ክርስቲያን የሚለው ስም የተጀመረው ከክርስቶስ
ሰው መሆን በኋላ ነው። ክርስቶስ ሰው ሳይሆን ክርስትና አልበረም። ባልነበረ ክርስትና እንዴት ሆኖ ነው በዓለመ መላእክት ቤተ ክርስቲያን
ነበረ የሚባለው? ማኅበረ ቅዱሳን ግን በድረ ገጹ ላይ ከክርስቶስ
ሰው መሆን አስቀድሞ ቤተክርስቲያን በዓለመ መላእክት ነበረ ይለናል። ይህ አዲስ ግኝት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያልተጻፈ ነገር
ግን በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር የተገኘ። ሰይጣን በዐመጽ ሳቢያ የነበረበትን ስፍራ ለቀቀ ማለት አንድ ነገር ነው፤ ነገር
ግን ሰይጣን ቤተክርስቲያንን መፈታተን የጀመረው በሰማይ ነው ማለት የማንን ክርስትና ለማስተጓጎል የሚል ጥያቄን ያስነሳልና ነገር
ዓለሙ አማረልን ብሎ ያለ የሌለውን ለማስመሰል መሞከር ትክክል አይደለም። ወይም ከክርስቶስ ሰው መሆን በፊት በሰማይ ክርስትና ተሰብኳል
በሉንና እስከወዲያኛው አስገርሙን። ያለበለዚያ የሌለ ነገር በመፍጠር ልታሞኙ ሳይሆን ልታሳስቱ አትሞክሩ።
ክርስትና ምንጊዜም የሚታሰበው ከክርስቶስ ደም
መፍሰስ በኋላ ነው። የድኅነት ደም ሳይፈስ ክርስትና እንደነበረ ማሰብ የጤንነት አይደለም። ክርስቶስ ስጋ ከመልበሱ በፊት የነበረበትን
ዘላለማዊ የመለኮት አገዛዙን ሁሉ የክርስትና ዘመን ነው ብለን ካላሰብን በስተቀር የቅድመ ዓለም ልደቱን ሁሉ የክርስትና የህልውና
ዘመን አድርገን እንድቆጥር የሚያስችለን አንድም ማስረጃ የለንም።
ማኅበረ ቅዱሳን ግን ቤተክርስቲያን አስቀድሞ እንደነበረች
በመቁጠር ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን መፈተን የጀመረው በዓለመ መላእክት ከመውደቁ በፊት ነው ይለናል። ማስረጃህስ ብንለው መጽሐፈ
ባልቴት ሊያቀርብ ካልሆነ በስተቀር የመጽሐፍ ቅዱስም፤ የሊቃውንትም አስተምህሮ እንደዚያ ሲል አይገኝም። በጽሁፉ ላይም ያንን የሚያረጋግጥለት ጥቅስም ሆነ ዋቢ አላቀረበም። ይህ አባባል በእነ በጋሻው በኩል
ተነግሮ ቢሆን ኖሮ «አቧራው ጨሰ» በሚል ፉከራና ሽለላ ዐሥር ገዳይ በሚል ክስ፤ ስም የማጥፋት ዘመቻውን በከፈተ ነበር።
አሁንም እንጠይቃለን! የቤተክርስቲያን ታሪክና
ሕልውና የታወቀው መቼ ነው? በዓለመ መላእክት ያለች ቤተክርስቲያን ማለት ምን ማለት ነው? አስረጂውስ?
መላእክት ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተባት የሞትና የትንሣዔው አካል አይደሉም። ክርስቶስ ለመላእክት አልሞተምና ነው። ቅዱሳን መላእክት
ዘወትር በቅድስና የምስጋናና የተልእኰ ሕይወት ውስጥ ነበሩ፤ አሉም።
ስለወደቀው መልአክም የሚደረግ የማዳን ስራ የለም። አይኖርምም። ታዲያ ስለየትኛዋ የድኅነት መንገድ ቅድስት ቤተክርስቲያን
ነው እየተናገሩ የሚገኙት? የክርስቶስ ቤተክርስቲያን በሞቱና በትንሣዔው የቆመች እንጂ በምናብ የነበረች የዓለመ መላእክት ሥፍራ
አይደለችምና አባባላቸውን ለማሳመር ፈጠራ ቢጤን ለማጣፈጫ መጠቀም ተገቢ አይደለም። ስለዚህ ከክርስቶስ ሰው መሆን በፊት በዓለመ
መላእክት የሚባል ቤተክርስቲያን አልነበረችም። ምክንያቱም ወንጌላችን ለእኛ ለሰዎች እንጂ ለመላእክት የተመሠረተች እንዳልሆነች በአጭር ቃል እንዲህ ይለናል።
«የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን
አይደለም» ዕብ 2፤16
ሁሉን የገዛው ሞት በክርስቶስ ሲገዛ ያኔ የቤተክርስቲያን ራስ የሆነው ክርስቶስ የሙላቱ አካል የሆነችው ቤተክርስቲያንን በትንሣዔው መሠረታት የምንለው።
ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና
ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም
ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ
ባደረገው ሥራ የብርታቱ
ጉልበት ይታያል፤ ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት
ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን
ሰጠው።
እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት። ኤፌ 1፤20-23
ከዚያ በፊት ቤተክርስቲያን አልነበረችም።« የለም? በዓለመ መላእክት ቤተክርስቲያን
ተመስርታ ነበረች» የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ
እንደዚያ የሚል ስለሌለ በምንፍቅና ከሰባቱ ተባራሪዎቻችሁ ጋር ትባረራላችሁ ማለት ነው? ዳሩ ግን የሚባረረው እውነት የሚናገር እንጂ ሀሰተኛ ባለመሆኑ እናንተን በዚህ የሚጠይቅ የለም።