመቀጠል ይወስናል። ይሁን እንጂ ድርጊቱ ግልጽ እየወጣና ሁሉም እያወቀው በመሄዱ ህግና ግብሩ፤ ምንኩስናውና ሕዝቡ አራምባና
ቆቦ ሆነው ይገኛሉ።
የማይችለውንና ዘወትር የሚያቃጥለውን የጭን እሳት ተሸክሞ ያለችሎታው እንዲኖር ከማስገደድ ይልቅ ሐዋርያው እንዳለው ከዝሙት
ጠንቅ ራሳቸውን እንዲከላከሉና ሕገ ጋብቻን አክብረው ፤ በክርስቶስ እስራት ስር እንዲኖሩ ማግባት የፈለጉ መነኮሳት ጋብቻ ሊፈቀድላቸው
ይገባል።
ወንጌል «ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ
ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት» 1ኛ ቆሮ 7፤2 የሚለው ሰዎችን ከዝሙት ለመከላከል እንጂ ለጌጥ አይደለም።
ያለበለዚያ ምንም እንኳን የጽድቅ መንገድ እንዳልሆነ ቢታወቅም ፤ በማኅበራዊ የሥነ ምግባር ቀውስ ውስጥ ራሳቸውንና ሕዝቡን
እንዳያበላሹ ሲባል በምንኩስና ስም ከተጠለሉት ጳጳሳት አንስቶ እስከ ተራው መነኩሴ ጭምር በሀገሪቱ ውስጥ ከፈሰሱበት ቦታ ሁሉ እየተለቀሙ ወደጫካቸው እንዲገቡና ወደበዓታቸው
ተከተው እዚያው ከምኞቶቻቸው ጋር እንዲኖሩ ሊደረግ ይገባል። ጳጳሳቱ ሥልጣን ተረክበው ማስተዳደር ያቃታቸው ቤተሰባቸውን በማስተዳደር
ልምድና እውቀት ስለሌላቸው ነው። ዳሩ ግን ይህንን ማንም የሚያስፈጽም ባለመኖሩ ከኃጢአት ጋር ተስማምቶ መኖሩ ቀጣይ ነው።
በቅርቡ የታላቋ ብሪታንያ አንገሊካን ቤተክርስቲያን መነኮሳት ሚስት አናገባም የሚለውን የራሳቸውን አስተሳሰብ ህግ ሲከተሉ
ለእግዚአብሔር የጋብቻ ሕግ ሳይገዙ በመቅረት ለአስነዋሪ ምግባር ተላልፈው የተሰጡ ሲሆን ግብረ ሰዶም የሚፈጽምና የሚፈጸምበት መነኩሴ
ሊቀ ጳጳስ ሆኖ እንዲሾም ከብዙ ክርክር በኋላ በሲኖዶሱ ጉባዔ ማጽደቁ
ይታወቃል። የሚገርመው ነገር ደግሞ ሚስት ለማግባት ያልወሰነ መሆን ይገባዋል የሚለው ድንጋጌ አብሮ መተላለፉ ነው። ሚስት ያገባ
ሲከለከል ግብረ ሰዶማዊ የሆነ ግን ይሾማል የሚለው ሕግ ከእግዚአብሔር የተገኘ እውቀት ሳይሆን ከሰይጣን የመነጨ አስተሳሰብ ከመሆን
ያለፈ አይደለም። የእግዚአብሔር ህግማ የሚለው መሾም ያለበት ህጋዊ ጋብቻን የፈጸመ ሰው ነው።
«እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው
የሚሰራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ» 1ኛ ጢሞ 3፤2
ከላይ ለማሳየት እንደሞከርነው «ያገባ መልካም አደረገ፤ ያላገባም የተሻለ አደረገ» እንዳለው የወንጌል ቃል ሳያገቡ መኖር
የተሻለ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ያለስጦታና ያለጸጋ በሥጋዊ ትግል የሚገኝ ምርጫ ባለመሆኑ በእውቀት ማነስና በመንፈሳዊ ብስለት ጉድለት የተነሳ በዚህ ቀንበር ስር የወደቁ
ሁሉ መኖር በሚችሉት የእግዚአብሔር ስጦታቸው ውስጥ በነጻነት እንዲኖሩ ሊፈቀድላቸው ይገባል። ያለበለዚያ ክልከላውን ጥሰው አሁን እየተደረገ ያለው ስውሩ ዐመጻ በሂደት ግብረ
ሰዶማዊም ጵጵስና መሾም አለበት፤ የወንድ ለወንድ ጋብቻም ይፈቀድልን የሚል ዐመጻ በሂደት መምጣቱ አይቀርም። በግልጽ/ኦፊሴላዊ/
አይሁን እንጂ ድርጊቱ አሁንም ከመጋረጃ ጀርባ እየተፈጸመ ይገኛል። ሰው ከእግዚአብሔር ሕግ ሲወጣ የጥፋት ባሪያ ነው። ባሪያ ሆኖ ለተሸነፈለት
ኃጢአት ከተገዛ አርነት በእሱ ዘንድ የለም። ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው
ሌላውን አርነት ትወጣላችሁ የማለት ብቃት የሚኖረው? በየመድረክ ስብከቱ፤ በየሽምግልናው እርቁ፤ በየስብሰባው ውይይቱ የመንፈስ ፍሬ
የሌለበትና እንደዝናብ አልባ ደመና ተበትኖ የሚቀረው ለዚህ ይሆናል።
«ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው። አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል፤ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ
ነውና» 2ኛ ጴጥ 2፤19
ምክንያቱም እየተጻረሩ ያሉት «ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ» የሚለውን
የእግዚአብሔር ሕግ በመጣሳቸው የተነሳ ሰይጣን በማይረባ አእምሮ አጥምዷቸዋልና ራሳቸውም ከአርነት በታች ናቸው፤ ሕዝቡንም በወንጌል
አርነት ነጻ ማውጣት አልቻሉም።